አሁን ላይ በኢትዮጵያ ለሚታዩ ችግሮች የብሔር ጉዳይና የማንነት ጥያቄ ሳይሆን፤ የቡድን ማንነትን የመንግሥት መዋቅር እንዲሁም የአስተዳደር ስርዓት ማድረጉ ነው። ይህን ሐሳብ የሚያነሱት መላኩ አዳል፤ ከዚህም ባለፈ ችግር እየተከሰተ ያለው የሕዝብ ታሪክ ስላልተጻፈ ብቻ ሳይሆን ሁሉም የፖለቲካ ታሪክ እንዲኖረው ስለሚፈልግ ነው ሲሉም ይሞግታሉ። እነዚህም ተደራርበው ለድህነት ምክንያት ስለመሆናቸው ያብራራሉ፡፡ አያይዘውም አገራዊ ፓርቲዎችን የመመሥረትን ጥቅምን በማንሳት፣ ይካሔዳል ተብሎ ከሚጠበቀው አገራዊ ምርጫ በፊት እንዲሁም በኋላ ሊደረጉ ይገባል ያሏቸውን ጉዳዮች ጠቆም አድርገዋል።
ለውጥ በሐሳብ፣ በተጨባጭ ያሉ መሠረታዊ ችግሮች ምን ምን እንደሆኑና ችግሮቹ የሚፈቱበትን መንገድ በለየውና ለዚህም የትምህርትና የተግባር ተሞክሮ ባካበተው ምሁር የሚመራ፣ ቢያንስ የሚታገዝ መሆን አለበት። ሐሳቦቻችን ዘረኝነትን ያስወገዱና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ታሳቢ ያደረጉ፣ የሚያስተምሩ፣ የሚያመራምሩ፣ የሚያከራክሩና የሚያፈላስፉ እንዲሆኑ መሥራት፤ የራሳችንን ኅብረተሰብ እውቀት የጨመሩና የዓለምንም እውቀት ያዋሐዱ እንዲሆኑ መጣር፤ የአገራችንን መልካም ምድሯን፣ ፀጋዋን፣ ሕዝቧንና ችግሯን በማወቅ የመፍትሔ አቅጣጫና መንገድን የሚጠቁሙ እንዲሆኑ ማድረግ ይኖርብናል።
አንዱ የእኛ ችግር፣ የችግርና የመንስኤ ግንኙነትን በደንብ ያለመለየትና የችግሩን መንስኤ መለየት የመፍትሔው አካል መሆኑን አለመረዳት ብሎም ጊዜያዊ መፍትሔ ፈላጊዎች መሆናችን ነው። ለአገራችን በልማትና በእድገት አለመግፋት መሠረታዊ ምክንያቶች ታሪክ፣ ጂኦግራፊ፣ ባህል፣ ፖለቲካ እና ተቋማት ናቸው።
ይህም ማለት የእውቀት ማነስ፤ በርእዮት አለመመራት፣ የሕግና ስርአት አለመኖርና እሱን ተከትሎ የመጣው ጦርነት (ጀብደኝነት)፣ መብትንና ግዴታን አለመለየትና አለመፈጸም፣ የሕግ የበላይነትን አለማክበር ወይም አለማስከበር፣ ፍትኀዊ የሃብት ክፍፍል አለመኖር፣ መደራጀት አለመቻል፣ ሐሳብን በነጻነት አለመግለጽ፣ የመምረጥ/አለመምረጥ መብት አለመከበር፣ የሚዲያ ነጻነት አለመኖር፣ የማኅበረሰብ ግልጽነት መጥፋት፣ አለመተማመንና አለመነጋገር፣ የመከባበር አለመኖር፣ ጥሩ መሪ ማፍራት አለመቻል፣ ሙስና፣ የትምህርትና የመጓጓዣ መሠረተ ልማት አለመሟላት፣ አባታዊ የቤተሰብ ደንብና አስተዳደግ፣ ጭቆናን እንደ ግዴታ መቁጠር፣ የስርአቱ ተጠቃሚና ተጎጂው ተቀላቅሎ መገኘትና ኅብረትን መቀነሱ፤ የደኅንነት ስጋት፣ የማኅበረሰብ እድገትና ማኅበራዊ ሃብት (social capital) ዝቅተኛ መሆን ናቸው።
