“የሚቀጥለው ምርጫ ከተጭበረበረ ተጠያቂው ዐቢይ አሕመድ ነው”

0
771

ጃዋር መሐመድ ተፅዕኖ ፈጣሪ የመብት ተሟጋች ሲሆን በአሁኑ ወቅት የኦሮሚያ ሚዲያ ኔቶርክ (ኦኤምኤን) የቴሌቪዥን ጣቢያ ዋና ዳይሬክትር ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል። ቀደም ሲል ጃዋር የሚታወቅበት በኢትዮጵያና በምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ በሳል የፖለቲካ ትንተና በመስጠት ሲሆን በተለይ በኢሕአዴግ ውስጥ የለውጥ ኃይል የሚባለው አመራር ወደፊት ከመውጣቱ በፊት ለዓመታት በኦሮሚያ ክልል ይካሔዱ የነበሩትን ሕዝባዊ ዓመፆች ከመሩት መካከል ግንባር ቀደሙ ነው። በፖለቲካ ሳይንስ ሁለተኛ ዲግሪ የያዘው ጃዋር ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባት ነው። የአዲስ ማለዳው ታምራት አስታጥቄ በወቅታዊና ሌሎች አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከጃዋር መሐመድ ጋር ቆይታ አድርጓል።

አዲስ ማለዳ፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሔደ ያለው የፖለቲካ ሂደት ምን ብሎ መጥራት ይቻላል?
ጃዋር መሐመድ፡ ቅይጥ (‹ሃይብሪድ›) የሆነ ሽግግር ውስጥ ነው ያለነው። በነገራችን ላይ ሽግግር ከታች ከሕዝብ አመፅ የነበረውን ሥርዓት በማፍረስ ሊመጣ ይችላል። ሌላው ደግሞ ሥርዓቱ ውስጥ በሚፈጠር ሁኔታዎች ባሉበት እንዲቀጥሉ በማይፈልጉ ኃይሎች የሚካሔድ ከላይ ወደታች የሚባለው ነው። ሦስተኛው እኛ አገር ላይ የመጣው ቅይጥ የሆነው ዓይነት አለ። የሕዝቡ አመጽ ሥርዓቱን አልፈነገለውም፡፡ እንደዚህ ዓይነት የድርድር ሽግግር ተብሎ የሚጠራው ነው። በመጣው ሽግግር ተስፋም አለ ስጋትም አለ።
ስጋቱ ሽግግሩ ለመቀልበስ አደጋ ሊያጋልጠው ይችላል የሚል ይሆን?
ሽግግሩን መቀልበስ አይቻልም። ያሉትን የቢሆን መላምቶች ብናይ፡- አንደኛው በቀጥታ ወደ ዴሞክራሲ መሸጋገር ነው። ሁለተኛው ወደ አንባገነንነት መለወጥ ሊያጋጥም ይችላል። ይሄ የሚቻል አይመስለኝም ምክንያቱም አንባገነናዊ ሥርዓት ለመገንባት የሚችል ቡድን የለም። የሕዝብ ኃይል ጠንክሯል፤ የመንግሥት አቅም ተዳክሟል።
የሽግግር አመራር የምንላቸው እነዐቢይ ወደፊት የመጡት በሕዝብ ድጋፍ ነው። ሽግግሩ አሁን በሁለት ሞtር ነው እየሄደ ያለው፤ በሕዝብ እና በመንግሥት። ሁለቱም ግን ሙሉ በሙሉ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር አይደሉም። ተቋማት የሚባሉትን ብንወስድ ደኅንነቱ ፈርሷል፤ መከላከያው ወጥ የሆነ አንባገነናዊ ሥርዓትን ለመደገፍ የሚያስችል አንድነት የለውም። በሕዝቡ ውስጥም ቢሆን አንባገነን ሥርዓት ለመሸከም የሚችል ሁኔታዎች የሉም።
ሦስተኛው ልንሄድ የምንችልው የቢሆን መላምት ወደ እርስ በርስ ጦርነት ሲሆን ይህም የመንግሥት መውደቅን ያስከትላል።
ስለዚህ አንባገነናዊነት ወይም መቀልበስ አይታሰብም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት ከውጪ ለመጡት ፖለቲከኞችና ተሟጋቾ የሰጡትን ትኩረት ያክል ላንተ አልሰጡም ይባላል። በዚህ ምክንያት የጃዋር የፖለቲካ ተሳትፎና ተጽዕኖ ፈጣሪነት አገር ውስጥ ከገባ ጀምሮ እየቀነሰ ነው ይባላል። እዚህ ላይ ምን ትላለህ?
