አዲስ አበባ በእንግዳ ዐይን

0
690

በአዲስ አበባ ለጥቂት ወራት የቆዩት ጌታውን መሳይ፣ ለእንግዳ ጎልተው የሚታዩ ችግሮችን ነቅሰው አስቀምጠዋል። ለዚህም በከተማ ልማት ላይ ከሚንቀሳቀሰው መንግሥት ጀምሮ የከተማዋ ነዋሪ የሚጠበቅበት እርምጃ ስለመኖሩም ጠቁመዋል። የመንገድ ሥራ፣ የሰፈሮች ገጽታ፣ የህንጻዎችን መልክ፣ አሰፋፈሩንም ጭምር በተመለከተ ያሉ መረጃዎችን አጣቅሰው፤ እንደ ከተማ አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ እንደ አገር በታደለችው ሀብት፣ በኃላፊነት ተወስዶ ሊመጣ የሚገባ መሻሻል አለ ሲሉ አቅርበዋል።

አዲስ አበባን የማውቃት ባለፉት 10 ወራት ብቻ ነው። ከልጅነቴ ስለ አዲስ አበባ እየሰማኋቸው ካደግኩት ነገሮች ግን ብዙዎቹ እውነት ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። ለምሳሌ የንጽህና ጉድለት። አንባብያን ከዚህ ቀጥሎ ስለ አዲስ አበባ በማቀርበው አስተያየት በአንዳንዱ ቅር እንዳይሰኙ ከወዲሁ እማጸናቸዋለሁ። የማቀርበው ሐሳብ አንዳንዱ በጥናት የተረጋገጠ፣ ሌላው ደግሞ በትዝብት ወይ ምልከታ ላይ የተመሰረተ መሆኑን እንዲረዱልኝ ጭምር እጠይቃለሁ። ተደርጐ እያለ ያለ በቂ መረጃ እንዳልተደረገ ያለፍኩት ግድፈት ካለ ደግሞ ለመታረም ዝግጁ ነኝ።
ዐይን ያፈጠጠ ድህነትና የገቢ ልዩነት
ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ከኢትዮጵያ ዓመታዊ ጥቅል አገራዊ ምርት 50 በመቶ ወይም ግማሹ አዲስ አበባ ነው ያለው። ይህ ማለት 80 ቢሊዮን ዶላር ከሚደርሰው የኢትዮጵያ ጥቅል ዓመታዊ ገቢ 40 ቢሊዮን ዶላሩ አዲስ አበባ ውስጥ የሚመነጭ ነው። ይህ የአዲስ አበባ ገቢ በአብዛኛው የአገልግሎት ዘርፍ (ከ60 በመቶ በላይ) ማለት ንግድ፣ ትራንስፖርት፣ ሆቴሎችና የፋይናንስ ተቋማት ያጠቃልላል። ቀጥሎ ግንባታና ማኑፋክቸሪንግ (ከ30 በመቶ በላይ) ይይዛል። በዚህ የመንግሥት ድርሻ ቢኖርበትም፣ የግሉ ዘርፍ ሚና ደግሞ ሀብቱን በመቆጣጠር የሚናቅ አይደለም።
ግን አብዛኛው የከተማዋ ነዋሪ፣ ከተማው ውስጥ ከሚፈጠረው ሀብት ምን ያህል ተጠቃሚ ነው? የከተማዋ የፍጹም ድህነት መጠን (በቀን ከ30 ብር በታች ገቢ ያለው ሕዝብ) ካየን 22 በመቶ ይደርሳል። ከዛ ሻል የሚለው በቀን ወደ 60 ብር የሚያገኘው ደግሞ 38 በመቶ የሚሆን ሠራተኛ ነው። በጥናቶች መሰረት አዲስ አበባ ውስጥ እያንዳንዱ ሠራተኛ የሚደግፋቸው 3 የቤተሰብ አባላት አሉት። ከሠራተኛ ሕዝብ ደግሞ 30 በመቶ አስተማማኝ ገቢ በሌለው መደበኛ ባልሆነ ሥራ የሚተዳደር ነው። መንግስት መሥርያ ቤት በሥራ ተሰማርቶ የምናገኘው ከ5 በመቶ አያልፍም።
