የኢትዮጵያ ፖለቲካን ጠርንፎ የሔደው የትግራይ፣ አማራና ኦሮሞ ፖለቲካ ነው

0
1866

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአክቲቪስትነት ስማቸው ገንኖ ከወጣና ተሳትፏቸው እንዲሁም ተጽእኖ ፈጣሪነታቸው ከጠነከረ ሰዎች መካከል ይገኛሉ፤ የኦሮሚያ ሚድያ ኔተወርክ ሥራ አስኪያጅ ጀዋር መሐመድ። ፖለቲካ ውስጥ በተወዳዳሪነት የመሳተፍ ፍላጎት ያልነበራቸው ጃዋር፤ በቅርቡ ነው ለመወዳደር ወደ መድረኩ እንደሚመጡ የሳወቁት። ከዚህና ከግል ጉዳያቸው ጋር በተገናኘም ወደ ባህር ማዶ አቅንተው ከጥቂት ቀናት ቆይታ በኋላ ተመልሰዋል። የአዲስ ማለዳዎቹ ተወዳጅ ስንታየሁ እና ሐይማኖት አሸናፊ እንደተመለሱ አግኝተዋቸው በብሔር ጥያቄ፣ አሁን ላይ በኢትዮጵያ በሚታየው የፖለቲካ እንቅስቃሴ፣ ተደርጎብኛል ስላት የግድያ ሙከራ እንዲሁም ብልጽግና ፓርቲ እና የመከላከያ ሚኒስትሩ ለማ መገርሳ በመደመር ላይ የሰጡትን አስተያየት በተመለከተ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል።

በአሁኑ ወቅት እየተበራከተ የመጣው የብሔሮች የክልልነት ጥያቄ የፌዴራሊዝም ውድቀት ነው ወይስ ስኬት?

የፌዴራል ስርዓት በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ዓይነቱ ኹለት ነገሮችን እንዲያሟላ ይጠበቃል። አንዱ እና ቀዳሚው ብሔሮች መዋቅራዊ ክልል እንዲኖራቸው ማድረግ ነው። ኹለተኛው ፍትኀዊ የሥልጣን እና የሀብት ክፍፍል መምጣቱ ነው። የመጀመሪያውን ያለ ዴሞክራሲ ማድረግ ይቻላል፤ የሥልጣንና ሀብት ክፍፍሉን ግን ያለ ዴሞክራሲ ማድረግ አይቻልም።

ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ እየሆነ ያለው በግማሽ ላጭቶ በግማሽ እንደመተው ነው፣ ፌዴራል ስርዓቱ። በአንድ ወገን የመዋቅር ለውጥ መጥቶ አገሪቱ በብሔር ክልሎች ተዋቅራለች። ኹለተኛው ወገን ግን የፌዴራሊዝም ዋናው ክፍል የሆነው የሥልጣን ክፍፍል ማለትም ራስን የማስተዳደር ሁኔታ አልተሟላም። ፌዴራሊዝም በዴሞክራሲ ስለሌለ ግማሽ ግማሽ ሆኖ የቀረ ስርዓት ነው ያለው።

አሁን ያለው የጥያቄዎቹ መነሳት ዴሞክራሲ መጀመሩን ነው የሚያሳየው። እነዚህ ጥያቄዎች ለምሳሌ በ1992 ወይም በ1995 ሕገ-መንግሥቱ ከተቀረፀ በኋላ ወደ ነጻ እና ፍትሓዊ ምርጫ ብንገባ ኖሮ ወይ ደግሞ የፖለቲካ ምኅዳሩ እየሰፋ ቢሆን ኖሮ ያኔ ነበር የሚነሱት። እንደውም ተነስተው ነበር፤ አልጎሉም እንጂ። የሲዳማ ጥያቄ በዚያን ጊዜ የጎላ ነበር፤ ደቡብ ክልል የሕዝቦችን ፍላጎት ተጋፍቶ የተቋቋመ ነው። ስለዚህ አሁን የምናያቸው የክልሎች ጥያቄ መነሳት ታፍኖ የነበረው የፌዴራል ስርዓት ወደ ሥራ እየተለወጠ መሆኑን የሚያሳይ ነው እንጂ፣ እንግዳ የሆነ ክስተት አይደለም። የፌዴራሊዝም ስርዓቱ መሥራት እና ማንሰራራት መጀመሩን ነው የሚያሳየው።

ተጨቁነናል እያሉ የሚገኙት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ብሔሮች ናቸው፤ በአብዛኛው አነስተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላቸው መብታቸውን ሲጠይቁ አይታይም በዚህ ላይስ ምን ይላሉ?

የምንኖረው በመደበኛ አገር ውስጥ አይደለም፤ ለረጅም ጊዜ አነስተኛ ቁጥር ያለው ብሔር ብዙ ቁጥር ያለውን ብሔር በበላይነት ያስተዳደረበት አገር ውስጥ ነው ያለነው። የፖለቲካ ጭቆና የቁጥር ብልጫን ወደ ፖለቲካ አናሳነት ሊለውጥ ይችላል። በኢትዮጵያም በቁጥር አብላጫ የነበራቸው ብሔሮች በፖለቲካው አናሳ ነበሩ ማለት እንችላለን። ትምህርት ቤት እያለሁ ትዝ ይለኛል ክርክር ነበር፤ ለምሳሌ እንደ ኦሮሞ ያሉ ቡድኖች አናሳ ናቸው ወይስ አብላጫ ናቸው? በፖለቲካው አናሳ ናቸው። አደጋ ውስጥ ያሉ አናሳ ቡድኖች ውስጥ ኦሮሞን ወይም ሱማሌዎችን ሲያስገቡ ለምን ተብሎ ሲጠየቅ በፖለቲካው አናሳ ናቸው የሚለው ነው የሚነሳው።

በመሠረቱ ግን ፌዴራሊዝም የኹለቱንም ፍላጎት ለማሟላት ነው የሚሞክረው። አብላጫው ፌዴራሊዝምን ነው የሚፈልገው፣ አናሳውስ ፌደራሊዝምን ለምንድነው የሚፈልገው የሚለውን ስንመለከት፤ አብላጫው እንደ ክልል ሰፊ ቆዳ ስፋት አለኝ እንዲሁም ሀብት አለኝ ብሎ ስለሚያስብ ባለቤትነትን ማረጋገጥ ይፈልጋል። በፌዴራል ደረጃም ከአስተፅዖው ጋር እና ከቁጥሩ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ድርሻ ማግኘት ይፈልጋል። ከዚህ አንፃር አብላጫ ቁጥር ያለው ፌዴራሊዝምን ይደግፋል። አነስተኛው ግን ራሱን ለመጠበቅ ነው የሚጠቀምበት። አነስተኛ ከመሆኑ የተነሳ የባሕል ወረራ ይመጣብኛል፣ የፖለቲካ መገለል ይደርስብኛል ብሎ ስለሚያስብ ራሴ የሆነ ግዛት ሊኖረኝ ይገባል፤ በሕገ መንግሥት የተረጋገጠ ሉዓላዊነት እና ድርሻ በፌዴራሊዝም ስርዓት ውስጥ ሊኖረኝ ይገባል ብሎ ነው የሚያስበው።

ከዚህ አንፃር ኹለቱም ይፈልጉታል፤ የፖለቲካ አለመመጣጠን ባለበት አገር ውስጥ።

የፌዴራል መንግሥቱ ሲጠነክርም ሆነ የክልል መንግሥታት ጠንካራ ሲሆኑ የተለያየ ተቃውሞዎች ይነሳሉ። የትኛው የጠነከረበት ስርአት ነው ለኢትዮጵያ የሚበጀው?

የሚሻለው የተመጣጠነ ሲሆን ነው። እነ ዐቢይ [የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር] ማዕከላዊ መንግሥት የሚለው እና የፌዴራል መንግሥት የሚለው ተምታቶባቸዋል። የተማከለ አገዛዝ ባለበት ስርዓት ውስጥ የማዕከላዊው መንግሥት ኃላፊነት ክልሎችን ማቆራኘት እና አገሪቱ እንድትቀጥል ማድረግ ነው። በዴሞክራሲ ስርዓት ውስጥ ግን ማስተባበር ነው። ለምሳሌ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተለያዩ ቡድኖችን ያስተባብራል እንጂ በኃይል አያስገድድም።

አሁን ባለው የፌዴራል ስርዓት መሆን ያለበት፣ ሕገ መንግሥቱን ወደ ሥራ መተርጎም ነው። ክልሎች በሕግ በተሰጣቸው ሥልጣን ሙሉ ባለቤትነት እንዲኖራቸው ማድረግ፣ ፌዴራል መንግሥቱም በሕግ በተሰጠው ሥልጣን ላይ ሙሉ መብት እንዲኖረው ከተደረገ፣ መገፋፋቱ ይመጣል ነገር ግን እኩልነትም እየተገኘ ይሔዳል።

ስርዓቱ ዴሞክራሲያዊ ቢደረግ በዐሥር ዓመት ውስጥ መመጣጠን ይመጣል። ዛሬ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በቀላሉ ስለገባን ብቻ በፌዴራል መንግሥቱ እና በክልል መንግሥት መካከል ያለው መገፋፋት ተፈጥሮአዊ ስለሆነ ፌዴራል መንግሥቱ ራሱን የበለጠ ፈርጣማ ማድረግ ይፈልጋል። ክልሎችም የራሳቸውን አስተዳደር ፈርጣማ ለማድረግ ይሞክራሉ። ይህ ዴሞክራሲ ማለት ነው።

አሜሪካ ውስጥ ከመጀመሪያ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ያሉ የሕገ መንግሥት ማሻሻያዎች አብዛኛዎቹ በፌዴራል መንግሥት እና በክልሎች መካከል ባለ የሥልጣን መገፋፋት ላይ የሚያተኩር ነው። በፌዴራሊዝም ስርዓት ኹለት ዓይነት ግንኙነት አለ፤ አንደኛው በክልሎች  እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል በሀብት ክፍፍል እና መሰል ጉዳዮች የሚደረገው ፍትጊያ እና መገፋፋት ነው። ኹለተኛው በክልል መንግሥታት መካከል የሚደረገው ፍትጊያ ነው። ኹለቱ ወደ ግጭት ሳይገባ በሕግ ተገርቶ የሚሔድበትን ሁኔታ ከፈጠርን ፌዴራል ስርዓቱ እየተጠናከረ ይመጣል።

የፌዴራል ስርዓቱ እንዳይሠራ ያደረገው አምባገነናዊ ስርዓት ነው። አንድ ግንኙነት ነው የነበረው፤  በክልሎች እና በፌዴራል መንግሥቱ መካከል። እርሱም በአንድ አቅጣጫ የተወሰነና በጉልበት ላይ የተመረኮዘ ነው። የፌዴራል መንግሥቱ ያዝዛል፣ ክልል ይታዘዛል። የክልል መንግሥቱ ይጠይቃል እንጂ ፍላጎት እንኳን አያሳይም ነበር። በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል መካከል ደራ ላይ ችግር ቢፈጠር ኹለቱ ክልሎች ምንም ዓይነት ውይይት ውስጥ አይገቡም፤ የፌዴራል መንግሥቱ ነበር የሚወስንላቸው። ይህም በክልሎች መካከል የጎንዮሽ ግንኙነቱ የቀጨጨ እንዲሆን በማድረግ የፌዴራል ስርዓቱም የቀጨጨ እንዲሆን አድርጎታል።

የፌደራል ስርዓቱ እንዲጠናከር ከተፈለገ ከላይ ወደ ታች ያለውም ሆነ የጎንዮሹ ግንኙነት ሕጋዊ መሆን መቻል አለበት።

በንጉሣዊ አስተዳደር ዘመን የነበረው ከዐፄው ስር ንጉሦች እና ሌሎች አስተዳዳሪዎች ግብር የሚሰበስቡበትና የራሳቸውን ጦር የሚያደራጁበትን ስርዓት እንደ ፌዴራል ስርዓት በመውሰድ ፌዴራሊዝም በኢሕአዴግ የተጀመረ አይደለም ለማለት እንችላለን ብለህ ታስባለህ?

