ከሸገር እስከ የፍቅር ሐይቅ

0
1123

አዲስ ማለዳ ጎዞዋን ቀጥላለች። ኅዳር 25/2012 ከረፋዱ 4 ሰዓት በመስቀል አደባባይ እንድንገኝ የተያዘው ቀጠሮ ላይ ሰዓት ማርፈድ በጋዜጠኞች መባሱ በሰዓቱ ለደረስነው አስደንጋጭ ነበር። ‹ጉዞው ተሰረዘ እንዴ?› በሚያስብል አኳኋን ከአንድ እጅ ጣቶች የማንበልጥ ተጓዥ ጋዜጠኞች ነበርን በስፍራው የተገኘነው። ደቂቃዎች ነጉደው መጀመር ከነበረበት የኹለት ሰዓታትን ዕድሜ ተጎትቶ ተጀመረ፤ ጉዞ ወደ ውቢቷ ከተማ ሐዋሳ።
በቀትር ያውም አዳሩን 280 ኪሎ ሜትር ወደ ምትርቀው ሐዋሳ ጉዞ ለማድረግ ማሰብ ስለ እውነት እንነጋገር ከተባለ የብልህ ምርጫ አይደለም። ሰዓቱ ስጋ ለባሽ ኹሉ ጥጉን የሚይዝበት፣ ጥላ ቢጤ ሽቶ በየአቅራቢያው የሚገኘውን የትኛውንም ዓይነት መጠለያ የሚሻበት ነው። በተለይ ደግሞ ጉዟችን በምሥራቃዊው የአዲስ አበባ በር ላደረግነው ለእንደኛ አይነቱ፣ እንኳንም ሊተገበር መታሰብ እንደሌለበት እኛን የያዘው መኪና ከተንቀሳቀሰ ከአፍታ በኋላ ነበር የተረዳነው።
ወደ ፍጥነት መንገድ የሚያስገባውን አዲስ አስፓልት መንገድ ይዘን መንደርደር እንደ ጀመርን ውስጣዊው የመኪናው ሙቀት የውጩን በመቀበል ተሳፋሪዎቹን ወዝ በወዝ ማድረግ ጀመረ። ኹሉም በየፊናው የሚከፈት መስኮት ፍለጋ ላይ ነበር። የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ እና አዲስ ማለዳ ለሐዋሳ እና ለጉዞው አዲስ ባይሆኑም፣ በዝናባማው እና ትንሽም ቢሆን ብርድ ቢጤ በሚሞካክርበት የክረምት ወራት ነውና የተጓዙት የአሁኑ ጉዞ ትንሽ ፈታኝ እንደሚሆን ከወዲሁ ተገንዝበዋል።
አሁን የፍጥነት መንገድን ተያይዘነዋል፤ ወሬው፣ ጭዋታው፣ ውይይቱ ቀጥሏል። አብዛኞቻችን ከዚህ ቀደም በተደረገ የመስክ ጉብኝት መርሃ ግብር ወይም በአንድ መግለጫ አልያም በአንድ የከተማችን ኹነት፣ ብቻ በአንዳች ጉዳይ ምክንያት ስለምንተዋወቅ ባይተዋርነት የሚሰማው ሰው አልነበረም። ወትሮውንም ጋዜጠኛ ለመግባባት ጊዜ አይፈጅበትም፣ እንኳንም ለአፍታ የምታክል ጊዜ ተያይቶ ቀርቶ። ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኦኮኖሚያዊ ጉዳዮች እየተነሱ እየተጣሉ፣ ዘለግ ያለ ትንታኔ እየተሰጠባቸው ብቻ ጉዞው ይሔ ቀረሽ የሚባል አይደለም።
የፈጣን መንገዱን ጠቀሜታ ወይም የመንገዱን ምቾት እና ሕግን የተረዱ የማይመስሉት ዕድሜ ጠገቡ አሽከርካሪያችን ከተፈቀደው የፍጥነት መጠን እጅግ ባነሰ አንዳንዴም ለመቆም በሚቃጣ ሁኔታ ነበር የሚያሽከረክሩት። በዚህ ምቹ እና ሰፊ መንገድ ላይ እንዲህ ካሽከረከሩ በቀጣይ በሚገጥመን መንገድማ ጭራሽ ቆመው ሐዋሳ የምንደርሰው በማግስቱ ነው በሚል ገና ለገና ቀጣዩን መንገድ በማሰብ ሐሞታችን መፍሰስ ጀምሯል።
