በፖለቲካ አመለካከት መለየት ሐጢአት አይደለም!

0
749

የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር እና የኦዲፒ ምክትል ሊቀመንበር ለማ መገርሳ በኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች የሚደረገውን ውህደት እንደማይቀበሉ ከተናገሩ በኋላ፣ ከተለያየ አቅጣጫ የተለያዩ ሐሳቦች ሲናፈሱ ነበር። የሐሳብ ልዩነታቸውንም ከሐሳብ ልዩነት ባለፈ የተለያየ ግብረ መልስ አስተናግዷል። ግዛቸው አበበ ይህን ነጥብ በማንሳት ለማ መገርሳ አስቀድሞ ሊታወቁ የቻሉበትን የለውጥ እርምጃ በመዘርዘር፣ የሐሳብ ልዩነታቸውን ከማውገዝ ይልቅ ሐሳባቸውን ማጤንና በአንጻሩ ያሉ ጉዳዮችን መመልከት ይሻላል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ባለፈው ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ለኖቤል ሽልማት ያሳጨሁት እኔ ነኝ የሚል እሽቅድድም ውስጥ የገቡ በስደቱ ዓለም የሚኖሩ ግለሰቦችን ውዝግብ ታዝበን ነበር። አሁን ደግሞ ሌላ ውዝግብን ከነዚያው የስደቱ ዓለም ኗሪዎች እየሰማን ነው። የለማ መገርሳን ‘ሿሿ’ ያጋለጥኩ እኔ ነኝ የሚል ፉክክር የገጠሙ ሰዎች እየተከሰቱ ነው። በእርግጥ አጋለጥኩት የሚሉት ‘የሿሿው’ አርእስት እንደ ተወዛጋቢዎቹ ሊለያይ ይችላል። ለአንዳንዶች የለማ ሿሿ ጸረ-አማራ ሲሆን በሌሎች ዘንድ ደግሞ ጸረ-ኢትዮጵያ እንደሆነ ተደርጎ እየተነገረ ነው።
የዚህ የሿሿ አጋላጭነት ፉከራ ጎልቶ የተሰማው የባልደራሱ ሰዎች በአሜሪካ ከጠሩት ስብሰባዎች በአንደኛውና አብርሃም ዓለሙ (ዶ/ር) የተባለ ሰው “የለማ መገርሳን ሴራ መጀመሪያ ያጋለጥኩት እኔ ነኝ” ብሎ ባጨበጨበበት አጋጣሚ ነው። ከልጅነት እስከ ጉርምስና፣ ከጉርምስና እስከ እርጅና ዕድሜያቸው አንድም ቀን ለኢትዮጵያና ለሕዝቦቿን በሙያቸውና በእውቀታቸው ለማገልገል ሐሳቡ ሳይኖራቸው፣ ዕድሜያቸውን በመቁጠር ላይ ያሉ ብዙ ምሁራን ከእነሱ በላይ ኢትዮጵያዊ እንደሌለ ከመናገር አልፈው በተቻላቸው አቅም ለኢትዮጵያ ሊሠሩ ቆርጠው የተነሱ ሰዎችን በዘር መነጽር እየለዩ በመዘርጠጥ ማስጨብጨብ የተለመደ የብልጣ-ብልጦች ታጋይነትን ማሳያ ዘዴ እየሆነ ነው። የእነዚህ ታጋዮች ዒላማ ሲሆኑ ለማ መገርሳ የመጀመሪያው ሰው አይደሉም።
‹‹የወደቀ ግንድ ምሳር ይበዛበታል›› ይባላል። በብዙዎች ዘንድ ለማ መገርሳ እንደወደቁ ተደርገው ተቆጥረዋል። ለማ መገርሳን መደመርንና የኢሕአዴግን ውህደት የተቃወሙት ለአገር፣ ለሕዝብ ወይም ለኦሮሚያ አስበው ሳይሆን፣ ግለሰባዊ በሆነ ተልካሻ ምክንያት የተነሳ ነው እየተባለ ይወራል። በጀርመኑ ዶቸቨለ፣ በአሜሪካው ቪኦኤ ላይ የቀረቡ የፖለቲካ ሳይንስ መምህራንና ምሁራን ጥቂት የማይባሉትም ለማ መገርሳን ተሳስተዋል ብለው በግላጭ ከመቦጨቅ አልታቀቡም።