አወቃቀሩ ፌደራሊዝም ሊመስል ይችላል። ነገር ግን ፌዴራል ስንል መዋቅራዊ ብቻ አይደለም። ቅድም እንዳልኩት በፌዴራሊዝም የሀብት እና የሥልጣን ክፍፍል ወሳኝ ነው። የተባሉት ንጉሣዊ አገዛዞች በነበሩበት ወቅት ግብር ይሰበስባሉ፣ የራሳቸው የጦር ሠራዊት ነበራቸው፣ ግብር ለተወሰነ ጊዜ ለምኒልክ የሚሰጡት ነገር ነበር። በአገራዊ ስርዓት ውስጥ ያሉ አነስ ያሉ አገር መሰል ግዛቶች (states within a state) ነበሩ ማለት ይቻላል። ችግሩ ከማዕከላዊ መንግሥቱ ጋር የነበራቸው ግንኙነት በሕግ የተለየ አልነበረም። ለምሳሌ ከኃይለሥላሴ ጋር ግጭት ውስጥ የገቡበት ነበር። በማዕከሉና በእነዚህ ግዛቶች መካከል የነበረው የተዋረድ ግንኙነት በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ እየተፈተነ እየበሰለ የሚሔድ አልነበረም።

የፌዴራል ስርዓት ሐሳቡ ከእነ ዋለልኝ ነው የሚጀምረው። ከዛ በፊት እንደ ስርዓት አልነበረም እንደ ልምምድ ግን ሊኖር ይችላል።

እንደ ባሕላዊ የፌዴራሊዝም ስርዓትስ ልንወስደው እንችላለን?

በደንብ ልንወስደው እንችላለን። ኢትዮጵያ ውስጥ ችግር የፈጠረው ኃይለሥላሴ ያንን ያፈረሱበት እና ከዚያ በኋላ በኃይለኛ ሁኔታ የተሔደበት መንገድ ነው። ብዙ ሰዎች ኃይለሥላሴን ስንተች ዝም ብሎ ይመስላቸዋል። በግምት አይደለም ያደረጉት፤ እነ አክሊሉ ሀብተወልድ ፈረንሳይ ነው የተማሩት። ፈረንሳይ በሔዱበት በ1930ዎቹ እና 40ዎቹ ውስጥ አውሮፓ ውስጥ የነበረው ትልቁ ክርክር ምን ነበር ብለን ማየት አለብን።

ከ19ኛው ክፍለ ዘመን በኋላ አውሮፓ ውስጥ ገዢ እየሆነ የመጣ አመለካከት ነበር። ብሔር እና አገር አንድ መሆን አለባቸው የሚል ነው። አንድ አገር ብዙ ብሔር ሊኖር አይችልም፤ ኔሽን ስቴት መገንባት አለብን የሚል። አንድ ዓይነት መሆን የሚል ሐሳብ ተነስቷል።

በሌላ በኩል እነዉድሮው ዊልሰን ያመጡት የራስን ዕድል በራስ የመወሰን አመለካከት ኔሽን እና ስቴት አንድ አይደሉም፤ የተለያዩ ማንነቶችን በአንድ አገር ውስጥ ጨፍልቆ ለማቆየት የሚደረግ ጥረት ቀጣይነት ያለው አይደለም የሚል ነበር። ስለዚህ ክልሎች የራሳቸውን መንግሥት መመሥረት አለባቸው የሚለው ሌላ ሐሳብ መጣ። እነ አክሊሉ እዛ በተማሩበት ወቅት ይህ ነበር የነበረው። በሌላ በኩል እነ ስዊዘርላንድ እና ቤልጅየም በፌዴራሊዝም ሙከራ እየሠሩ የነበረበት ጊዜ ነው። እነ አክሊሉ የወሰዱት የፈረንሳዩን ሞዴል ነው።

የኦሮሞ ጥያቄ ዛሬ የተነሳ ይመስላቸዋል። ነገር ግን እነ አክሊሉ ነበሩ ያነሱት። የኢትዮጵያ ስቴት የአማራ ማንነት እየያዘ ስለመጣና ከኦሮሞ ማንነት ጋር የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ መጋጨቱ ስለማይቀር ማመሳሰል (assimilate) አለብን ብለው ነው የገፉበት። የእነ ኃይለሥላሴ የኃይል ጥያቄ ከዘውዲቱ ባል ጋር የነበረው ሽኩቻ ብቻ አልነበረም፤ በአገር ግንባታ ውስጥ እነዚህን ራስ ገዝ የሆኑ አካባቢዎች በማጥፋት እና በመበታተትን ኃይል እና አስተዳደር ማዕከል ማድረግ አለብን። ያንን ካደረግን ብቻ ነው አገራዊ ግዛት የምንገነባው። ያለበለዚያ ኃይል እና አስተዳደር ይበታተናል። ግብር አሰባሰቡ ይቀንሳል፣ በዜጎች እና በንጉሡ መካከል ያለው ግንኙነት ቀጥተኛ መሆን አለበት የሚል ሐሳብ በወቅቱ ተነስቷል። መካከል ላይ እየገቡ የንጉሡን ተቀባይነት የሚቀንሱ ኃይሎች መኖር የለባቸውም የሚል ነው።

የዚህ አገር ሕዝብ ታጋይ ነው፤ ራስን የመግዛት ነጻነቱን ይፈልጋል፤ በቀበሌ ደረጃ ሳይቀር። እኔ እንደማየው ለምሳሌ ጎጃሜነት ስሜቱ የራሱን ሰው አድምቆ የማየቱ። ለበላይ ዘለቀ ያላቸው አድናቆት ከምንድን ነው? በጣልያን ጊዜ ባሳየው አርበኝነት ብቻ አይደለም። ኃይለሥላሴ ላይ ላሳየው እምቢተኝነት ነው።

የብሔር ፖለቲካና የዜግነት ፖለቲካን አንድ ላይ የሚጠቀም ሞዴል መጠቀም አይቻልም?

እሱን ስትጨፈልቀው የአማራና የኦሮሞ ፖለቲካ ማለት ትችላለህ። ዛሬ የዜግነት ፖለቲካ የሚባለው በሌላ ሥሙ የመደብ ትግል ይባል ነበር ድሮ፤ የሚያቀነቅነው ኢሕአፓ ነበር። በዓለም ላይም ሆነ በአገራችን ኹለት አንቀሳቃሽ ሐሳብ ወይም አካሔድ አለ። የተጨቆነና የተገለለ ማኅበረሰብ በቡድን መንቀሳቀስን ይፈልጋል፤ በማንነት፣ በፆታ፣ በመደብ ላይ ተመርኩዞ ያስባል። የሚያስበው የተጨቆንነው በብሔራችን፣ በፆታችን ነው በማለት ነጻ የምንወጣው በቡድን ነው ከሚል ሐሳብ የሚነሳ ቡድን አለ።

በአንፃራዊነት አንድ ለአንድ በነጠላ በሚደረገው ውድድር የተሻለ ጥቅም አለኝ ብሎ የሚያስበው የማኅበረሰብ ክፍል ደግሞ፣ የአንድዮሽ (የዜግነት፣ የግለሰብ) ፖለቲካን ይመርጣል። ከ10 ዓመት በፊት አካባቢ የነበረው ክርክር የቡድን ነው የግል መብት የሚል ነበር፤ አሁን ደግሞ የብሔርና የዜጋ ሆነ፤ የዳቦ ሥም ነው የቀየረው እንጂ ተዋንያኑ ተመሳሳይ ናቸው።

ግን የመደብ ፖለቲካን በብሔር መንገድ መተንተን እንችላለን?

ተጫዋቾቹን ነው የምልህ፤ በኢሕአፓ ቁንጮዎቹ የአማራና ትግራይ ልኂቃን ነበሩ። ዛሬኮ ‹‹ዜግነት›› የሚሉ ግለሰቦች ኢሕአፓ ውስጥ ነበሩ። ዛሬ ‹‹ብሔር›› የሚሉት መኢሶን ነበሩ። ስትጨፈልቀው የትግራይ ብቻ ነው እንጂ መንገድ የቀየረው፤ የአማራና የኦሮሞ ፖለቲካ ነው።

የልኂቃን ስሌትም ነው፤ በየትኛው ብሔድ ነው በአቋራጭ ሥልጣን ሊመጣ የሚችለው ነው። ከዛ አንፃር የብሔር እንቅስቃሴ የምንለው የቡድን ነው። ፈጣኑ ሒደትም በቡድን መሰባሰብ ነው። የበላይ የሆነው ቡድን ግን አንድ ለአንድ የሆነውን ነው የሚፈልገው።

ከትላንት ለውጥ በኋላ ዜጋ የሚለው ቃል ስለመጣ ነው። እነብርሃኑ በቀደመው ምርጫ ላይ ምን ሲሉ ነበር? አሁንም ያሉ ተመሳሳይ ሰዎች በ97 ምርጫ ምን ዓይነት እንቅስቃሴ ያደርጉ ነበር? እነ ሌንጮ ምን ሲሉ ነበር? ግራም አለ ቀኝ፤ የኢትዮጵያ ፖለቲካን ጠርንፎ የሔደው የትግራይ፣ አማራና ኦሮሞ ፖለቲካ ነው። እና ይህ በሦስቱ ልኂቃን እንደ ስልታዊ እቅድ የሚደረግ ለውጥ እንጂ ተጫዋቾቹና ቡድኖቹ አንድ ዓይነት ናቸው ለማለት ነው።