አልስማማም! እዛ [አሜሪካ] ሲመጡ ተወያይተናል፤ እዚህም ስመጣ በተደጋጋሚ ተወያይተናል። መንግሥትን ሆነ ተቃዋሚውን የመቀላቀል ፍላጎት የለኝም፤ በመብት ተሟጋችነቴ ነው መቀጠል የምፈልገው። እንደተሟጋች ከመንግሥት በመጠነኛ ርቀት መራቅ አለብህ ምክንያቱም ሕዝብ ከመንግሥት ጋር ነህ ብሎ ካሰበ ላንተ የሚኖረው ቀረቤታ የዛኑ ያክል ይሆናል። መንግሥትንም በጣም ከቀረብክና ትችት የምትሰጣቸው ከሆነ ‹እንዴት ጉያዬ ሥር ሆኖ ይተቸኛል› የሚል ነገር ይመጣል። ስለዚህ ተከባብረህ በመጠነኛ ርቀት ላይ መገኘቱ አስፈላጊ ነው።
ተፅዕኖና ተሰትፎን በተመለከተ ቀንሷል።
ለምን?
ምክንያቱም በጣም ተፅዕኖ ሲፈጠር የነበረው የአንባገነን ሥርዓት ስለነበረ ነው። አሁን ለውጡን እየመሩት ወደ ዴሞክራሲ እያሸጋገሩን ነው የሚል እምነት አለኝ።
ሁለተኛ እዚህ አገር መንግሥት በጣም ተዳክሟል፤ እንደኔ ያሉ ሰዎች ከገፋነው ፍርክስክሱ ሊወጣ ይችላል። ስለዚህ መጠንቀቅ አለብን። ተቃዋሚቹም የሚንቀሳቀሱት በጣም በጥንቃቄ ነው። እኛም ቢሆን መንግሥትን የመደገፍ ሥራ ነው እየሠራን ያለነው። ይሁንና ‹እንደዚሁ እንቀጥላለን ወይ› ለሚለው መልሴ እንደሁኔታው የሚል ነው። እነዐቢይ ወደ ዴሞክራሲ ሽግግር የሚሔዱ ከሆነ ድጋፋችንን እንቀጥላለን፤ ወደ መቀልበስ ከሔዱ ተፅዕኗችን እየጨመረ ይሔዳል።
በየጊዜው አቋምህን እንደምትለዋውጥ ይታወቃል፤ አንተም በአንዳንድ መድረኮች ላይ ይህንኑ አምነሀል። ይህ አካሄድ አሁን አገሪቱ የደረሰችበት የፖለቲካ ሂደት ላይ ጉዳት አያደርስም ትላለህ?
ሁሌም ያስኬዳል፤ የመብት ተሟጋች እንጂ ፖለቲከኛ አይደለሁም። የፖለቲካ ፓርቲ ከሆንክ ሁሌም ቀጥ ብለህ መሔድ አለብህ። ተሟጋች ከሆንክ ግን አንዱን አጀንዳ ትገፋውና ከዳር ስታደርሰው ሌላ አጀንዳ ትይዛለህ፤ ይህ ግዴታ ነው። ተራማጅ፣ ከሁኔታዎችን ራስን እያስተከለክ የምትሔድና የዓለማ ፅናት መኖር ወሳኝነት አላቸው።
እዚህች አገር ላይ ዴሞክራሲያዊ፣ ሠላማዊና ልማታዊ፣ ሁሉን ያማከለ፣ ሁሉን ያሳተፈ ሥርዓተ መንግሥት እንዲመሠረት እፈልጋለሁ። ያንን ለመመሥረት አንዳንዴ ከፍ ያለ ድምፅ ማውጣት አለብህ፤ አንዳንዴ ደግሞ ቀዝቀዝ ታደርገዋለህ። እንቅስቃሰያችን ብሔርን መሠረተ ያደረ በመሆኑ ሁል ጊዜ በጋለበት መሔድ አትችልም፣ ሞቅና ቀዝቀዝ እያደረክ ነው የምትሔደው። አንዳንዴም የገነባኸውን እያፈረስ የምትሔድበት ሁኔታ ይኖራል። ተለዋዋጫነት ወሳኝ ነው።
በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች ተበራክተዋል፤ በፖለቲካ ፓርቲዎቹም መካከልም በተለይ በኦነግና ኦዴፓ መካከል እሰጣ ገባ ቀጥሎ እንደነበር ይታወሳል። እንደ ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰብና የኦሮሞ መብት ተሟጋች ጉዳዩ በሠላም እንዲፈታ ምን የተለየ በጎ ተጽእኖ አሳድረኻል?