ለማ መገርሳ ውህደቱን አስመልክቶ የሰጡት አስተያየት፣ ከአገርና ከሕዝብ ጥቅም አንጻር ሲታይ ጊዜውን ያልጠበቀ፣ እንደገና ለመታየትና ላለመረሳት (ከፖለቲካ ጓዳና ከዐቢይ አሕመድ ጥላ ስር ወጣ ለማለት) ሲባል የፈነዳ፣ የወቅቱ ፋሽን በሆነው በፖለቲካዊ ቢዝነስ ተሰማርቶ በጎ-ፈንድ-ሚ ሚሊዮነር ለመሆን የተወጠነ ሴራ ያስከተለው ተቃውሞ ወዘተ… እንደሆነ ተደርጎ ተተርጉሟል።
ኦሕዴድ ወደ ኦዴፓ ከዚያም ወደ የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ከመቀየሩ በፊት፣ በወርኅ ሚያዚያ 2011 ‹ቲም ለማ/ አቶ ለማ ድምጻቸው ጠፋ› የሚል ዓይነት ጥያቄ ተነስ ነበር። ጥያቄው ያኔ የኦሕዴድ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ለነበሩት ታዬ ደንደአ ቀርቦላቸውም ነበር። ቦሌ ታይምስ ትባል በነበረች ጋዜጣ በኩል ለቀረበላቸው ለዚህ ጥያቄ ታዬ የሰጡት መልስ ‘ለማ ለማ አትበል’ የሚል ዓይነት ነበር።
ታዬ “… ቲም ለማ የሚባል ነገር የለም፣ አገሪቱን መርቶ የማሻገር ወይም ያለማሻገር ጉዳይ የቲም-ለማ አይደለም። የኢሕአዴግና የሌሎች ባለ ድርሻ አካላት [ጉዳይ] ነው…” ሲሉ ኮስታራ መልስ ሰጡ። ድሮ ድሮ በኢሕአዴግ ሥም ሕወሐትና አቶ መለስ ያሻቸውን ያደርጉ ነበረና፣ ይህ የታዬ ደንደአ መልስ በዚህ የለውጥ ጊዜም ለምድ ደርቦ የማስመሰል ድራማ የሚሠራ ግለሰብና ቡድን መኖሩን የሚያመላክት ነው። እናም ዛሬ መደመርን እየዘመረ ኢብፓ (የኢትዮጵያ ብልጽግና ፓርቲ) ነኝ ብሎ ተነስቶ ብዙም ሳይቆይ ኢትዮጵያን ሰርዞ ብፓ (ብልጽግና ፓርቲ) ብቻ ነው ስሜ ብሎ አገር እመራለሁ የሚል ድርጅት ተፈጥሯል ሲባል እየሰማን ነው።
በዚህ ሳምንት ደግሞ የኦሮምያ ብልጽግና ፓርቲ፣ የአማራ ብልጽግና ፓርቲ እየተባለ በአመራርና በአባላቱ እየተጠራ የመደመሩን እንዴትነት ግራ አጋቢ አድርጎት ለማየት በቅተናል። ምሁራንና ፖለቲከኞች ይህን መሰሉን አቅጣጫው የማይታወቅ አካሔድ ከመተቸትና ለማረም ከመጣጣር ይልቅ፣ ከዚህ ግራ መጋባት፣ ከዚህ የ‹ቸኮለ አፍስሶ ለቀመ› የሚለውን ተረት የሚያስታውስ መገለባበጥ፣ የለሁበትም ያሉትን ብቸኛ ሰው ለማ መገርሳን ለመዘርጠጥ እየተሽቀዳደሙ ነው።
እነዚህ በመገናኛ ብዙኀን ላይ ጉዳዩን አስመልክቶ ሐሳብ እንዲሰነዝሩ የተጋበዙ ምሁራን፣ የለማን መቃወም ያልተጠበቀ፣ አስደንጋጭ፣ የማይታመን፣ ተስፋን እንደ ጉም የሚያበን ክህደት፣ ብስለት የጎደለው ወዘተ… እያሉ ሲያብጠለጥሉትም ሰምተናል። “…እኔንና ዐቢይን ከሞት በስተቀር የሚለየን የለም ያሉት ለማ መገርሳ፣ እንዴት ተቃዋሚ ይሆናሉ” ብለው በመጠየቅም የማብጠልጠሉ ዘመቻ ተገቢ መሆኑን ለማሳየት የሞከሩ ምሁራን አሉ። የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርና መምህር የተባሉ ሰዎች ጠለቅ ብለው ማነፍነፍ ሲገባቸው፣ የለማን ንግግር ካልበሰሉ ልጅ-እግር ፍቅረኞች አንደበት እንደወጣ ቃላት ድርደራ አድርገው ማየታቸው ትዝብት ላይ የሚጥላቸው ነው።
ለመሆኑ ለማ መገርሳን እንዴትና መቼ ነው ያወቅናቸው?