ኹለቱን (የብሔርና የዜግነት ፖለቲካን) አብሮ ማስኬድ ይቻላል ወይ ለሚለው ይቻላል። እኛ የምንለው በጋራ ነጻ መውጣት የሚመጣው በጋራ በመንቀሳቀስ ነው። እነ ማርክስም እዚህ ላይ ጽፈውበታል። አንዱ ክርክር ብዙኀኑ የግለሰቦች ስብስብ ስለሆነ፣ ግለሰቦችን ነጻ ካደርግህ ሁሉም ነጻ ይሆናል የሚል ነው። ሌላው ግን አንድ ግለሰብ ራሱን ነጻ ማድረግ አይችልም። ዐሥሩ ጭቁን ተደምሮ ነው የአንድ አቅም ሊኖረው የሚችለው። ስለዚህ የተሻለው መንገድ ይህን ጭቁኑን መጀመሪያ እንደምር ነው። ለማ መገርሳ ያለውም መጀመሪያ መደመርን ከቤት እንጀምር ነው፣ ኦሮሞን ተወዳዳሪ ማድረግ የሚቻለው በግለሰብ ደረጃ ሔደን አይደለም። ይልቁንም በጋራ ተጠናክረን ከሔድን በኋላ ከዛ ድርድር ውስጥ መግባት እንችላለን ነው።

በአንድ ጎን ኦሮሞ ጭቁን ነው፣ ተጠቃሚ አልሆነም ይሉና መልሰው ደግሞ ፖለቲካውን ከተቆጣጠሩት ሦስቱ ቡድኖች መካከል ኦሮሞ አለበት የሚለውን ያነሳሉ። ኹለቱ አይጣረስም?

ክርክሩን ነው ምሳሌ የሰጠሁት። ክርክሩ በቡድን እና በግለሰብ መምረጥ መካከል የሚለው ነው። ትግሬዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ከሥልጣን ያላቸው ርቀት ስለሚቀያየር በቡድን እና በግለሰብ መካከል አቋማቸው ይቀያየራል።  የኦሮሞና አማራ ግን ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ቋሚ ነበር። ኦሮሞ በባሕል፣ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ የተገለልኩ ነኝ ብሎ ስለሚያስብ በግል ሳይሆን በጋራ ነጻ መውጣትን መርጧል። የቋንቋ፣ የሀብት ጥያቄዎችን በግለሰብ ደረጃ ልታገኛቸው አትችልም፤ በጋራ ኃይል ከገነባህ በኋላ ከፌዴራል መንግሥትም ሆነ በጎንዮሽ ድርድር ውስጥ ትገባለህ።

ከአማራ ወገን የሚመጣውም፣ በአብዛኛው አማራው ሲባል የከተማ ልኂቁ (urban elite) ነው። ፖስዋንግ እንደጻፈው ኹለት አማራ አለ፤ የብሔር (ኤትኒክ) አማራውና የባሕሉ (ካልቸራሉ)። የብሔር (ኤትኒክ) አማራው የገጠሩ አማራ ነው፤ ጎጃሜ፣ ጎንደሬ እና ወሎዬው። የባሕል (ካልቸራል) አማራ ደግሞ በመሪነት ላይ የነበረው ነው፤ እና ከተማ ያለው ነው። የአማራውን ፖለቲካ ወክሎ ሲከራከር የነበረው ከተማ ያለው ነው። የተሻለ ተጠቃሚ የነበረው።

የትግራዩን ስናመጣ፣ በ1970ዎቹ ከእኛ ጋር ነበሩ። ምክንያቱም የተገለሉ ስለመሰላቸው። ወደ ሥልጣን ከዛ በኋላ መጡ። የመለስ ሞት አካባቢ እየተለወጠ ነበር። ከግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ፣ ከቡድን ወደ ግለሰብ መጣ። ምክንያቱም የግለሰብ አቅም እየጨመረ መጥቷል ብሎ ስላሰበ። አሁን ደግሞ ሥልጣን ስላጡ ቀድሞ ወደ ነበሩበት ተመልሰዋል። የሦስቱን ማየት ያለብን በዚህ ሒደት ውስጥ ነው።

አባዱላ ገመዳ በጻፉት መጽሐፍ 1983 አካባቢ የኦሮሞ ፖለቲካ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር ብለዋል። የኦሮሞ ልኂቃን መካከል ሁሌም ያለው ክፍፍል የምንፈልገው ደረጃ ላይ እንዳንደርስ አድርጎናል ሲሉ ጄኔራል ዋቆ ጉቱ አንደነገሯቸውም ጠቅሰው ነበር። አሁንም እንደዚያ ዓይነት ክፍፍል እየታየ ነው። እርሶ የተቃወሙት የብልፅግና ፓርቲ የኦሮሞን የበላይነት ያመጣል በሚል መሆኑስ ለኦሮሞ ቆሜአለሁ እያሉ፤ እንዴት ነው ያስኬዳል?

የጋራ እንቅስቃሴ ከጥቂቶች ይልቅ ብዙ ለሆኑት ፈታኝ ነው። ምክንያቱም ቁጥሩ እየሰፋ በሔደ ቁጥር ይከብዳል፤ አነስ ካለ ግን ቀላል ነው። ለዛ ነው ለትግራይ ቀልሎ የቆየው። መቀስቀስና ማሰባሰብ ከሌላው ይልቅ ለኦሮሞ ከባድ ነው። አንዴ ማንቀሳቀስ ከቻለ ደግሞ ስኬታማ መሆን ቀላል ነው፤ አንዴ መተባበርን መፍጠር ከተቻለ።

እኔ ያደረኩት ምንድን ነው፤ ያንን በጥንቃቄ በማጥናት ሦስት ለውጦችን አይቻለሁ። የአባዱላን ስጋት ግን አልጋራም። ለቡድን ትልቁ ነገር ብሔርተኝነት (nationalism) ነው። ልኂቁ ቢከፋፈል እንኳ አገር መከፋፈልን አይፈቅድም። በለማ እና በዐቢይ ወይም በእኔ እና በዐቢይ መካከል ያለው ውጥረት አገሩን ይከፋፍላል ብሎ የሚሰጋ አለ፤ ግን አይሆንም። ብሔር እና ብሔርተኝነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ስለደረሰ ልኂቃን አገር የመከፋፈል አቅም አይኖራቸውም።

በእኔ፣ በዐቢይ እና በለማ መካከል የሆነው በ1970ዎቹ ቢሆን ተፅዕኖው ይከብድ ነበር። እና እሱ አያሳስብም፣ ስጋቱን [የአባ ዱላ ገመዳን] አልጋራም።

ብልፅግና ላይ የሚነሳው አንድ የጋራ ሥምምነት ሳይደረግ ወደ ውሕደት ከተገባ፣ ጥያቄዎችን በሙሉ ይዞ ስለሚገባ መቋቋም አይችልም ነው። በእርግጠኝነት ብልፅግና ፓርቲ አይዘልቅም። በአማራና በኦሮሞ መካከል ያለውን ሁኔታ በምን መልኩ ይዘውት እንደሚቀጥሉ ያሳስባል።

ሌላው በሽግግር ላይ ነው ያለነው። አገሪቱ በመፍረክረክ ላይ ባለችበት ሁኔታ የሚያስፈልገው ሰላማዊ ሽግግር ማምጣት እንጂ አዲስ ክርክር መጨመር አይደለም። የኦሮሞን የበላይነት ሊያመጣ ይችላል። የኦሮሞን ጥያቄ ሳይመልስ የኦሮሞ ግለሰቦችን የበላይነት ሊያመጣ ይችላል። ኢሕአዴግ በአንድ ፓርቲ፣ በሕወሓት የበላይነት የተያዘ ነበር፤ ብልፅግና ደግሞ በዐቢይ የበላይነት የሚያዝ ፓርቲ ነው፤ በአንድ ግለሰብ።

የኢሕአዴግ አብዩታዊ ዴሞክራሲን የሚተቹት በጣም የተማከለ ሥልጣን ይዞ ስለነበር ነው። የብልፅግና ፓርቲ አሠራር የበለጠ ሥልጣንን ማዕከላዊ ያደርጋል። አሁን ላይ ካያችሀት የክልል ሰዎች ከማዕከል ነው የሚሾሙት። አፋርን ሶማሌን ወክለው የሚመጡት የውክልና ሥልጣን የሌላቸው ናቸው። ይለያያል፤ ለምሳሌ አንድ ሰው ባሕርዳርን ወክሎ ሲመጣና ራሱን ወክሎ ሲመጣ ይለያያል። ራስን ወክሎ ሲመጣ በማንኛውም ጊዜ ሊሻር ይችላል፤ ሲወከል ግን ማንሳት የሚችለው የሆነ ቡድን አለ።

የእኛ ፍራቻ አንደኛ እኛንም ይጎዳል፣ በእኛ ምክንያትም ሌላው ይጎዳል ነው። የኦሮሞን ጥያቄ አይመልስም፣ ያድበሰብሳል። ያ ብቻ ሳይሆን በእኛ ሥም ሌላው ይጨፈለቃል የሚል ፍራቻ አለን።

ግን እንዳሉት ብሔርተኝነት ከመጠንከሩ የተነሳ የአንድ ሰው ግጭት የራ ብቻ ያልሆነበት ጊዜ በመሆኑ፣ በግለሰብ መቆሙና ሐሳብን እየገለጹ አየተከራከሩ መሔዱ አይሻልም ይላሉ?

