የቤት ውስጥ ጥቃት – ያለሰሚ – ያለተመልካች

0
737

ሴት ልጅ ለአባቷ ወንድ ልጅ ደግሞ ወደ እናቱ ቅርበት አላቸው ይባላል። በአንዳንዶች ሕይወት ደግሞ ይህ ፈጽሞ አይታይም። በተለይም የመርሐዊት ሕይወት ለዚህ ምስክር ይሆናል። መርሐዊት በሰው ልጅ ሕይወት ሊደርስ ይችላል ተብሎ በማይገመት ሁኔታ በአባቷ በደል ደርሶባታል። በስሙ የምትጠራበት ወላጅ አባቷ በተደጋጋሚ አስገድዶ ደፍሯታል።
ይህን መከራ መሸከም ያልቻለው ልቧና አካሏ መፍትሔ ያደረገው ካለችበት ቦታ መራቁን፣ መሸሹን ነበር። እናም አደረገችው፤ ወደ አዲስ አበባ አመራች። ሁሉም የየራሱን ሩጫ የሚሮጥባት አዲስ አበባ፣ መርሐዊት የምትጠጋበት ዘመድ ወይም የኔ የሚላት ሰው አልነበረባትም፤ እናም የእለት ጉርስ ለመሙላትና ማደሪያ ለማግኘት የታያት አማራጭ አንድ ነው፤ ሴተኛ አዳሪነት።
እንደ መርሐዊት ያለ ሕይወትን በተለያየ ምክንያት እንዲገፉ የተገደዱ ሴቶች እዚህም እዚያም አሉ። ይልቁንም የቤት ውስጥ ጥቃት የብዙዎችን ሕይወት በአካልም በመንፈስም አመሳቅሏል። የቤት ውስጥ ጥቃት ከሌሎች በይበልጥ በሴቶች ላይ ከሚደርሱ ጥቃቶች የሚከፋው በቅርብ ሰው ወይም በቤተሰብ አባል የሚፈጸም በመሆኑ ነው። በሚስት፣ በልጅ አንዳንዴም በእድሜ በገፉ አረጋውያን ላይ ይደርሳል።
በኢትዮጵያ ሁኔታ ደግሞ ነገሩ የሚብሰው ከይሉኝታ ባህል አንጻር ነው። ያም ብቻ ሳይሆን ጥቃቱ ልብ ሳይባል አልያም በቸልታ ሳይነገር ይታለፋል። አንዳንዴም ‹ገመና› ነው ይባላል፤ የቤተሰብ ምስጢር። የትዳር አጋሩን የሚደበድብን ባል የሰፈሩ ሰው ሁሉ እየሰማ ‹ጀመራቸው!› ከማለት በተለየ የሚያደርገው የለም፤ እንደተመለደ ተግባር ያልፈዋል። ‹ለመኖር› ስትል ጥቃት የደረሰባት ሴትም ዝምታን ትመርጣለች፤ ወጉ ነውና።
በእርግጥ የቤት ውስጥ ጥቃት በሴቶች ላይ ብቻ የሚደርስ አይደለም። ነገር ግን በዓለምም ሆነ በኢትዮጵያ ያሉ እውነቶችን ብንመለከት በወንዶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት በሴቶች ላይ ከሚደርሰው አንጻር እጅግ በጣም ትንሽ የሚባል ነው። ለዚህም በአገራችን የተሠሩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፣ 40 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ለቤት ውስጥ ጥቃት ሰለባ ናቸው። በአንጻሩ ከአንድ በመቶ በታች ወንዶች ናቸው የጥቃት ሰላባ የሆኑት።
በቤት ውስጥ ሴቶች ጥቃት የሚደርስባቸው በማኅበራዊ ሕይወት ባላቸው የተለያየ ድርሻና ኃላፊነት ውስጥ ነው። ማለትም እንደ ሚስት፣ እናት፣ እህት፣ ሴት ልጅ፣ ባልቴት፣ እንጀራ እናት…ወዘተ ሆነው በሚሰጡት ማኅበራዊ አገልግሎት ውስጥ ሴቶች የቤት ውስጥ ጥቃት ሰለባ ይሆናሉ። የጥቃቱ አውዶች ደግሞ ብዙውን ጊዜ በሴትና በወንድ መካከል ያሉ የተለያዩ ዓይነት ግንኙነቶች ናቸው። በዚህም መሠረት ጥቃት አድራሾች ባል፣ የወንድ ፍቅረኛ፣ አባት፣ ልጅ፣ የእንጀራ ልጅ ወይም ወንድም ናቸው ማለት ነው።
