ጦብያ ግጥምን በጃዝ – ከ100 መድረኮች በኋላ

0
1398

በየወሩ የመጀመሪያው ረቡዕ ከቀኑ ዐስር ሰዓት ሲቃረብ ጀምሮ ራስ ሆቴል በር ላይ ረዘም ያለ ሰልፍ ማየት የተለመደ ነው። በራስ ሆቴል ትልቁ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ የሚቀርበውን መሰናዶ መቀመጫ ወንበር ይዞ ከተቻለም ወደፊት ተቀምጦ ለመከታተል ቀድሞ መገኘቱን በቻለ መጠን እውን ያደርጋል፤ ታዳሚ። ትኬት ለመቁረጥ፣ አዳራሽ እስኪከፈት ከዛ ደግሞ የእለቱ መርሃ ግብር እስኪጀመር መጠበቅ ለጦብያ ግጥምን በጃዝ ወርሃዊ መሰናዶ ታዳሚ ደንብ ነው፤ ያውም በጉጉትና በደስታ የሚያደርገው።
እንዲህ ባለ መልኩ ቅርብ ዓመታትን ጨምሮ ከስምንት ዓመት በላይ ለተመልካችና አድማጭ ሲቀርብ የነበረው ጦብያ ግጥምን በጃዝ አንድ መቶኛ ክዋኔ ባሳለፍነው ወር የተከናወነ ሲሆን፣ ነገ ታኅሳስ 01 ቀን 2012 ደግሞ 100ኛ ወር ክብረ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ደመቅ ያለ ክዋኔ በኤልያና ሞል ተሰናድቷል። አዲስ ማለዳም ጦብያ ግጥምን በጃዝ ያለፈበትን መንገድ በሚመለከት ጥቂት ሐሳቦችን ልታነሳ ወደደች።
ግጥም በጃዝ እና ጦብያ
ጦብያ ግጥምን በጃዝ ከመመሥረቱ በፊት ግጥም በጃዝ በራሱ ቀድም ብሎ የጀመረ ነው። በእርግጥ የግጥም በጃዝ አጀማመርን በተመለከተ የተለያዩ የጥበብ ሰዎች የተለያዩ ሐሳቦችን ይሰጣሉ። በእነዚህ ግጥም በጃዝ የተጀመረበት ጊዜ እና ማን ጀመረ በሚሉት ጉዳዮች ላይ በሚነሱት የተለያዩ ሐሳቦች መካከል በጊዜ አውድ ጠባብ የሚባል የወራት ልዩነት ያለ በመሆኑ፣ ልዩነቱን በመተው ሁሉንም በየክስተታቸው ማየቱ ይቀላል።
ታድያ ግጥም በጃዝ ስሙ ሲነሳ ከስምንት ዓመት ተኩል በፊት በቦሌ ሮክ ተጀምሮ ቀጥሎም በዋቢ ሸበሌ ይካሔደ የነበረውን መድረክ የሚያስታውሱ አሉ። ይህም ሲጀመር በየሳምንቱ ይካሔድ የነበረና በቸርነት ወልደገብርኤል መሥራችነት የተጀመረ፤ የገጣምያን ደምሰው መርሻ፣ አበባው መላኩ እንዲሁም የደራሲና ገጣሚ እንዳለጌታ ከበደ ተሳትፎም የሚነሳበት ነው።
ከዚህ ቀደም ብሎ ግን ከጃዝ ውጪ ግጥሞች በገዛ ዜማቸው የሚቀርቡበት መድረክ በገርጂ ኢምፔርያል ሆቴል ይካሔድ እንደነበርም ይነገራል። ይልቁንም እስክንድር ኃይሉ በተባለ ሰው ጀማሪነት፣ አሁን ላይ አንጋፋ የሆኑ ገጣምያን ሥራዎቻቸውን የሚቀርቡበት አውድ ተዘጋጅቶ ነበር።
ገጣሚና ጦብያ ግጥም በጃዝን በዋናነት እያስተባበረች ያለችው ምሥራቅ ተረፈ በበኩሏ፤ ጦብያ ግጥምን በጃዝ በዚህ ስማ ሳይመሠረት በፊት በአልያንስ ኢትዮ ፍራንሲስ በ1999 የመጀመሪያ ሆኖ እንደጀመረ ለአዲስ ማለዳ ገልጻለች። ይህም አበባው መላኩ፣ ፍሬዘር አድማሱ፣ ዶክተር ፈቃደ አዘዘ፣ ምሥራቅ ተረፈ፣ ምሕረት ደበበ፣ ደምሰው መርሻ ከሐራ ሳውንድ ጋር አሃዱ ብለው ያቀረቡበት መድረክ ነው።
