ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ መንገዶች ግንባታ ውል ተፈረመ

0
610

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ 299 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍኑ የአራት መንገድ ፕሮጀክት ግንባታ ሥራ ለማስጀመር የውል ስምምነት ተፈራረመ።

መንገድ ፕሮጀክት ግንባታውን ለማካሔድ ጨረታ ካሸነፉ የሥራ ተቋራጮች ጋር በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የመሰብሰቢያ አዳራሽ ስምምነት የተደረሰባቸው የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች መካከልም የሃሙሲት እስቴ መንገድ ርዝመት 76 ኪሎ ሜትር ሲሆን የግንባታ ወጪውም 1 ቢሊዮን 395 ሚሊዮን ብር፣ ጩለሴ ሶያማ ሎት 2 የመንገዱ ርዝመት 90 ኪሎ ሜትር እና የግንባታው ወጪውም 1 ቢሊዮን 800 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ተገልጿል።

በተጨማሪም 55 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የአደሌ ግራዋ መንገድ እንዲሁም 88.5 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው ጎዴ ቀላፎ ሎት አንድ መንገድ ከ 2.5 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እንደሚገነቡ በውል ስምምነቱ ላይ ተጠቅሷል።

የመንገድ ፕሮጀክቶቹን ግንባታ ከሦስት ዓመት እስከ ሦስት ዓመት ከግማሽ ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የመንገዶቹ የግንባታ ወጪም በኢትዮጵያ መንግሥት የሚሸፈን ነው።

መንገዶቹ ከዚህ ቀደም በጠጠር መንገድ ደረጃ የነበሩ ሲሆን፥ ካላቸው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጠቀሜታ አንፃር ታይቶ በአሁኑ ወቅት በአስፋልት ኮንክሪት ደረጃ እንዲገነቡ ታቅዶ የውል ስምምነቱ መፈረሙንም የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን አስታውቋል።

ባለሥልጣኑ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶቹ በታቀደላቸው ጊዜና የጥራት ደረጃ ተገንብተው እንዲጠናቀቁ ተቋሙ አስፈላጊውን ድጋፍና ቁጥጥር እንደሚያደርግም ገልጿል።

ቅጽ 2 ቁጥር 57 ኅዳር 27 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here