በአማራ ክልል አዊ ዞን የተሠራ አንድ የዳሰሳ ጥናት እንደሚያመለክተው፤ ከአስር ሴቶች መካከል ስምንቱ የቤት ውስጥ ጥቃት ሰለባ ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ ግን አንዳቸውም ለእርዳታ ጥሪ አያቀርቡም ወይም ከአንድ በመቶ በታች የሚሆኑት ናቸው የሆነባቸውንና የደረሰባቸውን ለመናገር አቅምና ድፍረት ያላቸው።
በስለሺ አበያ የተሠራ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው ደግሞ፣ በምዕራቡ የኢትዮጵያ ክፍል ከአራት ሴቶች መካከል ሦስቱ በሕይወት ዘመናቸው ቢያንስ አንድ ጊዜ የቤት ውስጥ ጥቃት የደረሰባቸው ናቸው። ከእነዚህ ሴቶች መካከል ግን አሁንም አንዳቸውም በሚባልበት ደረጃ ከአንድ በታች የሆኑት ናቸው ለሚመለከተው አካል ያመለከቱት። ይህ ዝምታ የማኅበራዊ ሕይወት ተጽእኖ፣ አስተዳደግ፣ ባህል፣ ኀላፊነትን ተሸካሚ መሆን ወዘተ የሚያመጡት እንደሆነም ይገመታል።
የቤት ውስጥ ጥቃት አካላዊ ጉዳት ብቻ የሚያደርስ አይደለም። የዓለም ጤና ድርጅት ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት፣ ወሲባዊም ይሁን ሥነልቦናዊ አልያም አካላዊ፣ በጥቅሉ የቤት ውስጥ ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሴቶች ለከፋ የጤና ቀውስ የመጋለጥ እድላቸው በእጅጉ ከፍተኛ ነው። ከጤና አኳያም እንቅስቃሴ ማድረግ ከመራመድ ጀምሮ ከመቸገራቸው ባሻገር ለተለያዩ ሕመሞች ይዳረጋሉ። የማህጸን ሕመም አንዱ ሲሆን፣ ይህም በመደበኛ ሕይወታቸው ግንኙነት ለማድረግ እንዲቸገሩ፣ ሕመም እየተሰማቸው እንዲቆይም ያደርጋል።
በደብረማርቆስ ሆስፒታል የሥነ አእምሮ ሐኪም አዜብ አስማማው እንደሚሉት፤ ከወሲባዊ ጤና መታወክ በተጓዳኝ፣ የቤት ውስጥ ጥቃት ሰለባዎች ለስሜትና የአእምሮ ጤና ችግርም ተጋላጭ ናቸው። ‹‹አሰቃቂ ክስተት ለአእምሮ ጤና መታወክ ሊዳርግ ይችላል። ከእነዚህም posttraumatic stress disorder (PTSD), bipolar disorder, ጭንቀት, ስጋት, ራስን የማጥፋት ሐሳብ እና የእንቅልፍ መረበሽ ይጠቀሳሉ።›› ሲሉም ይዘረዝራሉ። ቀጥለውም ‹‹አንዳንድ ታካሚዎቼ በተፈጠረባቸው አሰቃቂ ክስተት ትውስታ፣ ሕልም እና ቅዠት ይሰቃያሉ›› ሲሉ አክለዋል።
የሥነልቦና ሕክምና ባለሞያዎች እንደሚናገሩት፣ ተደጋጋሚ ጥቃት በተጠቂዎች ሥነ ልቦና ላይ የአቅመ ቢስነት እና ተስፋ ቢስነት ስሜትን ይፈጥራል። ‹‹የዋጋቢነት ስሜት፣ ማንንም ሰው ለማመን መቸገር፣ ከማኅበራዊ ግንኙነትና ትስስር ራስን መነጠል፣ ‹ለምን በእኔ ላይ› ዓይነት ስሜት መዳበር ዓይነት ሁኔታዎች በቤት ውስጥ ጥቃት የመፈጠር እድሉ ሰፊ ነው።›› የሚሉት ደግሞ ሰናይት ተመስገን፤በማማከር የበርካታ ዓመታት ልምድ ያላቸው የሥነ ልቦና ሕክምና ባለሞያ ናቸው።
