ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኖቤል ሽልማት እና የተለያዩ አስተያየቶች

0
1185

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባሳለፍነው ሳምንት የኖቤል ሽልማታቸውን መቀበላቸውን ተከትሎ አዲስ ማለዳ ተፅእኖ ፈጣሪ ያለቻቸውን ሰዎች ከተለያዩ የሕይወት መንገዶች ተመሳሳይ ጥያቄዎችን አንስታለች። ቀዳሚው ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማቱ ይገባቸዋል ወይ የሚል ሲሆን፣ ቀጥሎም የኖቤል ሌክቸራቸውን እንዴት እንዳዩት ጠይቃለች። አክላም የሽልማት ሥነ ስርአቱ ላይ የነበሩት ሁነቶች፣ ንግግራቸው እንዲሁም ሽልማቱን ማግኘታቸው በራሱ በአገር ውስጥ ፖለቲካ ላይ የሚኖረውን ውጤት ጠይቃ በመጨረሻም ለሽልማቱ ምክንያት የሆነው የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት በትክክለኛው መንገድ ላይ ነው ወይ ስትል ጠይቃለች።
መልሶቻቸውም ሳይጨመር እና ሳይቀነስ እንደሚከተለው በዝግጀት ክፍሉ ተሰናድቷል።

ቄስ ዶክተር ገመቺስ
ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የኖቤል ሽልማት በሚገባ ይገባቸዋል ብዬ አምናለሁ። የኖቤል ኮሚቴ እንደገመገመው የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጦርነት እና መቃቃር፣ ይቅር ለኹለቱ አገራት ቀጠናውን በኢኮኖሚም ይሁን በፖለቲካው አንቆ የያዘ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩም እርቁን በዚህ ፍጥነት ለማምጣት የሔዱበት ርቀት ቀላል የማይባል ነው።
ንግግራቸው ግሩም ነው ብዬ ነው የማምነው፤ በተለይም ይዘቱን አድንቄዋለሁ። ይህንን በሦስት ቦታ ከፍለን ማየት እንችላለን። የመጀመሪያው ንግግራቸው ላይ የተሳለቸው ኢትዮጵያ ገፅታችንን መቀየር የሚችል ኃይል አለው ብዬ አምናለሁ። ይህንን አጋጣሚ ተጠቅመንም ብዙ ነገር መሥራት እንችላለን፣ በተለይ በቱሪዝሙ ዘርፍ።
ሌላው ለምሥራቅ አፍሪካ ይህ ንግግር የራሱን መልዕክት አስተላልፏል ብዬም አምናለሁ። በተለይም በሰላሙ ረገድ ወደ ፊት እንድንሔድ የሚያስችለን ነው። በተመሳሳይ ግን ሁሌም የችግር እና ግጭት ምንጭ ተብላ ለምትታሰበው አፍሪካ፣ መልዕክት ያስተላለፉበት ነበር። የሚና መለዋወጥ እንበለው? ምክንያቱም ሰላም ለኢትዮጵያ፣ ሰላም ለምሥራቅ አፍሪካ፣ ሰላም ለአኅጉሪቱ በሚባልበት ዓለም፤ ለምዕራቡ እና ለምሥራቁ ከአፍሪካ የሰላም መልዕክት ሲሰማ አይተናል።
ይህ በአገራችን ፖለቲካ ላይ ስለሚኖረው ሚና ሳስብበት ነበር። ይህ ሽልማት ለፖለቲካው ብቻ ሳይሆን ለሳይንስ እና ለትምህርት ጭምር ከዚህ በኋላ ደረጃችንን ከፍ የሚያደርግ ነው። የኖቤሌ ሽልማት አዲስ ሚዛን የሚፈጥር እውቅና ነው። ይህ ደግሞ አሁን ላለው ብቻ ሳይሆን ላለፈውም፣ ለሚመጣውም ሁሉ ማነፃፀሪያ ነው። ለጠቅላይ ሚኒስትሮች፣ ለተፎካካሪ ፓርቲዎችና ለፖለቲከኞች ከዚህ በኋላ ሚዛኑን ከፍ የሚያደርግ የሰላም ሽልማት ነው ኖቤል።
የዓለም ዐይኖች ኢትዮጵያ ላይ ነበሩ፣ ይህ በኢኮኖሚያችን ላይ ያለው ጫና ቀላል አይደለም። ከዚህ በኋላ ይህንን ሚዛን የሚመጥን ኑሮ መኖር የኛ ሚና ነው። ኳሷ በእኛ እጅ ላይ ነች፣ ይህ እንደ ሕዝብ፣ እንደ መንግሥት እና እንደ አገር ማለቴ ነው።