ዛሬ ሰው ሲጣላ ብሔሩ ነው ያልከው፣ ድሮስ? እነምኒልክና ሌሎቹ ሲዋጉ የብሔር ነበር። ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ምን ያህል ጎላ የሚለው ነው እንጂ የብሔር ፖለቲካ ነው ድሮ ጀምሮ ያለው። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሁልጊዜም የብሔር ፖለቲካ ነበር፤ ሌላው ውሸት ነው።

የንጉሡ ጊዜ ራሱ ብታየው የአማራ፣ የኦሮሞና የትግራይን ነገር ንግሡ ተጠንቅቆ የሚከታተለው ነበር። ፍላጎት ነበረው፣ የብሔርን ጉዳይ አልፎ ከፍ ብሎ ከፖለቲካው ለማስወጣት። ተመልሶ ሲጠቃቀም ግን እናይ ነበር። በ1950ዎቹ እና 60ዎቹ ለውትድርና የኦሮሞን ጄኔራሎችና ወታደሮች ይመለምል የነበረው ከሞጃ፣ ከምንጃር እና መንዝ የሚመጣውን የሊኂቃን ግፊት ፍራቻ ነበር። የብሔር ፖለቲካ ሁሌም ነበር፤ አሁን ዴሞክራሲያዊ እየሆነ መጣ፤ ክፍት ሆነ። ሕገ መንግሥት ይፋ እና ሕጋዊ አድርጎ አይነኬነቱን ሰበረው።

ግለሰቦች የምንፈልገው ቀውሱን እንዲፈቱልን ነው፤ አስተማሪ አይደሉም አያስምሩልንም። ለፓርላማ ሰዎች ስንመርጥ እኛን ወክለው እንዲወዳደሩ እንጂ ራሳቸውን አይደለም። የውክልና ዴሞክራሲ ማለት ነው። መካከል የሚገቡ ተመራጮች እኛን ነው መወከል ያለባቸው፤ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በመሠረታዊ ደረጃ የብሔሮች እሽቅድምድም ስለሆነ።

የአገር ምሥረታ ላይ ነበርን፣ የአገር ግንባታ ላይ ገብተናል ወደ ዴሞክራሲያዊነት በመሔድ ሦስቱን ደረጃ ማሟላት ይጠበቅብናል። አገር ግንባታው ድርድር ይጠይቃል፤ ዴሞክራሲ ግንባታው የበለጠ ይጠይቃል። አንደ ሰው ተወካይ ሆኖ ሸገር ላይ ሶማሌን ካላመጣ ዋጋ የለውም። ለኢትዮጵያም አይጠቅምም። የመጠቀ አእምሮ ቢኖረው በአማራ እና በኦሮሞ መካከል ያለውን ክፍተት ካላጠበበ ዋጋ የለውም። የፖለቲካን ጥያቄ አይመልስም። የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሊቀርጽ ይችላል፤ የፖለቲካውን ጥያቄ ግን ሊፈታው አይችልም። የፖለቲካው ሽኩቻ በኢኮኖሚው ላይና በደኅንነቱ አውድ ላይ ምን ዓይነት ተፅዕኖ እንዳለው እናውቃለን።

ዞሮ ዞሮ በሕዝብ ተወክሎ አይደል እንዴ የሚመጣው?

በፓርቲው ሒደት ግለሰቦች ናቸው አባል የሚሆኑት። ሶማሌ መርጦ የብልጽግና ፓርቲ ውስጥ የሚያስገባው የለም። ዴሞክራሲያችን እንዲሰፋ ከተፈለገ ፓርቲ ውስጥም መንግሥት ውስጥም የብሔሩ ውክልና ሊኖር ይገባል። አንተ እያልክ ያለኸው መንግሥት ከተመረጠ በኋላ ክልሉን ወክሎ ይመጣል ነው።

የብልጽግና ፓርቲ ዓላማ ክልሎችን ማፍረስ ነው፤ ይኼ ከእነሱ የሰማሁት ነው። ምርጫውን ካሸነፉ የፌዴራል ስርዓቱን ያፈርሳሉ፤ ምንም ጥርጣሬ የለኝም። መቶ በመቶ ስለማውቀው ነው። ከእኔና ከለማ የበለጠ ለዐቢይ የሚቀርብ በዓለም ላይ የለም። ሐሳቡን እናውቀዋለን፣ ወደ የት እየሔደ እንደሆነ እናውቃለን። ተከራክረንበት በስሎ የመጣ እንጂ የሐሜት ጉዳይ አይደለም።

ፓርቲ ውስጥ ስላለው ስንመለስ ሶማሌ የተገፋ ነበር ለረጅም ጊዜ። እኛ እንዲቀርቡ ነው የምንፈልገው። የሶማሌ ሕዝብ ለእኔ ሥራ የሚለው ሰው ካለ እዚህ ተደራድሮ የሚያመጣው ውጤት ዋጋ አለው። ከዚህ በፊት ሶማሌም፣ አማሮች፣ ትግሬም ሌላውም ደርግ ውስጥ ነበር እኮ። ለምንድነው የብሔር ጥያቄ ያልተመለሰው ታድያ። ብሔሮች ግን ተወካያችን ነው የሚሉት ሰው በፓርቲም ውስጥ በመንግሥትም ውስጥ አልነበረም። ታላቁ ድርድር (grand bargain) የምንለው ነገር በብሔር ልኂቃን መካከል እስካልተፈጸመ ድረስ እና አብሮ የመኖር ቀመር እስካልተሠራ ተመልሰን ወደ እዛው ስርዓት ነው የምንሔደው።

የህዳሴ ግድቡን በተመለከተ የጻፉት ነገር ነበር?

አዎን! ከ10 ዓመት በፊት ወጣት ሆኜ የጻፍኩት ነው።

ግድቡን ለአገር ግንባታ መጠቀም ይቻላል ብለው ያስባሉ?

ይቻላል ግን ያለ አግባብ አደረጉት። አገርን ያነሳሳ እና አገራዊ ምናብ የፈጠረ ፕሮጀክት ነበር። ሙስናው ምን ያህል እንደተበላበት መገለፁ የሕዝብን ተነሳሽት አዳክሞታል። በየቀበሌው ዋንጫ ከዞረበት በኋላ ይቅርታ አታልለናችኋል ሲል ሕዝብን ይጎዳል። እሱን መልሶ ማንቀሳቀስ ሊከብድ ይችላል። እንዴት እናቅርበው ወሳኝ ነው። ስህተቱን ተቀብለው በሌላ መንገድ ጉዳዩን አላቀረቡም። ሕዳሴው ግድብ ተረስቷል፤ በሦስት ወር አንዴ ይነሳል እንጂ ማንም አይከታተለውም። ትልቅ ገንዘብ የፈሰሰበት ሐብት ነው። ከደኅንነታችን፣ ከፖለቲካችን ጋር ይያያዛል።

ጽሑፍ ውስጥ ያለኝን አቋም በማየት ግብጽ ያሉት ሰዎች አይወዱኝም፤ በጣም። በዛ ጽሑፍ ምክንያት እስከማሰር ድረስ ደርሰው ነበር። የዚያ ጊዜ የነበረው ክርክር መለስ ለፖለቲካው ፍላጎት ነው የሚል ነበር። እኔ ያኔ ከዛ አሻግሮ ማየት እንችል ይሆን የሚል አቋም ነበረኝ። የመለስ የግሉም ፍላጎት ቢሆን እንኳን የአባይ ጉዳይ ማንም መጣ ሔደ የሚኖር ነው።

ኢትዮጵያ ተከፍላ ሦስት አራት አገር ብንሆን እንኳን በሕዳሴው ግድብ ላይ አንለያይም። ለምሳሌ ኦሮሚያ አገር ቢሆን፣ አማራ አገር ቢሆን፣ ትግራይ አገር ቢሆን ራሱ በአባይ ላይ አንለያይም። ምክንያቱም ለግብጽ ኢትዮጵያ አገር መሆኗ ሳይሆን ጉዳይዋ ውሃውን አትያዙብን ነው። በናይል ጉዳይ ላይ ልዩነቶች ሊኖር አይገባም። የኢትጵያም ሆነ የእነሱ ፍላጎት አንድ ነው። ኤርትራም ከግብጽ ጎን የማትሆነው ለዛ ነው።

መለስ እንደዛ ሲል ለፖለቲካ አስቦ ነው ሲሉኝ ይሄ ወሳኝ ነው፣ መጨረስ ከተቻለ መለስ ለራሱ ጥቅም ቢያደርገው እንኳን እግሩን ባንይዘው ለአገር ነው ጥቅሙ ብዬ ነበር። መጀመሪያ እንደ ኢትዮጵያ ነበር የጻፍኩት ነገር ግን ከኦሮሞ ሰዎች ጥያቄ ተነሳብኝ። ግብጽ በትግላችን ልትረዳን ትችላለች፤ ለምን ትቃረናለህ ሲሉኝ በአባይ ጉዳይ ኦሮሞ፣ ትግሬ የሚባል ነገር የለም በሚል ‹‹ኦሮሞ ስለአባይ ለምን ግድ ይለዋል›› በሚል ጻፍኩ። በአብዛኛው የአባይ ገባር ወንዞች ከኦሮሚያ ነው የሚወጡት።

ኦሮሚያ ሪፐብሊክ ሆና ራሱ ብትወጣ እነዚህን ወንዞች ካልተጠቀመች ልታድግ አትችልም። እነዚህን ወንዞች የምትጠቀም ከሆነ ደግሞ ግብጽን መጋፈጧ አይቀርም። የመለስ ዜናዊ መንግሥት ቢሠራ፤ እንኳን ወያኔን ተክተን በኢትዮጵያ ውስጥ አይደለም፤ አገር ሆነን ብንወጣ እንኳ ተጠቃሚ ነን። ቤኒሻንጉል አገር ቢሆን እንኳ ግድቡ ስላለው ተጠቃሚ ነው። በአባይ ወንዝ ኹለት ባለጉዳይ ብቻ ነው ያለው። የላይኛውና የታችኛው ተፋሰስ አገራት። ይህን ነው ስል የነበረው፣ አሁንም በዛው አምናለሁ።

በዚያን ጊዜ ለነ`መለስም፣ ውስጥ ላሉ ሰዎችም እጽፍላቸው ነበር። ግብጽ ውስጥ አብዮት በነበረበት ጊዜ እድሉን መውሰድ አለብን እል ነበር። ግብጾች የሕግና የሎጂስቲክ መፍትሔ ስለሌላቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ግጭት ይጠቀማሉ። እኛ የመጠቀም አቅማችን እያመነመኑ ይሔዳሉ። ስለዚህ ጥቅማችንን ማስጠበቂያ መንገድ የሚሆነው የውስጥ ችግሮቻችንን መፍታት ነው።

ደጋግሞ የምጮኸው ክርክሮቻችን ከፖለቲካ ምህዳር እንዳይወጡ ማድረግን ነው። ከፖለቲካ ምህዳር ወጥቶ ደኅንነት ምህዳር ውስጥ ከገባ ግን ረዳት ያስፈልጋል። ያኔ እጇን ላታሾልክ [ግብጽ] ትችላለች። ለምንድን ነው ከእኛ ሰዎች ጋር በሕወሓት ጉዳይ ክርክር የገባሁት? የትግራይን ጉዳይ ወደ ፖለቲካ እንመልሰው በሚል ነው። ካልገባ ይጎዳናል።

በኤል ቲቪ በነበርዎ ቆይታ አሁን የኦሮሞ ተራ ነው ብለዋል፤ በቅድሚያ ኦሮሞ ነኝም ብለዋል፤ ይህን ለብሔሮች እኩልነት ነው የምታገለው ከሚለው ንግግርዎ ጋር እንዴት ያስታርቁታል?