የፍጥነት መንገዱን የምንጠቀመው እስከ ደረቅ ወደቧ ከተማ ሞጆ ድረስ ነው። አሁን ሞጆ ደርሰን ከፍጥነት መንገድ ወጥተናል። ወደ አዳማ የሚሔደውን መንገድ አቋርጠን የሐዋሳን መንገድ ተያይዘነዋል። ሞጆ በየትኛውም ሰዓት እንደሞቀች እንደደመቀች ነው። ምናልባትም ወደብ ከተማ መሆኗ 24 ሰዓት ነቅታ እንድታድር ምክንያት የሆናት ይመስላል። ከሞጆ ተነስተን ወደ ሐዋሳ በምናደርገው ጉዞ የመንገዱ መበላሸት፣ የአሽከርካሪያችን ግዴለሽ አነዳድ (መንገድ አለመምረጥ) እና ተያያዥ ጉዳዮች ጉዟችንን ፈታኝ አድርጎብናል።
በእርግጥ አሁን ዕድሜ ጠገቡ አሽከርካሪያችን ፍጥነት መንገድ ላይ ያልነበረ ቅልጥፍናቸው፤ እዚህ እና እዚያ እንደ ገበጣ መጫወቻ በተቦረቦረ መንገድ ላይ እንደ እምቦሳ ሲፈነጩበት ለተመለከተ ሌላ አሽከርካሪ ሞጆ ላይ የተቀየረልን እንጂ እኛ ቅድም በፍጥነት መንገድ ላይ ሲያዘግሙ የነበሩት ናቸው ብሎ መቀበል ይከብደዋል።
በዋና ጋባዣችን እና ጉዞው አዘጋጅ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ንብረት የሆነው ኮስተር መኪና ከሞጆ ለምሳ ወደምንቆምበት እና በሐዋሳ መንገድ አካፋይ ርቀት ላይ ወደ ምትገኘው ዝዋይ (ባቱ) ከተማ እየሰገረ ነው። ቀድሞ የነበረው ሙቀት ወደ ምድር ጉያ እየተምዘገዘግን እስኪመስለን ድረስ ኪሎሜትር በጨመርን ቁጥር አብሮ ይጨምራል።
ከሞጆ ከወጣን ከደቂቃዎች በኋላ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በኃይል ማመንጫዋ በሚያውቃት ቆቃ ከተማ ደርሰናል። ቆቃ ከተማ የቆቃ ሐይቅን ተንተርሳ የተመሠረተች ከፊል አቧራ ከፊል እምቦጭ የሆነች ከተማ ነች። መሠረተ ልማት የረሳት የምትመስለው ቆቃ፣ ዘመን አመጣሹ እና ወራሪው እምቦጭ ሐይቋን ሊቀማት እየታገላት በሞት ሽረት ትግል ውስጥ እንዳለች ታስታውቃለች። እጅግ ለዓይን በሚከብድ ደረጃ መጨረሻው የማይታይ የእምቦጭ አረም ሐይቁን ወሮታል።
እጅግ ስጋት የሚሆነው ደግሞ ኢትዮጵያ ከቆቃ ሐይቅ 43 ነጥብ 2 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘቷ ነው። 180 ስኩዌር ኪሎሜትር የሚሸፍነው ቆቃ ሐይቅ፣ በየዓመቱ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በሚበጀት በጀት እምቦጩን የመንቀል ሥራ እንደሚሠራ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። ይሁን እንጂ ሥራው የይምሰል ነው እንጂ ስር ነቀል እና ዘላቂ አይደለም። ይህም ባለመሠራቱ አረሙን ለመቆጣጠር በሚከብድበት ደረጃ ላይ እንደሚደርስ መገመት አያዳግትም።