ከተዘጉ በሮች ጀርባ ያለውን ነገር ባናውቅም በውጪ ባለው እይታ ግን በኹለቱ አገራት [በኢትዮጵያ እና በኤርትራ] መካከል ያለው ትልቁ ግድግዳ ተሰብሯል። የአየር ትራንስፖርቱም ሆነ የቴሌኮሙ አገልግሎት ክፍት ነው። ከጦርነቱ በኋላ ባሉ ጊዜያት ኹለቱ አገራት መካከል ብዙ ውስብስብ ነገር ተፈጥሯል። የድንበር ጉዳዮች፣ የኢኮኖሚው ጉዳይ እና ሌሎችም እንዲሁ በቀላሉ የማይፈቱ ብዙ ችግሮች ተፈጥረዋል። እነሱም በአንድ ጀንበር የተፈቱ አይደሉም። ጅማሬው ቀላል ቢሆንም ከዚህ በኋላ የብዙ ዲፕሎማቶች፣ የዓለማቀፉ ኀብረተሰብ እና ባለሞያዎች ተሳትፎን ይጠይቃል። በዚህ አጋጣሚ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ደስ ያላችሁ ማለት እፈልጋለሁ።

ኮንቴ ሙሳ (ዶ/ር)
ይህ ሽልማት ይገባቸዋል ብዬ አምናለሁ፤ በተለይም እንደማበረታቻ። ከአንድ የስዊድን ፓርላማ አባል ጋር በመሆን ፓርላማው ለሽልማቱ እንዲያጫቸው ቅስቀሳ ስናደርግ የነበረውም ይገባቸዋል ብዬ ስለማምን ነው። ብዙ ሰዎች ፈጥኖ የመጣ ሽልማት ነው ቢሉም ከእርሳቸው በፈጠነ ጊዜ እነ ባራክ ኦባማም ወስደዋል።
ኖቤል በባሕሪው ወደ ኋላ ብቻ የሚያይ ሳይሆን፣ ወደ ፊትም የሚያይ ሽልማት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የፖለቲካ እስረኞችን ፈትተዋል፣ በቀጠናው ያሉ አገራት ቅራኔዎችን ፈትተዋል፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አንስተዋል ሌሎችም ብዙ የሰላም ሥራዎች ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት አከናውነዋል። ከዚህ በኋላ ይህንን ለማስቀጠል ትልቅ ጉልበት የሚሰጥ ይመስለኛል።
ንግግራቸውም ስሜት የሚነካ ነው። ከዚህ ቀደም የኖቤል ተሸላሚዎች ትምህርታዊ ጽሑፍ የሚመስል ንግግር ሲያደርጉ በተለይም በሥራ ጉዞአቸው ላይ የሚያተኩር ንግግር ማቅረብ የተለመደ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያቀረቡት ግን በግል ሕይወታቸው የተተረከ፣ ሰው ሰው የሚል ንግግር ነው ማለት ይቻላል። ስለ ሰለም የሚያነቃቃ በተለይም የእርሳቸው የትግል አጋሮች አልቀው ብቻቸውን የተረፉበት፣ ለኖቤል መድረሳቸውን የእድል ጉዳይ ባይሆን እሳቸውንም ሊቀጥፍ የሚችል ጦርነት መሆኑን ያስረዱበት መንገድ ስሜት የሚነካ ነበር።
ይህ ሽልማት ከግለሰብ አልፎ የአገር ሽልማት ነው። ይህ ሳይደበዝዝ የዲፕሎማሲ እና የቱሪዝም ማስተዋወቅ ሥራዎች ጠንክረው መሠራት ገባቸዋል። ባለሀብቶችን ለመሳብም የንግዱ ማኅበረሰብ በበጎ ጎኑ ሊጠቀምበት ይችላል። እኔ ብዙ ሕዝብ የሽልማቱ ዋጋ የገባው አይመስለኝም። የኢትዮጵያ ፖለቲካ በትንንሽ ነገሮች ላይ ጊዜውን የሚያጠፋ ስለሆነ፣ አሁን አድማሱ ከፍ እንዲል ያደርጋል።
አሁን ካለንበት የፖለቲካ ክፍፍል ወጥተን ወደ አገራዊ ምስል መግባት ያለመቻላችንንም ተመልክቻለሁ። ሁሌም ትንንሽ ነገሮች ላይ ስናተኩር ተስፋዎቻችን ያመልጡናል፤ ይህም እንደዚህ እንዳይሆን እፈራለሁ። የእኛ አገር ፖለቲካ በጥርጣሬ የተሞላ ነው፣ ሁሉ ነገር ሴራ ይመስለናል፤ ከጀርባው ምን ይኖር ይሆን እንጂ ያለውን ነገር ፊት ለፊት የመቀበል ችግር አለብን። ለመጪው ትውልድ ይቻላልን የሚያሳይ በቅንነት ካየነው ተስፋ የሚጭር ሽልማት ነው።
