በመዲናዋ የምግብ ዋጋ ያረጋጋሉ የተባሉ የገበያ ማእከላት ሥራ ጀመሩ

0
566

በአዲስ አበባ በሚገኙ ሦስት ክፍለ ከተሞች የአማራ፣ የኦሮሚያ እና የፌዴራሉ የኅብረት ሥራ ዩኒየኖች የግብርና እና መሠረታዊ የፍጆታ እቃዎችን ለተጠቃሚዎች በቀጥታ የሚያቀርቡባቸው የገበያ ማእከላት ባሳለፍነው ሳምንት አገልግሎት መስጠት ጀመሩ።
ከዚህ ቀደም በጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማት በተደራጁ ነጋዴዎች ተይዘው የነበሩት እነዚህ የገበያ ማእከላት፣ የታለመላቸውን ዓላማ ሳያሳኩ ተዘግተው የቆዩ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየናረ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም በሚል በድጋሚ በኅብረት ሥራ ዩኒየኖች አማካኝነት እንዲደራጁ መደረጉንም ለማወቅ ተችሏል።
የአማራ እና የኦሮሚያ ክልል የኅብረት ሥራ ኤጀንሲዎች የግብርና ውጤቶችን የሚያቀርቡ ሲሆን፣ የፌዴራሉ የኅብረት ሥራ ዩኒየን ደግሞ የኢንዱስትሪ ውጤቶችን ለማቅረብ ስምምነት ላይ መደረሱን የፌዴራሉ የኅብረት ሥራ ዩኒየን ለአዲስ ማለዳ ገልጿል። እንደ ፓስታ ያሉ የታሸጉ የምግብ ዓይነቶችን የሚያቀርበው ኤጀንሲው፣ በተጨማሪም ለልብስ ንፅህና የሚውሉ የተለያዩ ግብአቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ መጀመሩን አስታውቋል።
የአዲስ አበባ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ዋና ዳይሬክተር መስፍን አሰፋ በበኩላቸው፣ የገበያ ማእከላቱ ከኅብረተሰቡ ፍላጎት አንጻር በቂ ባይሆኑም ለአካባቢው ኅብረተሰብ ግን የተወሰነ ለውጥ ያመጣሉ ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
የገበያ ማዕከላቱ ዋና ዓላማ አትክልት እና ፍራፍሬን በቅናሽ ዋጋ ለኅብረተሰቡ ለማቅረብ ቢሆንም፣ ተዛማጅ የሰብል ምርቶችን በማስገባት የዋጋ ንረቱን ለማቃለል መታሰቡን የከተማ አስተዳደሩ ንግድ ቢሮ የግብይት ዳይሬክተር ሰለሞን በቀለ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ማእከላቱ ከሚያቀርቧቸው ምርቶች መካከልም ሽንኩርት፤ ድንች፤ ቲማቲም እንዲሁም የፍራፍሬ ምርቶች ሲሆኑ ከገበያ ዋጋው እስከ አምስት ብር ቅናሽ እንዳላቸው ኀላፊው ተናግረዋል።
በአንድ ጊዜ ከ ኹለት እስከ ሦስት መቶ ነጋዴዎችን የሚያስተናግዱት እነዚህ የገበያ ማእከላት፣ በምርት አቅራቢ እና በተጠቃሚ መካከል ያሉ አላስፈላጊ ሰንሰለቶችን እንደሚያስቀሩም ይገመታል። በማእከላቱ የሸማች የኅብረት ሥራ ማኅበራትም እንዲገዙ መመቻቸቱን ሰለሞን ተናግረዋል።
አንድ ኩንታል ጤፍ በመደበኛው ገበያ 3ሺሕ400 መቶ ብር ሲሸጥ በገበያ ማእከላቱ 3ሺሕ150 ብር መሸጡን ኀላፊው ገልጸዋል። በሰብል ምርቶች ቢያንስ የ50 ብር ቅናሽ ሲኖር፣ ቅናሹ ግን እስከ 300 ብር እንደሚደርስ ጠቅሰዋል። በማእከላቱ በቆሎ፣ ስንዴ እና የዳቦ ዱቄት ከሚሸጡ ሰብሎች መካከል ናቸው። ማእከላቱ ለሸማቾች ብቻ ሳይሆን ለምርት አቅራቢውም የተሻለ ዋጋን የሚሰጡ ናቸው ሲሉ ሰለሞን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ፣ ከወራት በፊት እንደሚገነቡ ይፋ ያደረጓቸው እና በመዲናዋ መግቢያ በሮች ላይ የሚገነቡት አምስት ዓለማቀፍ የግብይት ማእከላት ግንባታ ለማከናወን የካ እና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞች ለግንባታው የሚሆን ቦታ በማዘጋጀት የይዞታ ማረጋገጫ ለፌዴራሉ የኅብረት ሥራ ዩኒየን ማስረከባቸውን የፌዴራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ሲሳይ አረጋ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
‹‹ኮልፌ ቀራኒዮ፣ ቦሌ እና ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተሞች የይዞታ ማረጋገጫ አላስረከቡንም፣ ነገር ግን ቦታ አዘጋጅተው መረጣ አከናውነናል›› ሲሉ ሲሳይ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ‹‹ግንባታው ዓለማቀፍ ደረጃውን የጠበቀ በመሆኑ ቢሊዮኖችን ስለሚጠይቅ የፋይናንስ ማፈላለግ ሥራ እየሠራን ነው›› ብለዋል።
የዲዛይን እና የስፔስፊኬሽን ሥራዎችን ከቦታ መረጣው ጎን ለጎን በማከናወን ላይ መሆኑን ያስታወቀው ኤጀንሲው፣ ይህ እንደተገባደደም ዓለማቀፍ ጨረታ በማውጣት ወደ ግንባታው እንደሚገባ ይፋ አድርጓል።

ቅጽ 2 ቁጥር 58 ታኅሣሥ 4 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here