ጭራሽ የእምቦጭ አረም ቆቃ ከተማ ውስጥ በመንገድ ዳርና ዳር ሰሞኑን ዘንቦ በተቋተ ውሃ ውስጥ መብቀሉን ሳይ የእምቦጩን ስር መስደድ መረዳት ችያለሁ። ወደ ቆቃ ከተማ ገብተን፤ ከተማዋን አቋርጠን እስክንወጣ ድረስ ከዋናው ሐይቅ በእንቦጭ መወረር ይልቅ መንገድ ግራና ቀኝ የበቀሉትን እምቦጭ አረም በማየት ተደምመናል።
ቆቃን ጨርሰን ወደ ፊት እየተምዘገዘግን ነው። እንኳን ዓይን እያየ እና ጆሮ እየሰማ ቀርቶ አፍንጫውን በሚገባ ለሚጠቀም ሰው የሽንኩርት፣ ቲማቲምና ድንች ሽታዎችን ለሚለይ ተጓዥ መቂ ከተማ መድረሱን ሳያይ መናገር ይችላል። እነዚህ የጓሮ አትክልቶች ለመቂ ከተማ እና ነዋሪዎች ሲመገቧቸው ምግብ፣ ለገበያ ሲያቀርቧቸው ገቢ፣ ሽታቸው ደግሞ እጅግ ማራኪ ሽቷቸው ነው።
ጉዞው ወደ ሥራ ነው እንጂ ኹላችንም አዲስ አበባ ሰማይ የነካ ዋጋ ያላቸውን አስቤዛዎች እዚህ ገዝተን ወደ ቤት ብንወስድ ፍላጎታችን ነበር። ብቻ ግን ለመልስ ጉዟችን እንዲጠብቁን አደራ ብለን ወደ ፊት ተስፈነጠርን። ከመስቀል አደባባይ፣ ፈጣን መንገድ፣ ሞጆ የነበረው የጋዜጠኞች የሞቀ ጭዋታ እየደበዘዘ መጥቶ ኹሉም በየራሱ ሐሳብ ተመስጧል። ምክንያቱ ደግሞ፣ የኹሉም ለማለት ባይቻልም የአብዛኞቻችን፣ የተፈጥሮ ጥያቄ ነው፤ ረሀብ።
ተገኙ በተባልነበት ሰዓት ባንገኝም ነገር ግን የጉዞ ስንቃችንን ገና ከአዲስ አበባ አልጫንን ኖሮ የመንገዱ እና የአካባቢው ሙቀት ተደምሮ ሆዳችን ምግብ ጥያቄውን አቅርቦብናል። የጉዞው አስተናባሪ ከአሽከርካሪው ጋር በመመካከር ለምሳ የምንቆመው ዝዋይ ከተማ እንደሆነ ተነግሮናል። ቶሎ ለመድረስና ምግብ ጋር ለመገናኘት ካለን ጉጉት ነው መሰለኝ ከመቂ ዝዋይ ያለው መንገድ የዓለሙ ረጅም መንገድ ሆኖብናል። ሙቀት አለ፣ የምግብ ጥያቄ አለ፣ መንገዱ እጅግ ምቹ አይደለም ብቻ ጉዞው ምን ሊመስል እንደሚችል ፍርዱን ለአንባቢ እተዋለሁ።
አሁን ቀራኒዮ የሆነብን መንገድ ተገፍቶ ዝዋይ ደርሰናል። በአንድ ምግብ ቤት ውስጥ ጋዜጠኞች ከሚመስለን ጋር በመቀመጥ ምግብ አዘን የሆዳችንን ጥያቄ እያስታገስን ነው። የገባንበት ምግብ ቤት ከዛ በረሐ እና ሐሩር መሀል በዛፎች የተከበበ በመሆኑ እጅግ ቀዝቃዛ ከገሐነብ መሐል የተገኘ ቁራጭ ገነት የሚመስል ምቹ ቦታ ነው። እውነት ለመናገር ችግኝ እና ዛፍ የመትከልን ጠቀሜታ ይህ አካባቢ በሚገባ ማስተማሪያ ነው። በእያንዳንዱ መኖሪያ እና ንግድ ቤት ደጅ አንድ ለቤቱም ለአካባቢውም ጥላ እና መሰባሰቢያ የሚሆን ዛፍ ማግኘት የተለመደ ነው።
