ገበያ መር የውጪ ምንዛሬ ፖሊሲ ከተገበርን የምናተርፈው የዋጋ ግሽበት ነው

0
1423

አብዱልመናን ሙሐመድ የፋይናንስ ዘርፍ ባለሙያ ናቸው። በዘርፉ ከ16 ዓመታት በላይ ልምድ ያላቸው ሲሆን አካውንታት እና ኦዲተር በመሆን በተለያዩ ተቋማት አገልግለዋል።
በቢቢሲ፣ በዶቼቤሌ፣ ፎርቹን ጋዜጣና ኢትዮጵያ ቢዝነስ ሪቪው መጽሔት ላይ በሚሰጡት ትንታኔ የሚታወቁት አብዱልመናን፣ በአሁኑ ወቅት በታላቋ ብሪታኒያ የሎንዶን ፖርቴቤሎ በተባለ ድርጅት የአካውንት ማኔጀር ናቸው።
ከአዲስ ማለዳው ሳምሶን ብርሃኔ ጋር በወቅታዊ ኢኮኖሚ እና የፋይናንስ ጉዳዮችን በተመለከተ ቆይታ ያደረጉት አብዱልመናን በቅርቡ መንግሥት የውጭ ምንዛሬ ገበያ ስርዓቱን በተመለከተ እየወሰደ ያለውን እርምጃ በተመለከተ ያላቸውን ሐሳብ አጋርተዋል።

አይኤምኤፍ እና የዓለም ባንክ አጠቃላይ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ለኢትዮጵያ ለመስጠት ቃል ገብተዋል። ይህንንም ተከትሎ አንዳንዶች ተሰሚነቷ እያደገ ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ ሉአላዊነቷን አሳልፋ እየሰጠች ነው ይላሉ። እርስዎ ከየትኛው ነዎት?
ኢትዮጵያ ባለፉት 15 ዓመታት የተከተለችው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ትልቅ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ነበረው። አሁን ደግሞ ከመንግሥት ጣልቃ ገብነት በፍጹም ወጥቶ ነጻ ወደ መሆኑ ስለሔደ፣ አይ ኤም ኤፍ ድጋፍ እንዲህ ያሉ ለውጦችን መደገፉ አይቀርም። የኢትዮጵያ ተሰሚነት ያደገ አይመስለኝም፤ የኢኮኖሚ ለውጡ እነ አይ ኤም ኤፍ በሚፈልጉት መልኩ እየሔደ ስለሆነ ነው የገንዘብ ድጋፉ የመጣው። ለምሳሌ የውጪ ምንዛሬውን እለቀዋለሁ ወይም ተለዋዋጭ አደርጋለሁ ካልክ፣ በጣም ፈጣን የሆነ የገንዘብ ዋጋ መቀነስ እንዳይኖር፣ ገንዘብ ስለሚያስፈልግ እንደ አይ ኤም ኤፍ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል። እና የተሰሚነት ጉዳይ አይመስለኝም። ለውጡ በፈለጉት መንገድ እየሔደ ስለሆነ ነው። ቀደም ብሎ በ80ዎቹና 90ዎቹም ተካሒዶ በነበረ የመዋቅር ለውጥም ተመሳሳይ ለውጥ ነበር የተደረገው፣ ያኔም ድጋፍ አድርገዋል።
እና የአሁኑ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የሚነካ ነው ልንል እንችላለን?