ይህም ሥሙን አድምቆ ጦብያ ግጥም በጃዝ ተብሎ ወደ ራስ ሆቴል ሲያቀና፤ የጦብያ መሥራች ተብለው የተመዘገቡት አበባው መላኩ፣ ደምሰው መርሻ፣ ምህረት ከበደ፣ ግሩም ዘነበ እንዲሁም ራሷ ምሥራቅ በጋራ መሆናቸውንም ምሥራቅ አክላ ገልጻለች። የግጥም በጃዝ መጀመር፣ የጦብያ ግጥም በጃዝ የራሱን ቀለም ይዞ መምጣት፣ የተለያዩ ግጥምን በጃዝ ያጀቡ መድረኮችም ተከትለው መፈጠራቸው ለተደራሲ፣ ለተመልካችና አድማጩ ተጨማሪ እድል የፈጠሩ ናቸውና ሁሉም እጅ ሊነሱና ሊመሰገኑ የሚገባ ነው።
ግጥም በጃዝና ዲስኩር በጃዝ – በጦብያ
ጦብያ ግጥም በጃዝ እንደሥሙ አስቀድሞ ግጥሞች በብዛት የሚቀርቡበት፣ አዳዲስ ገጣምያን ከታዳሚ የሚገናኙበትና ነፍሳቸውን አድምጠው ያመጡትን ሐሳብ ለብዙዎች የሚያቀብሉበት መድረክ ነው። ‹‹እኛም ግጥም ስለምንጽፍ ትኩረቱ ግጽ ነበር›› ያለችው ምሥራቅ፣ ሌሎች የጥበብ ዘርፎችን ማካተት የሚለውም በጊዜ ሒደት የመጣ ሐሳብ ስለመሆኑ ትገልጻለች። በዚህም መሠረት ተውኔት፣ ሙዚቃ፣ ዲስኩርና መሰል መሰናዶዎች የጦብያ ግጥምን በጃዝ መድረኮች ላይ ተጨማሪ ድምቀት መሆን ቻሉ።
ለግጥም ልዩ ስሜት ያላቸው ሰዎች ትኩረቱ ግጥም ላይ እንዲሆን ከመሻትና አዳዲስ ገጣምያንን መስማት ከመፈለጋቸው የተነሳ፣ በዚህ ላይ ቅሬታ ሲያሲሙ ይደመጣል። ከዚህ መካከል አንዷ ትዕግስት አማረ ናት። ትዕግስት ጥቂት ቢሆኑም በሁሉም በሚያስብል ደረጃ የጥበብ ክዋኔዎ ላይ ታዳሚ ናት። ከሁሉም አብልጣ ግጥምን የምትወድ በመሆኑ ‹‹ግጥም ችላ ተብሎ ዲስኩር ነው ትኩረት እያገኘ ያለው፤ ግጥም ብቻ መስማት የሚፈልግ ሰው ግን አለ›› ስትል ትሟገታለች። በአንጻሩ ከግጥም ባሻገር ሐሳብን በዝርው፣ ከአንደበተ ርትዑ ሰው መስማትን የሚሻ ደግሞ በትዕግስት ሐሳብ አይስማማም። ‹‹ምን አለበት!›› ሲል ይጠይቃል።
ያም ሆነ ይህ፤ ጦብያ አይረሴና ብዙዎች ለቀናት የተቀባበሏቸውን ግጥሞች እንዲሁም ብዙ ተጽእኖ መፍጠር የቻሉ ዲስኩሮችን በመድረኩ ላይ አስተናግዷል። ያም ብቻ ሳይሆን ተመልካችና አድማጭ መፍጠር ችሏል ማለትም ይቻላል። ምሥራቅ በዚህ ላይ አስተያየት ስትሰጥ፤ ‹‹ስንጀምር ችግር ነበረው፤ ግጥም የለመደን ሰው አዳምጥ ስንለው የተለያየ ግብረ መልስ ይሰጠን ነበር፤ ረዘመብን ከሚሉ ጀምሮ። ቀስ እያለ ነው የተለመደው›› ብላለች። እንዲሁም አሁን ላይ ያለውን ለግጥም ክፍት የሆነ ጆሮም ዜማውና ተውኔቱ፣ ውዝዋዜውና ዲስኩሩ በጋራ አምጥተውታል።
በዚህ አዲስ ፍላጎት ውስጥ ታድያ ቢያንስ በአንድ መድረክ ላይ አምስት ግጥሞች እንደሚቀርቡ ነው ምሥራቅ የጠቀሰችው። በተጓዳኝ ጥሩ ግጥሞች አለመገኘትና ከገጣምያን ጋር አለመገናኘትን እንደ አንዱ ምክንያት ተነስቷል። ለዚህም ከአዲስ አበባ ባሻገር ያሉ ገጣምያንም እንዲሳተፉ ለማድረግ ጥረት ይደረጋል፤ በጦብያ ግጥም በጃዝ አዘጋጆች።