ዝዋይን ለመጎብኘት እግረ መንገዳችንም ሰውነታችን ለማፍታታት በሚል ሰበብ ዞር ዞር ለማለት ሞክረናል። ዋነው ጉዳያችን ከመጣን አይቀር የጋዜጠኛ ደንቡን ወሬ ማነፍነፍ ላይ ትኩረት አድርገን ነበር። በተለይ ደግሞ በከተማዋ ዋና መንገድ ላይ ከፍ ብሎ ስለሚውለበለበው እና የመንግሥት ተቋማት ሳይቀር ባሸበረቁበት የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር አርማ ጉዳይ ለዘብ አድርገን ነዋሪውን በጨዋታ መሐል ጠየቅን። አንድ አይነት ምላሽ ተቀብለናል ብል ማጋነን አይሆንም። ‹‹የቀባውን ሰው አይተነዋል ግን ማንነቱን አናውቅም፣ የባንዲራው ጉዳይ ደግሞ ደፍሮ ለማውረድ የሞከረ የለም›› የሚሉ ፍራቻ ያረበበባቸው ምላሾችን በተለይም ደግሞ ለአዲስ ማለዳ ሰጥተዋል።
የመጣንበት ደኅንነቱ ያልተጠበቀ እና የፈራረሰ መንገድ እና የደረስንባት ከተማ ዝዋይ ቀጣይ ጉዟችንን ለማድረግ ድፍረት እንድናጣ አድርጎናል። ግን ግዴታ ነው፤ አዳራችን ውቢቷ ሐዋሳ፤ ሐዋሳ ቤሌማ ነው። ለሐዋሳ አዲስ ባንሆንም ከዝዋይ ምን ያህል እንደሚርቅና ምን ያህል የእንግልት ጉዞ እንደሚጠብቀን ከዝዋይ አንድ ሰው ጠየቅን 110 እስከ 120 ኪሎ ሜትር እንደሚቀረን አረዱን። በዚህ መንገድ፣ በዚህ ሙቀት ከአሁን አሁን አንዱ ከባድ መኪና መጥቶ አናታችን ላይ ይወጣብን ይሆን በሚል ስጋት 120 ኪሎሜትር መጓዝ እንደሚከብድ አውቀን ወገባችንን ጠበቅ አድርገን ወደ መኪናችን ገባን፤ ጉዞ ወደ ሐዋሳ፤ መቆም የለም።
ጉዞው እንደጠበቅነው አይደለም። ምቾት ማለት ከውስጥ ነው ሲባል አልሰማችሁም? ምንም የተለወጠ ነገር ባይኖርም፣ መንገዱ እንደዛው እንደተቦረቦረ ቢሆንም፣ አነዳዱ የሚመች ባይሆንም ቅሉ የቀደመው ጨዋታችን ተመልሷል፣ ያለንበትን ሁኔታችንን ረስተናል፤ ሳቅና ቀልዱ እንደ አዲስ ታድሷል። ምክንያቱ ደግሞ አሁን ምግብ በልተናል፣ ውሃ ይዘናል፣ የተፈጥሮ ግዴታዎቻችንን ተወጥተናል፣ ነባራዊ ሁኔታዎችን ልንጋፋበት የምንችል አቅም ላይ ነና። ከቀኑ 10 ሰዓት ከ 30 ሲል ሐዋሳ ከተማ ገባን። በድካም የዛለው ሰውነታችን የመጀመሪያው ጥያቄ ቢሆን መጠነኛ ሙቀት ባለው ሻወር ለቅለቅ ማለትን ነው።
የኹሉም መንገደኛ ግንባር ወዝ በወዝ ሆኖ ጮማ በግንባራችን የመታን እንመስላለን። ለሐዋሳ ቆይታችን የጉዞው አዘጋጅ መንግሥታዊው ድርጅት የያዘልን ሆቴል እጅግ ቅንጡ እና አስደማሚ ነው። በጋዜጠኝነትም ሆነ በሌላ የሥራ ሕይወቴ በግሌ ካየኋቸው ኢትዮጵያ ሆቴሎች ውስጥ ይህን ሆቴል የሚስተካከል ማግኘት ለእኔ ፈታኝ እንደሚሆን ገብቶኛል። በአጭር ቃል ሆቴሉን ያምራል ብዬው ባልፍ ንፉግነት ነው።