አዎን አድርጊያለሁ። መጀመሪያም ቢሆን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግን) እና የመንግሥትን አመራሮች በማነጋገር ወደ አገር ቤት ከመጡም በኋላ ሁለቱም አመራሮች እንዲቀራረቡ አድርጊያለሁ።
በምዕራብ ኦሮሚያ ውጥረቱ ሲሰፋ ወደ አካባቢው ብዙ ከተሞች በመሔድ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከሃይማኖት መሪዎች ጋር በመሆን ከሕዝቡ ጋር ሰፋፊ ውይይቶች አድርገናል። እዛም አካባቢ ከሚንቀሳቀሱ ከመከላከያና ከክልሉ አመራር ጋር ሰፊ ውይይቶች አድረገናል። ያንን ጨርሰን እንደመጣንም ከፕሬዘዳንት ለማ፣ ከኦነግ እና ከመከላከያ አመራሮች ጋር የሕዝቡ ጥያቄና ሮሮ ምንድን ነው የሚለውን፣ የኛ መረዳት ምን እንደሆነና መፍትሔ ብለን ያሰብናቸውን ጨምረን አቅርበንላቸዋል። ያ ደግሞ እነሱ እየሠሩ ያሉትን ነገር ያጠናክርላቸዋል። አሁንም ቢሆን ዝም ብለን ያየነው ጉዳይ ሳይሆን እየተሳተፍንበት ነው።
የተፈጠረው ነገር ያን ያክል ትልቅም ጉዳይ አይደለም፤ ካለመነጋገር የመጣ ነው። ኦነግን በተመለከተ ረጅም ጊዜ ከአገር ውጪ እንደመቆየቱ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ባለማወቃቸው እና ራሳቸውን ከማቋቋም አንፃር የተከሰተ ክፍተት ነበር።
በብዙው የኦሮሞ ልኂቃን አንተን እንደ አገናኝ ድልድይ እንደሆንክ ይታመናል። የኦሮሞ ፖለቲካ ልኂቃን ወደ አንድነት ለማምጣት ምን ሚና እየተጫወትክ ነው?
እኔ ብቻ ሳልሆን ፕሮፌሰር እዝቅኤል ከአባ ገዳዎች ጋር እየሠራን ነው። ዝም ብሎ አንድ የማድረግ ሥራ አይደለም እየሠራን ያለነው፤ ከዛ ይልቅ የድርጅቶቹንና የአመራሩን ብቃት የመገንባት እና የአዕምሮ ሥራ ላይ አተኩረናል።
እነዚህ ድርጅቶች የትግል ፓርቲዎች ናቸው። አሁን የትግል ምዕራፉ አልቆ ወደ አስተዳደር መሸጋገር አለብን። ስለዚህ ፓርቲዎቹም እንደዚሁ ራሳቸውን ወደ አስተዳደራዊ ፓርቲ በተጨባጭ መለወጥ አለባቸው። ያንን ለማድረግ ከፍተኛ የማስተማርና የማስረዳት ሥራ መሥራት አለብን። እነዚህ ፓርቲዎች በምርጫ ተሳትፈው ማሸነፍ አለባቸው። ከዛም በኋላ ምርጫ ያሸነፈው ደግሞ አገር ማስተዳደር ስለሚጠበቅበት የአቅመ ግንባታ ሥራ ትልቁ የሥራችን አካል ነው። ሌላው ችግር ሲፈጠርም መንግሥትን የማገዝ፣ ሕዝብን የማረጋጋት ሥራ እንሠራለን።
የሆነው ሆኖ በሌሎች ሥራዎች በጣም ስለምንጠመድ የታሰበውን ያክል አልሠራሁም። የፓረቲዎች ብዛት ግን ያን ያክል የሚያሳስብ ጉዳይ አይደለም ምክንያቱም ምርጫው ሲቃረብ ወይ ይደመራሉ ወይ እየተዋጡ ይሔዳሉ።
የኅዳር 13ቱን የኦዲፒና የኦዴግን ውኅደት እንዴት አገኘኸው?
ድሮም ቢሆን አብረው የሚሠሩ ፓርቲዎች ናቸው፤ ያደረጉት ያንን ይፋ ማድረግ ነው። ኦዴግ መሠረት ያለው ድርጅት አይደለም ይሁንና ጥሩ ልምድ ያላቸው ሰዎች አሉት። ኦዲፒ ደግሞ የተማረ የሰው ኃይል እጥረት ስላለው መቀላቀላቸው እንዲጠናከሩ ያደርጋል።
ቄሮ መደበኛ አደረጃጀት እንዳልሆነ እንዲሁም ተልዕኮው የተቃውሞ እንደነበር ይታወቃል። ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ሒደት በማገዝ ረገድ የሚጫወተው ሚና ምን መሆን ይገባዋል ትላለህ?
አንደኛ የለውጡ ዘብ መሆን ነው። ለመቀልበስ የሚፈልጉትንም ዘብ ቆሞ ይጠብቃል። ሁለተኛ ምርጫው ላይ ከፍተኛ ሚና ሊጫወት ይችላል። በተለይ ደግሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ነፃ ምርጫ እንዲያካሒዱ ጫና በማድረግ ያግዛል። ሦስተኛው ከፍተኛው የቄሮ ኃይል በምርጫ ታዛቢነት ይሳተፋል። የተቀረው ቄሮ ደግሞ ወደ ፖለቲካ ፓርቲዎች በመግባት የሚቀጥለውን አመራር የመቀላቀል ይሆናል።
ኦኤም ኤን የትግል መሣሪያ ሆኖ ያገለገለ የመገኛኛ ብዙኃን እንደነበር ይታወቃል። አሁንም በዛው መንፈስ እንደቀጠለ ይገኛል። ከወቅታዊው አገሪቱ የፖለቲካ ሒደት አንፃር ነፃና ገለልተኛ የመገናኛ ብዙኃን ሆኖ ይቀጥላል?
