“እኔን ይወክለኛል”

0
958

በማኅበራዊ ኑሮ የተፈጠረውን የማዕረግ ተዋረድ ወንዶችን ከበላይ ሴቶችን ከታች አስቀምጧል። ይህም በዘመናት ሒደት የተገነባው የተዋረድ ስርዓት ከላይ ላለው ያለድካም ሲያደላ፤ ከታች ላስቀመጠው በአንጻሩ የሚነፍግ፤ በጥቅሉ የተዛባ የኃይል ሚዛን ፈጥሯል። ‹‹እኔን ይወክለኛል›› የሚሉት በፍቃዱ ኃይሉ፣ በራስ ጥረት ሳይሆን በማዕረግ ተዋረዱ ተጠቃሚ የሆኑ ሁሉ ስርዓቱ ‹‹እኔን ይወክለኛል›› ሊሉ ይገባል ሲሉ ይሞግታሉ።

ባለፈው ሳምንት በዚህ አምድ ላይ በታተመልኝ መጣጥፍ “እኔን አይወክለኝም” በሚል ርዕስ መጻፌ ይታወሳል። የጽሑፉ ጭብጥ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ተዋስዖ ውስጥ ‘አንዳንድ ግለሰቦች በጊዜ እና በቦታ ርቀት ውስጥ የፈፀሙት ተግባር በባሕላዊ ማንነታቸው ዝምድና ብቻ ቢጤዎቻቸው ሁሉ የሚወቀሱበት እና የሚሞገሱበት ልምድ አለ፤ ይህም አግባብ አይደለም’ የሚል በተለይ ንፁኀን ላይ በወንጀለኞች ጦስ የሚደርስባቸውን ዳፋ መከላከያ ነበር። የጽሑፉ መልዕክት ከተጠቀሰበት ዐውድ አንፃር ትክክል ቢሆንም ዘመንና ርቀት የማይገድበው ትሩፋት (legacy) ተቋዳሽነትን ለመካድ አገልግሎት እንዳይውል በማሰብ ይህንን ጽሑፍ ለማስከተል ወስኛለሁ።
እውነት ነው የኔን ቋንቋ የሚናገር ሰው ያጠፋው ጥፋት ሁሉ እኔን አይወክለኝም። የኔን እምነት የሚከተለው ሰው ያጠፋው ጥፋት ሁሉ እኔን አይወክለኝም። በተመሳሳይ የኔን ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች ወይም የኔን እምነት የሚከተሉ ቢጤዎቼ የሠሩት ሥራ ትሩፋትም አይገባኝም። ዘመናዊቷ ዓለም ግን አንዱን ያለሥራው ስትሸልም፤ ሌላዋን ያለጥፋቷ የምትቀጣ ዓለም ነች።

የማዕረግ ተዋረዶች
ፍራንሲስ ፉኩያማ በ1990ዎቹ በጻፉት ‘ዘ ግሬት ዲስራፕሽን’ በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ “ሰዎች ማኅበራዊ የማዕረግ ተዋረዶችን (social hierarchies) አይጠሉም፤ የሚጠሉት ከተዋረዱ ግርጌ መሆንን ነው” ይላሉ። ለዚህም ይመስላል የማዕረግ ተዋረዶችን ከዓለም ማጥፋት ያልተቻለው። በዓለማችን ቆጥረን የማንጨርሳቸው ‘…ኝነቶች” (…isms) በሺሕ ዓመታት ታሪካችን ተፈልፍለዋል። ዘረኝነት፣ ፆተኝነት፣ ዘውጌኝነት፣ መደበኝነት፣ ከተሜኝነት…። እነዚህ ‘…ኝነቶች’ እንዳለመታደል ሆኖ ከተዋረዱ ሥር ያስቀመጡት አፍሪካውያንን ነው። ከአፍሪካውያንም ሴቶችን፣ ከሴቶችም የገጠር ሴቶችን፣ ከነዚህም አካል ጉዳተኞችን ነው። በተቃራኒው በዓለማችን የማኅበራዊ ማዕረጎች ቁንጮ ተደላድለው የተቀመጡት እና የተቀመጡበትን የረሱት ደግሞ ወንዶች፣ ከወንዶችም የሰሜኑ ንፍቀ ዓለም ነዋሪ ወንዶች፣ ከነዚህም ነጭ፣ አካል ጉዳት የሌለባቸው እና የከበርቴ ቤተሰብ ፍሬዎች ናቸው።