የኹለቱ አገራት [የኢትዮጵያ እና የኤርትራ] የሰላም ጉዞ እንደ ጅማሬው እንዳልሆነ ይታወቃል። ይሄ ግን ከኹለቱም አገራት የቅንነት ወይም ፍላጎት ችግር ሳይሆን ከዚህ በኋላ ያለው ሂደት ጊዜ እና ጥናት ስለሚፈልግ ነው። ከአሰብ ቡሬ ያለውን መንገድ ኤርትራ ገንብታ መጨረሷን አውቃለሁ፣ ስለዚህ የሐሳብ ለውጥ አለ ብዬ አላምንም። ይልቁንም ከዚህ በፊትም እነዚህን አገራት ጦርነት ውስጥ የከተቱት የ ተቋማዊነት ያለመኖር ነበር። አሁንም ግንኙነቱ ተቋማዊ መደረግ ስላለበት ጊዜ ይወስዳል ብዬ አምናለሁ። የገንዘቦቻቸው ጉዳይ፣ የኮንትሮባንድ ንግድ ጉዳይ እና የመሳሰሉትን መፍታት ያስፈልጋል።

ዳንኤል ብርሃኔ
ሽልማቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለተጫወቱት የፖለቲካ ዓላማ የተበረከተ እንጂ በእርግጥም የኖቤልን የሰላም ሽልማት በማሳካታቸው የተሰጠ ነው ብዬ አላምንም። ይህንን ሽልማት እንዲያገኙ የአሜሪካ ተቋማት ያደረጉት ቅስቀሳ ውጤት ነው ብዬ አምናለሁ። ለአሜሪካኖቹ ከሃምሳ ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ለዘብተኛ የኢትዮጵያ መሪ ያገኙት። እናም እርሳቸውን አግዘው ማቆየት ይፈልጉ ነበር፣ ምንም እንኳን አሁን ያ ተስፋቸው ተሟጦ ቢያልቅም።
የኹለቱ አገራት [የኢትዮጵያ እና የኤርትራ] የውጪ ምንዘሪ ላይ መስማማት አለመቻል ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን አምባሳደር እንኳን ፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከአንድ ዓመት በኋላ ነው ተቀብለው ለማነጋገር ፈቃደኛ የሆኑት። ስለዚህ የኖቤል ኮሚቴ በተለያዩ ጫናዎች ውስጥ ገብቶ የወሰነው ውሳኔ ነው ብዬ አምናለሁ።
ሌክቸራቸውን ከሌሎች ጋር አላነፃፅረውም። ያው የውጪ አማካሪዎች ተሳትፈውበት የተጻፈ ነው።
ይህ ሽልማት የዛሬ ስድስት ወር ገደማ መጥቶ ቢሆን ኖሮ ምን አልባት የሚፈይደው ነገር ይኖር ይሆናል። አሁን ግን የፖለቲካ ድጋፋቸው ተሟጦ እና ደጋፊዎቻቸውም ብርቅዬ እስከመሆን ደርሰው በመምጣቱ፣ የሚፈይደው ነገር አለ ብዬ አላምንም። ከዛሬ ስድስት ወር በፊት ቢሆን ምን አልባት ‹የተወሰነ ጊዜ እንስጠው› በሚል ወይም ‹ይሄ ሰውዬ ነጮቹ ከሸለሙት ቢችል ነው፤ ስለዚህ እድል እንስጠው› ሊባል ይችላል። ነገር ግን ሕዝቡ በየቦታው በመሬት ላይ የሚያየው ግጭት እና ቀውስ ሆኖ በቴሌቪዥን ነጮቹ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሸለሟቸው ቢባል ምንም አይመስለውም። ድጋፋቸው በጣም ስላሽቆለቆለ ይህ ሽልማት ምንም የሚፈጥረው ነገር የለም።
አረቦቹ ቃል የገቡትን ገንዘብ አድርገዋል ወይ የሚለውን በተመለከተም፤ ማዕቀብ አንስተዋል [ለኤርትራ]፤ ከዛ ያለፈ ግን እስከ አሁን የሰማነው ነገር የለም። እኔም ብዙ ለማጣርት አልሞከርኩም። እና በዚህ ኢሳያስ አፈወርቂ ደስተኛ አይደሉም። መጀመሪያም መሬት ፈልገው አልተዋጉም፤ አሁንም ራሳቸው ጉዳዩ የመሬት አይደለም ብለዋል [ኢሳያስ]። ስለዚህ ኢሳያስ እፈልጋቸዋለሁ የሚሏቸው ነገሮች አሉ፤ በተለይ ሕወሓትን አጥፋልኝ፣ ኢሕአዴግን አጥፋልኝ እያሉ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሚያቀርቧቸውን ፍላጎቶች ካልተው በቀር፣ እንዴት አድርገው ወደፊት ሊቀጥሉ እንደሚችሉ አይገባኝም።