አሁን ያለው ትችት አንተ ካልከው በተቃራኒው ነው፤ በጣም ለዘባችሁ፣ ከልክ በላይ ተደመራችሁ፣ ኦቢኤና ኢቲቪን መሰላችሁ የሚሉ ናቸው። በጣም ለዘብ ያደረግነው መንግሥት አዲስ ከመሆኑ የተነሳ፣ አገሪቷ ወደ ዴሞክራሲ ያሸጋግራል ብለን ስለምናስብ ድሮ እንደምናደርገው አቃቂር ማውጣት፣ ነገሮችን እየተከታተሉ የማጉላት ሥራ ትተናል። ያ ደግሞ በኛ ተከታታዮች ዘንድ ቅሬታ ፈጥሯል።
ኦኤምኤን የትግል ሚዲያ ነው፤ ከዛ ብዙም አይወጣም ወደ መሃል ጠጋ የማለት ነገር ካልሆነ በስተቀር። ከፖለቲካው አንርቅም፤ ፖለቲካን ከተለያየ አቅጣጫ በውይይትም በክርክርም እንዲሁም አዳዲስ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን ይዘን እየመጣን ነው ያለነው።
ገለልተኛነቱን በተመለከተ ኦኤምኤን ጠጋ ብሎ ላየው ሁሌም ገለልተኛ ነው። የኦሮሞን ሕዝብ ጥቅምና ፖለቲካ ማዕከል ያደረገ እንቅስቃሴ ነው የሚያደርገው። ከዚህ አንፃር ሙያውን ከግምት ባስገባ መልኩ ነው የምንሠራው፤ በጥንቃቄ። ጠንከር ያለ አቋም ብናስተላልፍ ግጭቶችን በሚያስፋፋ መልኩ ሳይሆን በአብዛኛው መንግሥት ላይ ጫና በማምጣት የሥራ ለውጦች፣ ቅልጥፍና ማምጣት ባለበት መልኩ ማለት ነው።
አሁን የቴሌቪዥን ጣቢያውን እያጠናከር ነው እንገኛለን። የአማርኛንና የኦሮምኛ ቋንቋን በእኩል ደረጃ እያስተናገድ ነው። ወደ ሕትመትም በመግባት ‹‹ጉለሌ ፖስት›› የመባል መጽሔት ጀምረናል። የኤፍ ኤም ሬዲዮም በቅርቡ እንጀምራለን። በሒደትም እያሻሻልነው እንሔዳለን።
ሚዲያችን ከማታገል ይለቅ ያለውን አስተዳደር የአሠራር ቅልጥፍና፣ ተጠያቂነትን፣ ሕዝብን ማዕከላዊ ማድረግ ላይ መሥራት አለበት። ይህንንም ለማድረግ የጋዜጠኖቻችንን አመለካከት መለወጥ ይገባናል።
የገንዘብ ምንጫቸሁ ምንድን ነው?
ድሮ መቶ በመቶ የዳያስፖራው አስተዋጽኦ ነበር ምክያቱም ለትርፍ የተቋቋምን ስላልሆንን፤ እዚህ ስንመጣ ግን ድርሻ በመሸጥ የአክሲዎን ኩባንያ ለማድረገ እየሠራን እንገኛለን። ምንም እንኳን ለትርፍ የተቋቋምን ቢሆንም ድርሻዎችን ለሕዝባችን በመሸጥ መሠረቱን እንዳይለቅ እናደርጋል። የግል ሚዲያ ሳይሆን የሕዝብ ሚዲያ እንዲሆን እንፈልጋልን። ይህም ለድርሻ ባለቤቶቹ በሁለት መንገድ ይጠቀማሉ፡- አንደኛ ሕዝብን ያማከለ ጥሩ ሚዲያ ይኖራቸዋል፤ ሁለተኛም ትርፍ ሲኖር ትርፉንም ይጋራሉ።
የገንዘብ አቅማችሁን ለማሳደግ ማስታወቂያ የማግኘት ዕድላቸሁ ምን ያክል ነው?
አሁን ችግር የሚኖር አይመስለኝም። በተለይ በኦሮሚኛ ቋንቋ የሚሠሩትን እናገኛለን። የማስፋፋት ሥራ ስለምንሠራ ማስታወቂያዎች በደንብ እንደምናገኝ ምንም ጥርጠር የለኝም።
አንዳንዶች ጀዋርን በአንባገነንት ይከሳሉ። እንደማስረጃ ከሚጠቀሱት አንዱ ኦኤም ኤን ሲጀመር የነበሩ የቦርድ አባለት በሙሉ በተለያየ መንገድ ማባረርህ ወይም መግፋትህ ይነሳል። ይህ ተገቢነቱ ምን ያክል ነው? በኦኤምኔን ቀጣይነትስ ላይ ተጽዕኖ አይኖረውም?