የማኅበራዊ እርከን ተዋረዱ ባለብዙ እርከን ነው። ከቦታ ቦታ፣ ከጊዜ ጊዜ ዓይነቱ ይለዋወጣል። የሆነ ሆኖም ግን ሁሉም ቦታ፣ በሁሉም ጊዜ የኢ-ፍትኀዊነት መነሻ ነው።

ክብ ልፋት
መስፍን ወንድወሰን የተባለ ገጣሚ ‘ቪሺየስ ሰርክል’ የሚለውን የእንግሊዝኛ ሐረግ ‘ ክብ ልፋት’ በሚል አቻ ትርጉም ይፈታዋል። የኢትዮጵያን ነባራዊ ፖለቲካ ለመግለጽ የተጠቀመበት ፍቺ ነበር። ጉዳዩ ግን የኛ ብቻ አይደለም። ዓለማችን በክብ ልፋት ውስጥ እየዳከረች ነው የምትኖረው። የተለወጠ የሚመስለን ብዙ ጊዜ እዚያው እየረገጠ እናገኘዋለን።

ከላይ የጠቀስናቸውን እርከነ ብዙ መዋረዶች የዓለም ስርዓተ ማኅበሮች ፈጥረውታል። ግን አንዴ ከተፈጠረ በኋላ መቆሚያ የለውም። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመሔድ ዕድል አለው። የድሀ ልጆች ድሀ ሆነው ኖረው፣ ድሀ ሆነው የመሞት ዕድላቸው የሰፋ ነው። ‹‹ላለው ይጨመርለታል…›› እንዲሉ ባለፀጎቹ ይበልጥ እየበለፀጉ ይሔዳሉ።

ይህ ሳምንት የ16 ቀን ንቅናቄ እየተባለ ባለፉት ዓመታት በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ከሚከበሩ ሳምንታ ውስጥ አንዱ ነው። ፍትኀዊ የስርዓተ ፆታ ግንኙነት እንዲኖር የሚፈልጉ ሰዎች የጀመሩት ንቅናቄ ነው። ሴቶች በመላው ዓለም ሊባል በሚችል ደረጃ በዚህ ማኅበራዊ የማዕረግ ተዋረድ ከወንዶች በታች ተቀምጠዋል። ይህንንም በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ለመታገል እየሞከሩ ነው።

በዚህ ዓመት የ16 ቀኑ ንቅናቄ የሚካሔደው “የእኩልነት ትውልድ፥ አስገድዶ መድፈርን ይቃወማል” በሚል መፈክር ነው። በየዓመቱ ሚሊዮኖችን አስገድዶ የሚደፍረው ትውልዳችን “የእኩልነት ትውልድ” ተብሎ መጠራቱን በስላቅነቱ ብቻ ሳይሆን በማበረታቻነቱም ተቀብየዋለሁ። ነገር ግን “እውነት ትውልዳችን የእኩልነት ነው? እንዲያውም የኛ ትውልድ ይቅርና በእኩልነት የሚያምን እና የሚኖር ትውልድ ይመጣ ይሆን?” ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ የለኝም። ስፒኖዛ የተባለው ፈላስፋ “እኩልነትን እኩል ባልሆኑ መካከል የሚፈልግ ወለፈንዴነትን እየፈለገ ነው” (he who seeks equality between unequal’s seeks an absurdity) ብሎ ጽፎ ነበር። ይህንኑ አባባል የዘመናችን ምጡቅ አሳቢ ዩቫል ሃራሪ ‘ሳፒየንስ’ በተሰኘ መጽሐፉ ይደግመዋል። ሰዎች በማኅበራዊ እና ባዮሎጂካላዊ ዝግመተ ለውጥ ሒደት እኩል ዕድል ሳያገኙ ነው ዛሬ ላይ የደረሱት። ይህ መሠረታቸውን ባልተደላደለ መሠረት ላይ ላኖሩት የሰው ልጆች በምኞት ብቻ እኩልነትን ለማምጣት እንደማይቻል አሳቢዎቹ ያመለካቱበት መንገድ ነው።