ከዚህ ሌላ በጥያቄ ራሱ፤ ኢሳያስ አፈወርቂ ያቀረቧቸው ቅድመ ሁኔታዎች፣ ያኔ ጦርነቱ ሲጀመር ያቀረቧቸው ናቸው። መጠኑ ትዝ ባይለኝም የብር እና የናቅፋ ምንዛሬ ላይ ያቀረቡት ፕሮፖዛል ነበር፤ ከጥቂት ወራት በፊት። ባቀረቡት ቅድመ ሁኔታዎች ጥቅማቸውን ይፈልጋሉ። እናም እነዚህን ነገሮች ካላገኙ ወይም ከሕወሓት አንጻር የሚፈልጉትን ካላገኙ፤ በኢሳያስ በጎ ፈቃድ ላይ የተንጠለጠለ ነው።
ዞሮ ዞሮ በፊት ከነበረው የጦርነት ስጋቱ ቀንሷል። አሁን ግን ቆሞ ነው ያለው። አሁን ባለው ሁኔታ ሌላ የተለየ ነገር ካልተፈጠረ በቀር ሊያንቀሰቅስ የሚችለው፤ ከትግራይ ጋር የሚፈጠር ግጭት መፋጠጥ ነው። ይሄ ደግሞ ጤናማ አይደለም መነሻው። መነሻቸውም ላይ ምን ይዘው ነው የተስማሙት ግልጽ አይደለም፤ ቀጥሎ ተቋማዊና ግልጽ በሆነ መንገድ የሚሔድ ነገር የለም፤ በኹለት ግለሰቦች መካከል የተንጠለጠለ ነው። እና ያን ያሕል ጤናማ ተብሎ የሚወሰድ አይደለም [የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነት]።

ዩናታን ተስፋዬ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኖቤል ሽልማት በጣም ይገባቸዋል፤ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ በጣም አስቸጋሪ የነበረ ግንኙነት በመፈታቱ፤ የግል ጥረታቸውም ጎልቶ ስለሚታይ ይገባቸዋል ብዬ አስባለሁ።
ንግግራቸውም በጣም አስደናቂ ነበር። አንደኛ አነቃቂ ነው። ኹለተኛ ስለተሸለሙበት ሰላም ንግግር ያደረጉበት መንገድ፣ በዛ ውስጥ አገርኛ አባባሎችና ሃይማኖታዊ አስተምህሮውን አስተሳስረው፤ ከዛም አልፎ ዓለም አቀፍ የሆነ ሰላምን፣ ወንድማማችነት ያስተማሩበት ነው ማለት ይቻላል። ከዛ አልፎ መደመር የሚለውን እሳቤያቸውንም የሸጡበት መድረክ ነው ማለት ይቻላል፤ በዓለማቀፍ መገናኛ ብዙኀን መቀጥታ በሚተላለፍ መድረክ ላይ፤ ያን ሐሳብ አንስተው ለዚህ ስኬታቸው ያበቃቸው እንደሆነ አብራርተዋል። ስለዚህ ደረጃውን የጠበቀ፣ ለመድረኩ የሚመጥን፣ የራሳቸውንም ስኬት የሚያንጸባርቅና ምን ዓይነት ሰው እንደሆኑ የሚሳይ፣ ሽልማቱ ለምን እንደተሰጣቸው በተወሰነ መልኩ መግለጽ የሚችል በጣም ደስ የሚል ንግግር ነበር።
ከሽልማቱ ስንነሳ ሰሞኑን በርካታ ሰዎች እንኳን ደስ አለን መልዕክት ሲያስተላልፉ አስተውለናል። አብዛኞቹ ሰዎች ደግሞ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ከጥቂት ወራት በፊት በአንድም በሌላም መልኩ በፖለቲካ በጣም ቅራኔ እና ቁሮሾ ውስጠ የገቡ ናቸው። በዚህ ሽልማት የተደሰቱት ደጋፊዎቻቸው፣ የፓርቲ አባላትና የሚመሩት መንግሥት ሳይሆን አጠቃላይ የፖለቲካ ኃይሉ ላይ በአመዛኙ፤ ከጥቂት ኃይሎች በቀር፤ ደስታውን ሲገልጽ የነበረበት ነው። ይሄ አዲስ የፖለቲካ ባህል እንዲፈጠር መንገድ የከፈተ ይመስለኛል።
