ያምሉ ሞላ ከቤቲ ጂ ‹ወገግታ› አልበም ስኬት በስተጀርባ

0
955

ከማለዳ እስከ ንጋት እንቅስቃሴ ከማይጠፋት፤ ከቦሌ መድሀኒአለም ደብር እስከ የመማፀኛ ከተማ ቤተክርሰቲያን፤ ከትልልቅ ሆቴሎችና የንግድ ማዕከሎች እስከ ትናንሽ የኮንቴነር ኪዮስኮች ከከተሙባት የቦሌ ጫፍ ዋና መንገድ ዳር፤ ለሆሳስ ሹክሹክታ ጎልቶ ሊሰማበት የሚችል ፍጹም ፀጥ ያለ ክፍል ማግኘት ሊከብድ ይችላል።
የሙዚቃ አቀናባሪው ያምሉ ሞላ እንደ መንግሥት ሠራተኛ ጠዋት ከሁለት ሰዓት በፊት ገብቶ አመሻሹ ላይ ትቷት የሚሄደው የሙዚቃ ስቱዲዮው ግን እዚህ የከተማችን ዓይን ከሆነችው ቦታ ላይ ካሉ ሕንጻዎች መካከል ተሸጉጣለች። በዚህች ስቱዲዮ ውስጥ ነበር ያምሉ ከወዳጁ እና የመሃሪ ብራዘርስ ባንድ መሥራችና ድምፃዊ ከሆነው ከሔኖክ መሃሪ ‹እንኳን ደስ አለህ› የሚል የሥልክ ጥሪ የተቀበለው።
ድምጻዊት ቤቲ ጂ በዚህ ዓመት ለአድማጭ ላደረሰችው ወገግታ አልበም ሙሉውን ሊባል በሚችል ደረጃ የግጥምና ዜማ ድርሰቱን ያበረከተው እና ያቀናበረው ያምሉ ሞላ ‹እስከዚች ቅፅበት ድረስ በአፍሪማ የሙዚቃ የሽልማት መድረክ በሁለት ዘርፎች መታጨቴን አላውቅም ነበር› ሲል ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል።
ያምሉ ለአምስተኛ ጊዜ በተዘጋጀው የአፍሪማ የሙዚቃ ሽልማት ላይ ለመወዳደር ባያመለክትም የቤቲ ጂ ማናጀሮች የድምፃዊቷን አልበም ለውድድር ባቀረቡበት ወቅት ያምሉ ሞላም እንደ አልበሙ አዘጋጅ በአሕጉር ደረጃ የዓመቱ ምርጥ አዘጋጅ (‹ፕሮዲዩሰር›) እና የምሥራቅ አፍሪካ ምርጥ አርቲስት በሚሉ ሁለት ምድቦች ሊታጭ ችሏል። ድምጻዊት ቤቲ ጂ በስድስት ዘርፎች በታጨችበት የአፍሪማ የሽልማት መድረክ በወገግታ አልበሟ ‹‹የዓመቱ ምርጥ አልበም››፣ ‹‹የምሥራቅ አፍሪካ ምርጥ አርቲስት›› እና ‹‹የዓመቱ ክስተት›› (‹ሬቨሌሽን›) በሚሉ ሦሰት ዘርፎች አሸናፊ መሆን ችላለች። ቤቲ ጂ እነኚህን ሽልማቶች ልትጎናፀፍ የቻለችው እንደ ሼኪናህ እና ዲያመንድ ፕላቲነምዝ ከተሰኙ ከአሕጉራችን አልፈው ዓለም አቀፍ ዝናን ካካበቱ አርቲስቶች ጋር በመወዳደር ሲሆን በተቀሩት ዘርፎችም እንደ አንጀሊክ ኪጆ እና ዴቪዶን ከመሳሰሉ አርቲስቶች ጋር ለመፎካከር ችላለች። ቤቲ ጂ አሁን ባሸነፈችበት የዓመቱ ምርጥ አልበም ዘርፍ ከዚህ ቀደም ያሸነፈው ኤዲ ኬንዞ ተሰኘው ኡጋንዳዊ አርቲስት መሆኑ ይታወሳል።