ባህል መብልና አበላልን፣ ልብስና አለባበስን፣ ንግግርና አነጋገርን፣ ሐሳብንና አስተሳሰብን፣ ጥርጣሬንና እምነትን፣ ሥራና መሣሪያን፣ ፍርሃትና ጉብዝናን፣ ፍቅርና ደስታን፣ ደስታና ሃዘንን፣ በተጨማሪም የአገርን የፖለቲካና የአስተዳደር ባህልንም የሚያካትት፣ በአጠቅላይ ኑሮንና ሕይወትን የሚነካ የኅብረተሰብ ቅርስ ነው። በቅርስነቱም ለውጥን የመከላከልና ራሱን የመጠበቅ ዝንባሌ አለው፤ መለወጥ ግዴታ በመሆኑ ባይቀርለትም። ለዛም ነው ለልማትና ለእድገት ልዩነት አንዱ መንስኤ የሆነው።
ጠንካራ ተቋማትና አመቺ ፖለቲካ በሌለበት ወይም ባልጠነከረበት ሁኔታ ጥሩ የኢኮኖሚ አስተሳሰብና ፖሊሲዎች ብቻ መሠረታዊ ለውጥ ሊያመጡ አይችሉም። ይህም የሚያሳየን ፖለቲካና ተቋማት ከልማትና እድገት ጋር ያላቸውን ግንኙነት ነው። የመሪዎች መቀያየር ሳይሆን በመሪዎች የሚመጣው አዎንታዊ የፖለቲካ ለውጥና የተገነቡት ተቋማት ናቸው ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉት።
ሥልጣን ሕዝብን ለማገለገል ሳይሆን ለክብር፣ ለሃብትና ምቾት፣ ለኀይልና ተደማጭነት፣ ከሰው በላይ ሆኖ ለመገኘት በሚያዝበት አገር፤ ሃላፊነትን ለውጭ ኀይል ከመስጠት ይልቅ በራሳችን ለራሳችን ካልወሰድን ኑሯችን ማሻሻል፣ ከጨቋኞች ስር መውጣት፣ ከድህነትና ድንቁርና መላቀቅ አንችልም። ደካማ ቢሮክራቶች እንዲበራከቱ፤ እንዲያውም ጠንካራዎቹ እንዳይመጡ ይከላከላል። እነዚህም የበላይ አለቆቻቸውን በጭፍን ያመልካሉ፣ የአለቆችን ትእዛዝ ያለጥያቄ ይፈጽማሉ፤ ያስፈጽማሉም፤ የበታቾቻቸውን አቅም መጠቀም አይችሉም፣ አለቆቻቸውን ለማስደሰት የተጋነነ ሪፖርት ያቀርባሉ፣ በመጨረሻም እራሳቸውንም ሌላውንም ያስበላሉ።
የግራ ዘመም ፖለቲካ አራማጁ የነበረው የያ ትውልድ ወጣት ለአገሩ ጥሩ አሳቢ ቢሆንም በእውቀቱ ውስንነት ምክንያት ‹‹ሶሻሊዝም ተግባራዊ የሚሆነው ባካፒታሊዝም መቃብር ላይ ነው›› የሚለውን ሐሳብ ረስተው፣ በጉልተኛ ስርአትና ባህል ውስጥ በነበረች አገር ላይ ሶሻሊዝምን ተግባራዊ ለማድረግ በመሞከራቸው የራሳቸውን ሕይወት አጥተው፣ የአገሪቱንም የወደፊት እድገት አበላሽተዋል።