የቤት ውስጥ ጥቃት ሰለባዎች ለተባሉት በርካታ የጤና መቃወሶች መዳረጋቸው እንዳለ ሆኖ፤ ጥቃት ፈጻሚዎች ራሱ ጥቃት ለመፈጸም እንዲነሳሱ ምክንያት የሚሆናቸው ችግሮች እንዳሉ ሰናይት ያስረዳሉ። ከእነዚህም መካከል ዝቅተኛ የሆነ ለራስ ያለ ግምት፣ ከፍተኛ የሆነ ቅናት እና ንዴትን መቆጣጠር አለመቻል፣ የዝቅተኛነት ስሜት፣ ያልታከሙ ሥነልቦናዊ ችግሮች፣ ያልተፈቱ የልጅነት አሰቃቂ ክስተቶች/ገጠመኞች፣ ሱሰኝነት ተጠቃሽ ናቸው።
‹‹ነገር ግን እነዚህ የቤት ውስጥ ጥቃት መነሻ ምክንያቶች ለጥቃት ፈጻሚዎችና ለፈጸሙት ተግባር ማስተባበያም ሆነ፣ ለአጥፊዎች ምክንያት መስጫ ሆነው ሊወሰዱ አይችሉም። የቤት ውስጥ ጥቃት የሚፈጥረው ሥነ ልቦናዊ ጫና በራሱ የከፋ ነውና።›› ሲሉ ያብራራሉ።
ያም ሆነ ይህ ምክንያቱን አጥርቶ ማወቁ፤ ጥቃት አድራሾች ድርጊታቸው ምክንያታዊና ትክክል እንደሆነ እንዴት ሊያስቡ እንደቻሉ ለማወቅ ይረዳል ባይ ናቸው። ‹‹ጥቃት ፈጻሚዎች ራሳቸው በልጅነት የኃይል ጥቃት የደረሰባቸው ሊሆኑ ይችላሉ። እናም ኃይልን መጠቀም ግጭትን ለማብረድ ትክክለኛ መንገድ አድርገው ሊያስቡት ይችላሉ። ጥቃት ፈጻሚዎችን መረዳትና መርዳት መቻል፤ አዙሪቱን ለማስቆም ሊረዳ ይችላል። ይህ ማለት ግን ጥቃት አድራሾች ከሕግ ያመልጣሉ ማለት አይደለም።›› ሲሉ ጨምረው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የሴቶችን መብት ከማስከበር አኳያ ሴቶች ከየትኛውም ዓይነት የቤት ውስጥ ጥቃት እንዲጠበቁ ማድረግንም ይጠቅሳል። ይልቁንም አንቀጽ 35 እነዚህን መብቶች ለይቶ ያስቀመጠ ነው። የሕግ ባለሞያዎች እንደሚሉት ታድያ በጥቅሉ እንጂ በተለይም የቤት ውስጥ ጥቃትን በተመለከተ ይሄ ነው ተብሎ የተቀመጠ አንቀጽም ሆነ ሕግ የለም። ‹‹በተጓዳኝ ለቤት ውስጥ ጥቃት የተሰጠው ትርጓሜ ሁሉን ያማከለ ካለመሆኑ ይዘቱ ጠባብ ነው።›› ይላሉ ሎዛ ጸጋዬ፣ በሴታዊት ለሴቶች ነጻ የትምህርት እድል ድጋፍ ፕሮጀክት አስተባባሪ።
በሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር የሕግ አገልግሎት ዳይሬክተር ደረጄ ተግይበሉ በሎዛ ሐሳብ ይስማማሉ። ‹‹ሕጉ በቤት ውስጥ ጥቃት ውስት ሊካተቱ የሚችሉትን የኢኮኖሚ በደሎችን እና የትዳር ውስጥ መደፈርን አላካተተም። እንደውም የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ አንቀጽ 564 ላይ ብቻ ነው የቤት ውስጥ ጥቃት በግልጽ የሰፈረው›› ይላሉ። ቀጥለውም ‹‹ይህም አንቀጽ በትዳር አጋር ወይም ያለግብቻ በደባልነት አብሮ በሚኖር ሰው የሚፈጸምን የቤት ውስጥ ጥቃት ያጠቃልላል፤ ነገር ግን ከሴቷ ጋር ወሲባዊ ግንኙነት በሌላቸው በሌሎች ሊፈጸም የሚችልን ጥቃት ከቤት ውስጥ ጥቃት አይቆጥርም።›› ሲሉ ማከተት የሚገባውን ዓይነት ጥቃት ያማከለ ስላለመሆኑ አጽንኦት ይሰጣሉ።