ብዙዎቻችን ይህ ጥያቄ ቢቀርብልን አንዳንዶቻችን ለመጀመሪያ ጊዜ ሌሎቻችን ደግሞ ለማ መገርሳን ልዩ ትኩረት ሰጥተን በደንብ ያወቅናቸው በ2010 የተካሔደው፣ የሕወሐትን የበላይነት አስቀርቶ፣ ብዙዎች የኢሕአዴግ ማራቶን ብለው የጠሩት ስብሰባ በተጠናቀቀበት ወቅት ነው ማለት ይቻላል። በእርግጥ የኢሕአዴግ/ሕወሐት በተለይም የኦሕዴድ አባላት ከዚህ የተለየ ምላሽ ሊሰጡ ይችላሉ።
ብዙ ቀናትን የወሰደው ያ ስብሰባ በመካሔድ ላይ እንዳለ፣ ከተለመደው የሕወሐት/ኢሕአዴግ የስብሰባ ልምድና ስርዓት ውጭ ብዙ ወሬዎች እያፈተለኩ ለሕዝብ ይደርሱ ነበር። በዚያ ስብሰባ ላይ የሕወሐትን አውራዎች ከምንም ባለመቁጠር የሚቃወሙ ሰዎች መኖራቸውና የሕወሐት አውራዎችም ከተራ ስድብ ጀምሮ የውሃ መያዣ ላስቲክ እስከ መወርወር በደረሰ ቁጣ የበላይነታቸውን ለማስጠበቅ ይፋለሙ እንደነበረ በተደጋጋሚ መነገሩ ሊታወስ ይገባል።
ይህን መሰሉ አፈትላኪ ወሬ ከሕወሐት/ኢሕአዴግ ስብሰባዎች አንዳች ነገር ጠብ ይላል ብሎ የማይጠብቀውንና ስብሰባው ሲጠናቀቅ ምን የሚል መግለጫ ይሰጥ ይሆን ብሎ ተጨንቆ የማያውቀውን ሰፊ ሕዝብ፣ ነገሩን በጽሞናና በመገረም ወደ መከታተል አምጥቶትም ነበር።
ስብሰባው አለቀ ሲባልም ብዙ ሰው በዚያ ወቅት የኢሕአዴግ ሊቀ-መንበርና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ኃይለማርያም ደሳለኝ የሚሰጡትን መግለጫ ለመስማት የነበረው ጉጉት ቀላል አልነበረም። እርግጥ ነው ኃይለማርያም ደሳለኝ በተለመደው ባህል መሰረት ‘…መስመራችንን ለመከተል ሙሉ በሙሉ ተስማምተን ወጥተናል…’ ሲሉ ነበር የተሰሙት።
ሺፈራው ሽጉጤም በፊናቸው ተነስተው ኢሕአዴግ ጠንክሮ መውጣቱን፣ የአገሪቱን አንድነትና ሕገ-መንግሥታዊ ስርዓቱን ለማስቀጠል ስምምነት ላይ መደረሱን ነው የነገሩን። በስብሰባው የስድብ ቃላት ከመወራወርና ከመዘላለፍ ያለፈ ጠላትነት የሰፈነበት መሆኑ በሰፊው ተሰምቷልና፣ የኹለቱ ደኢሕዴናውያን ባለሥልጣናት ወሬ የተለመደው ፍርሃት የወለደው መሸፋፈኛ መሆኑን ያጣው የለምና ሕዝቡ አንዳች ነገር ከመጠባበቅ አልቦዘነም።