ይህ ወጣት የፕሮግራም፣ የአደረጃጀት፣ የርእዮት-ዓለም ምርጫ ያልለየ፤ አገር በፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንደምትመራ፣ ተቋማት ግንባታ እንደሚያስፈልግ፤ የሕዝብን እውቀት፣ የባህል፣ የሃይማኖትና የባህልን ትስስር ያልለየ እና በጠቅላላው አገሩን የማያውቅ ትውልድ ነበር። እንዲያውም ሃይማኖትን ሲተቹ ኢትዮጵያ ውስጥ የአይሁድ፣ ክርስትናና እስልምና ሃይማኖቶች፣ ከተቋምነት አልፈው ባህል መሆናቸውንና ሃይማኖትን ሲተቹ ባህላችንንም እየተቹ መሆናቸውን ረስተዋል። ይህም ማለት የግራ ዘመም ፖለቲካ አራማጁ ወጣት አሸናፊም ተሸናፊም፣ ተሸናፊነታቸው በአገሪቱ ሁሉም መስክ ውድቀት ተጋላጭ ሆኗል።
ጀግኖቻችንን በግዞት፣ በእስርና በግድያ ስናጣ የኖርን ሕዝብ ነን። አሁን ደግሞ ከሁሉም በከፋና ጽንፍ በያዘ ብሔርተኝነት ተጠምድን ለሥራቸው እንቅፋት እየሆንን ነው። በዚያ የትርምስ አብዮት ወቅት የተቀነቀነውን የብሔር ጭቆና የሐሰት ትርክት መሠረት ያደረገ የዘውግ ፖለቲካና የፌዴሬሽን አወቃቀር በመከተል፣ ለአገር አንድነትና ህልውና ብሎም እድገት እንቅፋት እየሆንን ነው።
ብሔርተኝነት በርእዮትነቱ አንድ ነገር ብቻ ነው፤ ዘረኝነት። ችግሩ የብሔር ጉዳይ የማንነት ጥያቄ መሆኑ ላይ ስምምነት አለመደረሱ አይደለም። የቡድን ማንነት እንዲከበር መሥራትም አለብን። የኢትዮጵያውያን ዋናው ችግራችን ይህ የቡድን ማንነት (ዘረኝነትን) የመንግሥት መዋቅራችንና የአስተዳደር ስርአታችን ማድረጋችን ነው። ይህም የፌዴራል መንግሥት በሕገ መንግሥቱ የተጣለበትን የክልል መንግሥታትና የፌዴራል መንግሥትን ግንኙነት ያለአድሎ የማስተካከል፣ ሥርዓት በያዘ መልኩ ያልተከናወነው የአገራዊ መግባባት፣ የተጠያቂነት እና የእርቅ ጉዳይ አለመከናወን እንዲሁም የሕግ የበላይነትን የማስከበር ተግባሩን ትቶ ለብሔሩ ብቻ የሚሠራ ተረኛና ዘረኛ እንዲሆን አድርጎታል።
የብሔር ጭቆና የሐሰት ትርክት የዳረገን አሁን ላለንበት የፖለቲካ ትርምስና ጽንፈኛ ብሔርተኝነት ብቻ አይደለም፣ ለኤርትራም መገንጠል የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል። አሁን ደግሞ ይህን ዘውጌነት በኢኮኖሚ የሚደግፉ እንደ ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ ኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ፣ ደቡብ ግሎባል ባንክ፣ አማራ ባንክ . . . ወዘተ እና ተጨማሪ ማንነትን ወደ ፖለቲካችን የሚያስገባ እስላማዊና ክርስቲያናዊ ባንኮች እየተፈቀዱ እንደሆነ ሲታስብ፣ ይህ እብደት የት ያደርሰን ይሆን ያስብላል? ለዚህም ነው አሁንም በነሱ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ፍልስፍና እየወደቅን ያለነው።