ታድያ በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ዓመታዊ ሀብት ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ የወሰዱትና ያከማቹት እነማን ይሆኑ? እነዚህ ጥቂቶቹ ባለ ሀብቶች መሆናቸው ነው። ይህ ሰፊ የገቢ ልዩነት፣ ከተማዋ ውስጥ ለሚታየው ዘግናኝ ድህነት ዋናው ምክንያት ነው። ሰፊ የገቢ ልዩነት ደግሞ ለድሃው ብቻ ሳይሆን ለሃብታሙም ደኅንነት አይሰጥም። ስለዚህ የሰውን ትጋት የሚመጥን የሃብት ክፍፍል ለሁሉም አስፈላጊ ነው።
ፍትኀዊ የሀብት ክፍፍሉ ጉዳይ ረጅም ጉዞና ከባድ ሥራ የሚጠይቅ ሆኖ፣ እነዚህ ባለሀብቶች ግን የአዲስ አበባ ከተማና የነዋሪዋን ችግሮች በመቅረፍ ድርሻቸውን እንዲወጡ ከዚህ በፊት ምን ዓይነት እገዛ አድርገዋል? የመንግሥት ፖሊሲስ ምን ዓይነት ግብዣና ማበረታቻ ያደርግላቸዋል? ባለሀብቶቹ ለራሳቸው ሥራ መዋዕለ ነዋይ ሲያፈሱ፣ ጐን ለጐን ለድሀው ኅብረተሰብ የቁጠባ ቤቶች፣ መንገድ፣ ክሊኒክ፣ ትምህርት ቤት፣ ውሃ፣ የስፖርት ስፍራ፣ ገበያ ወዘተ ዘርግተው ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተደርጓል ወይ? እነርሱስ ተነሳሽነት አሳይተዋል ወይ?
ከተማ ወይስ የ“ትልቅ የህንጻዎች” ክምችት?
አዲስ አበባ ባለፉት ቅርብ ዓመታት [እንደሚመስለኝ ባለፉት 20 ወይ 25 ዓመት አካባቢ] ብዙ ወጪ እንደወጣላት ታስታውቃለች። ነገር ግን በእነዚህ ዓመታት ከሰባና ሰማንያ በመቶ በላይ ቤቶቿ ሰው ሊኖርባቸው የማይገባ ፈራሽ ጭቃና ቆርቆሮ መሆናቸው፣ የዛሬ ኻያ እና ሠላሳ ዓመት፣ ከዛም በላይ ከተማዋ እንዴት ነበረች የሚል ጥያቄ ያስነሳል። በዋና መንገዶች የተሠሩ ትላልቅ ፎቆች ከበስተጀርባቸው ያለውን አንገብጋቢ ድህነት ለጊዜው መደበቅያ ሆነዋል። ሀብትና አስከፊ ድህነት ጐን ለጐን እየተያዩ እንዲኖሩ የተፈለገ ይመስላል። በአጠቃላይም ሠላሳ በመቶ የአዲስ አበባ ነዋሪ በስምንት በመቶ የከተማዋ የመሬት ስፋት ነው የሚኖረው።
አዲስ አበባ የአፍሪካ ዋና ከተማ (የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ) የኢትዮጵያ የመንግሥት፣ የፋይናንስ፣ የንግድ፣ የዲፕሎማሲ ማእከል መሆኗ የታወቀ ነው። ግን እንዲያው ከተማ ለሚለው ስም በሚገባ ትመጥናለች ወይ?