አንባገነን ማለት ቁጭ ብሎ ትዕዛዝ የሚያስተላልፍ ማለት ነው። እኔ ከጋዜጠኞቼ ጋር ሌት ተቀን ቁጭ ብዩ ነው የምሠረው። የምመራውመ በሦስት መርሆች ነው፡- ከፍተኛ ስሜት (‹ፓሽን›)፣ መስራት መቻል(‹ፐርፎርማንስ›) እና ሙያተኝነት(‹ፕሮፌሽናሊዝም›) ናቸው። ኦኤምኤን ዝም ብሎ ሚዲያም አይደለም።
በኦሮሞ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ የአቅጣጫና የስትራቴጂ ልዩነቶች ነበሩ። ስለዚህ በዛ ትርምስ ከባቢ የተመሠረተ ነው። በዚህም ልዩነቶች ይፈጠራሉ፤ ግማሹ ይባረራል፣ ግማሹም ሲሰለቸው ይወርዳል። ከዚህ አንፃር የወጡ ሰዎች አሉ። ኦኤምኤን ወያኔን ያንበረከከ ሚዲያ ስለሆነ ውጤቱ ሲታይ ሀጢያታችንን ይቅር ያስብለናል።
በቀጣይነት ደረጃም በመጀመሪያ አካባቢ እንዴት ይህንን የቴሌቪዥን ጣቢያ ያቋቁማል በሚል ብዙ ሰዎች ‹አይችልም› የሚል ከፍተኛ ጥርጣሬ ነበራቸው። ባልነው ቀንና ሰዓት ጀመርን፣ ሚዲያው ዓላማውን አሳክቷል፤ ቀጣይነቱንም በተመለከተ ፈተናውን አልፏል።
በቅረቡ መንግሥት ከሰብኣዊ መብት ጥሰትና ከተደራጀ ሌብነት ጋር በተያያዘ የወሰዳቸውን እርምጃዎች ካለንበት የሽግግር ወቅት አንጻር እንዴት ታየዋለህ?
ባለፈው ዓመት ጥቅምት ላይ ሥዓቱን ለመለወጥ እርግጠኛ በሆንበት ጊዜ በዚሁ ጉዳይ ላይ ውይይት አድርገናል። በዛ ውይይት ላይ የሽግግሩን የቢሆን መላምቶች የፍትሕ እና የሠላም ጉዳይ ሁል ጊዜ እየተወዳደሩ ይመጣሉ።
አንደኛ ሥልጣን ላይ የነበሩ ሰዎች ብዙ በደል፣ ብዙ ግፍ ይፈጽማሉ፤ ተበዳዮችም ፍትሕ ይፈልጋሉ። አጥፊዎችም ሊቀጡ ይገባል። የሚመጣውም ትውልድ ተመሳሳይ ጥፋት እንዳይደግም ይሆናል።
በሌላ ወገን አንባገነናዊ ሥርዓት ውስጥ ያሉ ሰዎች በተላይ ሠላማዊ ሽግግርን በሚደረግበት ወቅት ተቋማትን መንካት አደጋ ላይ ይከታል። ማንኛውም ሽግግር ውስጥ የሚገባ አገር በእንደዚህ የምርጫ አጣብቂኝ ውስጥ ይገባል። ይህን እንዴት መያዝ እንዳለብን ተወያይተን ነበር። ውሳኔያችን ለሠላማዊ ሽግግር ሲባል ፍትሕ መስዕዋት ትሁን የሚል ነበር። ጌታቸው አሰፋ ከሥልጣን አውርዶ ማሰር ይቻል ነበር፤ ኃይለማሪያም ደሳለኝንም እንዲሁ።
ይሁንና ይህንን ሥሌት በስህተት፣ በአቅም ማነስና በፍራቻ ወሰዱት። ፍትሕም ያጣንበት፣ ሠላምም ያጣንበት ሁኔታ ተፈጠረ፤ ሠላምም ፍትሕም አብረው የሚመጡበት ሁኔታ ውስጥ ተገባ። ለፍትሕ ማቅረቡ ለሠላም ዋስትና ወሳኝ ነው። ለዚህ ነው መንግሥት ወደ እርምጃ መውሰድ የገባው።
ሕወሓት ልዩ ዕድል አግኝቶ ነበር ይሁንና አመራር የለውም። መለስ [ዜናዊ] የይለፍ ቁጥሩን ይዞ ከሔደ ወዲህ አንድም ሰው የይለፍ ቁጥረን ሊይዝ አልቻለም። በአጭሩ ሕወሓት ያገኘውን ዕድል ማንም አላገኘውም።
ሕወሓት እና መንግሥትን ለማቀራረብ ሙከራ አድርገህ ነበር? መቀሌስ ሄደህ ነበር?