ኹለት ነገር መካድ አያስፈልግም። የአማራ አመራር የነበረበት ኢትዮጵያ ነበር፤ የትግራይ አመራር የነበረበት ኢትዮጵያ ነበር። አሁንም ከፍተኛ ሥልጣን ላይ ያለው የኦሮሞ ሰው ነው። የኦሮሞ ተራ ወደ አምባገነንነት ከሔደ ያለውን ማስቀጠል ሊሆን ይችላል። ተራችን አይደለም ብሎ በመካድ ከኃላፊነት መሸሽ ተገቢ አይደለም። ሕውሐቶች እኛ እንደ ኢሕአዴግ ነው ስናስተዳድር የነበረው እንጂ ብቻችንን ስላልነበርን ለምንድነው ጣት የሚጠቆምብን ይላሉ። ይህን ለውጥ የገፋው የኦሮሞ ኃይል ነው። ይህን መካድ አያስፈልግም። ዐቢይ አማራ ወይም ትግሬ ቢሆን ቤተመንግሥት አይገባም ነበር። ኦሮሞ ስለሆነ ነው ጠቅላይ ሚኒስትር የሆነው።

ኦሮሞና አማራ አብረው በመሥራታቸው ነው አይደለም ቤተመንግሥት የገቡት?

አዎን አማራው ደግፏል። ለምሳሌ ደመቀ መኮንን ተመራጭ ነበር። ደመቀን እግሩን ስበው ያስቀሩት እነገዱ ናቸው። ምክንያቱም ትልቁ መንግሥት ላይ የነበረው ግፊት የኦሮሞን ጥቅም ካልጠበቀ ስርዓቱ ስለሚወድቅ ስምምነት ነበር፤ ኢሕአዴግ ውስጥ፤ ከተወሰኑ ሰዎች በቀር። ኦሮሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን ነበረበት የሚለውን ከኦሮሞ አቅጣጫ አይደለም የቀረበው። እኛ ለማ ወይ ገዱ ነው ስንል የነበረው፤ ኦሮሞ ካልመጣ አይቻልም ነው።

አሁን የኦሮሞ አመራር መጣ። ኦሮሞው ያገኘው ነገር ባይኖርም ተራው የኦሮሞ ነው የሚል ነገር በሰው ጭንቅላት መጣ። ለመግፋት መሞከር ኃላፊነትን ካለመወጣት እንጂ አትችለውም። የዐቢይ አይዲዮሎጂ ከእኛ ይልቅ ለአማራ ነው የሚቀርበው። ግን ቢሆንም መገናኛ ብዙኀን ሳይቀር፤ የኦሮሞው ሰውዬ ይላል። ይህ ከሆነ ምን አካካደን፤ ከሌላው ልኂቅ የተለየ ሥራ መሥራት አለብን። ፍትኅን፣ እኩልነትን ለማምጣት መጣር አለብን እንጂ የእኛ ተራ አልነበረም ማለት አይደለም።

ከዛ ይልቅ ፍትኀዊነትና እኩልነት ያለበት አገር፤ ብሔሮች በራሳቸው ቀዬ ራስን የማስተዳደር ሥልጣን የሚያገኙበት። እንደ ብዛትና አስተዋጽኦ ተመጣጣኝ ድርሻ እንዲኖራቸው ማድረግ። ተረኝነት የሚለውን ነገር፤ ሃምሳ ዓመት ታግለን የመጣውን እንደ ዳቦ ሰልፍ እልፍ ብለን የገባንበት አይደለም። በተራችን የተሻለ አሳይተናል ባይ ነኝ። የኦሮሞ ተራ ሁሉም ባለተራ የሚሆንት መሆን አለበት። ፍትኅና ዴሞክራሲ ስርዓት ስንገነባ ነው፤ ያ ከሆነ በእኛ ተራ ተወቃሽ አንሆንም።

የውጪ ጉዞዎት ዓላማ ምን ነበር?

ዓላማው ኹለት አጀንዳ ማስያዝ ፈልጌ ነው። አንደኛው የምርጫ ጉዳይ ነው። የሕወሓትን ምሽግ ከሰበርን በኋላ ስለምርጫ ነው ማውራት የጀመርነው። በተለይ ዐቢይ ሊቀመንበር ከሆነ በኋላ ወደ ምርጫ ገባን። ብዙዎች ለምን ስለ ምርጫ ያወራሉ ይሉ ነበር፤ አምጋነናዊ ስርዓት መጣል አንዱ ደረጃ ብቻ ነው፤ ዴሞክራሲ ስርዓት መገንባት ኹለተኛው፤ በመሃል ያለው ለመሸጋገሪያ የሚደረገው ምርጫ ነው። ይህም ሦስት አማራጭ አለው። ወይ ወደ ዴሞክራሲ ይሻገራል፣ ወይ አምባገነን ይሆናል ወይም ወደ ጦርነት ይወስደናል። ዴሞክራያዊ ምርጫ የሥልጣን ሽግግር ነው፤ የሽግግር ዴሞክራሲ ግን የአገርን እጣ ፋንታ ነው የሚወስነው።

እንደመጣሁ አካባቢ የምርጫ ጉዳይን ስወቅስ ነበር። አጀንዳ አደርገው ነበረ። ለዐቢይ ስለው የነበረው በተመረጠ በማግስቱ ስለምርጫ ነበር ማውራት የነበረበት። አሁን ኢሕአዴግ ተሰብስቦ ምርጫው ይካሔዳል ተባለ። ዐቢይን አነጋገርነው ነበር፤ ላይካሔድ የሚችልበት አጋጣሚ አለ ወይ። ግን ምርጫው በእርግጥ ይካሔዳል። ምንም ዝግጅት ግን አይታይም፤ ሁሉም ዘና ብሏል። በስድስት ዓመትም የሚካሔድ አይመስልም። ዝግጅት ያልተደረገበት ምርጫ ችግር ያመጣል። ወደ አገር ማፍረስ ነው የሚያደርሰን።

‹‹ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ›› ቢሆንም ዝግጅት መደረግ አለበት። በበኩሌ በጣም ደስተኛ ነኝ። ፍጥነቱን እጨምራለሁ። ቅስቀሳ እሠራለሁ። በሰላማዊ ትግል ጊዜ የፖለቲካ ስትራቴጂ የሥልጣን ግንኙነት እንዴት መሔድ እንዳለበት አሳያቸዋለሁ። አሁን እንደጥንቸል ነው የማስሮጣቸው። በሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቅስቀሳ ማድረግ ጀመረ። ያንን ሳይ እኔ ቁጭ ብዬ ደስተኛ ነበርኩ። ኦነግም፣ እነ እስክንድርም ገቡበት፤ ደስተኛ ነኝ። ስለምርጫው እንዲያወሩ ነበር የፈለኩት።

ይህን ለማድረግ ውጪ መውጣት ነበረብዎ?

እዚህ ማድረግ እችል ነበር። ግን ዳያስፖራው ፈልጎኝ ነበር፤ እዚህ ከተፈጠረው ክስተት አንጻር። እዛም ማስተካከል ያለብኝ ጉዳይ ነበር። በአንድ ድንጋይ ብዙ ወፍ መምታት ፈልጌ ነው። በጣም ትልቅ ተቋም አለኝ። በዛም 67 ከተሞች መዋቅሮች አሉኝ፤ ኦሮሚያ 200 ከተሞች መዋቅሮች አሉኝ። በማንኛውም ደቂቃና ጊዜ ማስተባበር እችላለሁ። ሊቀመንበር የሌላቸው በበጎ ፈቃደኝነት የሚንቀሳቀስ ቡድን አለ፤ ዳያስፖራውም ለዚህ ጥማት ነበረው። ካለው ሁኔታና እዛም መሔድ ስለነበረብኝ ተጠቀምኩበት እንጂ እዛ ባልሔድ አምቦ፣ ሻሸመኔ፣ ሐዋሳ ወይም ሌላ ቦታ ላደርገው እችል ነበር።

እንደ ጥንቸል አስሩጠዋቸው ይወጣሉ ወይስ ይወዳደራሉ?

አሳምሬ ነው የምወዳደረው። እወዳደራለሁ፤ ሮጠው ካሸነፉኝ እቀበላለሁ። ካሸነፍኳቻው ግን ሳይወዱ በግድ እየተንጫጩ አስተዳድራቸዋለሁ።

ለጨፌ ነው የሚወዳደሩት ወይስ ለፌዴራል፣ ምን ዓይነት ፓርቲ ነው የሚሆነው?

እሱ ምስጢር ነው፤ በኋላ ኪስ ውስጥ ነው ያለው። እየተወያየሁ ነው።

ምን ዓይነት ውይይት?

በኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል ትልቁ ነገር መቀራብ እንዲኖር ነው የምፈልገው። ከነዐቢም ጋር እየተወያየን ነው፤ ምን ማድረግ እንዳለብን። ኹለተኛ ጠንካራ የሆነ የብሔር ፌዴራሊዝም ላይ ያሉ ኃይሎች ድምጻቸውን ከፍ የሚያደርግ፤ ይህ ምርጫ ሪፈረንደም እንዲሆን ነው የምፈልገው።

እዚህ አገር ባለፉት 50ዓመታት ክርክሮች ነበሩ። ለሕዝብ ቀርበው ውሳኔ አልተሰጠባቸውም። ትንሽ ደኅና የነበረው የ97 ምርጫ ነው፤ እስቲ ሕዝቡ ይከራከርና ልኂቁ ሐሳብ አቅርቦ ሕዝብ ይወስን። ያኔ የትኛው የተሻለ ገበያ እንዳለው እናውቃለን፤ እና ሁሉም ወደዛ እያቀራረበ ይሔዳል። ዋልታ ረገጥነትን ዝም ብሎ በፓርቲ ሊሞረድ አይችልም። አትታገለውም፤ ገበያ ላይ አድርሰህ ሕዝቡ ዋልታ የረገጠውን ትቶ የሚሆነውን ይመርጣል። ይሄ ጽንፈኝነት የምትለው ሐሳብ የበላይ ሊሆን ይችላል። የአብን አመለካከት በአማራ ጽንፍ የያዘ ነው ወይስ ዋናው አመለካከት ነው፤ ቅኝት እንኳ አልተሠራም፤ እንኳን ምርጫ።

ጽንፍ የምትላቸው ሐሳቦች የብዙኀኑ ተቀባይነት አላቸው። እነ አሳምነው ሰው የገደሉ ጊዜ አማራ ክልል ውስጥ በተሠራ ቅኝት 80 በመቶ የሚሆነው ዐቢይ ነው ያስገደለው የሚለውን አምኖ ነበር። እዚህ ተቀምጠን እንደ ልኂቅ እብዶች ናቸው እንላለን፤ ግን በብዙ ማኅበረሰብ ክፍል ታምኖ ነበር። እና ይህን ሐሳብ ለመለየት ይህ ምርጫው ወሳኝ ነው።