የአሁኑ ትንሽ የበዛ ነው የሚመስለው። ሙሉ ለሙሉ የእነርሱ ሐሳብ ነው የሚመስለው። ኢትዮጵያ ለምሳሌ የውጪ ምንዛሬን በተመለከተ ለረጅም ጊዜ ተከራክራለች፤ ላለመንካት ለመታገል ሞክራለች። አሁን የተሸነፈችና እነሱ በሚፈልጉት መልኩ እየሔደች ነው የሚመስለኝ። የፋይናንስ ዘርፉ ላይ የውጪ ባለሃብቶችን አናስገባም አሉ እንጂ ቀጣዩ እርምጃ ይህ ሊሆን ይችላል። ኹለት ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላሩን ካየን፣ ድጋፉ የሚውለው መንግሥት ድህነት መቀነስ እና ዋና መሠረት ልማት ላይ የሚበቃውን ወጪ መሰብሰብ የሚያስችለውን ገቢ እንዲያገኝ መርዳት ነው ይላል። ይህ ማለት መንግሥት በጣም መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩር፣ ሊበራል ኢኮኖሚክ ፖሊሲ እንዲኖረን ነው የሚፈለገው እንደ ማለት ነው።
ይህ ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር በጣም የበዛ ነው። እና ትንሽ መሰመሩን ያለፈ ይመሰለኛል። የተወሰኑትን እንኳ እንቢ ማለት ነበረባቸው። በተለይም የውጪ ምንዛሬ አቅምን ሳታሳድግ በቀላሉ የምትለቀው ጉዳይ አይደለም። የኤክስፖርት አቅም ማደግ አለበት። ካደገ በኋላ ወደ በገበያ የሚመራ የውጭ ምንዛሬ ገበያ ብትገባ፤ ምንም ላትሆን ትቸላለህ። የኢትዮጵያ የውጪ ንግዷ ሦስት ቢሊየን ዶላር ሆኖ ለረጅም ዓመት የቆመ ነው፤ የምርት ትስስርና ራሱ ምርትም ችግር ያለበት ነው። በዚህ ሁኔታ ባይስማሙ የተሻለ ነበር። እንደዚሁ ባለፈው 15 ዓመት በልማታዊ መንግሥት እንደሔድነው ሳይሆን በደንብ አሻሽለውት፣ ኢንደስትሪል ፖሊሲ ኖሮን፣ መንግሥት የተለያዩ ማበረታቻዎችን ተጠቅሞ መሄድ ሳያስፈልግ አይቀርም። አሁን ግን ሁሉም ነገር ለገበያ ይተው የተባለ ይመስላል።
ብዙ የውጪ ምንዛሬ ገበያ ውስጥ ባይኖርም የገበያ ስርዓቱን ለመቀየር እንዲሁም የተለያዩ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ለማድረግ የኢትዮጵያ መንግሥትም 10 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ካለኝ በቂ ነው እያለ ነው።
አስር ቢሊዮን ዶላር ይገኛል ቢባል፤ ቃል የተገባው ስድስት ቢሊዮን አካባቢ እንኳ በስንት ጊዜ ነው የሚመጣው? አንድ ጊዜ የሚመጣ ነው። ኢትዮጵያ የምትፈልገው የውጪ ምንዛሬ በጣም ብዙ ነው። ወደ አገር ለማስገባት የምናወጣው ወጪ 16 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ሲሆን፣ ከውጪ ንግድ የሚገኘው ገቢ 3 ቢሊዮን ዶላር ነው። ሰፊ ልዩነት አለ፤ ብዙ ነው የምንፈልገው። አሁን የተገኘው የውጭ ምንዛሬ ለጊዜው ጥሩ መፍትሔ ሊሆን ይችላል፤ ኹለት ዓመት ሊያቆየን ይችላል። ይሄ ያለቀ ጊዜስ ምንድን ነው የምንሆነው?
ኹለተኛ ይሄ ገንዘብ መከፈል አለበት፣ ስጦታ አይደለም። ዋናው መከፈል አለበት፤ አከፋፈሉ የጊዜ እፎይታ ቢኖረውም። ይህን ተጠቀምን ሲያልቅ፣ ከኹለትና ሦስት ዓመት በኋላ ወደ ነበርንበት ነው የምንመለሰው። ይሄ ለጥቂት ጊዜ ያረጋጋል እንበል፤ ከዛ በኋላስ የውጪ ገበያ አቅርቦታችንን በሰፊው ማሳደግ እንችላለን ወይ፣ አቅም አለን ወይ?
የውጪ ንግዱን የማሳደግ አቅም ያለን ይመስልዎታል ግን?
አይመስለኝም። እኛ ለውጪ ገበያ የምናቀርበው ቡና፣ ጫት ያሉ የግብርና ምርቶችን ነው። ይህም በራሱ የምርት እጥረት አለበት። ሌላው ዓለም አቀፍ ገበያ ላይ በጣም ተለዋዋጭ ነው። እዛ ገበያ ላይ በዚ ምርት አቅርበህ፣ ተወዳድረህ መላክ ረጅም ዓመት ወስዶብናል። አሁን መንግሥት ወደ ማኑፋክቸሪንግ እያተኮረ ነው። ኢንደስትሪ ፓርኮችን በማስፋት። እሱም ብዙ እየተሳካልን አይመስልም። ኢንደስትሪ ፓርኮች የሠለጠነ ባለሙያ፣ የሙያ ሥነምግባር ችግር አለባቸው። የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታም ችግር ውስጥ ነው። እነዚህን ነገሮች ቀድሞ ማስተካከል ያስፈልጋል።
ግን በሦስት ዓመት ውስጥ ነው እናሳካለን ነው መንግስት እያለ ነው። ኢትዮጵያ በሦስት ዓመት ውስጥ ያንን መተግበር አትቻልም ይሆን?