ታሪክ በጠቅላላው እንዲሁም የሕዝብ ታሪክ በተለይ እንዴት ይጻፍ የሚለው ጥያቄ መሠረታዊ ነው። የትንንሾችም ታሪክ ሊጻፍ ይገባል የሚለው ጥሩ ሐሳብ፣ በፖለቲካ ታሪካችን ውስጥ ያልተካተተው ስላልተጻፈ ነው ወደሚል የቡድኖች ማጠቃለያ እንዳይወስደን እሰጋለሁ። ሁሉንም ታሪክ መጻፍ ከባድ ቢሆንም፣ በሚጻፍበት ጊዜ በመረጃ የተደገፈ፣ ከአድሎ ነጻ፣ ሚዛናዊና አቃፊ መሆን እንዳለበት ሁላችንንም የሚያስማማ ነው።
የሕዝብ ታሪክ በተቻለ መጠን ከፖለቲከኞቻችንና የጦር መሪዎች ታሪክ በተጨማሪ የታሪካችን አካል እንዲሆን፣ ብዙ ሙያተኞች በማፍራት መሥራት እንደሚኖርብን ሁላችንንም ያስማማል። መታውቅ ያለበት ግን ሁሉንም የሕዝብ ታሪክ መጻፍ የቻለ ማንም አገር በዓለም ታሪክ የለም፣ ሊኖርም አይችልም። አሁን በታሪካችን ትርክት ችግር ውስጥ የገባነው፣ የሕዝብ ታሪክ ስላልተጻፈ ብቻ ሳይሆን ሁሉም የፖለቲካ ታሪክ እንዲኖረው ስለፈለገ ነው። ይህ ግን የማይሆን ነው። ምክንያቱም ምንም ዴሞክራሲ ቢሰፍን፣ የፖለቲካ ታሪክ የመሪዎችና በዙሪያቸው ያሉ የስርአቱ ሰዎች ታሪክ ከመሆን አያልፍምና።
ስለዚህም የፖለቲካ ታሪክ አልተጻፈልኝም በሚል ሽፋን ሙሉ የአገርን ታሪክ ማጣጣልና የኔ ታሪክ አይደለም ብሎ መካድ፣ የታሪክ ተፈጥሮን በደንብ ካለመረዳትና ከፖለቲከኞች መሰሪነት የመነጨ ነው። ስለዚህም ነው በሶስዮሎጂና አንትሮፖሎጂ የትምህርትና የጥናት ዘርፎች የብዙኀኑን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ታሪክ እንዲጠና የሚደረገው። ለዚህም ነው ይህ የኅብረተሰባችን ባህላዊ ታሪኩ (እሴቶቹ፣ ወግና ልምዱ፣ ምልክቶቹ፣ ቋንቋው፣ ሳይንስና ፈጠራው) እና ኢኮኖሚው ታሪኩ (የአመራረት ስልቱ፣ የማምረቻ ግብአቱ፣ የምርት ስብሰባው ዘዴ፣ የገበያና የልውውጥ ስርአቱ ወዘት) በደንብ መጠናትና የታሪካችን አካል እንዲሆን መሥራት የሚኖርበት።
ይህ ይመስለኛል፣ የጎደለውን የሕዝብ ታሪክ የሚሞላው። አሁን እየሔድንበት ያለው የፖለቲካ ታሪክ ሽሚያ ግን ለስህተትና ብጥብጥ እየዳረገን ስለሆነ፣ ልናቆመውና ወደ ትክክለኛው መንገድ ልንመለስ ይገባል።
ሰላም አፋዊ ጸጥታ ወይም ጦርነት አለመኖር ብቻ አይደለም። ሰላም የውስጥ ደስታ፣ ለራስና ለሌሎችም ሰዎች ሙሉ አክብሮትንና መተማምን ሲኖር፣ ባለው ሕግና ሥነ-ስርአት ላይ ሙሉ እምነት ሲኖርና በቅንነት የራስን ችሎታ በማዳበር የግል ኑሮን ለመምራት የሚያበቃ ሁኔታ ሲኖር ነው። ለሰላም መስፈንና ለእኩልነትና ለፍትኅ፣ ለነጻነትና መብት መከበር በመቆም ደግሞ እስከ ሕይወት መስጠት የሚደርስ ክፍያ አለ።
