ባለፈው አንድ ሳምንት የአዲስ አበባ ከተማ የሥጋ አቅርቦት በ 50 በመቶ ቀነሰ

0
758

በአዲስ አባባ ከተማ ከኅዳር 24/ 2012 ጀምሮ ሥጋ ቤቶች እያካሔዱት ባለው የሥራ ማቆም አድማ ምክንያት የሥጋ እርድ መጠን በ 50 በመቶ ቀንሶ፣ በቀን ሰባት መቶ በሬ የሚያርደው ቄራ ባለፉት ዐስር ቀናት ከ350 በሬ አለማለፉን የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት አስታወቀ።
ሥጋ ቤቶቹ የአዲስ አበባ ገቢዎች ባለሥልጣን ሳያሳውቀን አዲስ የግብር አወሳሰን መመሪያን ተግባራዊ አድርጎብናል በሚል በከፊል አድማ አድርገዋል። ግብር ሰብሳቢ ባለሥልጣኑ በ2010 ያወጣውን የቁርጥ ግብር መመሪያ ለግብር ከፋዩ ዓመቱን ሙሉ እንዲገለገልበት ሳያሳውቅ፣ በዓመቱ መጨረሻ ተግባራዊ አድርጓል። መመሪያውም ነጋዴውን የሚጎዳ ነው ሲሉ ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል።
የአዲስ አበባ ሥጋ ቤቶች ማኅበር አባላቶቹ በራቸውን በመዝጋት እያካሔዱት ስላለዉ የሥራ ማቆም አድማ በውል የሚያውቀው ጉዳይ እንደሌለ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል። ማኅበሩ በከፊል አባላቶቹ ሥራቸዉን ያቆሙበት ምክንያት ከአዲስ አበባ ገቢዎች ባለሥልጣን ጋር በተፈጠረዉ አለመግባባት እንደሆነ እና ቀሪዎቹ ግን ጥያቄአቸው ምን እንደሆነ ለመረዳት በመጪዉ ሳምንት አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ በመጥራት ለመወያየት ማቀዱን አስታዉቋል።
ይህንንም ጥያቄ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ፤ እንዲሁም የአዲስ አበባ ገቢዎች ባለሥልጣን እንዳቀረቡ እና መልስ እየጠበቁ መሆኑንም የማኀበሩ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ምትኩ ሞሻጎ ተናግረዋል። ማኅበሩ መንግሥት ያወጣዉን መመሪያ እንደማይቃወም፣ ነገር ግን ተግባራዊ ሲሆን ማወቅ እንደነበረባቸዉ ገልፀዋል።
በቁርጥ ግብር መመሪያው መሰረት አንድ በሬ፣ በአንድ መቶ ኻያ ኹለት ኪሎ ታስቦ የተሸጠበት የገንዘብ መጠን፤ ወለድ እንዲሁም ቅጣቱን ጨምሮ እንደተጠየቁ አቶ ምትኩ ገልፀዋል። በተጨማሪም በ2010 በነበረዉ የገበያ ዋጋ መሠረት የ2011 ግብር እንዲሰላ መሆኑ አግባብነት የለውም ሲሉም ቅሬታ አቅርበዋል።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው አንድ የሥጋ ቤት ባለቤት እንደሚሉት፣ ሁሉም በሬ መቶ ኻያ ኹለት ኪሎ አለመመዘኑ አንዱ የቅሬታ መሠረት ሲሆን ከቄራዎች ተመዝኖ የሚረከቡት ሥጋ እንኳን ጠዋት የተመዘነው ከሰአት ሙቀት ሲያገኘው እንደሚቀንስ እና ይህም ተረፈ ምርት ሲወጣለት ከፍተኛ ጉድለት እንደሚኖረው ተናግረዋል።
በተጨማሪም ሥጋ ቤቶች የተጠየቁት ግብር ከአቅማቸዉ በላይ መሆኑን እና አትራፊ እንዳልሆነ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። የአዲስ አበባ የገቢዎች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ታምራት ንጉሤ፣ መመሪያው ሕግ እስከሆነ ድረስ በሕግ አልገዛም የሚል ቅሬታ ሊኖር እንደማይችል ገልፀዋል። አክለውም በግብር አወሳሰን ሒደቱ ላይ ግን ቅሬታ ያለው ማንኛውም ሰው ለግብር ቅሬታ ሰሚ አቤቱታውን ማቅረብ ይችላል ሲሉ ጠቁመዋል።
‹‹ግብር ላለመክፈል የሚደረግ ማንኛውንም አይነት ድርጊት ግን አናስተናግድም፣ ከሕጋዊ ግዴታ መሸሽ አይቻልም›› ብለዋል።
በተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት በሥጋ ዋጋ ላይ የሚኖር ጫና የለም ሲሉ የስጋ ቤቶች ማኅበር ሰብሳቢው ምትኩ ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 58 ታኅሣሥ 4 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here