ምን አለፋችሁ! ሆቴሉ ውስጥ ስትገቡ ያችን ኹካታ እና ረብሻ ዓለም ወዲያው ከአእምሮአችሁ አውጥታችሁ ትጥላላችሁ። የአስተናጋጆች ፈገግታ እና ምቹ መስተንግዶ ያቺ በተረት የምናውቃት እንግዳ ተቀባይዋ ኢትዮጵያ በሐዋሳ በኩል እየሸሸች ሐዋሳ ላይ ኑሮ መሥርታ እዚህ ሆቴል ውስጥ የተቀመጠች ያስመስላታል። እጅግ ውብ ሆቴል ነው ያዝልቅላችሁ ብያቸዋለሁ፤ በልቤ።
በጉዞ የደከመው ሰውነታችን መንፈስን በሚያድስ ለብ ያለ ውሃ ተለቃልቀን ሐዋሳን በምሽት ለመጎብኘት ወጣን። ያቺ ድሮ እንኳን ፈልገዋት የሚመጡ እንግዶቿን ቀርቶ አቋርጠዋት የሚያልፉ መንገደኞችን ‹‹ዳኤ ቦሹ›› ብላ የምትቀበለው ሐዋሳ ፈገግታዋ ቀንሶብኛል። ገና ኹለት ሰዓት ሳይሆን የንግድ ደጆች መዘጋት ጀምረዋል፣የአዳም ዘር ወደ ማደሪያው ለመግባት ከሩጫ ባለተናነሰ እርምጃ ሲፈጥን መመልከት ግርታን ከመጫር ባለፈ ምን አዲስ ነገር ቢኖር ነው የሚል ጥያቄን ያጭራል።
ካረፍንበት ሆቴል ደጅ ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ ኮንትራት በመያዝ ወደ ምሽት ቤቶች እንዲያደርሰን ነገርነው። ለአፍታ ዞሮ ከገረመመን በኋላ ‹‹እንግዶች ናችሁ እንዴ?›› አለን እኛም ለሐዋሳ አዲስ ባንሆንም ግን እንግዶች መሆናችንን ነገርነው። ‹‹ብዙም የምሽት ቤቶች ወደ ሥራ አልተመለሱም፤ ከሆቴላችሁም ርቃችሁ ብዙ አትሒዱ። ከተማዋ እንደ ድሮ አይደለችም›› ሲል የወንድምነት ምክሩን በጣፋጭ የምላስ እጥፋት ነገረን።
እውነት ነው! ሐዋሳ በኮማድ ፖስት ስር ውላ በኮማንድ ፖስት ስር የምታድር ከተማ ናት። ከዚህ ቀደም ለሚያውቃት መደናገርን የምትፈጥር፣ ‹‹ምነው ሐዋሳ ፊት ነሳችኝ›› ቢል የማይፈረድበት ገጽታ ላይ ነው ያለችው። በእርግጥ እኛ በደረስንበት ጊዜ የሰዓት እላፊው ተነስቶ ኹሉም ባሻው ሰዓተ መንቀሳቀስ መብቱ ቢኖረውም፣ ባለፉት ጊዜያት የነበሩት እገዳዎች ድንጋጤን ፈጥሮባቸዋል።
አሁን ፒያሳ በሚባል ስፍራ ከተማዋ ዕምብርት አንድ የምሽት ቤት ተሰይመናል። ያሻንን አዘን በረንዳ ላይ ተቀምጠን አላፊ አግዳሚውን ስንቃኝ መንገዶች ደቂቃዎች በነጎዱ ቁጥር ጭርታቸው እየጠነከረ ወደ ሰው አልባነት ሲቀየሩ ለመታዘብ ቻልን። ይሁን እንጂ ያለንበት ቤት ከተወሰኑ የህንድና ቻይና ዜግነት ካላቸው ተስተናጋጆች ውጪ ሐበሾቹ እኛ ብቻ ነበርን። በዚህ ጊዜ ታዲያ የምሽት ቤቱ ባለቤት እኛ ወዳለንበት ጠረጴዛ ቀርበው ‹ምን ይጨመር› በሚል ጥያቄ ጭዋታ ጀምረው ወንበር ስበው ተቀመጡ፤ ጭዋታችንም ቀጠለ።
ገብሬ ገነሞ ይባላሉ። ለአራት ዓመታት በምሽት ክበብ የሥራ ዘርፍ ተሠማርተው ኖረዋል። በዚህ ሥራቸውም ሐዋሳ ውስጥ ቤት ሠርተው፣ የሥራ መኪና ገዝተው ይኖሩ እንደነበር አወጉኝ። ጨዋታችን ሔዶ ሔዶ አሁን ባለው የከተማዋ ጉዳይ ላይ ማጠንጠን ሲጀምር ‹‹ኮምናድ ፖስት ብለው የማይሆን አሰራር እየተጠቀሙ ይሄው ኹሉንም ሥራ አቀዘቀዙት›› የሚልና ምሬት ያዘለ ንግግራቸውን ቀጠሉ።
