ዛሬ ቅዳሜ ሕዳር 22/2011 ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ስር የሚገኘው የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የስነ ጥበባት ማዕከል 41ኛውን የጥበብ ውሎ ውይይት ያደርጋል።
የዛሬው ዝግጅት ማዕከሉ በስማቸው በተሰየመላቸው ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ሕይወትና ስራዎች ላይ ያጠነጥናል። ከ1871 እስከ 1931 በሚሸፍነው የብላቴን ጌታ ኅሩይ ህይወትና ስራዎች ላይ በተለይም ባለታሪኩ በ1916 እና በ1925 በጻፏቸው ‹‹አዲስ ዓለም›› እና ‹‹ወዳጄ ልቤ›› በተሰኙ መጻሕፍት ላይ ውይይት ይደረጋል።
የስነ ጽሑፍና ፎክሎር ባለሙያ እንዲሁም የስነ ጥበብ ማዕከሉ ዳይሬክተር እንዳለጌታ ከበደ የውይይት መነሻ ሀሳብ ያቀርባሉ። በዕለቱ ከብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የሕይወት ታሪክ በተጨማሪ አጭር ዘጋቢ ፊልም፣ ግጥሞች፣ ትረካዎችና ዲስኩሮች ይቀርባሉ ተብሏል። የብላቴን ጌታ ኅሩይ የልጅ ልጆችና ሌሎች እንግዶች በዛሬው የጥበብ ውሎ ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ምሑር የሚሰኙት ኅሩይ ወልደሥላሴ በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዘመን የመጀመሪያው የውጭ ጉዳይ ሚንስትርና ደራሲ ነበሩ።
ከአስራ አምስት ቀን በኃላ የሚኖረው ዝግጅት በኃይሌ ገሪማ ‹‹ጤዛ›› ፊልም ላይ ውይይት እንደሚደረግ ከወዲሁ ታውቋል ማዕከሉ በየሁለት ሳምንቱ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይት የሚያደርግ ሲሆን ፍላጎቱ ላላቸው ሁሉ ክፍት መሆኑን ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል።
ቅጽ 1 ቁጥር 3 ኅዳር 22 ቀን 2011