ሽልማቱ ይፋ ከተደረገ ጀምሮ ሕዝቡ ደስታውን ሲገልጽ ነው የቆየው። በፖለቲከኞች ዘንድ ግን ያልተለመደ ዓይነት ነው። በፊት መሪዎቻችን ምንም ቢያደርጉና በዓለማቀፍ መድረክ ምንም ዓይነት እውቅና ቢሰጣቸው ለመቀበል ክፍት ያልሆነ የፖለቲካ መንፈስ ነበር። ምክንያቱም ጠላትነት በጣም ስር ሰድዶ ስለነበር። አሁን ግን የእርሳቸውም ጥረት ይመስለኛል፤ ያ በጠላትነት የመተያየቱ ነገር እየቀነሰ ይታየኛል። ምክንያቱም ትላንትም ዛሬም በሐሳብ የማይስማሟቸው፣ ከሥልጣን እንዲነሱ የሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ፤ በተለይ ከኢትዮ ኤርትራ፤ ከሱዳን ጋር፤ በአገር ውስጥ ለጀመሩት ለውጥም እውቅና ሰጥተው እንኳን ደስ አለዎ ሲሏቸው፤ የሽልማቱን ተጽእኖ በዚህ ማየት ይቻላል። ሽልማቱ የአገሪቱ ፖለቲካ መስከን ላይ የራሱን አስተዋጽኦ ያደረገ ይመስለኛል።
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ መሪና መሰባሰቢያ ተደርጋ ስለምትታይ፣ በዚህ ላይ እንዲገፉ እንደ ማበረታቻ ነው። እውቅናውና ወደፊት በርትተህ ሥራ ሲባልም አገር ውስጥ ያለው ፖለቲካ ላይ ተጽእኖ የሚኖረው ይመስለኛል። ምክንያቱም በውስጡ ሰላም የሌለው የሚሰጠው ሰላም አይኖርም። ኮሚቴው ሲናገር እንደሰማነው፣ በአገር ውስጥ ያለውን የዴሞክራሲ ስርዓት እና የተቋማ ግንባታ ጅማሮ፣ የፖለቲካ ባህላችንን መዘመን በተመለከተ በጀመሩበት ቅንነትና ቀናዒነት በርትተው እንዲገፉበት የተሰጠ ኃላፊነት ጭምር ነው። መጨረሻ ላይ የኮሚቴው ሊቀመንበር የተናገሩት ይህንን ነው፤ ኃላፊነት ነው የተጣለብዎ ብለዋል። ይህ ተደማምሮ መጪው ምርጫ የተሻለ ይዘት እንዲኖረው ተጽእኖ የሚያሳድር ይመስለኛል።
የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነት በትክክለኛው አቅጣጫ እየሔዱ ነው የሚለውን ልመለስበት። ኢሳያስ እውቅና ስለመስጠታቸው ማኅበራዊ ሚድያ ላይ ሲናፈስ ነበር። ሆነም ቀረ ግን አንድ እውነት አለ። በዚህ ላይ የሕወሓት ሚና ትልቅ አንድምታ እንዳለው ይሰማኛል። ምክንያም ሻዕብያም፣ ኢሳያስ አፈወርቂ የሚመሩት መንግሥትም፣ ከሕወሓት ጋር የቆየ ጸብ ያላቸውና እልህ የተጋቡ ይመስለኛል። አንዱም ድንበር አካባቢ ሰላም ጠፍቶ የቆየውም የኹለቱ እልህ መጋባትና ለረጅም ጊዜ የዘለቀ የመናናቅ ታሪክ ያላቸው በመሆኑ ይመስለኛል።
ከዛ በመነሳት አሁንም ከሕወሓት ጋር ያላቸው ግንኙነት ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ግንኙነት ላይ የራሱን ጥላ ያጠላ አድርጌ እወስዳለው። ድንበር አካባቢ ‹መንገድ እየተሠራ ነው፣ ለጊዜው ነው የተቋረጠው፣ በቅርቡ ይከፈታል› የሚሉ ወሬዎች ሲዘዋወሩ ይሰማል። እኔ ግን ያ ብቻ ሳይሆን ከሕወሓት ጋር የተያያዘ ሌላ የፖለቲካ ውዝግብ እንዳለ ይሰማኛል፤ እሱም ጊዜ የሚፈልግ ነገር ነው። ሕወሓት ራሱ አሁን ካሉ የማዕከላወኪ መንግሥቱን ከሚመሩ ኃይሎች ጋር በተለይ ውህደቱ የብልጽና ፓርቲ የመሠረቱት ጋር የሚፈጥረው ድርድር፣ የአገረ መንግሥ ውስጠ የሚኖረው ሚና በድርድር ከተስተካከለ አብሮ ሊስተካከል የሚችልና የሚገባ ነገር አድርጌ እወስደዋለሁ።
