የመኪና ዋጋን ጣራ ያስነካው ኤክሳይስ ታክስ

0
691

በኢትዮጵያ የተለያዩ ዓመታት በተለይም ደግሞ ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ የተለያዩ ዕቃዎች እና መገልገያዎች ላይ መንግሥት ቀረጦችን ሲጥል መኖሩ የሚታወቅ ነው። የአንድ አገር መንግሥት በዋናነት አገር ከማስተዳደሩ በተጨማሪ ግብርን መሰብሰብና ቀረጥን መጣል ዋነኛ እና ተቀዳሚ ተግባራት ተብለው ከተቀመጡት ውስጥ መገኘቱ እሙን ነው።
በእኛም አገር ታዲያ የግብር እና ቀረጥን በተመለከተ በዓመታት መካከል በርካታ ማሻሻያዎች እየተሠሩ እና ተግባራዊ እየተደረጉ ዘልቀዋል፤ ወደፊትም እንደሚሠራባቸው አያጠራጥርም። ይህን ብለን ስናበቃ ታዲያ ባሳለፍነው ሳምንት ከወደ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንድ ዜና ተሰምቷል። ይህም ኤክሳይስ ታክስን ወይም የአንድ አገር መንግሥት የቅንጦት ዕቃ ናቸው ብሎ በፈረጃቸው ዕቃዎች ላይ የሚጥለው የቀረጥ አይነት ነው። ታዲያ ኢትዮጵያም ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ እና በአገር ውስጥ ተመርተውም የቅንጦት ዕቃ በሆኑት ላይ የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ እንዲወሰን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል።
በዚህ የኤክሳይስ ታክስ ዝርዝሮች ውስጥ ደግሞ መኪና ዋነኛው እና መነጋገሪያ ከሆኑት ዕቃዎች ውስጥ አንዱ ሆኗል። ከዚህ ቀደም በአዲስ እና በአሮጌ መኪኖች ላይ ይጣል የነበረው ቀረጥ ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ የነበረ ቢሆንም፣ በአሁኑ እና ይሻሻላል ተብሎ በሚጠበቀው ኤክሳይስ ታክስ ላይ ከሰባት ዓመት በላይ ያገለገሉ መኪኖችን ወደ አገር ውስጥ በሚገቡበት ጊዜ ከተገዙበት ዋጋ የ500 በመቶ ቀረጥ እንደሚጣባቸው የሚደነግግ ሕግ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል።
ይህን ተከትሎ እንዲያውም ሆድ የባሰው የመኪና ገበያ ጭራሹኑ እንዳይዳከም አስግቷል። ለነገሩ ይህ ከገበያው በተለይም ከአስመጪዎች ወገን ሆነ እንጂ፣ ከገዢውም ቢሆን የመኪና ዋጋ ሰማይ መንካቱን ገና ከአሁኑ በማለም መኪና የመግዛት ሐሳብን አርግፍ አድርጎ የመተው ውሳኔ ላይ የደረሱ ሰዎችም በዝተዋል።
ለዚህ ደግሞ የሰሞኑ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች አስተያየት ዋነኛው መነጋገሪያ ርዕስ ይህ ሆኖ ሰንብቷል። ወደ አገር ውስጥ የሚገቡትን ረጅም ዕድሜ ያገለገሉ መኪኖችን ለማስቀረት ታሳቢ ተደርጎ የሚጣል የቀረጥ ሒሳብ እንደሆነ የገቢዎች ሚኒስቴር በፌስ ቡክ ገጹ ቢገልጽም፣ አስተያየት ሰጪዎች ግን በመካከለኛ ገቢ ለሚተዳደረው ዜጋ የታሰበ አይደለም በሚል የመኪና መግዛት ትልሞቻችንን አምክኖብናል ሲሉ ትችት አሰምተዋል። የሳምንቱ መነጋገሪያ ርዕስ የሆነው ይኸው ሐሳብ፣ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል። ምናልባትም ማሻሻያዎች ሊኖሩም ላይኖሩም ይችላሉ፤ ተግባራዊነቱ ግን ገና ነው ተብሏል።

ቅጽ 2 ቁጥር 59 ታኅሣሥ 11 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here