የንግድ እና ሸማቾች ጥበቃ ጽንሰ ሐሳብ በስርዓተ ትምህርት ውስጥ ሊካተት ነው

0
559

የፍትኀዊ የንግድ ውድድር እና የሸማች መብቶች ጥበቃ ጽንሰ ሐሳቦች እና ሕጎችን በመደበኛው የትምህርት ስርዓት ውስጥ በማካተት፣ ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል ባሉ የትምህርት ደረጃዎች ከመጪው 2013 የትምህርት ዘመን ጀምሮ በሙከራ ደረጃ ለመስጠት ዝግጅቶች መጠናቀቃቸው ተገለፀ።
ስርዓተ ትምህርቱም ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ በሁለም የትምህርት ደረጃዎች የሚካተት ሲሆን፣ በአፍ መፍቻ ቋንቋ፣ እንግሊዝኛ ቋንቋ፣ ሥነ ዜጋ እና ሥነ ምግባር፣ ሂሳብ፣ አካባቢ ሳይንስ እና ማኅበራዊ ሳይንስ ትምህርቶች ላይ ተካትቶ በሁሉም ክልሎች ለመስጠት በዝግጅት ላይ ይገኛል። ሕጎቹ እና ጽንሰ ሐሳቦቹን በስርዓተ ትምህርት ውስጥ በማካተት ወጣቶች ስለ ንግድ ውድድር እና ስለመብታቸው ግንዛቤ እንዲኖራቸው የማድረግ ዓላማ እንዳለውም ተገልጿል።
ከአንድ ዓመት በላይ ከንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር ውይይት በማድረግ ስርዓተ ትምህርቱ መዘጋጀቱን፣ በትምህርት ሚኒስቴር ስርዓተ ትምህርት ጥናት እና ትግበራ ዋና ኀላፊ እሸቱ አስፋው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
አክለውም ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ከ ኹለት እስከ ሦስት ዓመታትን ይፈጃል ያሉ ሲሆን፣ በቀጣዩ የትምህርት ዘመን በሙከራ ደረጃ በሁሉም ክልሎች ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
የንግድ ውድድር እና ሸማቾች መብት ጥበቃ በበኩሉ፣ ጽንሰ ሐሳቦቹ በስርዓተ ትምህርት ውስጥ እንዲካተቱ ለማድረግ ከአራት ዓመታት በላይ ጥረት ሲያደረግ መቆየቱን እና አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ መዘጋጀት ለተግባራዊነቱ መልካም አጋጣሚ እንደፈጠረ በሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው አልቃድር ኢብራሂም በኩል ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።
በስርዓተ ትምህርቱ ውስጥም ነጋዴዎችን እና የሸማቾችን መብት እና ግዴታዎች የተመለከቱ ጉዳዮች ይዳስሳል ያሉት ኀላፊው፣ በተደጋጋሚ የሚስተዋለውን የሸማቾች መብት መጣስ እና መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ በሁሉም የትምህርት ደረጃ የሚገኙ ሕጻናት እና ወጣቶች እየተገነዘቡት እንዲያድጉ እና በሕግና በስርዓት የሚመራ የንግድ ስርዓትን ለመፍጠር ይረዳል ብለዋል።
ሕጎቹን በስርዓተ ትምህርት ውስጥ ለማካተት ከመነሻው ጀምሮ ከክልሎች ጋር ውይይት መደረጉን እና በቀረፃው ላይ እንዲሳተፉ መደረጉ የተገለፀ ሲሆን፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት በቋንቋቸው የሚሰጥ በመሆኑ አጋዥ መጽሐፍትን ለማዘጋጀት እና መምህራንን ስለጉዳዩ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከክልሎች ጋር እየሠራ መሆኑ ተገልጿል።
የአጋዥ መጽሐፍቱ ዝግጅትም በ 42 ቋንቋዎች ለሁሉም ክልሎች እንደሚዘጋጅ ይጠበቃል።
ገበያ ማለት ምን ማለት ነው፣ ምጣኔ ሃበትስ፤ አገራዊ እና ዓለም ዐቀፋዊ ሕጎች ስለ ንግድ ምን ያላሉ፤ እንዲሁም ነጋዴ እና የሸማች መብቶች እና ግዴታዎች ምን ምን ናቸው የሚሉ ዋና ዋና ርዕሶች መካተታቸውን አዲስ ማለዳ እጅ የገባው ሰነድ ያሳያል።
ተማሪዎችም ራሳቸውን እና በአካባቢያቸው የሚገኘውን ማኅበረሰብ ከፀረ ንግድ ውድድር እና ሸማቹን ከሚጎዱ ተግባራት መጠበቅ፣ ለአገሪቱ የንግድ ስርዓት ዘመናዊነት እና እድገት አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ይረዳቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ቅጽ 2 ቁጥር 58 ታኅሣሥ 4 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here