ቴአትር – በብዝኀነት እይታ

0
978

የተለያዩ ባህሎች ባሉበት አገር፣ ጥበብ ባለ ብዙ አማራጭና ባለ ብዙ ቀለም መሆኗ አይቀሬ ነው። ይህም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገራት ከውስጥ እንዲሁም ከውጪ ገቢ ለማግኘት ምቹ አጋጣሚም ሆኖ ሊያገለግል ይችላል። ከምንም በላይ ግን በሕዝቦች መካከል ትውውቅና ትስስር እንዲፈጠር፣ ሰዎች ራሳቸውን የሚያዩበት መስታወት፣ ያለፈውን የሚቃኙበት ማስታወሻ፤ ለወደፊቱም አቅጣጫ ጠቋሚ በመሆን ያግዛል፤ ጥበብ።

የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በመጣ ቁጥር በብዙዎች ዓይነ ሕሊና ተቀርጾ የሚታየው ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የተውጣጡ ተወዛዋዦች የሚያቀርቧቸው ባህላዊ ክዋኔዎች ናቸው። ምንም እንኳን ጥቂት ለማይባሉ ወራት ተዘጋጅተውና ብዙ ወጪ ተደርጎባቸው የተከናወኑ የጥበባዊ ትርዒት አቅርቦት መሰናዶዎች ቢኖሩም፤ በበዓሉ እለት ግን የተወሰነ ምንአልባትም ከአምስት ደቂቃ በታች ነው በተመልካቾች ቴሌቭዥን መስኮቶች ብቅ ብለው እልፍ የሚሉት።

በአንጻሩ ግን በቋሚነት እነዚህን ዓይነት የባህል ክዋኔዎችና ትርዒቶች ለእይታ ማቅረብ ላይ እንዲሠራ ይጠበቃል። ለዚህ ደግሞ ቴአትር ቤቶች፣ የፊልም ማሳያ ዘመናዊ አዳራሾች፣ የባህል ውዝዋዜና ጭፈራ ቤቶች፣ የሥነግጥምና ጥበባዊ ምሽቶች ምቹ አውዶች ናቸው። ነገር ግን ምን ያህል መጠቀም ተችሏል?
ደራሲ፣ ገጣሚና ጸሐፌ ተውኔት አያልነህ ሙላት ‹‹ብዙ ብሔረሰብ ያለባት አገር ኢትዮጵያ የኪነጥበብ ደሀ ልትሆን አትችልም።›› በማለት ይጀምራሉ። ነገር ግን የጥበብ ሥራዎች የሚከወንባቸው መድረኮች ላይ ይህን ለማዳበር የሚያስችል ሥራ አልተተገበረም ባይ ናቸው። የአያልነህ እይታ በተለይም የአውሮፓን አካሔድ መሠረት ያደረገ የትምህርት ስርዓት በመኖሩ ራስን ለመመልከት አላስቻለም የሚል ነው።

ብሔሮች በክልል እየተደራጁና ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ሥልጣንን እየያዙ/የያዙ በመሆኑ የራሳቸውን ባህል ማዳበር ላይ ሊያተኩሩ ይገባል፤ ይሁንና ያንን ሲያደርጉ አይታይም የሚሉት አያልነህ በዚህ ክልሎችን ይወቅሳሉ። ‹‹እነርሱ ክልሉን የሚያዩት በራሳቸው የግዛት አካባቢ እንጂ ምን መዳበርና መበልጸግ አለበት የሚለውን አያዩም። ለኅብረተሰቡ ምን አቅርበሃል ቢባሉ ምንም ነው።›› ሲሉ ያክላሉ።

የአንድ አገር እድገት በተገነቡ ሕንጻዎችና በተዘረጉ አስፋልቶች ብቻ የሚለካ ሳይሆን በሥነ ጽሑፍ እድገት አንጻርም የሚታይ ነው። አያልነህ እንደሚሉትም፤ በራስ ቋንቋ መናገር መቻል ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ ዋጋ የለውም። እንደ ብሒሉ ‹‹ወፍም ቋንቋ አለው›› ትልቅነትንም በዛ መለካት ተገቢ እንዳይደለ ይገልጻሉ። ዛሬ ላይ መነጋገሪያ ሆነው እያገለገሉ ያሉ ቋንቋዎችም፣ ትግረኛ፣ ኦሮምኛ፣ አማርኛ፣ ሶማሊኛ ወዘተ፤ ዘመናት ሲነገርባቸው የቆዩ ናቸው።