አዲስ አበባ በቅርብ ጊዜ የተሠሩና በመሠራት ላይ ያሉ ትልልቅና ግሩም ህንጻዎች አሏት። ነገር ግን እነዚህ ህንጻዎችና ከመሠረተ ልማቱ ጋር ተደምረው የከተማ ሕይወት ፈጥረዋል ወይ? በሞያዊ ቋንቋ ብናስቀምጠው ጥሩ የህንጻ ንድፍ ተሠርቶ፣ የተቀናጀና ውብ የከተማ ዲዛይን ከሌለ ከጥቅሙ ጉዳቱና ጭንቀቱ አይበዛም ወይ? እነዚህ ኹለቱ ማለት የህንጻ ንድፍ እና የከተማ ዲዛይን ደግሞ በከተማ ፕላኒንግ (የመሬትና ሌሎች ሀብቶች ወሳኝ ክፍፍልና የመሰረተ ልማት ዝርጋታ) እንዲመሩ ከተገባቸው፣ ቅንጅቱ ለምንድነው የማይታየው? ይህ ቅንጅት አልያም የቅንጅት ጉድለት ባለሙያውንም የፖለቲካ ሹመኛውንም ይመለከታል። ምክንያቱም በአንድ በኩል ሞያዊና ቴክኒካዊ ሥራ ይጠይቃል፤ በሌላ በኩል ደግሞ መሬትና ሌሎች ሀብቶች የማከፋፈል ጉዳይ ፖሊሲ ነክ ስለሆነ ከፖለቲካ ጋር የተቆራኘ ነው።
አዲስ አበባ በተቈረቈረችበት ጊዜ በፕላን ያልተጀመረች የወታደሮችና የደጃዝማቾች ሰፈር ስለነበረች መልካም መሰረት አለመጣሉ አሁን ላለው የውዥንብር ባህል አንድ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ግን የዛሬ 133 ዓመት ስትቈረቆርና ንግሥት ጣይቱ ሲሠይሟት የነበረችው 15ሺሕ ነዋሪ የነበራት አዲስ አበባ፣ በቀጣይ ዓመታት ከሰፋችው አዲስ አበባ አንጻር በጣም ትንሿ ነበረች። ስፋቷ ባለፉት ስድሳ ሰባ ዓመታት የጨመረውና የተገነባ ነው የሚሆነው። በተለይ ደግሞ ባለፉት 25 ዓመታት። ስለዚህ ብዙ የተጣመመውና የተዛባው የከተማ ልማቱ ባለፉት የስድሳ ሰባ ዓመታት ጊዜ ያጋጠመ ከሆነ፣ ለዛውም ከተማይቱ አሁን ከ60 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያለው ሁለገብ የምህንድስና ትምህርት የሚሰጥ ተቋም ባላት ጊዜ፣ ይህ ዓይነት ሁኔታ መፈጠሩ አግራሞት የሚጭር ነው።
የመንገዶች ጥበት
ከተማን ከተማ ከሚያሰኙ ነጥቦች መካከል ዋነኛው የመንገድ መረብ፣ ከዛም አልፎ ክፍት ሕዝባዊ ስፍራ፣ በንድፍ የተዋቀረ አረንጓዴ ቦታ ነው።እነዚህ አዲስ አበባ ውስጥ እንደጐደሉና በአብዛኛው አለመኖራቸው ምን ያህል ሕዝቡን ከከተማው ማግኘት ያለበትን ደስታና አገልግሎት እንዳሳጣው በከተማው ካለው ዕለታዊ የትራፊክ መጨናነቅና ጭንቀት በቀላሉ ማስተዋል ይቻላል። ደስታ የራቀው ሕይወት ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ማሰናከሉ ላይ ለሌሎች ዓይነት መልካም ያልሆኑ የአስተሳሰብ ተጽዕኖዎችና ሥነ ልቦናዊ አለመረጋጋት የተጋለጠ ነው።