የፍትኅ ሚኒስቴር የወንጀል ሕጉን በ2002 ሲያሻሽል ሴቶችን ከሁሉም ዓይነት የቤት ውስጥ ጥቃቶች ለመከላከል የሚያስችል አድርጎ እንዳሻሻለ ይባላል እንጂ፣ አሁንም ልዩነቱና ክፍተቱ በግልጽ የሚታይ ነው። በእርግጥ ማሻሻያው ላይ በጥሩ ጎን የሚነሱ ነጥቦች አሉ። በተለይም በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በተለያየ መንገድ ከፋፍሎ ማስቀመጡ አንዱ ነው። ይህም ቀድሞ ጥርት ብለው ያልተቀመጡትን በመዘርዘርና በማጥራት፣ አዳዲስ ጥቃቶችን በማካተት፣ የጥቃቶችን ዓይነት በትርጓሜ በድጋሚ በመበየን፣ ጥቃት አክባጅ ሁኔታዎችን በማከልና ቅጣቱንም ከፍ በማደረግ ማሻሻያው የተሻሉ ለውጦችን ያሳየ ነው። ምንም እንኳን ከዛን ጊዜ በኋላ ሌላ ማሻሻያ የተደረገለት ባይሆንም።
ደረጄ እንደሚሉት፤ የቤት ውስጥ ጥቃትን ለመገታል በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ የሕግ ድርሻ በእጅጉ የጎላ ከመሆኑ ላይ የባህል ልምዶችን መስበር ሌላው ወሳኝ ተግባር ነው። በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለማስቆምና ሰብአዊ ድርጊት እንዳልሆነ ከማሳወቅ ጀምሮ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች የደረሰባቸውን ለሚመለከተው በጊዜ እንዲያሳውቁና ፍትኅ እንዲሰፍን እስከማድረግ ድረስ እንዲበረቱ ማድረግን ይጠይቃል።
ደረጄ ታድያ ለዚህም አጋዥ ሊሆኑ የሚችሉት መንገዶች ያሏቸው ግንዛቤ መስጠት፣ የማኅበረሰብ ንቃት እና የባህል እሴቶች ላይ መሥራት፣ ደጋፊ ኃይሎችን በማደራጀት ጠንካራ ማኅበራዊ ግንኙነቶችን ማስቀጠልን ነው። ሰናይት በበኩላቸው ደግሞ በዚህ ሐሳብ ሲስማሙ፣ ‹‹የቤት ውስጥ ጥቃት ሰብአዊ መብት ጥሰት ነው። የሚለማመዱት አመልም ነው። እናም ልምድን ማስቆም ይቻላል።›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ይህም ሲሆን እንደ መርሐዊት ያሉ ሴቶች በደል ከደረሰባቸው በኋላ ፍትኅን አግኝተው ቀና ብለው እንዲሔዱ፣ አስቀድሞም በሌሎች ሴቶች ሕይወትም ተመሳሳይ ጠባሳ እንዳያርፍና እንዳይባክኑ ያደርጋል።
ከአዲስ ማለዳ ጋዜጣ እህት መጽሔት ኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪው 8ኛ ዓመት 77ኛ እትም የተወሰደና በኪያ አሊ ተዘጋጅቶ በሊድያ ተስፋዬ የተተረጎመ፤

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here