ዓለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት 2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ሊያደርግ ነው

0
513

አለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም አይ.ኤም.ኤፍ ለኢትዮጵያ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የሚውል የ 2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ መወሰኑ ተገለፀ።
አገር በቀል ማሻሻያው በኢኮኖሚው ላይ የሚታዩትን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት እና በኢኮኖሚው ላይ የዘርፍ እና መዋቅራዊ ለውጥ በማምጣት ምጣኔ ሀብቱን ለማነቃቃት በመንግሥት የተቀረፀ ሲሆን፣ መንግሥት ላስቀመጠው የ10 ዓመት እቅድ ዋናው መሠረት ነው ተብሏል።
አገር በቀል አኮኖሚያዊ ማሻሻያው የወጪ ንግዱን ማሳደግ፣ የገቢ ሥርዓትን ማዘመን እና የዕዳ ጫናን መቀነስ ላይ ትኩረት የሚያደርግ ሲሆን፣ በቀጣይ ዓመታት ተግባራዊ ለማድረግ እስከ 10 ቢሊዮን ዶላር የሚጠይቅ ነው። ከዚህም ውስጥ 60 በመቶ የሚሆነውን ዓለማቀፉ የገንዝብ ድርጅት እና ዓለም ባንክ ለመሸፈን ቃል መግባታቸው ተገልጿል።
የዓለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባሳለፍነው ወር በኢትዮጵያ የአንቀጽ 4 ምክክር ላይ የገንዘብ ድጋፉን አስመልክቶ፣ በኢትዮጵያ መንግሥት በቀረበ ጥያቄ መሠረት ጥያቄውን ለመቀበል ከስምምነት ላይ መድረሱም ተጠቅሷል። አሁን የተደረሰው የመጀመሪያ ደረጃ ስምምነት በ ዓለም ዐቀፉ የገንዘብ ተቋም ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ተመርምሮ ሲፀድቅ መሆኑም ታውቋል።
ኢትዮጵያ ያለፈችበትን ስኬት ከግምት ያስገባ፣ የገጠሙ ተግዳሮቶችን ያማከለ እና የወደፊት መድረሻ ላይ ትኩረቱን በማድረግ የሚተገበር ማሻሻያ ሲሆን፣ አዳዲስ የእድገት ምንጮችን ለመፍጠር አስፈላጊውን መደላድል ያበጃል ተብሏል። የማክሮ ኢኮኖሚ ማእቀፉን ለማዘመን እንደሚያግዝ የተነገረለት ማሻሻያው ወቅቱ በሚፈልገው ደረጃ የተረጋጋ የፋይናንስ ስርዓትን ለመዘርጋት፣ ዘመናዊ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችሉ መንግሥታዊ ተቋማትን ለመገንባት ሲባል አገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው ከሚተገበርባቸው ምክንያቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

ቅጽ 2 ቁጥር 58 ታኅሣሥ 4 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here