ባለፈው 15 ዓመት ምን ቻልን? ሦስት ዓመት ነገ ነው ግን ባለፈው 15 ዓመት ምን ተሳካልን? ስንት እቅድ ታቀደ ግን አልተሳካልንም። እና ሦስት ዓመት በጣም አጭር ነው፤ ነገ የሚመጣ ነው። የፖለቲካ ሁኔታውን እንኳ ማስተካከል በራሱ ጊዜ የሚፈልግ ነው። ቢዝነሱ፣ የውጪ ገበያው፣ ንግዱ፣ የትራንስፖርት መንገዶች እንዲሠራም ሆነ ሰዉ ተረጋግቶ እንዲሠራ ጊዜ ይጠይቃል። እና በሦስት ዓመት ይህን ማስተካከል በጣም አጭር ነው። ተመልሰን ችግር ውስጥ ነው የምንገባው። የዋጋ ግሽት ነው እንደውም ከገበያ-መር የውጭ ምንዛሬ ፖሊሲ የምናተርፈው።
በጣም ተለዋዋጭ የሆነ የምንዛሬ ተመን የዋጋ ግሽበቱን የት ያደርሰዋል ብለው ያስባሉ?
አሁን 32 ብር አካባቢ ነው ባንኮች ዶላር የሚሸጡት፤ ከፈጠነ 40 ሊገባ ይችላል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጣም እየወረደ ነው። ይህ ከሆነ ገቢ የምናደርግበት ገንዘብ በጣም ነው የሚጨምረው፤ የውጪ ገቢ ብዙም ላይጨምር ይችላል። ከውጪ የሚገቡ እቃዎች እንዳለ ነው ዋጋቸው የሚጨምረው። የብር የምንዛሬ ዋጋ በ20 እና 30 በመቶ በሚቀንስበት ሰዓት፣ ወደ እቃዎች ዋጋ ሲመነዘር፤ ነጋዴው ትርፍና በየተዋረዱ ላይ ያለው ወጪዎች ሲደረመሩ ግሽበቱ በጣም የተጋነነና እጥፍ ሊሆን ይችላል።
የሚገቡትን እቃዎች በሙሉ ነው የሚያስወድደው። ነዳጅ፣ መድኀኒት፣ ስንዴ፣ የፋብሪካ ማሽን ሳይቀር፣ የትራንስፖርት እቃዎችም ይጨምራሉ። ወደተጨባጭ ሁኔታ ስናመጣው፤ እነዚህ ሲጨምሩ ግሽበቱ እጥፍም ሊሆን ይችላል። ነጋዴዎችም ደግሞ የአቅርቦት ችግር ስላለብን ጨመረ ሲባል ይህን አጋጣሚ ይጠቀማሉ፤ እኛም ጨምሮብናል ዋጋ እንጨምራለን ይላሉ። እና ይህ የብር ዋጋ መቀነስ ወይንም ዲፕሪሽዬሽን የዋጋ ግሽበቱን በጣም ሊያባብሰው ይችላል፤ የውጪ ገበያችንን የሚያሻሽለው አይሆንም። ከዚህ የምናተፍረው ነገር አይታየኝም፤ በፊትም ያየናቸው ተመሳሳይ እርምጃዎች ግሽበት ነው ያመጡት እንጂ መሻሻል አላመጡም፤ የ2010ሩም የ2017ቱም የብር የውጭ ምንዛሬ ዋጋን ማዳከም ምንም ውጤት አላስገኙም።
የዋጋ ግሽበት እንዳለ ሆኖ ተጨማሪ የኤክሳይስ ታክስም አለ። ሰባት ዓመት በላይ የሆነ ዕድሜ ያሉ መኪናዎች ላይ ኤክሳይስ ታከስ ይጣላል ተብሏል። ይህን ጭማሪ ተከትሎ ግንኙነት የሌላቸውም ምርቶች ጭምር ዋጋቸው ሊጨምር ይችላል የሚል ስጋት አለ። ይህን እንዴት ያዩታል?