ከዛ ባለፈ ግን በተለይ ዐቢይ አሕመድ ከኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ባደረጓቸው ስምምነቶች አሁን ላይ የስልክ መስመሩ ክፍት ነው፤ አየር መንገድ ሰዎች ይመላለሳሉ። ቢያንስ ያ እንደምልክት አንድ የሚያሳየው ነገር አለ። የኢትዮጵያን አምባሳደሩ ለመቀበል የመቆየታቸውን ምክንያት አላውቅም፤ የኤርትራ መንግሥትም ምንም ዓይነት መግለጫ አልሰጠም። እዛ ላይ ‹በቸልታ ነው፤ የፖለቲካ ቁርሾ ኖሮ ነው› ለማለት አስቸጋሪ ነገር ነው። እንዳልኩት ተትቶ የነበረው የስልክና አየር መንገድ ግንኙነቶች ክፍት ሆነዋል፤ ኤርትራውያን በኢትዮጵያ የተወረሰባቸው ሐብት አንዳንድ ቦታዎች እንዲመለስ ጥረት እየተደረገ ነበር። በኢትዮጵያም ኤምባሲው ተከፍቶ አገልግሎት እየሰጠ ነው። እነዚህ ነገሮች ያ የነበረው ስምምነት ወደኋላ ተመልሷል እንድንል አያደርጉም። ከዛ ይልቅ ከሕወሓት ጋር ያለው ግን በጣም ጥራት የሚጎለው ግንኙነት እስኪስተካከል ድረስ፣ ድንበር ላይ ያሉ ነገሮች አሁንም ባሉበት የሚቆዩና መፈታት የሚገባቸውም ይመስለኛል። በተለይ ግንኙነቱን ዘላቂነት ባለው መልኩ ጤናማ እንዲሆን የውስጥ ፖለቲካው መፍታት የሚገባውና የፖለቲካ ስክነት የሚፈልግ ነገር ያለ ይመስለኛል።

አብረሃ ደስታ
አንድ ሰው ለሆነ ሽልማት ሲታጭ ከሌሎች ጋር ተወዳድሮ ነው። ከዓለም ካሉ ሌሎች መሪዎች፣ ታዋቂ ሰዎች የተሻለ ለሰላም የሠራ ተብሎ ነው የሚመረጠው። ስለዚህ ዶክተር ዐቢይ ከሌሎች የተሻለ የሰላም እንቅስቃሴ አድርገዋል፤ የኢትዮ ኤርትራን ችግር ፈትተዋል፣ በተለያዩ የአገራችን እና ጎረቤት አገራትም ላይ ለሰላም ጥረት አድርገዋልና፣ ይሄ ሽልማት ይገባቸዋል ስንልም በአንጻራዊነት በሠሩት የሰላም ሥራ ነው። ከእርሳቸው በላይ ስለ ሰላም የሠራ ቢኖር ኖሮ ያ ሰው ያሸንፍ ነበር፤ ስለዚህ በአንጻራዊነት ሽልማቱ ይገባቸዋል ብዬ አስባለሁ።
ንግግራቸውም በጣም አሪፍ መልዕክት አለው። የተናገሩት በአገራችን በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት ነው፤ እንደሚፈቱም ተስፋ አደርጋለሁ። አገር ውስጥ ብዙ የሚሠራ ነገር አለ። ብዙ እንዲሠሩ ምክንያት ይሆናል ብዬም አስባለሁ።
በመጀመሪያ ሽልማቱ ለኢትዮጵያችን ክብር ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግላቸው ቢሸለሙም ኢትዮጵያ እንደተሸለመች ነው የምናስበው፤ ሽልማቱ የተሰጠው ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ ነው። በሽልማቱ ሰበብ ኢትዮጵያ ጥሩ ሲወራላት ነው የዋለው፤ እናም ክብር ነው። ኢትዮጵያችን በዓለም ተከብራ ነው የዋለችውና ለሁላችን ክብር ነው። እኛም ይህን የሰላም ሁኔታ ለጥሩ መጠቀም እንችላለን። በአገራችን ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ ለማስተካከል ሊጠቅመን ይችላል። በሌላ በኩል ግን አሁን የኢትዮጵያ ፖለቲካ በስሜት፣ በብሔር የተከፋፈለ ነውና፤ ይህን አኅጉራዊ ሽልማት የሚያሳጡንም አሉ። ስለዚህ ዶክተር ዐቢይ የሰላም ሳይሆን የግጭት ተመሳሌት እንዲሆን ጥረት የሚያደርጉ ይኖራሉ። ይህን ለማበላሸት የሚጥሩ ሰዎች አይታጡም። ብዙ ፈተናዎች አሉ፤ ነገር ግን በአገራችን ብዙ መሠራት ያለበት ነገር ስላለ፤ በዓለማቀፍ የተሸለሙትን ያህል በአገር ውስጥ እንዲሠሩና ለአገር ደኅንነት፣ አንድነት፣ ለሕዝቦች ደኅንነት እንዲሠሩ ነው የማሳስበውና፣ ምክሬን የምለግሰው።
የኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ ችግሩን ለመፍታት የተሔደበት መንገድ ጥሩ ነው። ነገር ግን አላስፈላጊ ፍጥነት ነበር፤ ምክንያቱም ተቋማዊ አሠራር አልነበረውም ብዬ ነው የማስበው። ለዛ ነው አሁን ወደ ግርታ ውስጥ እየገባን ያለነው። በተቋም ደረጃ፣ በውጪ ጉዳይ በኩል መሠራት ይገባ ነበር። ግን አንዱ ችግር ያለው፣ ከኤርትራ አንጻር ስናየው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ኹለት መንግሥት እንዳለ ይሰማኛል። የፌዴራል መንግሥት አለ፤ እዚህ ደግሞ ከኤርትራ አጠገብ ያለ የትግራይ ክልል መንግስት አለ።
ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር በምታደርገው ግንኙነት የትግራይ ሁኔታም ወሳኝ ነው። በትግራይ ያለው ደግሞ ሕወሓት ነው፤ ሕወሓት ብዙ ጊዜ ከፌዴራል መንግሥት ጋር አይስማማም። እና የኤርትራ ጉዳይ በዶክተር ዐቢይና እና በኢሳያስ አፈቀርቂ ለመፍታት፣ ሕወሓት ካልፈለገ ሊያበላሸውም ይችላል። እነርሱ ተማምነው ሊወስኑ አይችሉም፤ ይቸገራሉ። ሦስት መንግሥታት እንዳሉ ዓይነት ነው፤ አሁን። በኤርትራም በኩል፣ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በትግራይ ክልልም። እና የሕወሓት ማፈንገጥ ለሰላም ሒደቱ እንቅፋት የሚሆን ይመስለኛል።
ሌላው ተቋማዊ አሠራር ባለመከተሉ የሚያጋጥም ችግር ነው። የሰላሙ ጉዞ በተጀመረበት እንዲያልቅ ነው ተስፋ የምናደረግው። ምክንያጡም ኹለቱም አገራት ከሰላም ውጪ ሌላ መንገድም ሆነ አማራጭ ሊኖራቸው አይችልም። ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የፖለቲካ ሒደት፣ አንዱ አንዱን እየጎዳ እየመሰለው ችግር የመፍጠር ነገር ሊኖር ስለሚችል፤ በጥሩ መንገድ መያዝ ያለበት ነው። ተቋማዊ አሠራርም መከተል ያለበት ይመስለኛል፤ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ነው።

በኃይሉ ፈድሉ
ለሽልማቱና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቀባበል ለማድረግ አንደኛ ትራንስፖርት ተዘጋጅቶ ነበር። በርገን ከምትባለው ከተማ ባሶች ነበሩ፤ ወደ ኦስሎ የሚወስዱ። ሰዎች ተሰባስበው በብዛት ሲሔዱ ያየሁት ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። የማውቃቸው ኢትዮጵያውያን ጓደኞቼም አቀባበል ለማድረግ ሔደዋል። ባለንበት ከተማ ትንሽ ስለነበርን መገናኛ ብዙኀን ያሉትን አናግሯል፤ ብዙ ሰው ደስተኛ መሆኑን ሲገልጽ ነበር።
ከበርገን ኦስሎ በአውቶቢስ ስምንት ሰዓት ነው። ወደ ኦስሎ ለመሔድ ቅርቡ የኹለትና ሦስት ሰዓት መንገድ ነው፤ ወይ በባቡር ወይ በባስ። ብዙዎች ይህን አቋጠው ነው ለአቀባሉ የተገኙት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ ከእርሳቸው ጋር ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ቀደም ብለው የተዘጋጁ ነበሩ። ሆነ ብሎ ነው ያደረጉት። ብዙ ሰው ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣው በፈረንጆቹ ገና በዓል ላይ ነው፤ ግን አንድ ሳምንት ቀድመው ነው ኢትዮጵያ የመጡት። ፍቃድ የሚገኘው በክረምት ወይ በፈረንጆች ገና ነው። አሁን ግን ይህን አጋጣሚ ተጠቅመው አብረውት ወደ አገር ቤት የሔዱ አሉ። በጣም ጥሩ አጋጣሚ ሆኗል ለእነሱ።