ለገብሬ የአራት ልጆቻቸውን ቀለብ እና ትምህርት ወጪ የሚደጉመው በዋናነት ይሔ የምሽት ክበብ ነው። የባለቤታቸው ሴቶች ፀጉር ቤት ገቢ፣ ከቤት ኪራይ አልፎ እዚህ ግባ የሚባል ትርፍ አያመጣም። ከዚህም በላይ በሳምንት ዕቁብ ይጥሉ እንደነበር ይናገራሉ። ይሁን እንጂ በከተማዋ ከተከሰተው አለመረጋጋት ጋር ተከትሎ በኮማድ ፖስት እጅ ላይ የወደቀችው ሐዋሳ የንግድ ዝውውሯ በእጅጉ ተቀዛቅዟል።
ገብሬ አሁን በየቀኑ እዚህ ግባ የማይባል ገቢ ከምሽት ክበቡ ላይ በመሰብሰብ ይሄ ቀን አልፎ የቀደመው የአዝመራ ወራት እንዲመጣ በመናፈቅ በተስፋ ይኖራሉ። ‹‹ከመዝጋት ምንም አይገኝም እንጂ መክፈታችን ምንም ጥቅም የለውም›› የሚሉት ገብሬ፣ እያንዳንዷ የማለዳ ጮራ ምን ይዛ እንደምትምጣ አይታወቅም የሚል መላምት አላቸው።
ገብሬን እንደማሳያ አነሳን እንጂ በተዘዋወርንባቸው የምሽት ቤቶች በጣት የሚቆጠር ተስተናጋጅ ብቻ ነው ማየት የቻልነው። ለሐዋሳ አዲስ ያልሆነው እኛ ደግሞ ምናልባት ከሰዓት አስቀድመን መገኘታችን ይሆን እንዲህ ብቻችንን እንድንሆን ያደረገን ብለን ጠይቀናል። ግን እውነታው ከዚህ የተለየ ነው፤ ሰዓቱ ቢገፋም የተስተናጋጅ ቁጥሩ ከዚህ ከፍ የሚልበት አዝማሚያ እንደሌለ ህያው ምስክሮች ሆነናል።
በሐዋሳ ከተማ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ሲል የሚንቀሳቀስ ህያው ማግኘት እጅጉ ከባድ ሥራ ሆኗል። በእርግጥ በአዲስ አበባ በፎቅ ጫካ ታጥሮ ለሚኖር ሰው ወደ ሐዋሳ ጎራ ብሎ ከተፈጥሮ ጋር እያወሩ መንፈስን ለማደስ ኹነኛ ከተማ ናት። በተለይ ደግም በምሽት እጅግ ቀልብን የሚገዛ ውበት አላት።
ከአረፍኩበት ሆቴል በረንዳ ላይ ሆኜ ተፈጥሮን በማደንቅበት አንድ ሐዋሳ ምሽት መታዘብ የቻልኩት ነገር ረጅም መንገድ መለስተኛ ጭነት መኪኖች (አይሱዙ) ብቻ የሚከንፉባቸው በሐዋሳ መንገዶች ብቻ ነው። ከዛ ባለፈ ግን በዋናነት የወታደራዊ ጭነት መኪኖች (ሩሲያ ሥሪት ኦራል) መኪኖች ናቸው የሐዋሳን ከተማ መንገዶች በቀን እና በሌሊት የሚፈነጩባቸው።
ሐዋሳ ከተማን ጎብኝቶ ሰው የፍቅር ሀይቅን ካልጎበኘ ጉዞው ምሉዕ አይሆንም ይላሉ፤ አስተያየት ሰጪዎች። ብዙ የተጻፈለት፣ የብዙ አገርኛ ፊልሞች መቼት የሆነ፣ እውነተኛ ፍቅር ታሪክ የተተረከበት የሐዋሳ የፍቅር ሐይቅ አሁንም ውበቱ አልረገፈም። ብዙዎችን በፍቅር አስተሳስሮ በትዳር እያኖረ ነው፤ ለዕልፍ ትውልድ ደግሞ ለመቀበል ደከመኝን የማያውቅ ፍቅርን የሚተነፍስ ሰላማዊ ሐይቅ።