በዚህ ምርጫ የፖሊሲ ክርክሩን ከፍ እናደርገዋለን፤ ቅስቀሳውን ራሱ ከዛሬ ጀምሮ፤ እኔም የዛሬ ሳምንት ጀምሮ ቅስቀሳ እጀምራለሁ። ገጠር አርሶ አደሩ ጋር፣ ዘላን እያሉ የሚተዉት ቀበሌና ወረዳ ነው የምንሔደው። ምክንያቱም አዲስ አበባ የተቀመጡ ሰነፍ ፖለቲከኞች ሊወጡ ይገባል። እንዲወጡ እናደርጋቸዋለን።

ኢሕአዴግ የነበረው አንድ ጥቅም ተቃዋሚው ከተማ ላይ ብቻ ነበር የሚወዳደረው። እኛ እስከ ሞያሌ ድንበር እንወዳደራለን። በእያንዳንዱ ጥግ እንወዳደርና እኩል እውቀትና አቅም ሁሉም ጋር እናወጣለን። በወረዳ ደረጃ እየሠራን ነው። በእያንዳንዱ ቀበሌ ያለውን ሰው ፍላጎት መሠረተ ልማት ነው፣ ፖለቲካ ነው፣ የትኛው ልኂቅ ነው የሚበዛው፣ የባህል ወይስ የሃይማኖት የሚለውን እናወጣለን። እያንዳንዱ ተፎካካሪ ፓርቲ ለእያንዳንዱ ድምጽ እንዲወዳደር ነው የምናደርገው።

ፓርቲው ሳይመሠረት ነው ቅስቀሳ የሚጀመረው፤ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ? ሐሳቡ ምንድን ነው?

ይህን አልመልስም። ዋናውና ትልቁ ዓላማችን በምርጫው ላይ የአገር ትኩረት እንዲመለስ ነው። በዳያስፖራው ባደረግነው አድርገናል። በአገር ውስጥም እናደርገዋለን። ኹለተኛው ዙር እንደተመራጭ የምንቀርብበት ነው። አሁን እንደተመራጭ አይደለም፤ አሁን አብዛኛው የምርጫውን ጠቀሜታ ላይ ነው። እና የሐሳብ ልዩነቶችን ነው ሳቀርብ የነበረው።

በፓርቲ ስንመጣ ፕላትፎርም ይዘን ነው። አንዱ ደኅንነት ነው። እንዴት ነው ይህን የምንፈታው፤ የብሔር ግንኙነትና የውጪ ግንኙነት እንዴት ይያዛል የሚለውን በደንብ አድርገን ሠርተነዋል። እሱን ከፓርቲው ጋር ይፋ የሚደረግ ይሆናል። አሁን የምናደርገው ስለምርጫው ጉጉት በሰው ውስጥ የመፍጠር ሥራ ነው የምሠራው።

በኦሮሚያ 200 ከተሞች ላይ አለኝ ያሉት መዋቅር የቄሮ መዋቅር ነው?

አይ! ከዛም በላይ ሔደናል።

ምን ዓይነት መዋቅር ነው?

መዋቅር አይደለም። እዚህ አገር የነበረው ችግር የእኛ ፖለቲካ ከኹለት ነገር ነው የወጣው። ከአቢሲኒያ እና ኮምዩኒስት ባህል ነው። ኹለቱም ከላይ ወደታች የሚወርድ ነው። አሁን እንደዛ አይደለም። አሁን ዘመናዊ ማኅበረሰብ ጎንዮሽ ትስስር ነው ያለው። እነዚህ በቄሮ ላይ ሞክረን አስፋፍተናቸዋል። ለምንገነባው ፓርቲ ግን አይደለም።

ከስድስትና ሰባት ዓመት በፊት ከኦነግ ጋር የነበረኝ ግጭት ከላይ ወደታች ተዋረድ አይሠራም የሚል ነው። የፖለቲካ ክፍሉ ሽባ ሆኗል፣ ተከፋፍሏል፣ ንቅናቄው ተሳስሯል ነው። ወያኔን መታገል የምንችለው በፖለቲካው ማኅበረሰብ አይደለም። ስናገር የነበረውም ጭንቅላትን ማምጣት ካቃተን እግር ማምጣት አለብን፤ ከዛ ጀርባና ሆድ። እግር ሰፊው ነው። መካከል ላይ የተማረው ኃይል አለ።

የፖለቲካ ማኅበሰብ ክፍሉ አለ፣ ቀጥሎ የሲቪክ ማኅበረሰብ አለ፤ ከዛ ነው ሰፊው ሕዝብ የሚመጣው። የእኛ ትኩረት ሲቪክ ማኅበረሰቡ ነው። እድር፣ እቁብ፣ ቤተክርስትያኖቹ፣ መስጂዶቹ፣ መምህራኖቹ ፖሊሶች፣ ዶክተሮች ናቸው አሸናፊውን የሚወስኑት። እነዚህን ካስተሳሰርክ በማኅበራዊ ሚድያ ካሳወቅካቸው፣ ኒኩሌር መሣሪያ በለው። እሱን ማግኘት ያስፈልጋል። እኛ በደንብ አጥንተናል። በደንብ አስተባብረናል ብለን እናስባለን።

ይህ ለእኛ ፓርቲ ብቻ አይለደም፤ ያስተባበርነው በተለያየ ፓርቲ ሊሳተፍ ይችላል። የርዕዮተ ዓለም ምርጫ የለንም። ዋናው ኦሮሙማን መደገፍ ነው። ከዛ ውጪ የትኛው ፓርቲ ደጋፊ ነህ የሚለው አያስጨንቀኝም። የትኛውንም ፓርቲ ደግፍ፤ በሚያደርገው ነገር ውስጥ የራሱን ፈጠራ ይጨምርበታል ወይ፣ የተግባር ሰው ነው ወይስ ተራ ወሬኛ፣ ሦስተኛ ከራሱ አልፎ ማኅበረሰቡን ያገለግላል ወይ ነው ጥያቄው። እነዚህ ሰዎች ወሳኝ ድርሻ ይጫወታሉ።

ዜግነቱ ጉዳይስ?

የሚመለሰው እዚህ ነው፤ ሒደቱ ተጀምሯል።

በምዕራቡ ዓለም ባካሄዱት ዘመቻ የገጠሞት ተቃውሞ የክርስትና እምነት ተከታይ የሆኑ የኦሮሞ ተወላጆች ራሳቸውን ከጃዋር አርቀዋል የሚል አስተያየት አስነስቶ ነበር፤ እዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?

የኦሮሞ ብሔርተኝነት ከመጀመሪያው ጀምሮ መሠረቱ ከአንድ ሃይማኖት የሚሻገር ነው። እኔን እንዳዛ የሚሉ ሰዎች ወያኔ በቀደደው ቦይ ሲፈሱ ነው፣ ምክንያቱም እነሱም እንደዛ ሲያስቡ ነው ጉድ የሠራኋቸው። የኦሮሞ አመራሮች ከአንድ ሃይማኖት የተሸገረ አካሄድ ነበራቸው፣ ታደሰ ብሩ ሲያደርግ የነበረውን ብታይ፣ አሰላ መንገድ ጌራ ላይ ሔዶ አባ ገዳዎችን ጠርቶ በሬ አሳረደ፣ በዛ ጊዜ የማይታሰበውን ከሙስሊምም ከክርስትያንም አብረው በሉ።

ኢትዮጵያ ከዚያድባሪ ጋር ግጭት በነበራት ጊዜ መገርሳ በሪ የሚባል የኦነግ አመራር ነበር። ወደ ሶማሊ ሲሔዱ ተይዘው ሙስሊሞቹን ጥላችሁ ውጡ ቢሏቸውም ያኔ ሙስሊሞቹ ታሪካዊ ነገር ፈጸሙ። እኛ አብረን የወጣነው እንደ ኦሮሞ እንጂ እንደ ክርስትያን ወይም እንደ ሙስሊም አይደለም፣ ስለዚህ ከለቀቃችሁ አብራችሁ ልቀቁን ከጨረሳችሁ አብረን ጨርሱን ብለው መውጣት ሲችሉ አብረው ተገደሉ።

ይህ ትርክት የሚፈጥረው ነገር አለ። ያኔ የፈጠረው ብሔርተኝነት ውስጥ ነው እየተንቀሳቀስን ያለነው። ኦሮሞን በክልልና በሐይማኖት ነው ለመከፋፈል የሚሞከረው። ለምሳሌ የማስተር ፕላኑ ጉዳይ ብንመለከት አብዛኛው የሸዋ መሬት ቢሆንም የተወሰደው ሐረርጌ ሲያልቅ የነበረው ለምንድነው? ማስተር ፕላኑን ተቃውሞ የታገለው ወጣት አብዛኛው አዲስ አበባን የማያውቅ እና ስንዝር መሬት እንደማያገኝ የሚያውቅ ነበር።

የአማራው ልኂቅ ትንሽ ተምታቶበታል። ዙሩን በጣም ስላጦዝነው ለመድረስ አየሞከረ ነው። ባለፉት ኹለት ዓመት የተሞከረውን ስናይ ቀላል መስሏቸው የሞከሩት የብሔር ፖለቲካ ተሞከረ ፈነዳባቸው፤ ስለዚህ አሁን ከብሔር ፖለቲካው አፈግፍገዋል። የዜጋ ፖለቲካም አለ አማራው፤ ይህንን አልሆን ስላለ ቀጥሎ ያለው የሃይማኖት ፖለቲካ ነው። በኦርቶዶክስ ያለውን የቋንቋ ክርክር አነሱና እያሰፉ እየገፈፉ ለመሔድ እየተፈለገ ነው ያለው፤ ግን አልሠራም።

በዳያስፖራው የሆነው የሚገርም ነበር። እዛም ሃይማኖታዊ አቅጣጫ ማስያዝ ፈለጉ። እዚህ የተጀመረው ነው እዛ የሔደው በነገራችን ላይ። በቀዳሚነት ኢዜማና አዴፓ ናቸው የያዙት። ለምሳሌ የኦርቶዶክሱ ተቃውሞ አማራ ክልል ላይ ሲደረግ ነበር፤ በአማራ ክልል መንግሥት ትብብር። በዳያስፖራውም እንደዛው። ጨዋታውን ሐይማኖት ውስጥ ማስገባት መፈለጉ፤ እርግጥ ነው የኦሮሞን ልኂቅ ለመምታት የሚደረግ ነው።