አፍሪማ ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ጋር በመተባበር የሚዘጋጅ ዓመታዊ ሽልማት ሲሆን እ.ኤ.አ ከ2014 ጀምሮ በአፍሪካ ውስጥ ያሉ ሙዚቀኞችን እና የአፍሪካን የሙዚቃ ባሕል ለመደገፍ በሚል የተቋቋመ የሽልማት ተቋም ነው። ባለፉት ዓመታት ፍቅርአዲስ ነቃጥበብን ጨምሮ ፣ ቴዲ አፍሮ፣ ጃኖ ባንድ፣ ሄለን በርሄ፣ አቤል ሙሉጌታ፣ ክብሮም ብርሀኔ እና አንተነህ ምናሉ በአፍሪማ መድረክ ታጭተው የነበሩ ሲሆን ሄኖክ እና መሀሪ ብራዘርስ፣ ሀመልማል አባተ እና ፀደኒያ ገብረ ማርቆስ በተለያዩ ዘርፎች ማሸነፋቸው ይታወሳል።
ለቤቲ ጂ ሁለተኛዋ የሆነውን አልበሟን አዲስ ሊባል ከሚችለው ከወጣቱ አቀናባሪ ያምሉ ሞላ ጋር ለመሥራት የወሰነችው በጃኖ ባንዱ ጊታሪስትና አቀናባሪ ሚካኤል ሀይሉ ጥቆማ ሲሆን፤ ያምሉ እንደሚለው አልበሙን ሠርቶ ለማጠናቀቅ ከአምስት ወር በላይ አልፈጀባቸውም። በታጨችባቸው ዘርፎች በቀጥታ ያላሸነፈው ያምሉ እንደሚለው ያዘጋጀው አልበም የአፍሪካ የዓመቱ ምርጥ አልበም መባሉ እና በሌሎች ዘርፎችም ማሸነፉ በራሱ ለእሱ እና ለቤቲ ጂ እንዲሁም ለአገራችን ኢትዮጵያ ትልቅ ስኬት መሆኑን ያምናል። ከዚህ ቀደም በአፍሪማ መድረክ ላይ ምርጥ የአርኤንድቢ እና ሶል ዘርፍ አሸንፎ የሚያውቀው ሄኖክ መሀሪ፤ ‹‹ወገግታ›› አልበም በአፍሪማ መድረክ በትልልቅ ባለሙያዎች ግምገማ ይህንን ዕውቅና ማግኘቱ በትክክልም የሚባው መሆኑን ይናገራል። አልበሙ ተወዳደሪ በሆነ ጥራት፤ ለገበያ ሲባል ብቻ ሳይሆን ጠለቅ ባለ የፈጠራ ክህሎት ኢትዮጵያዊ ቀለሞች ተንፀባርቀውበት እንደተሰራ የሚናገረው ሄኖክ ‹‹እኔ በግሌ የኢትዮጵያ ሙዚቃ እንዲሆን በምፈልገው የደረጃ ልኬት የተሰራ›› ነው ሲልም ያሞካሸዋል።
የ34 ዓመት ወጣቱ ያምሉ በታዳጊነቱ እንደነ ዶክተር ድሬ፣ ፋሬል፣ ኩዊንሲ ጆንስ፣ አበጋዝ እና ኤሊያስ መልካ ሥራዎች ይማርኩት እንደነበር ያስታውሳል። በተለይም ኤልያስ መልካ ከሙዚቃዎቹ ባለፈ የግል የሕይወት ልምዶቹን በማካፈል ትልልቅ ቁም ነገሮችን እንዳስተማረው ይናገራል። ያምሉ ሞላ ከሌሎች የአገራችን የሙዚቃ አቀናባሪዎች በተለየ በቤተክርስቲያያ መድረኮች፣ በምሽት ክበቦች እና በባንዶች ውስጥ ሳያልፍ በቀጥታ ወደ ማቀናበር የመጣ መሆኑ ይናገራል። ከታዳጊነቱ ጀምሮ የታላቅ ወንድሙን ፈለግ በመከተል የሙዚቃ መሣሪያዎችን መለማመድ የጀመረ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱ ባጠናቀቀበት ወቅት ይህን ዝንባሌውን በማየት ወላጅ እናቱ ወደ ኮሌጅ ከመግባት ይልቅ ወደ ሙዚቃ ትምህርት ቤት እንዲሄድ እንዳደረጉት ያስታውሳል። ይህ አጋጣሚ ለራሱም እንደሚገርመው የሚናገረው ያምሉ የሙዚቃ ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ በቀጥታ በወላጆቹ ቤት ውስጥ ባሰናዳት ስቱዲዮ ውስጥ የተለያዩ ሙከራዎችን ማድረግ እና መንፈሳዊ ሙዚቃዎችን ማቀናበር እንደጀመረ ይናገራል። ‹‹ወላጆቼ ያን ያህል የሙዚቃ ሰው ባይሆኑም እኔም ራሴ አስቤ በማላውቀው መልኩ ሙዚቃን እንደ ሙያ እንድከተለው ድጋፍ ማድረጋቸውን እንደ ትልቅ እድለኝነት እቆጥረዋለሁ›› ይላል ያምሉ።
የቤቲ ጂን አልበም ከመሥራቱ በፊት የወንድሙን የዘሩባቤል ሞላን እና የቸሊናን ‹ወገኛ ነች› እና ‹ሳይ ባይ› የተሰኙ ነጠላ ዜማዎች የሠራ ሲሆን በዚህም በሙዚቀኞች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። ‹‹ከቤቲ ጂ ጋር ተገናኝተን በምንሠራው አልበም ዙሪያ ማውራት እንደጀመርን በቀላሉ ምን መሥራት እንደምንፈልግ ተግባባን፤ ቤቲ ጂ ሁለተኛ አልበሟን እንደምትሠራ ዝነኛ ሰው ሳይሆን ልክ እንደ አዲስ ዘፋኝ ነበር ያላት ተነሳሽነት እና ጉልበት›› ሲል ለአዲስ ማለዳ ያጫወተው ያምሉ ከቤቲ ጂ ጋር ከዓመታት በፊት ሲተዋወቁ የነበረዉን ትዝታ ገልጿል። ‹‹ለሽልማት አልነበረም የሠራነው፤ ሁለታችንም ጋር የነበረውን አስተሳሰብ እና እይታ ነበር ለማንፀባረቅ የሞከርነው፤ ዜማውን ከሠራን በኋላ ግጥሙ ላይ በጣም እንጨነቅበት ነበር። ጠንካራ ሐሳቦች ለማንሳት ብንፈልግም ሰዎች ሰምተውት በቀላሉ የሚረዱትና ውስጣቸው የሚቀር እንዲሆን ጥረናል፤ ቤት ከመምታትም በላይ ሥሜት የሚሰጡና ከቤቲ ጂ የአዘፋፈን ዜይቤ ጋር የሚሄዱ የድምፅ አጣጣሎችን ለማግኘት ብዙ ደክመናል። አሪፍ ምትትሮሽ ነበር፤ በእኔ በኩል ካሳየሁት ጠንካራ ነገር በበለጠ የሚገርም ነገር ሰርታ ስታሳየኝ እኔም ምላሹን የበለጠ ለማድረግ ባደረግነው ጥረት ነበር ብዙ አሪፍ ነገሮች የወጡት›› ሲልም የአምስት ወር የስቱዲዮ ቆይታቸውን በትዝታ ወደኋላ ተመልሶ ያስታውሳል።
“‹ኧረ ማነው› የሚለው ሙዚቃ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊባል በሚቻል ደረጃ አገርኛዉ ማሲንቆ የጊታር ዲስርሽን ተካቶበት ቀርቧል። በተጨማሪም ማሲንቆን እንደቫዮሊን እና እንደ ቼሎ ለመጠቀም መሞከራችን አልበሙን ልዩ ሊያደርገው ይችላል” ሲል የሚናገረው ያምሉ ‹‹ከሚታወቁት ጥቂት ዜማዎች ውጪ ያሉት ሙዚቃዎች የለፋንባቸውን ያህል አልተሰሙም፤ በጣም መሠማት የነበረባቸው ሙዚቃዎች አልበሙ ውስጥ ተካተዋል፤ በዚህ ረገድ ሚዲያው ትልቅ ሚና መጫወት አለበት›› በማለት ቁጭት አዘል ትዝብቱን አቅርቧል።