‹‹ልዩ ሊያደርጉት የሚችሉት አንድ ነገር ብቻ ነው።›› ይላሉ አያልነህ፤ ‹‹ቋንቋውን የሥነ ጽሑፍ ቋንቋ ማድረግ።›› በቋንቋ ብቻ ሳይሆን ክውን ጥበባቱ፣ የብሔረሰቡ እሴትና ዋጋ የሚሰጠው የተቀባበለው ባህሉ ላይም ማተኮር እንደሚገባ ነው አያልህ የሚያሳስቡት። ግዛትን ከማስፋትና ገዢ ሆኖ ከመታየት ርብርብ ለአፍታ ገለል በሎ ጥበብና ማዳበር ላይ ሊሠራ እንደሚገባም ጭምር ያነሳሉ።

የልምድ ልውውጥ የባህል ሽግግር አስፈላጊነት ላይ ጥያቄ አይነሳም የሚሉት አያልነህ፤ ይሁንና ጥበባት ሁሉ ወደየ ክልሉ ከአዲስ አበባ እየተጫኑ እንዲሔዱ መጠበቅም ትክክል እንዳይደለ ሳይጠቅሱ አያልፉም። ቴአትር ቤቶችና ባለሙያዎች፣ ሙዚቀኞችና ገጣምያን ከአዲስ አበባ ተሻግረው ማገልገልና ባህልን ማተዋወቅ

እንደሚኖርባቸው ሳያነሱ ያላለፉት አያልነህ፤ከአዲስ አበባ መጠበቅም ብቻ አይደለ፤ ክልሎችም ወደ አዲስ አበባ ሥራዎቻቸውን መውሰድ እንደሚጠበቅባቸው ጭምር ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ከተሰጠው ኃላፊነት መካከል የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችን ትውፊታዊ ክውን ጥበባት በማጥናት፣ ባህላዊ እሴታቸው ተጠብቆና ወደ ኪነጥበባዊ ክዋኔ ተለውጠው ተደራሽ እንዲሆኑ ማድረግ ነው። የቴአትር ቤቱ የክውን ጥበባት ጥናትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኃይለማርያም ሰይፉ በዚህ ላይ አስተያየት ሲሰጡ፤ ቴአትር ቤቱ ይህን ኃላፊነት ለመወጣት በብዙ ችግሮች ውስጥ ሆኖም ጥረት እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

በዚህ መሠረት በደቡብ የጉራጌ ብሔረሰብ ተጠንቶ ‹‹የቃቄ ውርድወት›› ለእይታ የቀረበ ሲሆን፣ ይህም ትውፊታዊ ቴአትር በጉራጌ ብሔረሰብ አስተዳደር እርዳታና ድጋፍ እውን ሊሆን እንደቻለ ኃይለማርያም አስታውሰዋል። ከመኢኒት ‹‹የአሻ ልጅ›› ለመድረክ የበቃ ሌላው ትውፊታዊ ቴአትር ነው። በተጓዳኝ የባስኬቶ፣ የአማሮ፣ የሲዳማ፣ የካፊቾ፣ የዳውሮ ተጠንተው ወደ መድረክ ትዕይንት ለመቀየር በሒደት ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በተመሳሳይ ከኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይ፣ አፋር፣ ሶማሊ የተለያዩ አካባቢዎች ጥናቶች የተከናወኑ ሲሆን፤ እስከሁን ጋምቤላ እና የድሬዳዋ ክልል ብቻ ላይ ጥናት ሳይደረግ እንደቆየ አንስተዋል።

የጥናቱ ትኩረት ታድያ ገላጭ ባህሉ ላይ ነው፤ ለኪነጥበብ ግብዓት እንዲሆን ለማስቻል። በዚህም መሠረት አካባቢው፣ መልከዓ ምደሩ፣ ኢኮኖሚው፣ እደጥበቡ፣ የቤት አሠራሩ፣ ዘፈኑ፣ ጭፈራው፣ ግጭት አፈታቱ፣ አገር በቀል እውቀቱ፣ የኑሮ ፍልስፍናው፣ አለባበሱ፣ ተመሳሳይነትና ልዩነቱ፣ ከትውልድ ትውልድ ሲሻገር ያመጣው ለውጥና ያጋጠመው ችግር ወዘተ በጥናቱ ይታያል። ይህንን ሁሉ አጣጥሞ በኪነ ጥበብ ለታዳሚ ወደ መድረክ ለማምጣትም ሥራው ከጥናቱ ይነሳል።