ከፍተኛ ጫና በማድረግ በጣም ሞክሬ ነበር፤ ከነዐቢይም ጋር ከዲፕሎማቶችም ጋር በጉዳዩ ላይ ተወያይቻለው። ከለውጡ ሕወሓት ሙሉ ለሙሉ መገለል እንደሌለበት፣ አዲሱን አመራር ለማጠናከር መደገፍ እንዳለባቸው እንዲሁም በኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት በንቃት መሳተፍ እንዳለባቸው ሠፊ ዘመቻ አካሒጃለሁ።
ወደ መቀሌ ለመሔድ በተዘጋጀሁበት ወቅት ሕወሓት ጌታቸው አሰፋን መልሰው የአስፈፃሚ አካል አደረጉት። ያ የጦርነት አዋጅ ነው ምክንያቱም ራሱን ብቻ ሳይሆን ለውጡን ለመቀልበስ በከፍተኛ ወንጀል የተሳተፈበት፣ አሁን ደግሞ በሚደረጉ ረብሻዎች ያለምንም ጥርጥር ቀጥተኛ ተሳትፎ ያለውን ሰው መልሰህ አመራር ላይ ስትከተው ‹‹ኑ እንዋጋ፤ ኑ ሞክሩን›› የሚል ነው። ይህንን እያወቅኩ ወደ መቀሌ ብሔድ ያንን የደገፍኩ ስለሚመስለኝ ጉዞዬን ሰርዛዣለሁ።
ስለፍትሕ መስፈንና ሁሉም ሰው በፍርድ ቤት እሰካልተፈረደበት ድረስ እንደ ጥፋተኛ ያለመቆጠር መብት እንዳለው እያወቅክ የቀድሞው የደኅንነት ኃላፊ ጌታቸው አሰፋን በግልጽ ወንጀለኛ ስትላቸው ይሰማል። ሁለቱ ነገሮች አይጋጩም?
እንደ ጥፋተኛ ያለመቆጠር መብትን የተቃወምኩት የመንግሥት ሚዲያና ዶክመንተሪ ፊልሙን በተመለከተ ነው። ፖሊስ ይይዝሃል፤ ዐቃቤ ሕግ ይከስሃል፤ ሚዲያው ይፈርድብሃል፤ ፍርድ ቤቱም ይፈርድብሃል። ሰውየው[ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው] መዳኘት ያለበት በሁለት ፍርድ ቤት አይደለም። ተጠርጠሪው ሊዳኝ የሚችለው ፍርድ ቤት ብቻ ነው። የመንግሥት ሚዲያው ሲጨመርበት የሕግ አካሔድ ሳይሆን የፖለቲካ እርምጃ አደረጉት ነው ያልኩት።
ጌታቸው አሰፋን በግልጽ በአደባባይ ወንጀለኛ ያልካቸውንስ በተመለከተ?
እኔ አንደኛ የሰብኣዊ መብት ተሟጋች ነኝ። እኛ ባንጮህ ኖሮ ዛሬም ዐቃቤ ሕግ ጌታቸው አሰፋን ተጠርጣሪ አይለውም ነበር። በርግጠኝነት ላለፉት 17 ዓመታት እዚህ አገር ለተፈፀመው የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት ከመለስ የበለጠ ወንጀለኛ ጌታቸው አሰፋ ነው። መለስ ዜናዊ ከሞተ በኋላ ሲያዘርፍና ሲያስገድለል የነበረው ጌታቸው አሰፋ ነው። እንደሱ ዓይነት ሰውን አብጠልጥዬ እኔ ካልተናገርኩ ለተጎጂዎቹ፡- ለሞቱት፣ ለታፈኑት፣ ዱካቸው ለጠፋ ማን ይናገርላቸው። የጌታቸው ታስሮ ፍርድ ቤት መቅረብ ፍትሕ ለተጠሙት እንባቸውን ለማበስ በጣም አስፈላጊ ነው።
ሲደርሰኝ ከነበረው መረጃ እዚህ አገር ሲፈፀም የነበረውን ግፍ ዐሥር በመቶ እንኳን አላወጣሁም። ጌታቸው ‹እኔ በግሌ አላደረኳቸውም› ለሚለው እስከ ማዕከላዊ በመሔድ አካላዊ ሥቃይ በግሉ እየተቆጣጠረ ሲያስፈፅማቸው የነበሩ አሉ። የእሱ መያዝ ለፍትሕ ተፈፃሚነት ወሳኝ ነው። ሠላማዊ ሽግግር እንዲደረግ መያዙ ወሳኝ ነው። ትግራይ የኢትዮጵያ አካል ሆና እንድትቀጥል የሱ መያዝ ወሳኝ ነው። የጌታቸው መያዝ ለምስኪኑ ትግራይ ሕዝብ ጥቅም አለው። የትግራይ ሕዝብ እጣ ፈንታ ስለማያሳስበኝ ጭምር ነው። በነገራችን ላይ በኦሮሚያ ዞኖች ሰው ሲገድሉ የነበሩት ባለሥልጣናት ላይም ዘመቻ አድርገያለው፤ አደርጋለሁም።
በ2012 ይካሔዳል ለሚባለው ምርጫን በተመለከተ ይራዘም አይራዘም የሚለው ላይ ያለህ አቋም ምንድን ነው?