ይቅር ድሃው፣ ባላቸው መሬት ላይ ተጨማሪ መሬት ለማካበት የሚቃጡና የሚዘርፉም ቢሆኑ፣ ከአካባቢያቸው ማግኘት ያለባቸውን ደስታና አገልግሎት እያጡ ለመሆናቸው በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። በተባበሩት መንግሥታት የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት፣ በአንድ ከተማ ውስጥ የመንገድ ዝርጋታ በበዛ ቁጥር የከተማዋ ተጨማሪ ሕዝብ የመያዝ አቅም ያድጋል። የሕዝቧ ጤናና የማምረት አቅም ይጨምራል፣በዚህም ብልጽግናዋ ይረጋገጣል። አዲስ አበባ ውስጥ በዋናነት ከከተማዋ ጠመዝማዛና ጠባብ መንገዶች የተነሳ መሠረተ ልማት በሚገባ ለመዘርጋት ብሎም ጸጥታ ለመጠበቅ ጭንቅ፣ ይህን ለማሻሻል የሚጠይቀው ገንዘብ ጥቂት የማይባል መሆኑ፣ ልማቱ አዳጋችና ውስብስብ እንደሚሆን ያደርገዋል።
በአንድ ከተማ በቂ የመንገድ ስፋት፣ በቅርብ ርቀት የተዘረጉ እርስ በእርሳቸው ከሌሎች መንገዶች የሚገናኙ ትይዩ ጎዳናዎች ለተሳለጠ የከተማ እንቅስቃሴና ዘመናዊ ኑሮ የግድ አስፈላጊ ናቸው። ይህ በጽሑፍ ሲባል በጣም ቀላል፣ መሬት ላይ ሲወርድ ግን ከባድ እንደሆነ የታወቀ ነው። በአዲስ አበባ ነባራዊ ሁኔታ ደግሞ ከአብዮት ያልተናነሰ ትግል የሚጠይቅ ነው። እርግጥ በአንዳንድ የከተማዋ ቦታዎች በቀላሉ ሊሠራ የሚቻልበት ሁኔታ እንዳለ ግልጽ ነው።
በአዲስ አበባ ውስጥ ከዋና ዋና መንገዶች በቀር፣ ለምሳሌ ከመስቀል አደባባይ ወደ ቦሌ ኤርፖርት፣ ከመስቀል አደባባይ ወደ አያትና ጦር ሀይሎች፣ ከስታድየም ወደ ፒያሳ፣ ከመስቀል አደባባይ ወደ ደብረዘይት እያሉ ከሚሔዱ ትልልቅ የመንገድ ኮሪዶሮችና ቀለበት መንገዶች በስተቀር፤ ሌላው አብዛኛው መንገድ ጠባብና ጠመዝማዛ ነው። ይህም ለዕለታዊ እንቅስቃሴና ሥራ አስቸጋሪና ምን ያህል ጊዜ አባካኝ እንደሆነ መገመት አያስቸግርም።
አስቀድሞ ተመሥርተው የነበሩ ሰፈሮችስ ይሁን፣ ግን በአዲስ መልስ የተዋቀሩት አዳዲስ ሰፈሮችስ ለምንድነው ተገቢ የመንገድ መረብ የሌላቸው? ለምሳሌ ሲኤምሲ ፊት ለፊትና ጐን ያሉት ሰፈሮች፣ የለቡና የጀሞ አዳዲስ ሰፈሮች ለምንድነው በሕንጻ ብቻ የሞሉት? መንገዳቸውም ቢሆኑ ጠባብ፡ የተራራቁና ቀጥተኛ መስመር የማይከተሉ ሆነው የተሠሩት ለምንድነው?
መሀል ከተማ የሚባሉትና ትልልቅ ፎቆች የተሠሩባቸው እንደ ቦሌ ያሉ ሰፈሮችም ተመሳሳይ ችግር አለባቸው። ለምሳሌ ከኤድና ሞል ወደ ፍሬንድሺፕ ሆቴል የሚወስደው መንገድ ብዙ የታወቁ ሆቴሎች የያዘ ጐዳና ሆኖ፣ የመንገዱ ድንበር የማይታወቅ፣ ቅርጹ ጠመዝማዛ፣ ህንጻዎቹ ወጣ ገባ ስለሆኑ አእምሮን አስጨንቈ መንፈስን የሚያውክ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። በጐናቸው ያሉት ጐዳናዎችም ለምን በዛን ያህል ጥበትና አለመስተካከል እንደተሠሩ ግልጽ አይደለም።
