የአማራ ሜዲካል አክሲዮን ማኅበር በመቶ ሚሊዮን ብር ሊመሠረት ነዉ

0
792

አማራ አክሲዮን ማኅበር የተሰኘ የሕክምና አገልግሎት ሰጪ እና ቁሳቁስ አቅራቢ አክሲዮን ማኅበር ለመመሥረት የአክሲዮን ሽያጭ ተጀመረ።
አክሲዮኑ ሁሉን ዐቀፍ የሆነ የጤና አገልግሎት ለማቅረብ በሚል የተቋቋመ ሲሆን፣ የሕክምና አገልግሎት፣ የመድኀኒትና የሕክምና መሣሪያዎችን ምርት፣ ሽያጭ እና ማከፋፈል የአጭር እና የረዥም የሕክምና የትምህርት እና ሥልጠና ማእከላት መክፈት እና አገልግሎት የመስጠት ዓላማ ያለው ነው።
በተጨማሪም በዉጭ አገራት ካሉ የጤና ተቋማት ጋር በወኪልና በኮሚሽን ኤጀንሲነት መሥራት፤ የሕክምና ቱሪዝም አገልግሎት፤ የሕክምና ፅዳት ኬሚካሎች እና የሕክምና አልባሳት አቅራቢነት፤ የጤና እና ጤና ነክ ጥናትና ምርምሮችን ማካሔድ እንዲሁም የማማከር አገልግሎት መስጠት እና ሌሎች የጤና አገልግሎቶችን መስጠት ዓላማው ማድረጉንም ገልጿል።
ማኅበሩም ለሕክምና አገልግሎት የሚውሉ መሠረተ ልማቶችን መገንባት ዓላማዬ ነው ያለ ሲሆን፣ የማማከር አገልግሎትና መድኀኒት የማምረት ሥራዎችም እንደሚያከናውን የአክሲዮን ማኅበሩ ሰብሳቢ ከተማ ስንታየሁ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
‹‹የጤና አገልግሎት ጥራትን ማሻሻል መጀመሪያ እንጂ መጨረሻ የለዉም የሚል እምነት አለን›› ያሉት የአደራጅ ኮሚቴው ሰብሳቢ፣ እቅዶቻቸዉ ሊሻሻሉ እና ሊከለሱ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
በጤናዉ ዘርፍ ሰፊ ልምድ ባካበቱ ባለሞያዎች ተደራጅቷል የተባለው ማኅበሩ፣ አክሲዮን መሸጥ መጀመሩን እና እስከ ተገባደደው ሳምንት ድረስም ከኹለት ሚሊዮን ብር በላይ አክሲዮን መሸጡን ከተማ ተናግረዋል።
ኅዳር 19/2012 የተጀመረው የአክሲዮኑ ሽያጭ የካቲት 16/2012 የሚያበቃ ሲሆን፣ ዝቅተኛው የአክሲዮን መጠን 10 ሺሕ መሆኑን አደራጅ ኮሚቴው ለአዲስ ማለዳ ገልጿል። የአንድ አክሲዮን ዋጋ አንድ ሺሕ ብር ሆኖ ከፍተኛው የአክሲዮን ዋጋ 125 ሺሕ ብር ወይም 125 አክሲዮን መሆኑ ተገልጿል።
ከአማራ ክልል ንግድ ቢሮ በተሰጠው ንግድ ፈቃድ በአምስት ባንኮች ባሳለፍነው ሳምንት አክሲዮን መሸጥ የጀመረ ሲሆን፣ በአባይ ባንክ፣ ዳሽን ባንክ፣ ቡና ባንክ፣ አቢሲንያ እና ንግድ ባንኮች ሽያጩ መጀመሩ ተገልጿል። አክሲዮን ማኅበሩ የአማራ ቲንክ ታንክ ቡድን አባላት የመሠረቱት ሲሆን፣ የማደራጀት ሒደቱ ሲጠናቀቅ ለቦርድ በማስረከብ ከሒደቱ እንወጣለን ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ድርጅቱ ከአማራ ባንክ ጋር ግንኙነት አለው ቢባልም፣ ትስስሩ ሕጋዊ ሳይሆን የአማራ ሕዝብን ኢኮኖሚያዊ አቅም በማጠናቀር አጀንዳዎች ላይ ለመሥራት ነው ሲል አስተባባሪ ኮሚቴው ገልጿል።
አክሲዮን ማኅበሩ የአክሲዮን ሽያጩን ሲያጠናቅቅ በቀጥታ የሚገባበት የሕክምና ዘርፍ ምን እንደሆነ አዲስ ማለዳ ላቀረበችው ጥያቄም ‹‹ለጊዜው ይሄንን ማለት አንችልም፤ ነገር ግን የተጠኑ ጥናቶች ስላሉ በዛ መሠረት ቅድሚያ እየሰጠን እንሔዳለን›› ሲሉ የአደራጅ ኮሚቴው አባል ተናግረዋል። ‹‹እና አደራጆችም አክስዮን ገዝተን ነው የምንገባው፣ የሕክምና ዘርፍ አትራፊ በመሆኑ በቻልነው አቅም ሕዝቡንም አባላቱንም የሚጠቅም ሥራ እንሠራለን›› ብለዋል።
በክልሉ፣ በመንግሥት ወይም በግሉ ዘርፍ ያልተሸፈኑ አካባቢዎችን ይሸፍናል የተባለው አክሲዮኑ፣ ለጊዜው ከአማራ ክልል ውጪ መዋዕለ ነዋዩን የማፍሰስ ሐሳብ እንደሌለውም ለማወቅ ተችሏል።
በወራት ጊዜ ውስጥም በአዲስ አበባ እና በባህር ዳር ከተማ ጽሕፈት ቤቶቹን ከፍቶ ሥራ ይጀምራል የተባለ ሲሆን፣ አክሲዮን ማኅበሩ ሥያሜው ‹‹የአማራ›› ይባል እንጂ ማንኛዉም አክሲዮን መግዛት የሚፈልግ ሰዉ መግዛት ይችላል ሲሉ አደራጆቹ ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 58 ታኅሣሥ 4 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here