ለምሳሌ የቤት ኪራይ ዋጋ ሊጨምር ይችላል። ሰው ግንኙነት ያለው ላይመስለው ይችለል ግን አለው። የገንዘብ መግዛት አቅምን ሲቀንስ፤ ከውጪ የሚገቡ እቃዎች ዋጋ ይጨምራል። ከውጪ የሚስገቡ ሰዎች ዋጋ ቢጨምሩ ልክ ናቸው፤ የቤት አከራይ ግን እንዴት ጨመረ? አስመጪው ዋጋ ሲጨምር የቤት አከራዩን ይነካዋል። ከውጪ የተገዛውን እቃ አከራዩ ስለሚጠቀም ይነካዋል፤ ሕይወቱን ስለሚነካም የቤት ኪራይ ይጨምራል።
እንዲሁ ነው፤ አንድ ቦታ ላይ ብቻ ጨምሮ የሚበቃ ጉዳይ አይደለም። አከራዩን ደግሞ ከነካ እህል የሚሸጠውንም ይነካል ማለት ነው። አብሮ የተያያዘው ገቢን መጨመር የሚል ጉዳይ ነው። መንግሥት የኢኮኖሚ መሻሻያው ላይ የጠቀሰው አንዱ ነገር ገቢ መጨመር ነው። አንዳንድ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የሚሉት መንግሥት ሒሳቡን ባላንስ ያድርግ ነው። ይህ ማለት ብዙ ገቢ መሰብሰብ አለበት ነው። ይሄ ኤክሳይስ ታክስ መጨመር አንደኛው ገቢ መሰብሰቢያ ነው።
መንግሥት ታክሱን መጨመር ስላለበት ሰባት ዓመት የቆዩ እቃዎች ላይ፣ መጠጥ፣ ውሃ፣ ቅንጦት ተብለው የሚታሰቡ ላይ የመጨመሩ ነገር አለ። እነዚህ ነገሮች ሌላው ላይ ተጽእኖ ላይፈጥሩ ይችላሉ። የተወሰነ መካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል የሚነካ ይሆናል። በቂ የሕዝብ ትራንስፖርት ባልተሟላበት ሁኔታ እንደዚሁም አዳዲስ የሚመጡ መኪናዎች ላይ ማሻሻያ ባልተደረገበት ሁኔታ፣ አሮጌ መኪኖች ላይ ስለተጨመረ የመኪናን ዋጋ [አስቀድሞ የገቡትንም] ከማሳደግ ውጪ ብዙ የሚያመጣው ነገር አይኖርም። የመንግሥትን ገቢን ይጨምራል።
መንግሥት ለዚህ የሚያስቀምጠው ምክንያት የበጀት እጥረቱን ነው። እና ከዚህ ሌላ ምን አማራጭ አለው?
የበጀት እጥረት ሲያጋጥም ኹለት አማራጭ አለ። ወይ ወጪ መቀነስ አልያም ገቢ መጨመር ነው። ሌሎች አገራት ላይ ወጪ መቀነስ ነው የሚመረጠው። ሠራተኞችን መቀነስ፣ ፕሮጀክቶችን ማጠፍ የመሳሰለው። ያ ደግሞ ለኢትዮጵያ ከፖለቲካ አኳያ አዋጭ አይደለም። ስለዚህ ያለው አማራጭ ገቢ መጨመር ነው። ገቢ ደግሞ ልጨምር ስትል የተወሰነ የማኅበረሰብ ክፍል ላይ ነው የሚሆነው፤ ገቢው መካከለኛ የሚባል ነጋዴው ኅብረሰተሰብ ላይ።
አብዛኛው ገበሬ ነው፤ የራሱን ኑሮ ለማሸነፍ የሚታገል። እና ከዚህ ኅብረተሰብ ክፍል ግብር ልታገኝ አትችልም። ስለዚህ ከተማ ላይ ያለው ነጋዴ ላይ ነው ልትጭን የምትችለው። ስለዚህ መንግሥት ያለው አማራጭ እዛ ነው። ለወደፊቱ ግን መታሰብ ያለበት የገቢ መሠረቱን እንዴት አሰፋዋለሁ የሚለው ነው። ሌሎች የገቢ ምንጮችን መታሰብ አለባቸው። ለምሳሌ የቤተሰብ መጠንን መሠረት ያደረገ ታክስ መጫን ሊሆን ይችላል።
የኢትዮጵያ የግብር መሠረቱ ያልሰፋበት ምክንያት መደበኛ ያልሆነ ዘርፉ ትልቅ ስለሆነና ያንን ወደ መደበኛ ዘርፍ ማስገባት ስላልቻለ ነው። እንዴት አድርጎ ነው ግን ታዲያ ማስፋት የሚቻለው?
መደበኛ ካልሆነው ባሻገር ኢኮኖሚው ግብርና ላይ ጥገኛ ነው። ግብርና ላይ የሚተዳደረውን ማኅበረሰብ ሰፊ ግብር ልትጭንበት አትችልም፤ በራሱ የሚታገል ነው። አንደኛው የሚሰፋው ኢንዱስትሪያላይዝ ስታደርግ ራሱ ግብርናውን እየተወ እሴት ወደሚጨምረው መደበኛ ዘርፍ ይመጣል። የሠራተኛ ግብርም ለመጣል ይመቻል።
ብዙ ኅብረተሰብ ግብርና ላይ ሆኖ ብዙ ግብር አገኛለሁ ማለትም አይቻልም። የሚደጎም ነው እንጂ ግብር የምትወስድበት አይደለም። መደበኛ ያልሆነው ዘርፍ ላይ አሁንም መንግሥት በጣም ከብዶታል። አንደኛ የሰነድ ጉዳይም ነው። ኹለተኛ አብዛኛው ንግድ እኛ አገር የሚከናወነው በግለሰብ ትውውቅ ነው። እነዚህ ግብይቶች የግብርን ሕግ ላይከተሉ ይችላሉ። ያ ለመንግሥት ከብዶታል። እዛ ላይ ማሻሻልና የመረጃ አያያዝንም ማዘመን ያስፈልጋል። ሌላው ቢሮክራሲው፤ የራሱ የተቋሙ ችግር ነው ታክሱ እንዳይሰበሰብ ያደረገው። ጥሩና በጣም ሙያተኛ የሆነ ተቋም ቢኖር ኖሮ ምንአለባት መሰብሰብ ይቻል ይሆናል።
ግን በኢትዮጵያ ሁኔታ ሙያተኛ ተቋም ማድረግ ይቻላል? የብሔርም ጉዳይ ግምት ውስጥ የሚገባም ከመሆኑም አኳያ፤ ይህንን ማድረግ ከባድ አይደለም?
ኢትዮጵያ ውስጥ ችግር የፈጠረው መሠረታዊ ነገር ኢኮኖሚ እድገት ትመኝና የፖለቲካ ጉዳይ ደግሞ ይነሳል። ኢኮኖሚ እድገት ትፈልጋለህ፤ ይሄ ደግሞ ሙያተኛ ተቋም ነው የሚፈልገው። በተመሳሳይ መንግሥት አብሮ ሌሎች ግቦችንም ይዞ ይመጣል። ለምሳሌ የፓርቲ አባሎቻቸውን ከላይ እስከ ታች ይሞላዋል። የኢኮኖሚ እድገት ይህን አይፈልግም፤ ባለሙያ ሰዎች ነው የሚፈልገው። እንዲህ ስትቀላቅልበት ልክ ያለፍነው 15 ዓመት የታየው ችግር ይመጣል። ልማታዊ መንግሥት ትላለህ ግን ልማታዊ መንግሥት የሚፈልገውን ነገሮች አታደርግም። አንደኛው ሙያተኛ ቢሮክራሲ ነው።
ሙያተኛ ቢዝነስን ሊደግፍ የሚችል፣ በሙያው የተመረጠ፤ መንግሥት በተወሰነ ደረጃ ነው ፖሊሲ የሚያወጣው እንጂ ከላይ እስከ ታች ፖለቲከኛ ሊሆን አይገባም። ፖለቲከኛ የፖለቲካ ፓርቲ ተጠሪ ነው እንጂ የአገር ተጠሪ አይደለም። ብሔራዊ ፍላጎትን የሚያስቀድም ከፖለቲካ ወጣ ያለ ባለሙያ ያስፈልጋል። እውነት እድገትን የምንፈልግ፣ ብዙ ታክስ የምንፈልግ ከሆነ የፖለቲካ ጉዳዮችን ከዚህ ማውጣት ሳይሻል አይቀርም። የብሔር ኮታ እናሟላለን ካልን ደግሞ ያኛውን ዓላማ [በኢኮኖሚ ማደጉን] መተው ነው።