የመጀመሪው ኹለት ሦስት ክዋኔ ላይ ቄሶች በብዛት ቢሳተፉም ከአራተኛው ስብሰባ በኋላ እየቀነሱ መጡ።  የተጠበቀው እነርሱ የሐይማኖት መፈክርና እርግማን ይዘው ይመጣሉ ነው። ከእኛ በኩል ቀድመን ግምገማ ሠርተን አውቀናል። በጣም አፍላ የሆኑ ወጣቶች እንቁላል እየተወረወረባቸው ሲያልፉ ነበር። ይህን ሲመለከቱ ለነበሩ እና በማሃላቸው ለነበሩ የሃይማኖት መሪዎች ላይ ያ ጫና ነበረው። ኹለተኛ የሐይማኖት አባቶች ባሉበት ጸያፍ ቃል ይናገሩ ይሳደቡ ስለነበር ቀስ በቀስ እየራቁ መጥተው [የሃይማኖት አባቶች] ከቬጋስ በኋላ ምንም ቄስ አልነበረም።

ኹለቱ አማራ ነው የተንቀሳቀሰው፤ የባህሉና የብሔር አማራው። አንዱ ወግ አጥባቂ ነው፤ ሌላው ደግሞ አራዳ ነው። የምንወቀሰው ጥላቻ የሚዘሩ ናቸው እየተባለ ነው፤ የበለጠ ጥላቻ ነበር ይሰማ የነበረው ግን። ፈረንጆቹ የሚሆነውን ሁሉ እያዩ ነበርና ያኔ ማን በጥላቻ የተሞላ እንደነበር ተገለጠ። ኢትዮጵያዊነት እያሉ ስድባቸው ግን መጥፎ ነው፤ የኦሮሞ ጥላቻ ነው።

በመሆኑ የኢትዮጵያ ካምፕ ውስጥ የቀረው ኦሮሞ እየወጣ ነው። እኔ በጠራሁት ጉባኤ ላይ አንድ ቄስ ሊመርቁና ሊገስጹን መጡ፤ በግልም ብዙ ጥያቄ አነሱ። ግጭት አያስፈልግም ሊሉን ነው የመጡት። ግን ሲመለሱ አባረሯቸው። አባራሪው ግን ውጪ ሲቃወም ነበር። በአንድ ቤተክርስትያን ውስጥ ለአንዱ መርገም ትክክል ሆኖ ለሌላው መመረቅ ኃጢአት ሲሆን ቀውስ ውስጥ ከተታቸው። በዛ ተሳክቶልን ነበር፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብም ለዓለም ሕዝብም በራሳቸው ቃል፣ በራሳቸው መፈክርና ገንዘብ መቀስቀስ ቻልን።

ቀድመን በመረዳታችን በየቦታው ሦስት አራት አዳራሽ ነው የተከራየነው። አንዳንዱን እንነግራቸዋለን፤ እሱን ሔደው ያሰርዙታል ሌላው ይቀጥላል።

ከአረብና መካከለኛው ምሥራቅ አገራት የምትቀበለው የገንዘብ ድጋፍ እንዳለ ተደጋግሞ ይነሳል፤ ትክክል ነው?

ከመካከለኛው ምሥራቅ የተባለው እኔ ከእነሱ አይደለም ከአጎቴ ገንዘብ ብወስድ ኖሮ እዚህ አልደርስም ነበር። እኔን ስኬታማ ያደረገኝ በጣም እብሪተኛ (Arrogant) መሆኔ ነው።

ያን ትግል በማደርግበት ቦታ ብዙ የጎረቤት አገራትና ሌሎችም ጥያቄ ያቀርቡልኝ ነበር። ግን ለስኬቴ ምስጢር በማንም ላይ ጥገኛ አለመሆን ነው። የእኛን ትግል ያዳከመው አንዱ ኤርትራ ላይ ጥገኛ መሆናችን እና ለሕዝቡ መታገለ ትቶ ውጪ ውጪ ማየቱ ነወ።

የመካከለኛው ምሥራቅ ይቅርና የምዕራቡ ስሙኒ እኛ ጋር የለም። ይህን እንቅስቃሴ ከጀመርኩበት ጊዜ አንስቶ ቡና የጠጣሁባት ደረሰኝ አለ። አሁን ባለፈው ስሔድ ይወራ ነበር፤ ስስቅ ነበር። ይሄ ያልተደራጀ ዝም ብሎ የሚጮኽ ቡድን ተውና ሕወሓት እኔን ጸጥ ለማድረግ አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ዶላር ለአንድ ድርጅት ይከፍሉ ነበር።

ይህን ስለምናውቅ ቀዳዳችን ኹለት ብቻ ሲሆን ይህም የፋይናንስ እና የሚዲያ ሕግ ነው። የአሜሪካ ስርአት መሠረቱ ግለጽ ነው። ይቅር እና ጥቁር ግራጫ መዝገብ ሳይሆን በነጩ መዝገብ መሃል ላይ መሆን ነው ያለብን። በቦርዳችን ውስጥ ራሱን የቻለ ልምድ ያላቸው ሰዎች የሚሠሩበት የኦዲት ኮሚቴ ነበረን። የራሳችንንም ስለማናምን አንድ ትልቅ ድርጅት ዓመታዊ ገቢአችን ላይ አምስት በመቶ እየከፈልን ነበር የሒሳብ ሥራችንን የምናሠራውና የምናስፈሸው።

ለብሮድካስት ሲባል አሜሪካ እያለን ሳተላይት ከተለያየ አገራት እንከራያለን። እነሱ የሚሉት የፋይናንስ ተጋላጭነት ቢኖር እሱን ይመዛሉ እንጂ ሊገድሉኝ አይሞክሩም ነበር። በፖለቲካ ሊገድሉኝ ስላልቻሉ ነው በአካል ሊገድሉኝ የሞከሩት። ሚዲያዎችም አንድ ነገር ቢያገኙ ይጠቀሙት ነበር። እኔ ግን ጥንካሬዬን አውቃለሁ። የኔ ብርታት አረብ አገርና ገንዘብ ወይም የአሜሪካን ዶላር አይደለም፤ አርሶ አደሩ፣ ተማሪውና ወጣቱ ነው።

ባለፈው የተከሰተውን አስመልክቶ መከበብህን በሚመለከት መንግሥት ኃላፊነት ይውሰድ ብለህ ነበር። የ86 ሰዎች ሕይወት አልፏልና ያንን ተከትሎ መምጣቱ፤ በግጭቱ ቄሮም ተሳታፊ ነበርና እንደ ቄሮ መሪነትህ አንተን እንደ ተጠርጣሪ ማየት አይቻልም?

አየህ! እኔ ላይ ሊወረውሩ የሞከሩት ቦንብ እጃቸው ላይ ሲፈነዳ እጃቸው በመቃጠሉ እኔ ላይ ሊያሳብቡ ነው የሞከሩት። ሊገድሉኝ ፈልገው ነበር፣ አልሠራም። እኔ ሁሉንም ሰው የምጠይቀው እኔ ቦታ ቢሆኑ ምን ያደርጉ ነበር ብዬ ነው። ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ናቸው የአንተ ሕይወት ላይ የሚደርስ አደጋ ለአገር አደጋ አለው ብለው ጥበቃ ያስመደቡት። እኔ ልጆቹ እየሰለሉኝ ነው የሚል ጥርጣሬ ሁሉ ስለነበረኝ ብከራከርም መቆየት አለባቸው በሚል ክርክር ነበር። ክስተቱ ከመፈጠሩ ቀናት በፊት ራሱ ኃይል እንጨምርልሀለን ተብሏል። በእኩለ ሌሊት ሳትነግሩት ውጡ ሲባሉ አንተ በእኔ ቦታ ብትሆን ምን ታደርጋለህ?

በእኔ ቦታ መሆን ይቅርና አንድ ሰው ከውጪ የአጥርህን በር ቢደበድብ ምን ታደርጋለህ? ባደኩበት አገር 911 ትወደውላህ፣ እዚህም ፖሊስ ጋር ወይም ቀበሌ ትደውላለህ፤ ካልሆነ ኡኡ ነው የምትለው። እንጂ መቼም በሩን ከፍቶ ገብቶ እስኪገድልህ አትጠብቅም። ይሄ የሰው ተፈጥሮ ነው።

እኛ ፕሮቶኮል ተከትለናል። መጡ፤ ልጆቹን ውጡ ሲሏቸው ኮማንደሩ ጋር ደወሉና ካረጋገጡ በኋላ ለኔ መጥተው ነገሩኝ። ኮማንደሩን ማን እንዳዘዘው ስጠይቀው ነገረኝ። እሱ ላዘዘው ሰው ስደውል አያነሳም፣ ለደኅንነት ኃላፊው ደወልኩ አላነሳም፤ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ደወልኩ አላነሳም፣ መከላከያ ጋር ደወልኩ አላነሳም፣ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ጋር ደወልኩ አላነሳም። የተለያዩ ሰዎች ጋር ስደውል ማንም አላነሳም። እንደውም መፈንቅለ መንግሥት ነበር የመሰለኝ፣ እነሱን ጨርሰው እኔ ቅስቀሳ እንዳላደርግ የመጡ ነበር የመሰለኝ።

መጨረሻ ከውጪ አንድ ሰው ደወለልኝና ከመንግሥት እንደሆነ አረጋገጠልኝ። እና የሆነ ሴራ ነው ተነቅቶባቸዋል ፈርሷል፤ ልጆቹን ተዉና ቁጭ በሉ ጠዋት ትሄዳላችሁ አልኳቸው። ኃይል ጨምረው መጡ። በዛኛው ፌዴራል ፖሊስ በዚህ አዲስ አበባ ፖሊስ ለመግባት ሞከሩ። የእኛ ልጆች ንቁ ናቸው፤ ምክንያቱም ንቁ ሁኑ ብለዋቸዋል። ኮማንደሮቹ ቤቱን ከበው ያዙ።

የኔ ፍርሃት ተኩስ መከፈቱ አይቀርም፤ ከተከፈተ አይደለም የታጠቁት እዚህ ሰፈር ያለው ደሃ ሊያልቅ ነው። ስለዚህ ለሕዝብ መንገር ነበረብኝ። እኔ ካደረኩት የተሻለ አደርጋለሁ የሚል ካለ ይምጣ። የዛን ጊዜ የመጣው ይምጣ ብዬ ‹‹በለው!›› ብለው ተጠያቂ ሆኜ እስር ቤት እሆን ነበር። በሞራልም በሕግም ተጠያቂ እሆን ነበር። ለመንግሥት ነግሬ መንግሥት ስላልሰማ ራሴን ተከላከልኩ ብል፤ በዛ ውስጥ ወታደር ብቻ ሳይሆን ልጆችና ሽማግሌዎች ቢያልቁ አሁንም ከዛ አላመልጥም ነበር።