በዚህ ገጽ ቦታ እንዳናጠብ እንጂ በጉዳዩ ለአብነት የሚሆኑን ብዙ ጐዳናዎችና ሰፈሮች ማቅረብ ይቻላል። ከመገናኛ እስከ ጎላጉል ያለውን 1.5 ኪሎሚተር የሚሆን መንገድ ብቻ ብናይ፣ ግራና ቀኝ ከአንድ ወይም ኹለት መንገዶች በቀር በህንጻዎች ተጠቅጥቋል። ከተማዋ ውስጥ ህንጻ መንገድ ላይ ገብቶ፣ መንገዱ ተጣቦና አስቸግሮ ማየት የተለመደ ነው። አንዳንድ ቦታዎችም የከተማን መንገድ በግቢያቸው በጠቀለሉ ባለቤቶች “መንገድ ጠፋ” ሲባልም ይሰማል።
በመልሶ ማልማት ዓላማ፣ በጠባብ ጐዳናዎች የጭቃ ቤቶችን አፍርሶ ትልልቅ ፎቆች ሲሠሩ፤ ጠባብ መንገዶቹ በነበሩበት ስፋት ይቀጥላሉ። በተሠሩት ረጃጅም ፎቆች የሚሰፍረው አዲስ ነዋሪ ብዛቱ፣ የሚመጡ መኪኖች ቁጥር፣ የፍሳሹና ደረቅ ቈሻሻው መጠኑ፣ የአደጋ ተጋላጭነት ወዘተ እንዴት ነው በጠባብ መንገዶቹ እንዲስተናገድ የታሰበው? ትንንሽ ቤቶች ፈርሰው ትልልቅ ህንጻዎች ሲተኳቸው መቼም አስቀድሞ ከነበረው የበለጠ ለመኪና መንገድ በቂ ስፋት፣ ለእግረኛ መንገድ ቦታ ተሰጥቶ፣ አዲሶቹ ህንጻዎች ገባ ብለው መሠራት እንዳለባቸው የታወቀ ይመስለኛል። ለዚህ ሁሉ ደግሞ የመሬት እጥረት ያለ አይመስለኝም። የአዲስ አበባ አስተዳደር እንዳጠናው የከተማዋ 46 በመቶ መሬት ጥቅም ላይ ያልዋለ ባዶ ወይ በጅምር የቀረ መሬት ነው። ታድያ ለምን አስፍቶ መጠቀም አልተቻለም?
የበጀት እጥረት ከሆነ፣ የመንገድ አጣዳፊነት ታይቶ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የአዲስ አበባ ወንዞችን በማጽዳትና በማስዋብ የከተማዋን መልክ ለመለወጥ ካላቸው ድንቅ እቅድ ተያይዞ፣ የመንገዶች መቅደድ የፕሮግራም አካል ሆኖ ቢነደፍ ጠቃሚ ይመስለኛል። የተፋሰስ ፕሮጀክቱ በጀት እስከ 30 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ነው ተብሏል። ከዚህ ገንዘብ ጥቂቱም ቢሆን ትንፋሽ ለነሳው የመንገዶች ጥበትና መሳሳት ለመፍታት ቢውል ምን አለበት? ለምሳሌ ሕዝብ በሥራና በኑሮ በብዛት የሚገኝባቸውን ስፍራዎች እየለዩ በቶሎ ሰፋፊ ውስጥ ለውስጥ መንገዶች [የጠጠርም ይሁን] ቢቀደዱና የተቀላጠፈ የትራንስፖርት ሁኔታ ቢፈጠር።
የትራፊክ መጨናነቅ
አዲስ አበባ ያለው የትራፊክ መጨናነቅ በሕዝብ ብዛትና በመኪና ብዛት የተነሳ የሚመስለው ሰው ሊኖር ይችላል። ስለዚህ የሕዝብ መጠን እድገት ቢገታ፣ መኪኖች ማስገባትም ቢከለከል መፍትሔ የሚገኝ ሊመስለው ይችላል። ስለ መኪኖች ከተናገርን፣ በቁጥር ወደ 600 ሺሕ የተጠጉት የከተማዋ መኪኖች ከከተማዋ ስፋት አንጻር ብዙ የሚባሉ አይደሉም። መኪኖቹ የተጨናነቁበት ዋናው ምክንያት የመንገድ እጥረት ነው። የአዲስ አበባ የመንገዶች ሽፋን ከጠቅላላው የከተማዋ ስፋት ገና 13 በመቶ ነው። ይህም ከዓለም ትልልቅ ከተሞች ሲታይ ግማሽ ሲሆን በከተሞች የመንገድ ሽፋን አመዳደብ ደግሞ ዝቅተኛ የሚባለው ነው።