ከዚህ ሌላ ከሐምሌ 2008 ጀምሮ ከብአዴን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጥቂት የማይባሉት የሕወሐት ባለሥልጣናት ‘በቃችሁ!’ ብለው በተገናኙበት አጋጣሚ ሁሉ፣ እንደ እኩያ ከማነጋገር፣ ሲያስፈልግም አምርረው ከመቃወም አልፈው ከአማራ ክልላዊ መንግሥት ፈቃድና እውቅና ውጭ የፌዴራል ይሁን የአግአዚ ኀይል ከትግራይ ይሁን ከአዲስ አበባ እየተነሳ ወደ አማራ ክልል እንዳይገባ እስከ ማድረግ የደረሰ ተጋፋጭነት እያሳዩ ስለነበረ፣ የእነ ኃይለማርያም ደሳለኝ መግለጫ ማንንም ለማታለል አልቻለም ነበር።
እንዲያውም ኃይለማርያም ከዚህ ስብሰባ በፊት፣ በብአዴን እና በኦሕዴድ ባለሥልጣናት በኩል የሚታየውን አፈንጋጭነት ለመኮርኮም ፈልገው ‘….ትምክህተኞች እና ጠባቦች ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ አካሔድ እያፈነገጡ …’ ነው ብለው ለሕወሐት ከገቡበት ተንበርካኪነት ቀና ለማለት የሚውተረተሩ የብአዴን እና የኦሕዴድ ሰዎችን የሚነካ መግለጫ በመገናኛ ብዙኀን ላይ ሰጥተው ነበረ። እናም ‘…ተስማምተን ወጣን…’ የሚለውን መግለጫቸውን የአድርባይነታቸው ማሳያ አድርጎ ከመውሰድ አልፎ ከቁም ነገር የቆጠረው ሰው ብዙም አልነበረም ማለት ይቻላል።
እንግዲህ ይህ በእንዲህ በነበረበት ጊዜ ነው፣ ከዚህ ስብሰባ ተካፋይ ከነበሩት አንዱ ምርር ባለ አንደበት ‘… ተቋስለን ነው የተለያየነው…’ በማለት፣ ስብሰባው ክፍት ቢሆን ኖሮ የዚህች አገር ጠላትና ወዳጅ ማን መሆኑን ሕዝብ አሳምሮ የሚያውቅበት አጋጣሚ ይሆን እንደነበረ ጭምር በመናገር ጉዱን ያፍረጠረጡት። እኚህ ሰው ለማ መገርሳ ናቸው። ብዙዎቻችን ለማ መገርሳን በሚገባ ያወቅናቸው፣ ትኩረትም የሰጠናቸው በዚህ ጊዜ ነው።
የወቅቱን ሁኔታ ለመገምገም የደፈሩ ምሁራን አንድ ሊጠየቁት የሚገባ ጥያቄ አለ። ይህን የለማ መገርሳን ደፋር መግለጫ ተከትሎ የኢሕአዴግ ስብሰባ ለሕዝብ ክፍት እንደሚሆንና በር ተዘግቶ የሚካሔድ ስብሰባ እንደማይኖር ቃል ተገብቶ ነበር። ነገር ግን ይህ ቃል ሲተገበር አላየንም። አንድም የገዥው ቡድን ስብሰባ ክፍት ሆኖ ተካሒዶ አያውቅም። ምሁራኖቻችን ይህን በሚመለከት ጥያቄ ሲያነሱ ሰምተን የማናውቀው ለምንድን ነው? ለማን ጥቅም ተብሎ ነው ሕዝብ በኢሕአዴጉ ሊቀመንበር የተመረጠውን ወይም የተቀመመውን ወሬ ብቻ እንዲሰማ የተፈረደበት?