በእለቱ ሰላማዊ ሰልፍ እየተካሔደ ነበር። እኔም አምስት ሰአት አካባቢ ‹አልሞትኩም፤ የሆነው ይህ ነው› ብዬ ተናገርኩ። ከዐቢይ ጋር ያለንንም ጉደይ ጎልቶ ስለነበር ወንድም ነን እንፈታዋለን አልኩ። የግለሰብ ንብረት አትንኩ፣ አትጋጩ አልኩኝ። እንዴት መንግሥት ይደፈራል የሚል ቅስቀሳ በማግስቱ ተጀመረ። ብዙ ቦታ የታጠቁ ሰዎች ቄሮዎች መንገድ ክፈቱ ስንላቸው መንገድ ሲከፍቱ ተገድለዋል። ቁጥሩንም አይተነዋል አብዛኛው የሞተው ኦሮሞ ነው።

ለተፈጠረው ችግር በሙሉ ተጠያቂው የፌዴራል መንግሥት ነው። እኔን ማሰር ከፈለጉ እኔን አይደለም ራሳቸውን ሰው የሚጠብቁኝን ማዘዝ ይችላሉ። በሕወሓት ጊዜ ኮረኔል ደመቀን ለመያዝ በሌሊት ሄዱ፣ እሱም ተከላከለ፤ ሰው ገደለ። እሱን እንደ ጀግና የሚያቀርቡት ሰዎች እኔን ከሰሱኝ። እኔ ተጠያቂ የምሆነው በመትረፌ ነው፤ ሊገድሉኝ ፈልገው ነበር ተረፍኩ።

እኖራለሁ፤ አሸንፋቸዋለሁ። ምክንያቱም እውነት አለኝ፤ ሕዝብ አና እውነት ይዤ ነው የምንቀሳቀሰው። ኹለተኛ በጉልበት አይደለም በጭንቅላቴ ነው የምጠቀመው። ወደ እነርሱ ያንባርቃል በዚህ በቀጠሉ ቁጥር። ተጠያቂ የሚሆነውና መሆን ያለበት መንግሥት ነው።

እዚህ አገር እየሆነ ያለው ምንድን ነው፤ የሰኔ 16ቱ ምን እንደሆነ አናውቅም፣ የጄነራሎቹ ግድያን አናውቅም፣ የአማራ ክልል አስተዳደር ግድያንም ምን እንደተፈጠረ አናውቅም። ክስተት ይፈጠራል፤ ሰዎች ያልቃሉ እንቀጥላለን። የመንግሥት ድርሻ ምንድን ነው? መንግሥት ተጠያቂ መሆን አለበት።

ቄሮን መደበኛ አደረጃጀት አደርጋለሁ ብለው የነበረ ቢሆንም ተግባራዊ አልሆነም ለምን ይሆን?

አስበነው ነበር ተውነው። ምክንያቱም መተማመን አልተፈጠረም። በመደበኛ መንገድ ማደራጀሩ ቄሮን ማስመታት ነው የሚሆነው። እዚህ ስመጣ ስወተውት የነበረው ፖለቲካው ከትግል ወደ አመራር ይሻገር የሚል ነው። አሁን መንግሥት እያደረገ ባለው ስህተት ወደ አመራር መሔዳችን ቀርቶ፣ ከፖለቲካ ምኅዳሩ ወደ ደኅንነቱ ምህዳር ገብተናል። በዚህ ሁኔታ ተመልሰህ ያንን ማድረግ ሰው ማጋለጥ ነው።

ቄሮን መደበኛ አለማድረጌ የሠራሁት ትክክለኛ ነገር ነው። ግን መደበኛ ማድረጋችን አይቀርም፤ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ። ፖለቲካውን ከትግል ስናርቀውና መደበኛ ሲሆን ቄሮ በተለያየ ሲቪክ ማኅበረሰብ ውስጥ ይገባል። ከዛ ውጪ ቄሮ የተባለ ድርጅት አይኖርም።

የለማ መገርሳ ተቃውሞ ከምን የመነጨ ወይም ምን ለማድረግ ታስቦ ይመስሎታል?

በዚህ ውሳኔአቸው ዙሪያ ምንም ማለት አልፈለግም። ነገር ግን ባለፉት የፖለቲካ ዘመናት የለማ መገርሳን ያህል የኢትዮጵያ ባለውለታ የለም። እናንተ የምታውቁትና የማታውቁት፤ ትእግስት እና ቁርጠኝነት ያለው ሐቀኛ ሰው ነው። እኔ በእድሜም ቢሆን ባለን ግንኙነት ዐቢይን ነው የምቀርበው። ለማ ጭምት ስለሆነ መደበኛ ሥራ እንጂ ብዙ ቅርበት የለንም።

ያኔ ኢሬቻ ላይ ከገጠመን አደጋ በኋላ ስርዓቱ እንደሚፈርስ ባውቅም ሕዝብ የሚያምንበት ሰው ወደፊት እንዲወጣ እጠብቅ ነበር። በዛ ልክ ይዞ መውጣት ለኦሕዴድም ለኢሕአዴግም ለኢትዮጵያም ከፍተኛ ባለውለታ ነው። የኦሮሞ ሕዝብ እንደ አውሬ የሚያያት፣ የሚንቃትን ኦሕዴድ እድል እንዲሰጣት፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብትንትኑ እንዲወጣ የሚፈልገውን ኢሕአዴግ እድል እንዲሰጠው ያደረገ ሰው ለማ ነው። የዐቢይ እናትን ህልም እውን እንዲሆን ያደረገው፤ ዓቢይን የመረጡት ለማ እና አባዱላ ናቸው እንጂ ድርጅቱ አይደለም።

ለማ አሁን ባለው ፖለቲካ ትልቅ ክብር፣ በሕይወት እያለ ሐውልት ሊቆምለት የሚገባ ሰው ነው። ባለፈው ኹለት ዓመት የነበረው ግጭትና ውጥረት እንዲሁም የደረሰበትን መዋረድ በጣም ጥቂት ሰዎች ናቸው ሊቋቋሙና ፈገግ እያሉ ለማለፍ የሚችሉት። አሁንም ቢሆን የትግል አጋሩ የሆነውን የዐቢይን ብልጽግና መመሥረቱን ጠበቆ ነው እንጂ የተቃወመው፣ ቀድሞ ቢናገር ኖሮ ብልፅግና የሚባል ነገር አይኖርም ነበር፤ ሊያስቆመው ይችል ነበር። ድርጅቱ ካለቀ በኋላ ነው አቋሙን ግልጽ ያደረገው። የራሱን ሞራልና ሕሊና ጠበቀ፣ የወንድሙንና የትግል ጓዱን ፍላጎት ጠብቆ ነው ያደረገው።

ግን አሁንም ለማ ላይ የሚደረገው ዘመቻ የኔን አቋም በድጋሚ ነው ያረጋገጠው። ኦሮሞ ከሆንክና ለመርህ እና ለሕዝብህ የቆምክ ከሆንክ፣ ኢትዮጵያ ብለው የሚምሉ ሰዎች ይጠሉሃል። የሚጠሉህ ለማ ስለሆንክ ገመዳ ስለሆንክ ወይም ጃዋር ስለሆንክ አይደለም፤ ለኦሮሞ ሕዝብ መብትና ለእኩልነት የምትቆም ከሆነ፣ ኃይሌ ፊዳን እንደጠሉት፣ ታደሰ ብሩን እንደሰቀሉት፣ ሌንጮ ለታን እንዳብጠለጠሉት ያብጠለጥሉሃል። ለማን እላይ ሰቅለው ይዘውት የነበሩትን ሰው፣ ለመርህ ስለቆመ ብቻ ዛሬ የሚደረግበት ዘመቻ ሳይ ለዚህ ትውልድ ምን ዓይነት አዲስ ትምህርት መጣ ነው ያልኩት።

እና የእሱን [የለማ መገርሳን] ያህል የአገር ባለውለታን ምንም አያደርገውም፤ ይልቁንም ያጠናክረዋል። ግን ለተወሰኑ ልኂቃን ኪሳራ ነው የሚመስለኝ። ለማ ግን ወደፊት ከፍተኛ ድርሻ ይዞ እንደሚቀጥል ጥርጥር የለኝም።

ፖለቲካው እንጂ ኢኮኖሚው ጉዳዮች ላይ አስተያየት ሲሰጡ አይሰማም የኢኮኖሚ መፍትሔ ምንድነው?

የእኔ እይታ የኢትዮጵያ ችግሮች ሁሉ ምንጭ ፖለቲካው ነው። የአገራችን ችግር ሦስት ማእዘን ነው። ፖለቲካው ከላይ አለ፣ ኢኮኖሚው እና የደኅንነት ችግሩ ደሞ ሌሎች ቀውሶቻችን ናቸው። የተበላሸ ፖለቲካ በተለይ በፖለቲካ ልኂቃን መካከል ልዩነት እና ሽኩቻ ሲኖር ሕዝባችንን ያጋጫል። የደኅንነት ችግር ሲኖር ኢኮኖሚውን ይነካል፤ የመዋዕለ ነዋይ ፈሰሱን ይጎዳል፣ ልማትን ያቀጭጫል።

የደኅንንት ቀውስ የፖለቲካ ሥራውን ትተው የደኅንንት ሥራ ውስጥ እንድትገባ ያደርጋል። ልማትና ፖሊሲ ላይ እንዳያነጣጥሩ ያደርጋል።

የኔ ድርሻ መሆን ያለበት ነገ የምናፈርሰውን መሰረተ ልማት ዛሬ መገንባት ሳይሆን፣ ነገ ቦንብ እንዳይኖር የፖለቲካውን ችግር መፍታት አለብን ባይ ነኝ። ስጽፍበት የነበረው ችግርም ይህ ነው። ኃይለሥላሴ ብዙ ነገር ሠርተዋል፣ የፖለቲካ ችግር ግን ባለመፈታቱ የሠሩት ወድሟል።

እዚህ መሠራት ያለበት ትልቁ ሥራ የፖለቲካ ነው። በዐስር ዓመት ኢትዮጵያ ካለች ስኬት ነው ለእኔ። የእኛ  ሥራም በ10 ዓመት ውስጥ ኢትዮጵያን የምትባል አገር መኖሯን ማረጋገጥ ነው። ፖለቲካችንን ማቆየት ከቻልን ቀጣዩ ትውልድ ከድህነት ይወጣል። ፖለቲካችንን ካላስተካከልን ግን የዛሬ 10 ዓመት የኢኮኖሚ እድገት ሳይሆን ስለመኖር ነው የምናወራው፤ እሳቱን የእርስ በእርስ ጦርነቱን እንዴት እናጥፋው የሚል ነው ጥያቄ የሚሆነው።

 

ቅጽ 2 ቁጥር 57 ኅዳር 27 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here