በዋናነት በመንገዶች እጥረት የተነሳ በየቀኑ ትራፊኩ ተጨናንቆ ይታያል። በዚህ መጨናነቅ መሀል ሕመምተኛ የጫኑ አምቡላንሶች ጩኸታቸውን ሲያሰሙ ሕሊናን የሚወጋ ነው።
በየቀኑ ባለመኪኖች ወይም ሕዝባዊ ትራንስፖርት ተጠቃሚዎች በትራፊክ መጨናነቅ የሚያጠፉት ጊዜ በዋጋ ቢተመንስ ምን ያህል ትልቅ ሃብት ከተማዋና ሕዝቧ እያጡ ይሆን? ለምሳሌ በትንሹ እያንዳንዱ ሰው ባለ መኪናም ይሁን፣ በሕዝብ ትራንስፖርት የሚመላለስ፣ መንገድ ላይ በቀን በትራፊክ መጨናነቅ ከሚገባ በላይ ተጨማሪ ኹለት ሰዓት እያጠፋ ከሆነ፣ የሚሊዮኖች የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ብክነት ስንት ሰዓታት ሊሆን ነው? ይሄን ክቡር የሥራ ጊዜ በሰዓት፣ ለምሳሌ በሰዓት 10 ብር ብለን ብናሰላ እንኳ፣ በዛ ሁሉ ሕዝብ ተባዝቶ ሲሰላ፣ በቀን ስንት ሚሊዮን ብር ሊሆን ነው? በዓመትስ? የመኪኖቹ ወጪስ ለምሳሌ የነዳጅ ፍጆታው፣ የመኪኖች በከባድ ማርሽ መሄድ በጤናቸው ላይ ያለው ተጽእኖና ኪሳራ፣ ከሁሉ ደግሞ በመንገድ መጨናነቅ ምክንያት የሚከሰተው አደጋ ወዘተ እያልን ብናሰላው ምን ያህል ከባድ ኪሳራና የሃብት ብክነት በከተማዋ እየደረሰ እንዳለ በግርድፉ መገመት ይቻላል። ምናልባት አንድ ሰው አዲስ አበባ ውስጥ ዕድሜው 60 ዓመት ከደረሰ፡ የኖረው ግን ከ50 ዓመት ላይበልጥ ይችላል።
ጽዳትን በሚመለከት
አዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ቆሻሻ ይታያል፤ የተከማቸ ድንጋይ፣ ፍርስራሽ፣ ሳር ወዘተ። ባንኮችና ኤምባሲዎች ደጃፍ እንኳ የተጣለና የተረሳ የቆሻሻ ወይም ፍርስራሽ ክምችት ይስተዋላል። በየመንገዱ በተለይ በየእግረኛ መንገዱ የተከማቹ የአዲስ ግንባታ ፍርስራሽ ለምንድነው በቶሎና በግንባታ ሕግ መሰረት የማይነሱት? ለወራት ወይም ከዛም በላይ የቆየ ፍርስራሽና ቆሻሻ ካልጸዳስ ማዛጋጃ ቤቱ ለምንድነው ተገቢ ቅጣት ወስኖ የገቢ ምንጭ የማያረገው? ማዘጋጃ ሕጉ የሚፈቅደውን መቀጮ ባለቤቶቹን እያስከፈለ ለጽዳት፣ ለሥራ ፈጠራና ሌሎች ልማቶች የገቢ ምንጭ ይሆኗል። ይህ በወረዳዎች ደረጃም ሊሠራ የሚችል ይመስለኛል።
የሰው ባህሪ ለውጥ ከተገኘ፣ እያንዳንዱ ሰው በደጃፉ ያለውን ቆሻሻም ይሁን ሌላ በኀላፊነት በማንሳት ከተማውን የማጽዳትና የመጠበቅ አቅሙ በእጁ እንዳለ ያረጋግጣል። ደጃፉን ያላጸዳ እንዴት ትልቅ ነገር ከመንግሥት ይጠብቃል? የ50 ሚሊዮን ብር ህንጻ ገንብቶ፣ ደጃፉ ላይ የቀረውን አፈር ለማንሳት ግድ የማይለው ሰው ምን ሊባል ይችላል። ብዙ ሰው፣ አነሰም በዛ መንግሥት እንዲያደርግለት የሚፈልግ ይመስላል። በደጃፉ ለሚጥለውም ቆሻሻ ጭምር።