ከ2011 ጀምሮ የመንግሥት ሚዲያዎችና እና የሕወሐት/ኢሕአዴግ ስርዓት ንብረቶች መሆናቸው የሚታወቅ መገናኛ ብዙኀን፣ አሠራራቸውን ቀድሞ እንደነበረው የተባለውን ወደ መድገም መልሰው እየተዘፈቁ እንደሆነ በገሃድ አይተናል። ምሁራኖቻችን ይህም ሆነ ሚዲያዎቹ የጥቂት ሰዎች አሽከር መሆን አሳስቧቸው አያውቅም። ከዚህ አልፈው ይህን መሰሉ አካሔድ ተደማምሮ ለማ መገርሳን የመሳሰሉ ሰዎችን ሊያስከፋ እንደሚችል ለመገመት ቅንጣት ፍላጎት አላሳደሩም።
ምሁራኖቹ ይህን ሁሉ ችላ ብለው ነው ለማ መገርሳን የዴሞክራሲ ሒደትን አደናቃፊ አድርገው ሊስሏቸው የሞከሩት። ለውጡ እኮ ለማ መገርሳን የሚያህሉ ሰው ብቻ ሳይሆን ማንኛውም የፓርላማ አባልና ማንኛውም ተራ ዜጋ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተለየ ሐሳብ ካለው ሐሳቡን በነጻነት ማራመድ እንዲችል ማድረግ ነው ያለበት!!
የፖለቲካ ሳይንስ መምህራኑና ምሁራኑ ሌላም ችላ ያሉት፣ ነገር ግን በፖለቲካ ሳይንስ ሚዛን በሚገባ ሊተችና አደገኛነቱ ሊተነተን የሚገባው ነገር አለ። ለመሆኑ የስምንት ፖለቲካ ቡድኖች ሕልውና ‹‹ያለ አንዳች ተቃውሞና ቅሬታ›› ቀጠለ ሲባል ምንም ያልመሰላቸው ምሁራን፣ የለማ መገርሳ በሐሳብ መለየት እንዴት አስደንጋጭ ሆነባቸው? ከዚህ ሌላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ የረዥም ጊዜ አማኝነት ወደ መደመር ፍልስፍና አባትነት ያደረጉበት እመርታዊ ለውጥ፣ ለምሁራን ግራ ያላጋባውና ለማ ይህን ፍልስፍና ‹አሜን!› ብሎ መቀበልና መከተል ነበረበት ብለው ለመፍረድስ የትኛው የምሁርነት አመክንዮ ነው የሚፈቅድላቸው?
ጠቅላይ ሚኒስትሩና ፓርቲያቸው (ኢሕአዴግ) ኦሕዴድን እና ብአዴንን ወደ ኦዴፓ እና አዴፓ ቀይረው፣ ሕዝብ የሕወሐትና የደኢሕዴን ጉዳይ እንዴት ሊሆን ነው ብሎ በመጠባበቅ ላይ እያለ ‘ጨዋታ ፍርስርስ ያደረ እንጀራ ቁርስርስ’ ዓይነት ድምዳሜ ላይ ተደርሶ ስለ ብልጽግና ፓርቲ ብቻ መወራት ሲጀምርስ ምሁራኑን ‘ምን እየተደረገ ነው?!’ ብለው እንዲመራመሩ ያላነሳሳው ምንድን? ምሁራኑ ዐቢይ አሕመድ ፍጹም ናቸው ብለው ያምኑ ይሆን!
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹መደመር›› የተሰኘ መጽሐፋቸውን አሳትመው ወደ ብልጽግና ፓርቲ ተሰባሰብ የሚል ጥሪ ካደረጉበት ጊዜ ጀምሮ፣ ወደ ብልጽግና ፓርቲ ያልተቀላቀሉና መደመርን የሚቃወሙ ወገኖችን፣ ሌቦች ስለሆኑ የሸሹ፣ ውስኪ አስቀምጠው መደመር ያልቻሉ፣ መደመር ባይስማማቸውም ማባዛት የሚል ፍልስፍና መፍጠር ያልቻሉ ወዘተ….. እያሉ የማሸማቀቅና የማንጓጠጥ ዘዴ ሲጠቀሙ ታይተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእነዚህና በሌሎች አጋጣሚዎች የቀድሞ ኢሕአዴጋዊ አጋሮቻቸውን እንደ ጓደኛ ወይም የትግል ጓድ አድርገው ማየት ያቆሙና፣ ግንኙነታቸው ወደ የንጉሥና ሎሌ ግንኙነት እንዳሳደጉት ወይም እንዳወረዱት በገሃድ የታየ ጉዳይ ነው።
ታዲያ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራኑና መምህራኑ የብልጽግና ፓርቲ ጉዞ ወዴት መሆኑንና የትስ እንደሚደርስ እርግጠኛ ስለሆኑ ነው የአቶ ለማ መገርሳን ወራጅ አለ ማለት የሚኮንኑት?!