እኔ የማውቃቸው ኖርዌያውያን ሳይቀሩ ዜናውን አልጠበቁትም፤ አስቀድሞም ማሸነፉን ሲሰሙ። ስለኢትዮጵያ ብዙ የሚውቁት ነገር አልነበረም። በማግስቱ እንደውም መሥሪያ ቤት ስገባ፣ እንኳን ደስ አለህ ሲሉኝ፤ ምን ተገኝቶ ነው ስል፤ የጠቅላይ ሚኒስትርህን መሸለም አይተን ነው ብለውኝ ነበር። ኩራት ነው። ለኢትጵያውያን እውቅና ሲሰጡ ደስ ይላል። ክፉ ባይሆኑም አንዳንዴ ሳይታወቅ የሚዳብር ስሜት አለ፤ እና በዚህ ሽልማት በአዲስ ምልከታ ነው ያዩን እና በዛም ደስተኛ ነው የሆንኩት። ከዛ እኔም ስለ ኤርትራ ማውራት፤ ብዙዎቹ ለጉብኝት ኬንያ ይሄዱ ነበርና ስለኬንያ እንዲሁም ስለሶማሌም ጠቅላይ ሚስትሩ ያደረጉት ላይ መነጋገርና ለእኔም መንገር ጀመሩ፤ በጣም ተቀብለውታል።
ሚድያው መጀመሪያ አካባቢ ሲያስሱ ነበር፤ ኢትዮጵያ የነበሩ ኖርዌውያንን ጨምሮ። በቁጥር ትንሽ ስለሆንን ኢትጵያውያንን ፈልገው እየዞሩ ነው ያናገሩት። ገና መጀመሪያ በሚድያ ሰበር ዜናው ከተሰማ ጊዜ ጀምሮ በጣም ሲያወሩበት ነበር። ኢትዮጵያ ብዙ የኖሩ ፈረንጆችም ሳይቀሩ አስተያየት ሰጥተዋል። ከዜና አለፍ ብሎ ሐተታ በብዛት ተሠርቶበታል። ብዙዎቹን ተጋርተናል፤ በዚህም ኩራት ይሰማናል።
እኛ ከተማ ትንሽ ስለሆንን ብዙ ሰውም የአዲስ አበባ ልጅ ነውና ተቃውሞ ብዙ የለም። ኦስሎ ሊኖር ይችላል። ከባዱ እዛና በርገን ነው። እኛ ያለንበት ከተማ ብዙ ሰው ያወራል፤ ይከራከራል እንጂ ብዙ ተቃውሞም የለም። ብዙ ችግር ያለበት የለም። አንዳንዴ የወረቀት ጉዳይ እንደሆነ ይሰማኛል። እውነተኛ ተቃውሞ ነው ወይስ ለወረቀት ነው ያሰኛል። እንዳንዱ ጉዳዩን ይረሳና መንግሥትን መቃወም ብቻ ላይ ያተኩራል። ለወረቀት [ለመኖሪያ ፈቃድ] መንግሥትን መቃወም አለበት። በኖርዌይ እንደ ድንገት ሆኖ ሁሉም ወረቀት ያለው ስለሆነ በምክንያት የሚያወራ ነው። ብዙ ካምፖች ያሉት፤ ወረቀት የሌለውም የሚበዛው በሌሎች ከተማ ስለሆነ።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር አሪፍ ነው። ሐሳቡና ጭብጡም። ግን በአማርኛ ቢሆን ይመቸኝ ነበር። ጭብጡን ከሆነ መጀመሪያ መነሻው ለዓለም የሚስፈልጉ ነጥቦች ናቸው። ከአገር ውስጥ የጀመሩት፤ ከኤርትራ ጋር የነበረው፤ የኤርትራን ችግር ማንሳታቸው፤ ከራሳቸው ታሪክ ጋር ማገናኘታው መልካም ነው። የሚሰማቸውን መናገር ስላለባቸው። በአማርኛ ቢሆን እንደዛ የሚሆን ይመስለኛል ወይም በግሌ በአማርኛ ብሰማው በጣም የሚመቸኝ፤ ለእርሳቸውም ቀላል የሚሆንላቸው ይመስለኛል።
ሽልማቱ በጎ ተጽእኖ ይኖረዋል። የአገርን ምስል ሊቀይር የሚችልበት ጎን አለው። ግን የሌሎችም ፍላጎት አለ። ለምሳሌ የኖርዌያውያንን አመለካከት ይቀይርልናል። ገለልተኛ ናቸው፤ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ፍላጎት የላቸውም። ለእኛም ራሱ አሪፍ ነው የሚሆነው፤ ጥሩ የሆነ አንድምታ ይሰጣል። ግን የኢንግሊዝ ዜናዎችን ብታይ፣ ዜናዎች በሙሉ ተቃውሞና ‹ይገባዋል ወይ?› ‹አይገባውም ወይ?› የሚለውን መጠየቅ ነው የጀመሩት፤ በፍላጎታቸው መሠረት።

ቅጽ 2 ቁጥር 58 ታኅሣሥ 4 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here