ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋን ሳተላይት ወደ ጠፈር አመጠቀች

0
1448

በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነችው “ETRSS-1” የሚል ሥያሜ የተሰጣት ሳተላይት ከቻይና የሳተላይት ማስወንጨፊያ ጣቢያ ወደ ህዋ መጠቀች።
72 ኪሎ ግራም የምትመዝነው የኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሳተላይት፣ ከቻይና ዋና ከተማ ቤይጂንግ 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘው የቻይና ሳተላይት ማስወንጨፊያ ጣቢያ ታኅሳስ 10 ጠዋት 01:06 ደቂቃ ላይ ወደ ህዋ ተወንጭፋለች። በተወነጨፈች በግማሽ ሰዓት ውስጥ ከመሬት 700 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ምህዋርዋን በመያዝ መረጃ መላክ መጀመሯ ተገልጿል።
ሳተላይቷ በኢትየጵያ ታሪክ የመጀመሪያዋ ስትሆን፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቆጣጠር፣ ከግብርና ጋር የተያያዙ ጥናት እና ምርምሮችን ለማከናወን እንዲሁም ለከተማ ልማት እና ሌሎች ዘርፈ ብዙ የመሠረተ ልማት ተግባራትን ለማከናወን የሚያስፈልጉ መረጃዎችን በማቀበል ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖራታል ተብሏል።
ሳተላይቷ በቻይና አገር ውስጥ ከሚገኝ የማምጠቂያ ማእከል ከፍተኛ የመንግሥት ኀላፊዎች በተገኙበት ወደ ህዋ የመጠቀች ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ውስጥም ይህን ታላቅ ታሪካዊ ክስተት የሚዘክሩ በርካታ ዝግጅቶች እንደሚከናወኑ ይጠበቃል።
በእንጦጦ ስፔስ ኦብዘርቫቶሪ ተቋም በተካሔደ ልዩ ዝግጅት ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የቴክኖሎጂ ልማት እና ዓለማቀፋዊ የተወዳዳሪነት ጉዞ መጠናከር እንደሚገባው ተናግረዋል።
ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ህዋ የተወነጨፈችው ETRSS-1 ሳተላይት ለኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ ታሪካዊ መሠረት የምትጥል መሆኗንም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገልፀዋል። ‹‹ይህ ክስተት እኛ ኢትዮጵያውያን ጨለማን እየፈራን ብርሃን የምንናፍቅ ሕዝቦች እንዳልሆንን በተግባር የተረጋገጠበት ታሪካዊ እርምጃ ነው” ብለዋል።
መጪው ዘመን ከየብስ ተሻግሮ በህዋ ሳይንስ ሊኖር የሚገባውን የተወዳዳሪነት አቅም ከወዲሁ መገንባት እንደሚገባም አፅንኦት ሰጥተውበታል።
ሳተላይቷ ወደ ህዋ ከመጠቀች በኋላ በእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪ እና ምርምር ማእከል ቅጥር ግቢ ውስጥ ለሳተላይቷ ትዕዛዝ ለመስጠት፣ ለመከታተል እንዲሁም ከሳተላይቷ የሚገኘውን መረጃ ለመቀበልና ለተጠቃሚ ለማዘጋጀት የሳተላይት መረጃ መቀበያ ጣቢያ ማእከል ግንባታ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቱ ገልጿል።

ቅጽ 2 ቁጥር 59 ታኅሣሥ 11 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here