‹‹አዲስ ወግ›› በሚባሉትና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት እየተዘጋጁ ይካሔዱ ከነበሩት ስብሰባዎች በአንደኛው ላይ፣ ተሰብሳቢወች የጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥት ሕግንና ስርዓትን ማስከበር ላይ የሚታይበትን ድክመት ነቅሰው ሲናገሩ፣ በዚህ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደ ዋዛ ‘…ወደ 5 ወይም 6 አገራ ለሥልጠና የተላከ ጦር እንዳላቸው፤ ይህ ጦር ሠልጥኖ ሲመጣ በየመንገዱ የሰውን ማንቁርት እያነቀ ይጥላል ብለው እንደሚፈሩ….’ ያላቸውን ስጋት ይሁን ተስፋ ተናግረው ነበረ።
በፖለቲካ ሳይንስ ምሁራኖቻችን ዘንድ ይህ ነገር እንደ ተራ ጨዋታ ተቆጥሮ ነው ያለፈው። በኢሕአዴግ ስብሰባዎች ይህን እና ይህን መሰል ጉዳዮች ተወስተው ሲያነጋግሩ ምን እንደሚባል የምናውቀው ነገር የለም። እንግዲህ ለማ መገርሳ ‹‹በብዙ ጉዳዮች ሰሚ ካጣሁ ብዙ ጊዜ ሆኖኛል›› ብለዋል፤ ስለዚህ በቅቷቸዋል። ምሁራኖቻችን ግን ሕወሐት ሲያደርገው ለከፍተኛ ነውጥ የዳረገውና የሚከፈል ዋጋ ተከፍሎ በሕዝብ አመጽ የተገታው ዜጎችን በየጎዳናው አንቆ የመድፋት ‹ዴሞክራሲ› እንዴት እንደሚሰፍን ትምህርት ሊሰጡን ይገባል¡
ማንም ሊክደው የማይችለውና ሊክደውም የማይገባው፣ በ2010 ከተካሔደው በሕወሐት የበላይነት ሊካሔድ ከተሞከረው የመጨረሻ ስብሰባ ማግስት፣ በለማ መገርሳ የተሰጠው ግልጽና ድፍረት የሞላበት መግለጫ ብዙዎችን በግንባር ሆኖ ወያኔን የሚፋለም ሁነኛ መሪ እንዳገኙ ሆኖ እንዲሰማቸው ያደረገ መግለጫ መሆኑ ነው። አቶ ለማ መገርሳ ነፍሳቸውን ሸጠው ስብሰባው የሕወሐት/ኢሕአዴግ አውራዎችን የኢትዮጵያና የሕዝቦቿ ጠላቶችና ወዳጆች ብሎ መክፈል የሚያሰችል አጋጣሚ እንደነበረ በአደባባይ መናገራቸው በኢትዮጵያዊነታቸው የሚያምኑ፣ ብዙዎችን ከለማ ጎን እንዲሰለፉ እንዳደረጋቸውና ስለ አቶ ለማ መገርሳ ብዙ ለማወቅ እንደገፋፋቸው፣ በተቃራኒው ኢትዮጵያ አለቀላት የሚል የደስታ ሲቃ ይተናነቃቸው ጀምሯቸው የነበረ ‘ነጻ አውጭ’ ግለሰቦችንና ቡድኖችን በለማ ላይ ጥርስ እንዲነክሱ እንዳደረጋቸው በወቅቱ በየዜና ማሰራጫውና በየማኅበራዊ ሚዲያው ከሚዘዋወረው ሐሳብ በቀላሉ መረዳት ይቻል ነበር።