ታድያ እነዚህን የጥበብ ሥራዎች ከብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ አንስቶ ከአዲስ አበባ አውጥቶ ወደ ክልል ከተሞች ማዳረሱም ሌላ ሥራ ነው። እንደውም ቴአትር ቤቱ ተደራሽነትን በተመለከተ ገና ከጥናቱ ጀምሮ እንደሚያስብበት ነው ኃይለማርያም የሚጠቀሱት። ‹‹በቅድሚያ ትኩረት የሚደረገው አውደጥናት ማዘጋጀትና አስተችቶ ግብአት መሰብሰብ ላይ ነው። ይህም ከመስክ በጽሑፍ ወይም በምስል የተገኘውን አቀናብሮ ቤተ መጻሕፍት ማስቀመጥንም ያካትታል፤ ለመረጃ ፈላጊዎች ምቹ ለማድረግ።›› ብለዋል።

በተያያዘ በጥናት መጽሔት ላይ እንዲታተም እንደሚደረግም ጠቅሰዋል። ‹‹ዋናውና ግቡ መድረክ ላይ ማቅረብ ነው።›› ያሉት ኃይለማርያም፤ በዚህ ብዙ የተሳካው በሙዚቃው በኩል መሆኑንም ያወሳሉ። የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን ሙዚቃና ውዝዋዜን በማስተዋወቅ በኩል አመርቂ ሊባል የሚችል ውጤት እንዳመጣና በአንጻሩ በቴአትር ግን ብዙም የተሳካ እንዳይደለ ነው የጠቀሱት። ይህም በእቅድ ላይ ያለው እንደሚበዛና ለዚህም ከገንዘብ አቅም ጀምሮ በርካታ ችግሮች ስለመኖራቸው ጠቅሰዋል።

‹‹ባህሉ እየተከለሰ፣ እየተረሳና እየተተወ፣ ዘመናዊነት እየዋጠው ስለሆነ፤ ትግላችን ቢያንስ እንመዝግብ ነው።›› ይላሉ ኃይለማርያም። ከገንዘብ አቅም ማነስ በተጓዳኝ ደግሞ የባለሙያ እጥረት መኖሩን ይጠቅሳሉ። ይልቁንም በጥናትና ምርምር ክፍሉ ውስጥ መኖር ከሚገባው ብቁ የሰው ኃይል ብዛት አንጻር ግማሽ እንኳ እንዳልሞላና የሚገባውም ከሥራው ፈታኝነትና ክፍያውም ዝቅተኛ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ በዝውውር እንደሚለቅ አንስተዋል።

ከተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ቴአትር ጥበባት ትምህርት ክፍል ጥቂት የማይባሉ ተማሪዎች በየዓመቱ ተመርቀው ይወጣሉ። እነዚህም ከአንድ አካባቢ ሳይሆን ከተለያየ አካባቢ የሚወጡ በመሆናቸው ለዘርፉ ትልቅ ጠቀሜታ ሲሆን እንደሚችል ይገመታል። ይሁንና በሚጠበቀው ልክ አገልግሎት ሲሰጡና በየአካባቢያቸውም በጥበቡ ዘርፍ በሙያቸው ሲያገለግሉ የሚታዩ ጥቂቶች ናቸው።

ደራሲ፣ ገጣሚና ጸሐፌ ተውኔት አያልነህ ለዚህ ጉዳይ ምክንያት ነው ያሉት አሁንም ክልል ሆነው የተደራጁና ሁሉን በኃላፊነት የተረከቡ ባለድርሻዎችን ነው። በተለይም በቴአትር ጥበባት የተመረቁ ወጣቶች ከሙያው ርቀው በተለያየ መስክ ላይ ተሠማርተው ይታያሉ። ይህ የሆነው በየአካባቢያቸው ወይም በሁሉም አካባቢ ለኪነጥበብ እንዲሁም ለሥነ ጥበብ ትኩረት ተሰጥቶ መድረክ ባለመፈጠሩ ነው ባይ ናቸው።

