የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ የ22 ሰዓት የቤተ መጻሐፍት አገልግሎት እንደጀመረ ገለጸ፡፡
የኤጀንሲው የህዝብና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ከፍተኛ ባለሙያ አዘዘ ጌትነት ለአዲስ ማለዳ እንዳሳወቁት ከሕዳር 20/2011 ጀምሮ የ22 ሰዓት አገልግሎት ጀመሯል፡፡
ኤጀንሲው ከዚህ ቀደም ከጠዋቱ 2፡00 እስከ ምሽቱ 1፡00 ሰዓት ድረስ አገልግሎቱን ይሠጥ የነበረ በሆንም ከተገልጋዮች በኩል የሰዓት አጠረ ጥያቄ ይነሳ ነበር ተብሏል፡፡ ይህም በተቋሙ ዘንድ አመርቂ ውጤት እንዳይመዘገብ ማድረጉም ተጠቅሷል፡፡
የሕብረተሰቡ የማንበብ ፍላጎት መጨመር እንዲሁም ሁሉም ሰው ተመሳሳይ የማንበቢያ ጊዜ የሌለው መሆኑን በመገንዘብ ሕብረተሰቡ የሚፈልገውን መረጃ በሚፈልገው ሰዓት እንዲያገኝ ሲባል በቀን ለ10 ሰዓት ተወስኖ የነበረውን አገልግሎት ወደ 22 ሰዓት ማሳደግ ማስፈለገን አዘዘ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
ኤጀንሲው በአንባቢያን ፍላጎት ከፍ ማለት የ22 ሰዓት አገልግሎቱ ይጀምር እንጂ፣ በሌላ በኩል ሲታይ የሕፃናት ቤተ መጻሕፍትንና የብሬይል (የዓይነ ስውራን ስርዓተ ፅሕፈት) ቤተ መጻሕፍትን ተገልጋዮች በሚፈለገው ልክ አልተጠቀሙበትም ብሏል፡፡ ስለሆነም ወላጆች ለራሳው ብቻ ሳይሆን ልጆቻቸውንም በማምጣት እንዲያነቡ ቢያደርጉ መልካም ስለመሆኑ አስታውሷል፡፡
የኤጀንሲው 22 ሰዓት አገልግሎቱን ቀድመው በነበሩት ሰራተኞች ያስጀመረ ሲሆን በትርፍ ሰዓታቸው ለሚሰሩ ሰራተኞች ከደመወዛቸው በተጨመሪ ክፍያ እንዲታሰብላቸው ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
ቅጽ 1 ቁጥር 3 ኅዳር 22 ቀን 2011