የጎሃ ጽዮን ደጀን መንገድ ላይ ጥናት እየተደረገ መሆኑ ተገለፀ

0
627

በተደጋጋሚ በመሬት መንሸራትት ምክንያት ችግር የሚገጥመውን እና አዲስ አበባን ከባህር ዳር እና ጎንደር የሚያገናኘውን የጎሃ ጽዮን ደጀን መንገድ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ጥናት እየተደረገ እንደሚገኝ ፌዴራል መንገዶች ባለሥልጣን አስታውቋል።
በአካባቢው ባለው መልከአ ምድራዊ አቀማመጥ እና የአየር ፀባይ ምክንያት በመንገዱ ላይ በተደጋጋሚ የመሬት መንሸራተት አደጋዎች እንደሚከሰቱ የተገለፀ ሲሆን፣ በአካባቢው የሚስተዋለውን ከፍተኛ የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ እንዳይስተጓጎል ተደጋጋሚ ጊዜያዊ ጥገና ሲደረግለት እንደቆየ ባለሥልጣኑ ገልጿል።
የዚህን የመንገድ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት እንዲያስችለም የጃፓን ባለሙያዎች በቦታዉ ተሰማርተው ጥናት ማድርግ መጀመራቸው ተጠቅሷል። ከጥናቱ በኋላም ውጤቱን መሠረት ባደረገ መልኩ ሊወሰድ የሚገባው ዘላቂ መፍትሔ ለመንግሥት ቀርቦ ውሳኔ እንደሚሰጥበት ተገልጿል።
ባለሥልጣኑ በያዝነው ወር በ 6.1 ቢሊዮን ብር አራት የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ለማከናወን ከአሸናፊ ተቋራጮች ጋር የውል ስምምነት መፈረሙ የሚታወስ ሲሆን፣ ከፕሮጀክቶቹ መካከልም የሃሙሲት እስቴ መንገድ ርዝመት 76 ኪሎ ሜትር፤ የግንባታ ወጪውም 1 ቢሊዮን 395 ሚሊዮን ብር፣ ጩለሴ ሶያማ ሎት 2 የመንገዱ ርዝመት 90 ኪሎ ሜትር፤ የግንባታ ወጪውም 1 ቢሊዮን 800 ሚሊዮን ብር ናቸው።
እንዲሁም የአደሌ ግራዋ መንገድ 88.5 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው ጎዴ ቀላፎ ሎት አንድ መንገድ፣ በ2.5 ቢሊዮን ብር የውል ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል። የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶቹ በሦስት ዓመታት ውስጥ እንደሚጠናቀቁ ይጠበቃል።

ቅጽ 2 ቁጥር 59 ታኅሣሥ 11 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here