ኹለቱ ዓላማ በጣም የሚጻረር ነው። ማመዛዘንም ያስቸግራል። አንድ ሰው የብሔር ኮታ እሞላለሁ ብሎ የኢኮኖሚ እድገት ሊያስብ ወይም ብዙ ግብር እሰበስባለሁ ሊል አይችልም። መንግሥት ግልጽ ሆኖ የብሔር ጉዳይ የሚፈታበትን ሌላ መንገድ ማሰብ አለበት። አንድ ሰው በብሔሩ እንደ ማንኛውም ሰው ለፍቶ አድሮ የሚሻሻልበት እኩል እድል መፍጠር ነው። መወዳደሪያውን ማስተካከል እንጂ ድልድሉ ላይ ማስተካከል ብዙ አያስኬድም። እስከሚገባኝ ድረስ የትም ዓለም ላይ መወዳደሪያ ነው የሚስተካከለው፣ እንጂ ኮታ እየተደረገ ማስገባት ሁላችንንም ይዞ ነው የሚወርደው። እዛ ላይ መሥራት ነው፤ አንድ ሰው በብሔሩ ምክንያት ያለው ስርዓት የሚያገለው ከሆነ፣ ያን መቅረፍ ነው። መወዳደሪያ ከተመቻቸ በኋላ ሰዎች እንዲወዳደሩ ማድረግ ያስፈልጋል። ችግሩን በኮታ እፈታዋለሁ የተባለ እንደሆነ ንቅነቅ አንልም። ሙያተኛ ሰዎች የሚያስፈልጓቸው ተቋማት አሉ፤ እዛ ቦታ ላይ ብሔር አያስፈልግም።
ተቋማት የፖሊሲ ግዴታ አለባቸው ይባላል፤ በንጽጽር አየር መንገድ እና ቴሌን ብንይዝ፣ በአንድ ሠራተኛ ብዙ ያሠራል። የሚያዋጣኝን ብሎ ይይዛል። ሌሎች ግን አላስፈላጊ ክፍሎች ጭምር አሉ። እንዴት ማመጣጠን ይቻላል?
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚወዳደርበት ገበያ ምንድን ነው፤ ቴሌኮም የሚወዳደርበትስ? የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደ ቴሌ ልዝረክረክ ቢል ከገበያ ነው የሚወጣው። አየር መንገድ የሚወዳደረው በጣም ጠንካራ በሆነ ዘርፍ ነው። አየር መንገድ በመዝረክረክ በገበያው መቆየት አይችልም። አየር መንገድ በገበያ ሕግ እንዲመራ የተተወ ነው። ለዛ የሚመጥን ቁመና በራሱ ፈጥሯል። የውስጡም ባህሪ እንደዛው ነው። ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችል ባህል አዳብሯል።
ኢትዮ ቴሌኮም እንደዛ ዓይነት ገበያ ውስጥ አይደለም ያለው፤ የሚወዳደረውና ጫና የሚፈጥርበት ኃይል የለም። እንደፈለገ ላለመሥራት ሁኔታው ተመቻችቶለታል። እናም ያለበት ዘርፍ ወሳኝ ነው። አየር መንገድ አመራር ‹ጣልቃ የምትገቡብን ከሆነ መዝለቅ አንችልም› ሊል ይችላል። አየር መንገድ በዓለም ላይ ብርቱ ፉክክር ያለበት ዘርፍ ነው። ዘርፉ ተወዳዳሪ መሆን ይፈልጋል፤ ሌላ የፖለቲካ ፍላጎትና መሰል ዓላማ መቀላለቅ አያስፈልግም፤ ዘርፉም ያንን አይፈልግም። ኢትዮ ቴሌኮም ጋር ስትመጣ የአገር ውስጥ ገበያ ነው፣ ጥበቃ ይደረግለታል፣ ብቸኛ ነውና መንግሥት እንክብካቤ ያደርግለታል። ወደፊት አዳዲስ የቴሌ ተቋማት ሲገቡ እናያለን፤ በቀደመ አካሔዱ ይቀጥላል አይቀጥልም የሚለውን።