የአርከበ ሱቆችና ሌሎች የመንገድ ዳር ገጽታዎች
እነዚህ በመንገድ ዳር የሚገኙ ለሺዎች የሥራ ዕድል የፈጠሩ በቆርቆሮ ወይም ኮንቴይነር የተሠሩ የሰፈር ሱቆች ብዙ የኑሮ ችግር እየቀረፉ እንዳሉ አስተውላለሁ። የከተማ አንዱ ዘለቄታዊ ባህሪ ለነዋሪዎች የሥራ ዕድል መፍጠር ነው። በእነዚህ ሱቆች የሚሠሩ ታታሪ ዜጎችና ዕድሉን የፈጠረ አስተዳደርም ሊመሰገኑ ይገባል። ነገር ግን እነዚህ ሱቆች የከተማዋን ምስል ደግሞ አበላሽተዋል። እንደሚመስለኝ መጀመሪያውኑ ለሕዝቡ የሥራ ገበታ ለመፍጠር ጊዜያዊ መፍትሄ ተብለው የተሠሩ ናቸው። አሁን ግን ለምንድነው መስተዳድሩ እንደ ቀጣይ እርምጃ ከመንገድ ገባ ባሉ ስፍራዎችም ይሁን የቀበሌ/ወረዳ ቦታ አደራጅቶ በአንድ ግቢ ውስጥ በትንንሽም ይሁን እንደ የገበያ ማእከል የሚያገለግል ቦታ የማይሸነሽንላቸው? አቅም እያካበቱ ሲሔዱ ደግሞ ልክ እንደ መርካቶ በአክስዮን መልክ ወደ ትልልቅ ገበያ ማእከላት ሊቀየሩ ይችላሉ።
ስለ መንገድ ዳር ገጽታ ካነሳን፣ የኤሌክትሪክ ፖሎችና ኬብሎች የትም ተንጠልጥሎ ማየት፣ የቆርቆሮ ገጽታ በመንገድ ዳር ተጋድሞ ማለፍ የተለመደ ነገር ይመስላል። የኤሌክትሪክ ፖሎች ተዘርግተውና ቆመው መብራት ግን የማይበራውስ ለምንድነው? አብዛኛው የአዲስ አበባ ጐዳና በመብራት እንጨት አለመተከል ሳይሆን ብርሃን ሰጪ ብርሃን ባለመስጠታቸው ምክንያት ጨልሞ ነው የሚያመሸው። ይህ ለምንድነው? እነዚህ ፖሎች ምን ሊያደርጉ ነው የቈሙት?
ለምንድነው አብዛኛው እግረኛ መንገድስ ክዳን በሌላቸው ጉድጓዶች የሞላው? የዛፎች፣ የአረንጓዴ መስመሮች፣ የኤሌክትሪክ ፖሎችና የቆሻሻ ማጠራቀሚያዎች አቀማመጥ በወጥ ስታንዳርድ ካለመደረጋቸው የተነሳ፣ በእግረኛ መንገድ የባሰ ጥበት የሚፈጥሩ ናቸው። እንደዚህ የሆኑ እግረኛ መንገዶች፣ እግረኛው ሊጓዝባቸው አስቸጋሪ ነው። እግረኛ መንገድ ላይ የተተከሉ ብዙ ዛፎች ደግሞ እግረኛ መንገዱን በስራቸው የሚፈነቃቅሉ ሆነው ይታያሉ። እንደሚመስለኝ ለእግረኛ መንገድ የሚሆኑ የዛፍ ዓይነት አይደሉም።
የአንዳንድ አሽከርካሪዎችና ባለመኪኖች ሥነ ምግባር
አንዳንድ አሽከርካሪዎች መንገድ ላይ ለአንድ ሴኮንድ በትዕግስት ሌላውን ሰው ላለማሳለፍ በሚያደርጉት ራስን የማስቀደም ጥረት፣ የትራፊክ መቈላለፍ ሲያጋጥም ይታያል። አንዳንድ ባለመኪኖች ደግሞ ሌላ ሰው ቅድሚያ ሲሰጣቸው ውረታውን የሚያስተውሉት አይመስሉም። ወይም የሌላውን ቅድሚያ ከተሻሙ በኋላ በአብዛኛው ይቅርታ ለመጠየቅ ግድ የሚላቸው አይመስሉም።