በዚያን ጊዜ ከራሱ ሕይወት ይልቅ ለለማ መገርሳ ሕይወት መሳሳት የጀመረውን ሰውም ቤቱ ይቁጠረው። ሰው በላው የሕወሐት/ኢሕአዴግ ስርዓት በለመደ ጨካኝ ልቡ እኝህን ሰው አጥፍቶ መርዶ እንዳያሰማቸው የሚጸልዩ፣ ሕወሐት/ኢሕአዴግ ከዚህ በፊት እንደገደላቸው የሚወራላቸውን ሰዎች በማስታወስ ስለ ለማ መገርሳ ያደረባቸውን ስጋት በገሃድ የሚያስተጋቡ ብዙዎች ነበሩ። አለማየሁ አቦምሳ በስርዓቱ ሰዎች ተመርዘው መገደላቸው እየተወሳ፣ ለማ መገርሳንም አውሬዎች እንዳይነጥቋቸው ከልብ የሚሰጉ ጥቆቶች አልነበሩም።
ቆየት እያለ ለማ ብቻቸውን አለመሆናቸው፣ ከኦሕዴድና ከብአዴን የተውጣጡ ጥቂት ሰዎች ቲም-ለማ ተብለው አብረው አገርንና ወገንን የማዳን ሥራ እየሠሩ የቆዩ መሆኑን መሰማቱ፣ በአገር ደረጃ ምን ዓይነት ስሜት እንደፈጠረም መለስ ብሎ ማስታወስ ይቻላል። የለማ ግልጽ አነጋገርና የቲም-ለማ ኅልውና ይፋ መውጣት ከአገር ቤት አልፎ በስደት የሚኖሩ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያን ከልብ የሚወዱ ወገኖቻችንን ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያውያንን መቁሰልና መድማት በራስ ላይ እንደደረሰ ጉዳት የሚያዩት አና ጎሜዝን የመሳሰሉ የውጭ ዜጎችን ልብም በደስታ የሞላ ነበር። እንግዲህ በአገር ቤትም ሆነ በውጭ ያሉ የኢትዮጵያ ጉዳይ ከልብ የሚያሳስባቸውና የኢትዮጵያን ጉዳይ የሚከታተሉ ሰዎች ለማ መገርሳን እንዲህ ነበር ያወቋቸው።
‘ሰው ማለት፣ ሰው ሲጠፋ ሰው ሆኖ የተገኘ ዕለት’ እንዲሉ፣ ለማ መገርሳ የልብ ሰው የሆኑት እንዲህ በዋዛ ፈዛዛ አይደለም። ዝናን፣ ሹመትን፣ ጭብጨባንና ፉጨትን ወዘተ… ፈልገው ሳይሆን መግደል ምንም የማይመስላቸውን አለቆቻቸውን ተጋፍጠው፣ አገርንና ሕዝብን ሊታደጉ ለሕይወታቸው ሳይሳሱ ቆርጠው የተነሱ ሰው ናቸው፤ ለማ መገርሳ። ለመሆኑ ይህንን ስብሰባ ተከትሎ የስርዓቱ ሰዎች ሁሉ ኃይለማርያም ደሳለኝና ሽፈራው ሽጉጤ እንደተንበረከኩት እነርሱም ተስማምተናል ብለው ቢንበረከኩ ኖሮ ምን ይከተል ነበር? ቲም-ለማስ በጤናውና በጽናት በድብቅ በጀመረው ጉዞ ይቀጥል ነበር?