ከዚህ ላይ ተያይዞ የሚነሳው የፖለቲካው ነገር ገንኖ የመውጣቱ ጉዳይ ነው። ለአዲስ ማለዳ አስተያየቷን የሰጠችው ምሥራቅ፣ ‹‹ጥበብ ኃላፊነት አለባት ብዬ አስባለሁ፤ ሰዉም ዘመኑን ይመስል የለ? እንኳን ገጣሚ የሃይማኖት አባቶችም ፖለቲካውን ያነሳሉ፤ የዘመኑ ሁኔታ ጫና ይፈጥራል›› ትላለች። እናም ፖለቲካ በየቤቱ መግባቱ ገጣሚውም ጋር በመሆኑ እሱን ነው እያወጣ ያለው።
ሆኖም ገጣሚ ከዚህ [ከሚታየው] አሻግሮ ማየት እንዳለበት እምነቷን ገልጻለች። አዲስ እይታን በማምጣትም ጥበብን ከፍ አድርጎ ለከፍታ ማዋል ይገባልም።
በዚሁ በጦብያ የቀረቡና እየታዩ የነበሩ ተውኔቶችን እናንሳ። በተለይም በ2011 እይታው ያበቃው በ በድሉ ዋቅጅራ (ዶክተር) ተጽፎ በተዋንያኑ ሽመልስ አበራ እና እታፈራሁ መብራቱ የሚቀርበው ‹የደብተራው ተውኔት› ይነሳል። ይህም ዝምታ የተሻለ ምሽግ በነበረበትና ፖለቲካው አስጨናቂ ሆኖ በቆየበት ጊዜ ለብዙዎች መተንፈሻ የነበረ ተውኔት መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። በጦብያ ግጥም በጃዝ ታድያ ከዚህም በሻገር ‹እያስመዘገብኩ ነው› ‹እያዩ ፈንገስ› ‹ኮሚቴው› ‹ከድር ሰተቴ› አሁን ላይ ደግሞ ‹ፍራሽ አዳሽ› የተሰኙ አጫጭር ተውኔቶችን አስተናግዷል። ከእነዚህም የሙሉ ጊዜ ቴአትር ሆነው የቀረቡ መኖራቸውን ልብ ይሏል!
ጦብያ በአርትስ ቲቪ
ጦብያ ግጥምን በጃዝ በየወሩ ባለው መድረክ ላይ ለመታደም ላልቻሉ አዲስ አማራጭ መንገድ ይዞ ከመጣ ውሎ አድሯል። ምሥራቅ እንዲህ አለች፤ ‹‹ፕሮግራሙ ለ7 ዓመታት መድረክ ላይ ብቻ ተቀብሮ ነበር። እውነት ስለሚነገርበት ዘመኑ አይፈልገንም ነበር፤ የሰባት ዓመት ፊልሞች አልታዩም። ከዓመት በፊት ግን አርትስ ቲቪዎች ጋበዙን››
ጦብያ ከመድረክ ተሻግሮ በየሰዉ ቤት የትዕይንተ መስኮት በመቅረቡ ብዙ ነው ያተረፍነው ትላለች አዘጋጇ ምሥራቅ። ‹‹የተለያየ ዓለም ክፍል ያሉ ሰዎች ስሜቱን ተጋርተው ሲያመሰግኑና ሲመርቁ እናያለን፤ አሁን በደንብ ነው እየታየ ያለውና ትልቅ ሥራ ነው የተሠራው።›› ስትልም ምስጋናውን ለአርትስ ቲቪ ሰጥታለች።
ፈተናዎችና እቅዶች
‹‹ሁሌም ፈተናችን አዳራሽ ነው›› ስትል ጀመረች ምሥራቅ። ክዋኔው ከ100 ወራት በፊት አንድ ሺ ኹለት መቶ ሰው በሚይዘው የራስ ሆቴል አዳራሽ ነበር የተጀመረው። ‹‹አሁን በተፈጠረው ብዙ ፍላጎት መካከልም በዛው በራስ ሆቴል አዳራሽ ነን።›› ስትል ሁኔታውን ታስረዳለች። ይልቁንም አሁን ባለው ሁኔታ ጥበብን በማክበር መሬት ላይ ቁጭ ብለው ሳይቀር እስከ ፕሮግራሙ ፍጻሜ የሚታደሙ መኖራቸውን ታነሳለች።