የከተማ ሚኒባስ ሾፌሮቹ መሀል መንገድ በፈለጉት ቦታ አቁመው ተሳፋሪ ይጭናሉ ወይም ያራግፋሉ። አብዛኞቹ ሹፌሮች በዕድሜ ወጣቶች ናቸው። በዚህ ዕድሜ ለጫኑትና መንገድ ላይ ለሚያልፈው የሰው ሕይወት ምን ያህል ክብደት ይሰጡት ይሆን? ሹፌሮቹ መንገድ ላይ በፈለጉት ጊዜና ቦታ ሲቆሙ ያለው ለአደጋ ተጋላጭነት ትራፊክ ፖሊሶች እንደሚገባው ክትትል የሚሰጡት ሆኖ አልታየኝም። ስለዚህ ጉዳይ የጠየቅኳቸው አንዳንድ ሰዎች፣ ‹‹ሚኒባሶቹ ይህን ሁሉ አገልግሎት እየሰጡ ከተሳፋሪ የሚያገኙት ክፍያ ትንሽ ስለሆነ፣ ባለ ሚኒባሶቹ ደስተኛ ስላልሆኑ ነው የትም የሚቆሙት›› ብለውኛል። ለዚህ ነው ትራፊኮቹም ብዙ የማይቆጣጠሯቸው ይላሉ።
ከዚሁ ሳንርቅ የአየር ጥራትን ነገር ላንሳ፤ የአዲስ አበባ የአየር ጥራት መጉደል በትንሹ ለመገምገም በተባበሩት መንግሥታት የዓለም የጤና ድርጅት መመዘኛ መሰረት በአንድ ሜትር ኩብ አየር ውስጥ የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠን ቢበዛ 25 ማይክሮ ግራም መሆን አለበት። አዲስ አበባ ላይ የተሰሩ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ግን፣ የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠኑ 63 ማይክሮ ግራም ደርሷል። ይህ ከሚፈቀደው የብክለት መጠን በኹለት እጥፍ የሚልቅ ሲሆን በጣም አሳሳቢ ደረጃ ነው።
መደምደምያ፡
‹‹ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!›› የሚለው መልካም ምርቃት በተደጋጋሚ ይሰማል። ይህ ማለት እግዚአብሔር ምድሯን እንዲባርክ፣ አየሯን፣ ወንዞቿን ባርኮ ዝናብ ሊሰጣት ነው? እንደውም ከዚህ በላይ አድርጎላታል፤ ለእርሻ፣ ለእንስሳት እርባታ፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለከተሞች፣ ለቱሪዝም የሚስማማ መሬት፣ ንፋስና የከርሰ ምድር ሃብት ሰጥቷታል። ታድያ ምንድን ነው የቀረው? መልሱ፤ የሰው የአእምሮና የመንፈስ ተነሳሳሽነት። ይህንንም ማድረግ ያለበት እግዚአብሔር ነው? መዳፈርና ሥነ መለኮትን መንካት እንዳይሆንብኝ እንጂ፣ እንግሊዝኛ ተናጋሪዎቹ እንደሚሉት “እግዚአብሔር ራሳቸውን የሚያግዙትን ነው የሚያግዘው” ስለዚህ አሁንም ለከተማ መጣበብም ይሁን ለልማት ችግር መፍትሔው መጀመርያ እጃችን ላይ አለ። በጐ አሳቢ የአገር ሰው ካለ፣ መንግሥትን ሳይጠብቅ ተደራጅቶ ገንቢ ሚናውን ሊጫወት ይችላል።

መላኩ አዳል የዶከትሬት ዲግሪ በባዮ ሜዲካል ሳይንስ በማጥናት ላይ ናቸው። በኢሜል አድራሻቸው melakuadal@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here