እንግዲህ ለማ መገርሳን ቢያንስ ከ2010 ጀምሮ ስናውቃቸው፣ እንዲህ ዓይነት ሰው ናቸው። ግፍን መከራንና የዕብሪተኞችን የበላይነት ተሸክሞ ሩቅ ለመጓዝ የሚፈቅድ ሕሊና የሌላቸው። ለማ መገርሳ ሕዝብ እምነት አሳድሮባቸው እያሞካሻቸውና እያጨበጨበላቸው እንኳ ‘…. ወጣቱን ያሳሳትነው፣ ያለ ታሪኩ ታሪክ ነግረን ወደ ስህተት የመራነው እኛ ነን…’ ብለው ከመናገር ወደ ኋላ ያላሉ ሰው ናቸው። ለማ መገርሳ ሕዝብ በተለይም ወጣቱን ማሳሳታቸውን ከመናገር አልፈው፣ ስህተቱን ለማረም ሩቅ ለመጓዝ ቆርጠው የተነሱም ሰው ‘ነበሩ’። አዎ! ‘ነበሩ’ እንበል።
ለማ መገርሳ የኦሮሚያ አባ ገዳዎችን፣ ምሁራንን፣ ፖለቲከኞችን ብቻ ሳይሆን በአማርኛ መዝፈን አይፈልጉም በመባል የሚታወቁ ታዋቂ አርቲስቶችን ጭምር አስከትለው ባህር-ዳር ገብተው ስብሰባ በተቀመጡበት ጊዜ፣ በኹለቱ ሕዝቦች (በአማራና በኦሮሞ) መካከል የተዘራው የጥላቻ አዝመራ ኹለቱንም ሕዝቦች የሚጠቅም አለመሆኑ፣ ኹለቱንም ሕዝቦች ጎድቶ ጠላታቸውን ለመጥቀም የተሰናዳ ወጥመድ መሆኑን ተናግረው፤ ሁሉም ወደየ ልቡ ተመልሶ ከዚህ ወጥመድ ራሱንና ወገኖቹን እንዲያድን መወትወታቸው፤ ከኹለቱ ክልሎች የተውጣጡ ተሰባሳቢዎችም ኦሮሞውንና አማራውን ማጋጨት የሰላቢዎች ዘዴ መሆኑን እያወሱ፣ ይህ አካሔድ ይብቃ መባሉ ተገቢ መሆኑን ሲመሰክሩ ሰምተናል።
ነገር ግን ይህ አጋጣሚ ከአማራውም ሆነ ከኦሮሞው በኩል ጠላት አልቀሰቀሰም ማለት አይደለም። ከኦሮሞና ከአማራ ፖለቲከኞች፣ አክቲቪስቶች፣ ጥራዝ ነጠቅ ምሁራን ወዘተ ጥቃት ይሰነዘርባቸው የጀመረው በጣም ፈጥኖ ነው። አንዳንድ የኦሮሞ ፖለቲከኞች፣ አክቲቪስቶችና ምሁራን ለማ መገርሳን እንደ ከሀዲና ጫፍ ላይ የደረሰውን የቄሮን ትግል ለማኮላሸት በወያኔ የተቀጠሩ መሰሪ ሰው አድርገው አብጠልጥለዋቸዋል። የኦሮምያ መገንጠያ ሲደርስ የተከሰቱ አደናቃፊ ጠላት አድርገዋቸዋል።
አንዳንድ የአማራ ፖለቲከኞች፣ አክቲቪስቶችና ምሁራን ደግሞ ለማ እላይ ላዩን ለኢትዮጵያ አሳቢና ተቆርቋሪ መስለው የኦነግን ዓላማ ለማሳካት ውስጥ ለውስጥ የሚሠሩ መሰሪ ግለሰብ እንደሆኑ አድርገው ይገልጿቸው የጀመሩትም እንደዚያው ብዙም ሳይቆዩ ነው። እነዚህኞቹ ደግሞ ‹የአማራ ሕዝብ ለእኛ ሰጥቶት የነበረውን ክብር ለማ መገርሳ ነጠቁን›› ባይ ስስታሞችና ምቀኞች የሚበዙባቸው ናቸው።
በዚያን ጊዜ ኢሳትና ኦ.ኤም.ኤን. ላይ ሲነዛ የነበረውን ውግዘትና ርግማን መለስ ብሎ ማስታወስ ተገቢ ነው። ከዚህ ጀምሮ፣ ሰበብ የተገኘ በመሰለ ቁጥር፣ ቃላትን እየሰነጠቁና እየሰነጠሩ ስለ ለማ መገርሳ ብዙ እንቶ ፈንቶዎችን አውርተዋል፣ አስነብበዋል፣ አስደምጠዋል። አሁን ደግሞ ለማን ማጥቂያ አዲስ በር ተከፍቶላቸዋል።
ግዛቸው አበበ መምህር ናቸው።
በኢሜይል አድራሻቸው
gizachewabe@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 59 ታኅሣሥ 11 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here