በኦሮሚያ የሚፈጽመው ሰው ማፈናቀል፣ መግደል፣ ባንክ መዝረፍ፣ ቤተ-ክርስትያን መዝረፍን፣ ማቃጠልንና መከፋፈልን፤ በአጠቃላይ ለሺሕ ዘመናት የተሠሩ የኢትዮጵያ እሴቶችን ማፍረስ ከኦዴፓ በሐሳብ መከፋፈል ጋር የተገናኘ መሆኑን እየታዘብን ነው። በኦሮሚያ የሚንቀሳቀሱ የሌሎች ፓርቲዎች እጅ እንዳለበትም ግሃድ ወጥቷል። በዚህም የ21ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ የማይመጥንና የኢትዮጵያ ወደ ኹለተኛው ዘመነ መሳፍንት ዘመንም የሚመራና ለአገር ህልውና አደጋ የሚፈጥር ጉዳይ ነው።
የአገራዊ ፓርቲዎች መመሥረት እጅግ ጥሩ ፖለቲካዊ ጅማሮ ነው። ብልጽግና ግን እንደ መሪ ፓርቲ ከምርጫ በፊት ማከናወን ያለበት ተግባራት አሉ። የሕወሓትን የገንዘብ አቅም ማዳከም፣ ይህ እንዲሆን ግን አጋዦቹን ኦነግና ጃ-ወርን ጥጋቸውን ማስያዝ ያስፈልጋል። እጅግ የደከመውን የታችኛውን የመንግሥት መዋቅርም ማስተካከልና ማጠንከር ይገባል። በተጨማሪም ተቋማትን ማደራጀትና ማስተካከል ይጠይቃል።
ይህን ለማድረግ ምርጫውንም ማራዘም አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። ከምርጫ በኋላ ደግሞ ሕገ መንግሥትን የማሻሻልና ትልልቅ ክልሎችን የሀብት፣ የሕዝብ ብዛትን፣ የአስተዳደር አመቺነትን ጨምሮ ተመጣጣኝ በማድረግ ፌዴራል አወቃቀሩን ማስተካከል ያስፈልጋል። ይህን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ካልተንቀሳቀስንና ወደ ምርጫ ዘው ተብሎ ከተገባ ግን፣ አገራችንን ወደ ትርምስ ለማስገባት ለሚያስቡ ሰዎች ጥሩ አጋጣሚ መፍጠር እንዳይሆን ያሰጋል።
ስለዚህም፣ ቁጭ ብሎ መነጋገር፣ የተሻለውን መንገድ ተነጋግሮ መምረጥ፣ ሕገ-መንግሥቱን፣ ፌዴራል አወቃቀሩንና የትምህርት ስርአትን ማስተካከል ያሻል። የ1960ዎቹ ፖለቲካ ካመጣብን አሉታዊ ጉዳቶች መማርም ይጠቅማል። ነገር ግን አሁን እያደረግነው ያለነው ያኛውን ነው። እናም የትናንቱ ኪሳራችን፣ አሁንም ሊደገም ይችላል። ከታሪካችን፣ ከውድቀታችን መማር አልቻልንምና። ነገ ከመቆጨት አሁን ቆመን እናስብ፤ ከትናንት እንማር፤ ሁሉንም አቃፊ ለሆነ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ምስረታ እንጣር እላለሁ፤ ‹‹ጅብ ከሔደ ውሻ ጮኸ›› እንዳይሆን።
መላኩ አዳል የዶከትሬት ዲግሪ በባዮ ሜዲካል ሳይንስ በማጥናት ላይ ናቸው። በኢሜል አድራሻቸው [email protected] ሊገኙ ይችላሉ።
ቅጽ 2 ቁጥር 58 ታኅሣሥ 4 2012