ይሁን እንጂ የፍቅር ሐይቅ ለምን ይቅርብኝ ያለ ይመስል የእምቦጭ አረም ተጠቂም ነው። እጅግ ልብን በሚሰብር ሁኔታ ወደ ሐይቁ ደርሰው ነፋሻማ እንቅስቃሴ በሚያደርጉበት ቀኝ አቅጣጫ የነበረው የውሃ ክፍል ሙሉ በሙሉ በእምቦጭ በመወረሩ ደርቋል። በምስል በምናስቀርበት ወቅትም አንዲት አነስተኛ ጀልባ በስፍራው መውጣት አቅቷት እዛው የተተወችበትን ሁኔታም ታዝበናል።
ሐዋሳ ጉዟችን በዋናነት ኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ የደቡብ ዲስትሪክት ከሐዋሳ ከተማ በ20 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የመድኃኒት መስወገጃ ገንብቶ ማስመረቁን ለማየት እና ዜና ሽፋን ለመስጠት ነበር። የመድኃኒት ማስወገጃው በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ከሚገነቡት አንዱ ሲሆን፣ በአንድ ጊዜ እስከ 500 ኪሎ ግራም የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድኃኒቶችን የማስወገድ አቅም አለው። በ51 ሚሊዮን ብር ወጪ በ5 ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው ማስወገጃ ማዕከሉ፣ ከአካባቢ ብክለት እጅግ በጸዳ መልኩ ሥራውን የሚያከናውን ማዕከል ነው።
ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ እንደ አገር ወደ ባህር ማዶ በብዙ ውጭ ምንዛሬ ልካ የምታስወግዳቸው መድኃኒቶችን የሚያስቀር ነው።
በሐዋሳ የነበረን አጭር ቆይታ እየተገባደደ ነው። ‹ሰላምሽ ይብዛ፣ መጥተን አንጣሽ› ብለን ለመሰነባበት ግን የአንድ አዳር እድሜ ይቀረናል። ድካም እና ሙቀት ተደማምሮ መላወስ አቅቶናል። ስለዚህ በሆቴላችን ክፍል ውስጥ ለመቆየት ተገድጃለሁ። ምክንያቱ ደግሞ ለቀጣዩ ቀን የመልስ ጉዞ አቅም ማሰባሰብ ይኖርብኛል፤ አመጣጣችንን የምናውቀው እኛው ነን።
ነግቷል። አሁን የመልስ ጉዞ የምናደርግበት ቀን ነው። በጉዞ አስተባባሪያችን እንደተነገረን ከሆነ መገኘት ያለብን ከረፋዱ ሦስት ሰዓት ነው። ስለዚህ ሐዋሳን በጠዋት ተነስተን ልብን የሚሰርቀውን የፀሐይ አወጣጥ እየታዘብን ከልባችን ሐዋሳን ተሰናበትናት። መቼ እንደምንመለስ አናውቅም፤ ብቻ ግን ሰላምሽ ይብዛ፣ ልጆችሽ ይርቡ፣ ጥንዶችሽ ይጋቡ ብለን መርቀናታል። እየሳቅሽ ውለሽ እየተፍለቀለቅሽ እደሪ፤ ሐዋሳ ቤሌማ፤ ቸር ይግጠመን።

ቅጽ 2 ቁጥር 59 ታኅሣሥ 11 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here