ንግድ ባንክን ማየት ትችላለህ፤ የግል ባንኮች ሲገቡበት ያደረገው ጥረት አለ። ምንአልባት በደርግ ጊዜ እንዲህ አልበረም፤ አሁን ግን ብዙ ተወዳደሪና ገበያውን የሚነጥቀው አለበት፤ የቢራ ኢንዱስትሪውም እንደዛው። እና ውድድር ያስገድዳል። ውድድር ከሌለ ግን እንደፈለጉ ውጤታማ ላለመሆን በሩን የከፈተላቸው መንግሥት ነው። የፖለቲካ ማስፈጸሚያ ያደረጋቸውም ለዛ ነው እንጂ ውድድር ውስጥ ቢሆኑ እንደዛ ላያደርጉ ይችሉ ነበር።
አንዳንድ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ቴሌን የግል መደረጉ ፕራይቬት ሞኖፖሊ ነው የሚወስደን እንጂ ሌላ ለውጥ አያመጣም ይላሉ።
ኢትዮ ቴሌኮም ብቻ አይደለም፤ እሱ ወደ ኹለት ይሰነጠቃል ነው የተባለው። አንደኛው መሰረተ ልማት ላይ ሲሰራ፣ ኹለተኛው ኔትወርክ አቅራቢ ነው። ሌላም ተጨማሪ ኹለት ፈቃድ ይሰጣል። ሦስት ሆኑ ማለት ነው፤ ሦስት ከሆኑ እንዴት ነው ፕራይቬት ሞኖፖሊ የሚሆነው፤ አይሆንም። ሦስት ከሆኑ መንግሥት የሕግ ክትትሉን ማሳደግ ነው። እሱን ካሳደገና ሦስትም ሆነው፣ መቆጣጠር ይችላል። ሦስት ከሆኑም ውድድር ይኖራል፤ መንግሥት ክትትሉ ላይ ነው መሥራት የሚኖርበት።
መንግሥት ኢኮኖሚካል አቅሙን ያጣል የሚለውስ፣ በተለይ ተቋማቱ የበጀት እጥረትን ከመሙላት አኳያ ትልቅ ድርሻ ስላላቸው?
በመጀመሪያ ደረጃ በአንድ ተጠቃሎ የተያዘ ስለነበር ነው ያን ያህል ትርፍ የነበረው። ይህም አለአግባብ ኅብረተሰቡን እየስከፈለ ነው። ቀጥታ ባልሆነ መንገድ ግብር እየተቀበለ ነው ማለት ይቻላል። ኢትዮ ቴሌኮም የሚሰጠው አገልግሎት ከሌሎች አቅራቢዎች አንፃር በጣም ውድ ነው፤ አላግባብ ነበር ሲወስድ የነበረው። አሁን ሦስት በሚሆን ሰዓት መጀመሪያ የግል ሲደረግ በሽያጭ የሚገኝ ገንዘብ አለ። 49 በመቶ ቢሸጥ ራሱ፣ ከመሰረተ ልማት ብዙ ገንዘብ ነው የሚገኘው።
በኹለተኛ ደረጃ እነዚህ ድርጅቶች ታክስ ይከፍላሉ። እና ከሦስት ድርጅቶች ታክስ እናገኛለን። የባንክ ዘርፉን ስናይ፣ ብዙ ታክስ ይገኛል። ከንግድ ባንክ በተጨማሪ ከግል ባንኮች የሚገኘው ታክስ ቀላል አይደለም። መንግሥት በፊት ታክስም ትርፍም ያገኝ ነበር፤ አሁን ታክሱን ያገኛል፤ ትርፉን ባያገኝም መጀመሪያ የሸጠበት ገንዘብ እጁ ላይ አለ። አሁንም ደግሞ የበለጠውን ይቆጣጠራል። ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ ይሆናል። ዋናው እንደውም ኅብረተሰቡን መጥቀሙ እንጂ የሚያገኘው ትርፍ አይደለም። የባከነውንም ማሰብ ያስፈልጋል። እነዚህ ነገሮች ሲካተቱ የግል መደረጉ ይጠቅማል፤ መንግሥት ግብሩን ይሰበስባል፣ ትርፍም ያገኛል፤ መጀመሪያ የሚሸጥበትን ገንዘብም ያገኛል። ከዛ በላይ የሚያሳስበው እነዚህ የሚመጡ ኩባንያዎች ግብር በአግባቡ ይከፍላሉ አይከፍሉም የሚለው ነው።
እዚህ ላይ ለምን ፈሩ?