ዩኤን ውመን ሴቶች ሲደፈሩ መልሰው ተወቃሽ እንደሚሆኑ የሚያሳዩ የበይነ መረብ ዘመቻ ግራፎችን ሲጠቀም ከርሟል። ለምሳሌ አንዲትን ሴት እንዳትደፈሪ እንዲህ፣ እንዲህ አድርጊ በማለት ፈንታ፤ ወንዱን እንዳትደፍር ማለት መቅደም እንዳለበት አመልክተዋል። ለዚህ ዘመቻ መግፍኤው ነባራዊው እውነታ ነው። ሴታዊት የተሰኘችው ኢትዮጵያዊት የፌሚኒስት ንቅናቄ ‘ምን ለብሳ ነበር?’ የሚል የቀሚስ ዐውደ ርዕይ አዘጋጅታ ነበር። የዐውደ ርዕዩ ዓላማ ለሴቶች መደፈር እንደ ሰበብ የሚሰጠውን ምክንያት ማምከን ነበር።

ብዙዎች ሴቷ የምትለብሰውን ልብስ ወንዱን ለመድፈር እንዳነሳሳው ይናገራሉ። በሰበቡ ለወንዱ በደልና ግፍ ማኅበራዊ ምኅረት ያገኙለታል። ይህ የሆነው እንዲሁ አይደለም። ብዙ ሺሕ ዓመታትን በፈጀ ሒደት የተገነባው ስርዓተ ማኅበር በማዕረግ ተዋረዱ መሠረት ከላይ ላለው ያደላል። ከታች ያለችውን ደግሞ ይወቅሳል። ስለዚህ ሴት ልጅ ስትደፈር የምትወቀሰው ራሷ ነች። ዓለም ዛሬ የቆመችበት መደላድል በአጭሩ ይኼን ይመስላል።

“እኔን ይወክለኛል”
ይህ በማዕረግ ተዋረድ ላይ የተገነባ ዓለም፣ ይህ በኢ-እኩልነት ላይ የተገነባ ዓለም – እኔን ይወክለኛል? ሞጋቹ ጥያቄ ይኼ ነው። “ይህን የማዕረግ ተዋረድ አትርፌበታለሁ ወይ?” ብለን ከጠየቅን ግን መልሱ ይቀላል። የማዕረግ ተዋረዶች የሚፈጥሩት ነገር ቢኖር የተዛባ የኀይል ሚዛን ነው። የኀይል ሚዛን ደግሞ በብዙኀኑ እምነት (myth) ውስጥ ይገኛል። አንዳንድ ሰዎች ከዚያ እምነት ማፈንገጥ ይችሉ ይሆናል። ነገር ግን ብዙኀኑ እስካላፈነገጡ ድረስ በስርዓተ ማኅበሩ የማዕረግ ተዋረድ ወይ ተጠቃሚ ወይም ደግሞ ተጎጂ መሆናቸው አይቀርም። የማዕረግ ተዋረዱ ላይ ያሉት ያልሠሩበትን እና የማይገባቸውን ኀይልና ክብር ሲያጎናፅፋቸው፤ ታች ያሉት ደግሞ የደከሙበትን ኀይል እና ክብር ይነፍጋቸዋል።

