ጀርመናዊው ግለሰብ በዐስር ዓመት ፅኑ እስራት ተቀጡ

0
540

የአምስት መቶ ብር የገንዘብ መቀጮም ተጥሎባቸዋል

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ችሎት በትውልድ ጋናዊ እና በዜግነት ጀርመናዊ የሆኑት ግለሰብ ሐሰተኛ ሰነድ ከውጪ አገር በማስገባት እና በመጠቀማቸው ምክንያት በቀረበባቸው ክስ ጥፋተኛ በማለት የዐስር ዓመት ጽኑ እስራት ፈረደባቸው።
ከአንድ ዓመት በፊት የፓን አፍሪካ ካውንስል ተወካይ እንደሆኑ እና ‹የአፍሪካ ኅብረት ቅርንጫፍ ባንክ በአዲስ አበባ ለመክፈት ነው የመጣሁት› በሚል ከዛፍ ፋርማሲትውካልስ ባለ ሰባት ፎቅ ህንፃ የተከራዩት ግለሰቡ፣ ወደ ሕግ የቀረቡት በጥቆማ ነበር። በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 የሚገኘውን ይህንን ህንፃ በወር 55 ሺሕ ዶላር እከራያለሁ በሚል ወደ ድርጅቱ ባለቤት የቀረቡት ፍራንክሊን፣ ለ30 ዓመት የሚል አማላይ ውል በማቅረብ መጠቀማቸውን የአቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል።
በደላላ አማካኝነት ባለ ሰባት ወለል ህንፃቸውን ያከራዩት የዛፍ ፋርማሲቲካልስ ዋና ሥራ አስኪያጅም ለሰባት ወር የኪራይ ገንዘባቸውን ቢጠብቁም የውሃ ሽታ በመሆኑ በገባቸው ጥርጣሬ ወደ ፌዴራል ፖሊስ በመሔድ አቤት በማለታቸው ምክንያት ምርመራውን ማካሔድ የጀመረው ፖሊስ፣ ተጨማሪ ወንጀሎችን በማግኘቱ ምርመራውን አጠናክሮ ይቀጥላል። ለዛፍ ፋርማሲትውካልስ ቀርቦ የነበረው 33 ሺሕ ዶላር የሚያወጣ የባንክ ማስተማመኛ ሰነድ በታንዛኒያ ተሠርቶ የመጣ የሀሰት ሰነድ መሆኑንም ፖሊስ አረጋግጧል።
የዛፍ ፋርማሲቲካልስ ዋና ሥራ አስኪያጅም በደረሰባቸው ከባድ የማታለል ወንጀል በሰጡት ቃል መሰረት ዐቃቤ ሕግ ክስ እንዲመሠርት ምክንያት ሆኗል። በተጨማሪም ግለሰቡ ህንፃውን ከተከራዩ እና ፈቃድ ካገኙ በኋላ ከኢትዮጵያ ባንኮች ገንዘብ የመዝረፍ ሐሳብ ነበራቸው ሲል ፖሊስ ሌሎች በተከሳሽ ቤት የተገኙ ሰነዶችን በመጥቀስ ክስ መሥርቷል።
ተከሳሽን የዋስትና መብት የነፈገው ፍርድ ቤቱ፣ በተከሰሱበት ወንጀል የእምነት ክህደት ቃላቸውን እና የቀረበባቸውን ማስረጃ በማረፊያ ቤት እያሉ ላለፉት አንድ ዓመት ተከታትሏል።
በትውልድ ጋናዊ የሆኑት ግለሰቡ፣ ከአፍሪካ ኅብረትም ሆነ ከኢትዮጵያ መንግሥት ፈቃድ ሳያገኙ የድርጅቶቹን ሥም በመጠቀም ሃሰተኛ ሰነድ ከውጪ አገር በማስገባት፣ በማዘዋወር እና በመጠቀም ክስ ተመሥርቶባቸዋል። በተጨማሪም ዛፍ ፋርማሲቲካልስን በወቅቱ ምንዛሬ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ በማሳጣት ለፈጸሙት ወንጀል ጥፋተኛ ናቸው ሲል ፍርዱን ሰጥቷል። ንብረቱን በመከራየት የኢትዮጵያ ባንኮችን ለመዝረፍ ዝግጅት ማድረጋቸውንም ዐቃቤ ሕግ በመስረጃው አስረድቷል።
ፍርድ ቤቱም ሰኞ ኅዳር 30/ 2012 በዐስር ዓመት ጽኑ እስራት እና በአምስት መቶ ብር የገንዘብ መቀጮ የቀጣቸው ሲሆን፣ ተጠርጣሪው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሌላ መዝገብ ተጨማሪ ክስ እየተከታተሉ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።
በመዝገቡ የግል ተበዳይ የሆነው ዛፍ ፋርማሲቱካልስ በ1991 በአዲስ አበባ በ50 ሺሕ ዶላርና በአምስት ሠራተኞች የተመሠረተ ሲሆን፣ በአሁን ሰዓት ሦስት ሚሊዮን ዶላር የተከፈለ ካፒታል እና 110 ቋሚ ሠራተኞችን የያዘ የመድኀኒት ጅምላ ንግድ ድርጅት ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 58 ታኅሣሥ 4 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here