‹‹ይህንን የፈጠረው በየክልል የተደራጀ መንግሥት ለጥበብ የሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ መሆን ነው።›› ይላሉ አያልነህ። እና ለማንኛውም አገራዊ እድገት የጥበብ ሚናንና ድርሻን መዘንጋት፣ መድረክ አለመፍጠርና ስፍራ አለመልቀቅ አግባብ አይደለም፤ ጥበብ መዘንጋት የለባትም ሲሉ ያሳስባሉ። ክልል ፈጥረው ለጥበብ መድረክ መንፈግ በራሱ ወንጀል ነው ሲሉም ይኮንናሉ። ይህም እስካልሆነ ድረስ አዲስ አበባ ለሁሉም መሰባሰቢያ ባለ መድረክ ሆና መቀጠሏ አይቀሬ ነው።

ኃይለማርያም እንደሚሉት ደግሞ ክልሎችም ላይ ቢሆን የባለሙያ እጥረት አለ ነው። የተወሰኑ አካባቢዎች የራሳቸውን ባህልና እሴት በማስተዋወቅ በኩል በባህል ቢሮ ወይም መምሪያ ሙከራ እንደሚያደርጉ ያነሳሉ። ግን ይህ የባለሙያ እጥረት ለእነርሱም ፈታኝ ሆኗል።

ይህም ከገንዘብ እጥረቱ የሚገናኝ ነው። ኑሮ ውድ በሆነበት ጊዜ በ83 ብር የቀን አበል የመስክ ሥራዎችን መሥራት የሚታሰብ አይደለም፤ ለዚህም የሚገቡ ባለሙያዎች ሳይቆዩ እንዲወጡ አንዱ ምክንያት ሆኖ ይቀመጣል። የመስክ አገልግሎት የሚሰጡ መኪናዎች እጥረት፣ አንዳንድ ብሔረሰቦች ‹ሊጠቀሙብን ነው› በሚል መፍራታቸውና እምነት ማጣታቸው ወዘተ እንደችግር የሚጠቀሱ መሆናቸውን ያነሳሉ።

እዚህ ላይ የተመልካች ነገርም ሳይነሳ አይቀርም። ‹‹እንደኛ ከሆነ የባህል ሥራዎች ገንዘብ ትርፍ አምጪ አይደሉም፤ ቴአትር ቤት የሚታዩም አይደሉም።›› ይላሉ ኃይለማርያም። ከክፍያ ውጪ በተለያዩ ስፍራዎች ትውፊታዊ ቴአትሮች ሲቀርቡ ተመልካቹ ደስ የሚያሰኝ ግብረ መልስ እንደሚሰጥ ይናገራሉ። እናም የብሔሮችን ባህል የሚያሳዩ ትውፊታዊ ቴአትሮች ያለገንዘብ ሲቀርቡና በገንዘብ ሲቀርቡ ልዩነት ያለው በመሆኑ፤ በገንዘብ የሚታይ ሳይሆን እየተደገፈ እንዲተዋወቅ መደረግ እንዳለበት ኃይለማርያም ይጠቅሳሉ። ‹‹በመንግሥት በኩል አሁንም ይደግፋል፤ ግን ወጪው በጣም ብዙ ስለሆነ ነው።›› ሲሉ ያክላሉ።

ክውን ጥበባት የማኅበረሰቡን ባህል አንድም ለውጪው ማኅበረሰብ አንድም አንዱን ከሌላው ለማስተዋወቅ ቁልፍ መሣሪያ መሆናቸው ግልጽ ነው። አያልነህ ሙላት እንደሚሉት እንደውም ከአገር አልፎ የዓለም መድረክን መቃኘት ያሻል። ‹‹አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና ጭምር ናት›› ሲሉ የሚያስታውሱት አያልነህ፤ የውጪ አገር ዜጎች በብዛት ይገኙባታልና ሲሆን በኢንግሊዘኛ እንዲሁም በፈረንሳይኛ ጭምር ቴአትሮችን ልታስተናግድ ይገባል። ‹‹ፍቅር እስከ መቃብርን ዓለም አያውቀውም…ጥበቡ ጠፍቶን ሳይሆን ማስተዋወቅ ስላልቻልን ነው›› ሲሉም ትልቁን ምስል በማሳየት የአገር ውስጥ የእርስ በእርስ ትስስሩንና ባህልና እሰት ማበልጸጉን በቀላሉ ሊከወን የሚገባ የቤት ሥራ መሆኑን ይጠቁማሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 57 ኅዳር 27 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here