ምርጫው መራዘመም ሳይሆን መቃረብ ነው ያለበት። በመጀመሪያ ያለምርጫ ወደ ዴሞክራሲ ሽግግር ሊካሔድ አይችልም። ሁለተኛ ከታች ያለው የመንግሥት መዋቅር ፈርሷል፤ ደክሟል። ከታች ያለው ካድሬ ሲገዛ የነበረው በአፈሙዝ ነበር። አሁም በሕዝባዊ ተቃውሞ ተሸንፋፏል፤ በለውጡ አመራር ከጥቅም ውጪ ወጥቷል፤ ስለዚህ ሥልጣን የለውም። ሌላው ሲሰርቁና ሲዘርፉ የነበሩ በመሆኑ የሕዝብ ታማኛነት የላቸውም። ሦስተኛ መለስ በየሰፈሩ የኮለኮላቸው አብዛኞቹ ብቃትም ዕውቀት የላቸውም በሕዝብ የማይታመኑ ሕዝብ የማያምኑ ናቸው።
በተጨማሪም ኢኮኖሚው በመዳከሙ ለሕዝብ አገልግሎት እየሠጡ አይደለም። ስለዚህ አይፈሩም፣ አይከበሩም፣ አይታመኑም፣ ጥቅምም አይሰጡም። ከዚህ አንፃር ከዞን ጀምሮ ያለው አስተዳደር መለወጥ መቻል አለበት። ይህንን ደግሞ ምርጫ ካላደረከ በስተቀር እንዴት ትተካቸዋለህ። ከታች ያለው መፈረካከስ ወገብ አልፏል።
ያለ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ግንባታ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ማካሔድ ይቻላል?
በመጀመሪያ መታወቅ ያለበት ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዳይካሔደ ያደረገው እኮ መንግሥት ነው። መንግስት ከተለወጠና ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ አካሒዳለው ካለ ይደረጋል።
ምርጫውን ከሚያካሒዱት ወሳኝ አንዱ የምርጫ ሕግ ነው፤ እሱን ተወያይቶ መለወጥያስፈልጋል። ሰባት ወር እንደዚሁ አባከኑት እንጂ የአካባቢ ምርጫ ግንቦት ላይ ማድረግ ይችሉ ነበር፤ ምርጫውን ለመስረቅ መንግሥት ፍላጎት እስከሌለው ድረስ። በማንኛውም አገር ምርጫ የሚሰረቀው ገዢ ፓርቲ ነው። የሚቀጥለው ምርጫ ከተጭበረበረ ተጠያቂው ማንም ሳይሆን ዐቢይ አሕመድ ነው።
የምርጫ ቦርድን ከተቃዎሚ ፓርቲዎች ጋር በመደራደር ከላይ እስከታች ተቀባይነት ያላቸው ሰዎች ታስቀምጣለህ፤ ይሄ የአንድ ወር የሁለት ወር ሥራ ነው።
ከዚያ ቀጥሎ ሚዲያ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ማድረግ ነው። በሚገርም ሁኔታ በሰባት ወር ውስጥ የኢትዮጵያ ሚዲያ ያደረገውን ምን ያህል በሀያ ሰባት እንዳቆረቆዘን ነው የሚያሳየን። ከአንድ ዓመት በኋላ ሚዲያው ምን ያክል ሊድግ እንደሚችል መገመት ይቻላል። ስለዚህ የሚዲያ ጉዳይ አያሳስባቸውም።
የምርጫ ታዛቢ ጉዳይን በተመለከተ ደግሞ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን በመጋበዝ የአቅም ግንባታ ሥራ እንዲሰሩ ማድረግ ይቻላል። ሰበብ አስባብ እየፈለጉ ከሚርመጠመጡ እዛ ላይ መዘጋጀት ያስፍልጋል። የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ ‹አልተዘጋጀንም› የሚሉት ነገር አለ። ከውጨ የገቡት ፓርቲዎች አገር ውስጥ ከገቡ በአማካኝ ቢያንስ አራት ውር ሆኗቸዋል። እኛ ሚዲያ ለመገነባት የፈጀብን አራት ወር ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሥራዬ ብለው ጠንክረው መሥራት አለባቸው። ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ ለማቋቋም አንድ ዓመት ተኩል ከበቂ በላይ ነው። ምሳሌ ብሰጥህ በ1997 ቅንጅት ያንን ሁሉ ነገር የሠራው በአራት ወር ጊዜ ውስጥ ነበር።
ዐቢይ የሽግግር ጠቅላይ ሚኒስትር እንደመሆን መጀመሪያ መሥራት የነበረበት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር መደራደር ነበር። ሰባት ወር ሥልጣን ይዞ በስምንተኛው ወር ነው ከፓርቲዎች ጋር መወያየት የጀመረው፤ መጀመሩ ጥሩ ነው ÷ ሠፋ ብሎ መጀመር ግን አለበት። በአጭሩ ምርጫውን ማሳለፍ የሚቻል አይመስለኝም።
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ የፖለቲካ ልኂቃን ተሳትፎ ምን መሆን ይገባዋል ትላለህ?