‹‹ምርጥ መሆን [አያኮራም] የተሻለ ምርጥ ሊመጣ ይችላልና በጊዜ ትታሰራለህ:: [የወቅቱ] ምርጥ ብቻ ነው መሆን የምትችለው፤ ልዩ ከሆንክ ግን መቼም ቢሆን አትሰለችም›› ይላል ያምሉ ለፈጠራ ስለሚሰጠው ቦታ ሲገልጽ። በሙዚቃ ኢንደስትሪ ውስጥ ማበርከት ስለሚፈልገውም አስተዋፅዖ ሲያብራራ ‹‹ሙዚቀኛ ስለሆንኩ ብቻ ማድረግ ያለብኝን ነገሮች አድርጌ ማለፍ አልፈልግም። ጤነኛ ይዘት ያላቸው፣ ሚዛን የሚደፉ ጠንካራ ሐሳቦችን በሙዚቃ ውስጥ ማበርከት እንዲሁም ጤነኛ ከባቢ ውስጥ ሙዚቃን መሥራት እፈልጋለሁ። ጠዋት ተነስቼ ወደ ስቱዲዮ ስመጣ እኔ የምሠራው ነገር ከእኔ አልፎ ሌሎች ላይ ተፅዕኖ ማሳደር እንደሚችል አስባለሁ›› ብሏል።
ያምሉ ‹አፍሪማ› ላይ የቤቲ ጂ አልበም ማሸነፉ የያዝኩት መንገድ ትክክለኛ መሆኑን የሚያረጋግጥልኝ ቢሆንም ከታዳጊነቴ ጀምሮ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ግራሚ መድረክ ላይ አሸናፊ ሆኖ ወይም ቢልቦርድ ላይ ምርጥ ዐሥር ውስጥ ገብቶ ማየት እደሚመኝ ይናገራል።
ድምጻዊ ሄኖክ መሃሪ በበኩሉ ‹‹በመሰል ውድድሮች ላይ መሳተፍ የአገራችንን ሙዚቃ ለዓለም ለማስተዋወቅ [የሚረዳ] መድረክ በመሆኑ የአገራችን አርቲስቶች በንቃት ሊሳተፉባቸው ይገባል›› ሲል ያሳስባል፤ አርቲስቶች ተገቢውን ጥረት እንደማያደርጉ በሚያሳብቅበት ድምፀት።
በተለያዩ የጃዝ እና የሬጌ የሙዚቃ ዝግጅቶ ላይ ጥዑም ዜማዎችን በማቀንቀን የምትታወቀው እና በቅርቡም ለተመልካች ባደረሰቸው ‹ሳይ ባይ› በሚል የሙዚቃ ቪዲዮዋ የምናውቃት ድምጻዊት ቸሊና ‹‹ከሌሎች ሙዚቀኞች በተለየ ያምሉ ሞላ እንደ ቢሮ ሠራተኛ ጠዋት ገብቶ አምሽቶ መውጣቱ ለሥራው እጅግ የሚጨነቅ ባለሙያ መሆኑን ያረጋግጣል›› ትላለች። የመጀመሪያ አልበሟን ከያምሉ ጋር ሠርታ እያገባደደች ያለችው ቸሊና እንደምትለው ያምሉ ከሱስ የፀዳ የሥራ ቦታ መፍጠሩ እና የሌሊት ሥራን አለመምረጡ ለሷ የሚመች የሥራ ከባቢን ፈጥሮላታል። የመጀመሪያ ነጠላ ዜማቸውን ከሠራላቸው ዘሩባቤል እና ቸሊና በተጨማሪ ‹ደስ› በሚል መጠሪያ ከሚታወቅ የሂፖፕ አርቲስት ጋር ያልተለመዱ ዓይነት የሙዚቃ ሥራዎችን ለአድማጮች ለማቅረብ የአፍሪማ ሽልማት ተጨማሪ ጉልበት እና የራስ መተማመን እንደሰጠው ያምሉ ተናግሯል። እነዚህን ጨምሮ የመረዋ ኳየርን እና የሌሎች ጀማሪና ነባር አርቲስቶች ሙዚቃዎች ተጠናቀው በቅርቡ ገበያ ላይ እንደሚውሉ ይጠበቃል።

ቅጽ 1 ቁጥር 3 ኅዳር 22 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here