በነባራዊው ዓለም ነጮች ነጭ ሆነው በመወለዳቸው ብቻ ከጥቁሮች የበለጡ ማዕረጎች፣ ክብር እና ዝናን ይጎናፀፋሉ። ወንዶች ከሴቶች፣ ከተሜዎች ከገጠሬዎች፣ የባለፀጋ ቤተሰቦች ከድሆች የበለጠ ኀይል እና ክብር አላቸው። ይህንን ተዋረድ በተበዳይ ወገን ያሉትም አምነው ተቀብለው፣ ይገብሩለታል። ለዚህ ነው የማይገባንን አምነን ስለ ፍትሕ ሲባል “እኔን ይወክለኛል” ብለን መጮህ ያለብን።

እኔ (የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ) ለወንዶች የሚያደላው ስርዓት ሲፀነስ አልነበርኩም። ነገር ግን የስርዓቱ ተጠቃሚ ነኝ። በቀላሉ ለመግለጽ እህቶቼ በልጅነታችን ወደ ማጀት ሲላኩ እኔ ግን ወደ ጥናት ወይም ወደ ጫወታ እሠማራ ነበር። ወንድ በመሆኔ ብቻ እህቶቼ የተሰረቀ ተጠቃሚነት አፍርቻለሁ። አሁን ንቃተ ሕሊናዬ ዳብሯል በምልበት ወቅት ለፍትሕ ተቆርቋሪ ከሆንኩ አባታዊው ስርዓት “እኔን ይወክለኛል”፣ እኔም ተጠቃሚ ነኝ፣ ተወቃሽ ነኝ ብዬ ማመን አለብኝ። ከቻልኩ ከእህቶቼ (እና ሌሎችም) የሰረቅኩትን ትሩፋት መመለስ አለብኝ። የተጠቃሚነት ግብር ማለት ነው። ሴቶች የተጎጂነት ግብር ሲከፍሉ ኖረዋል። (ፈረንጆች ‘black tax’ የሚሉት ነገር አለ። ይኸውም በምዕራቡ ዓለም ጥቁሮች ከባርነት ስርዓት የቀጠለ ድህነት ተጠቂዎች ናቸው። እናም፣ አንድ ነጭ እና አንድ ጥቁር እኩል ወርሐዊ ገቢ ቢኖራቸውም፣ ጥቁሩ/ሯ ታሪክ ወለድ ድህነት የጣለባቸውን ብዙ ቀዳዳ ይሸፍናሉ፤ ብዙ ወዳጅ ዘመድ ይረዳሉ። ስለዚህ ጥቁሩ/ሯ ደሃ ሆነው የመቀጠል ዕድላቸው የሰፋ ነው ይሉና፣ ምክንያቱንም “ብላክ ታክስ” ይሉታል።)

የከተማ ልጅ በመሆኔ ብቻ የገጠር ልጆች ያላገኙትን ዕድል አግኝቻለሁና የፍትሕ ሞራላዊ ኀላፊነት አለብኝ። የአገሪቱን የገበያ ቋንቋ አቀላጥፌ በመናገሬ ብቻ ያተረፍኩትን ዕድል ስለ ፍትሕ ለሌሎቹ ልናገርበት ይገባል። እኔ እኔን ይወክለኛል እንዳልኩት የባለፀጋ ልጆች በመሆናቸው ብቻ እኔ ሳላገኘው ያደግኩትን ዕድል አግኝተው የበለፀጉ ሰዎች፣ በአድሎ የሚያበለፅገው ስርዓት “እኔን ይወክለኛል” ሲሉ መስማት እመኛለሁ።

በፍቃዱ ኃይሉ የሰብኣዊ መብቶች ተሟጋች እና ጸሐፊ ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው befeqe@yahoo.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 57 ኅዳር 27 2012

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here