ለዚህ መፍትሔ የሚሆነውም የባለሀብቶች ተሳትፎ ስለመሆኑም ሳትጠቅስ አልቀረችም። ባለሀብቶች ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን በጥበብ በኩል መወጣት እንደሚችሉና፤ ወጣቶች በሚያደርሱት ጥፋት ከመቆጣት ይልቅ አስቀድሞ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ማስተማር ይገባቸዋልም ብላለች።
ይህን ችግር በመፍታት ውስጥ ታድያ የትኬት ሽያጩም ጉዳይ ይነሳል። የመርሃ ግብሩ ተከታታይ ታዳሚዎች ከሚያነሱት ሐሳብ መካከል አንዱ ይኸው የትኬት ጉዳይ ነው። ምሥራቅ በዚህ ላይ ጥሪው 11፡30 ቢልም ታዳሚ ከ10 ሰዓት ጀምሮ በራስ ሆቴል በሮች እንደሚገኝና በዛን ሰዓት ወደ አዳራሽ ማስገባት ደግሞ አስቸጋሪ መሆኑን ጠቅሳለች፤ የመድረክ ቅድመ ዝግጅት ስለሚኖር።
ታድያ በእለቱ የሚሸጠውን ትኬትም በተመለከተ በኢንተርኔት፣ በድረ ገጽ ቀድመው እንዲሸጡና በወንበሮች ልክ እንዲሆኑ ለማድረግ እንደታቀደ ምሥራቅ ገልጻለች። ‹‹ለእስከ ዛሬው ይቅርታ እንጠይቃለን፤ ግን ይህንን ስሜትና ፍላጎት ሌላውም [የሚመለከተው] እንዲረዳ እንፈልጋለን። ሚድያውም ችግሮቻችንን አደባባይ በማውጣት ሊረዳን ይገባል›› ስትል ጥሪዋን አቅርባለች።
በዚሁም ከጦብያ በኋላ የተጀመሩ የግጥም በጃዝ ክዋኔዎች መኖራቸውን ጠቅሳ፣ ሁሉም በግል ጥረት የተከፈቱ ናቸው። ማንም ድጋፍ አድርጎ ሳይሆን በግል ጥረት የተደረሰበት ነው በማለት አዘጋጆች ሁሉ መደነቅ እንደሚገባቸው ጠቅሳለች።
ገጣሚና ሰዓሊ ቸርነት ወልደገብርኤል እንደሚለው፤ ግጥም በጃዝ ካልነበረበት ተነስቶ አሁን ያለው ተቀባይነት ላይ የደረሰው በቀላል አይደለም። ‹‹ብዙ ዋጋ ተከፍሎበታል፤ ያለውን የኪነጥበብ ሰው ማብዛትም ቀላል አይደለም። እናም መደነቅ አለበት፤ የሚሠሩትም ሊደነቁና ሊመሰገኑ ይገባል።›› ሲል ለአዲስ ማለዳ አስተያየቱን ሰጥቷል።
ሁሉንም ሐሳብ የሚያስረው ይህ ነው፤ ‹‹ትውልድን ለመቅረጽ ከየትኛውም መንገድ ይልቅ የጥበብ መንገድ ዋና እና አስፈላጊ ነው›› ምሥራቅ እንዳለችው። በዚህ ሁሉ መካከል ታድያ ዋናውና ወሳኙ ይኸው ነው፤ የጥበብን ጥቅምና ዋጋ መረዳት መቻል። ምሥራቅም ጥሪዋ እንዲህ የሚል ነው፤ ‹‹አገር እናሳድግ፣ ወጣቱ ላይ እንሥራ፣ ኢትዮጵያን እንጠብቅ ካልን እያንዳንዳችን ኀላፊነት አለብን። ሆኖ ከማዘን በፊት ቅድመ ሥራ ያስፈልጋል፤ ወጣቱን እንርዳው፣ እናስተምረው፣ እናግዘው፣ ስለአገሩ እንስበከው፣ ኢትዮጵያን ይውደድ፤ ያኔ ስለ እያንዳንዱ ጠጠርና ጠብታ የሚያስብ ትውልድ መፍጠር ይቻላል።››

ቅጽ 2 ቁጥር 58 ታኅሣሥ 4 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here