እዚህ አገር እንቅስቃሴ እያደረጉ ያሉት ሦስት ፓርቲዎች ብቻ ናቸው። የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ፣ ኦነግና የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ናቸው። እንደኔ ያሉ ሰዎች ካልሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎቸ በመንግሥት ላይ ጫና እየፈጠሩ አይደለም። በወሳኝ ጉዳዮች ላይ እንኳን እየተወያዩ አይደለም።
ምርጫው ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ብቻ ሳይሆን ተፎካካሪ መሆን ይገባዋል። ኢሕአዴግን ብትወስድ ፋናና ዋልታ ጨምሮ በጣም ብዙ የንግድ ድርጅቶች አሉት። ስለዚህ ፓርቲ ሚዲያ እንዳይኖረው መከራከር አለባቸው፤ እነዚህም ሚዲያዎች ወደ ግል ወይም ወደ መንግሥት መዘዋወር አለባቸው። እነዚህን በመሳሰሉ ጉዳዮች ዙሪያ መከራከር ብሎም በሚካሔደው የለውጡ ሒደት ውስጥ መሳተፍ አለባቸው።
የውጪ ፓስፖርት የያዙ ግለሰቦች የፖለቲካ ተሳትፎ ምን መሆን አለበት ትላለህ?
በአሜሪካ ጉብኝታቸው ወቅት ጠቅላይ ሚኒስተሩ ‹ጥምር ዜግነትን በተመለከተ ሊሻሻል ይችላል› የሚል ፍንጭ መስጠታቸው ብዙዎችን አሳስቷል። ሶማሌ ክልል ላይ የውጪ ፓስፖርት የያዙት አማካሪ እንኳን እንደይሆኑ ከለከሉ፤ የራሱን ፕሬስ ሴክሬተሪ ግን ከሌላ ዜጋ አደረገ። ወጥነት በጣም ወሳኝ ነው።
በተቃዋሚዎች በኩል አብዛኞቹ የውጪ አገር ፓስፖርት ይዘን ወደ አገር ውስጥ እንሒድ የሚል ፍላጎት የላቸውም። ግን መቼ ነው የውጪ ዜግነታቸውን መተው ያለባቸው? እኔ እንደሚመስለኝ ኢሕአዴግ ለማታለል የሚፈልግ ይመስለኛል። ምርጫ ሲቃረብ ‹ዜግነታችሁን መተው የነበረባችሁ ከሁለት ዓመት በፊት ነው› ካለ ተቃዋሚውን ከጥቅም ውጪ ያደርገዋል፤ አገሪቷን ደግሞ ወደ ባሰ ግጭት ይከታታል። ስለዚህ በመንግሥት ደረጃ እንደዚህ ዓይነት ጨዋታ መጫወት የለበትም። ተቃዋሚዎችም በዚህ ጉዳይ ላይ በግልፅ መወየየት ይገባቸዋል።
አንተ ምን መሆን አለበት ትላለህ?
ይሄ የታማኝነት ጥያቄ ስለሆነ ፖለቲካ ለመሳተፍ፣ የመንግሥት ኃላፊነት ለመያዝ እና የአገር ደኅንነት በተመለከተ የሌላ አገር ፓስፖርት ይዞ መወዳደር ያለበት አይመስለኝም። ጥምር ዜግነት በተለይ ለንግድ ሰዎች ይጠቅማል። የውጪ ቀጥታ መዋዕለ ነዋይ ማፍሰስን በተመለከተ የዳያስፖራው ተሳትፎ እንዲቀጥል ከተፈለገ ጥምር ዜግነት ወይም ተቀራራቢ ነገር ማድረጉ ለአገሪቱ ጠቃሚ ነው። ለፖለቲካው ሳይሆን ለንግድ ጥምር ዜግነት ቢፈቀድ ጥሩ ይመስለኛል።
አንተ የያዝከው የምን አገር ፓስፖርት ነው?
የያዝኩት የአሜሪካ ፓስፖርት ነው። ፓስፖርት ለማሳደስ ብጠይቃቸው እንደ ጀማል ካሾግጂ ሊያጠፉኝ በአካል ኤምባሲ መቅረብ እንደሚያስፈልግ ነገሩኝ። ለማንኛውም ጉዳዩ በዝርዝር ቢጠና ጥሩ ይመስለኛል።
ማስተላለፍ የምትፈልገው መልዕክት ካለህ
ሚዲያው ለውጥ ለማምጣት ከፍተኛ ሥራ ሠርቷል። አሁንም ቢሆን ጠንከር ያለና ሚናውን በሚገባ መወጣት ያልቻለ ልኂቅ ባልወጣበት አገር የሚዲያው ሚና በመዘገብና በመተንትን ብቻ ሳይወሰን ምሁራንንና የፖለቲካ አመራሮችን በማሳተፍ ሽግግሩን መስመር ማስያዝ አለበት። በተጨማሪም ተለጉሞ የተፈታ ሕዝብ ስለሆነ ሚዲያው ግጭቶች እንዳይስፋፉ መጠንቀቅ አለበት። ሚዲያው ተቀራርቦ ራሱን በራሱ የሚቆጣጠርበት ካውንስል ማቋቋም አስፈላጊ ይመስለኛል።

ቅጽ 1 ቁጥር 3 ኅዳር 22 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here