እነዚህ ትልልቅ ኩባንያዎች በብዙ አገር የተንቀሳቀሱና ብዙ አገር የሚሠሩ ናቸው። ገቢውን እንደፈለጉ ማንቀሳቀስ ይችላሉ። ብዙ አገልግሎት እናገኛለን ብለው ከሌላ ተቋም በተለያየ ክፍያ ሰበብ ገቢ ሊሰበስቡ ይችላሉ። ከትልልቅ ኩባንያዎች የምሰጋው በጣም ባለሙያ አላቸው፤ ብዙ አገራት ይሠራሉ። እዚህ ያለው ኩባንያ የአመራር አገልግሎት አገኘሁ ብሎ ከሌላ አገር ትልቅ ክፍያ ይመጣል፤ ትርፉ ወደሚፈለግበት ይወስዱታል። የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ላይ ምን ያህል ባለሙያ አለው። ከሌሎች አገራት መረጃ መጋራቱ ምን ያህል ነው? የኩባንያው ዓለማቀፋዊ ምልልስ አለው ወይ? የትልልቅ ኩባንያዎች ትልቁ ችግር ግብርን ማሸሽ ነው። እና ኢትዮጵያ የሚገባትን ድርሻ ታገኛለች ወይ ነው።
ትርፍን በውጪ ምንዛሬ በሕጋዊ መንገድ ማስወጣትስ?
ለዚህ የውጪ ምንዛሬ ያስፈልጋል። የኢንቨስትመንት አዋጅ ላይ ትርፍን በውጪ ምንዛሬ የማስወጣት ጉዳይ አለ። ኩባንያዎችም ይህን ይጠይቃሉ። እዚህ ኢንቨስት እድርጉ እየተባሉ ነበር። ምክንያቱም አገሪቱ የነበራት የውጪ ምንዛሬ በጣም ችግር ውስጥ ስለነበር ነው።
እና መጀመሪያ ሲገዙ አኛ እናገኛለን፣ ከዛ ትርፋቸውን እናወጣለን በሚሉ ሰዓት ወረፋ ጠብቁ መባላቸው አይቀርም። እና ይህን አምነውበት ነው የሚመጡት። ከበቂ በላይ አጥንተውት ነው የሚመጡት። ምንአልባት ማስፋፊያ ላይ ሊያውሉትም ይችላሉ፤ ቅድሚያ ሊሰጣቸውም ይችላል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ላይ ሊያስብበት የሚገባ ነገር የለም፤ ለተወሰነ ዓመት ገንዘብ እንዳያወጡ ወይም እዚሁ ኢንቨስት እንዲያደርጉ?
እሱም ላይ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ጉዳዮችም ላይ መስማማት ይኖራል። ሠራተኛ መበተን ይኖራል፤ ህንጻና ትርፍ መሬቶች እንዲሁም እቃዎች ይኖራሉ። ለትርፍ ስለሚሠሩ ምክንያታዊ ናቸው፤ ጥቅም ላይ ያልዋሉትን ያስወግዳሉ። ንብረት መሸጥ፣ ከውጪ አገር ባለሙያ ማምጣት ያሉ ነገሮች ሲኖሩ፤ በተጨማሪ አናሳ ስለሚሆኑ መብት ይጠይቃሉ። መንግሥት እንደፈለገ እንዲወስን ላይፈልጉ ይችላሉ። ስለዚህ በሁሉም ጉዳይ ላይ በሰነድ ላይ የሚኖርና የሚታይ ነው።
ሌላው አሁን ያለው እንቅስቃሴ የአገር ባለሀብችን ከግምት ያስገባ አይደለም ይባላል። በተወሰነ መልኩ የሚገቡበት መንገድ መመቻቸት የለበትም?
ለዜጎችም መታሰብ ነበረበት። ለምሳሌ እንደ ኢትዮ ቴሌኮም ያሉትን 10 በመቶ በላይ እንዲገዙ ማድረግ ይቻል ነበር። ማንም ሰው ሼር እንዲገዛ ማድረግ ይቻላል። እንደዛ ቢደረግ የተሻለ ይመስለኛል። የውጪ ምንዛሬውን እንፈልገዋልን፣ ግን ለውጪ ዜጎችና ኩባንያ እንደሚሸጠው ለግለሰቦች መሸጥ ነበረበት። ለተራ ዜጎችም የተወሰነ እንዲገዙ እድሉን ቢሰጥ በጣም ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ።
የግልና የመንግሥት አጋርነትን በተመለከተም፣ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ናቸው የተፈጠሩት፤ አደጋም አለው። እስከ አሁን መንግሥት ያሳወቀው መንገድ እና ኀይል ላይ ነው። የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በዚህ ላይ ልምዱም ያላቸው አይመስለኝም፤ እናም የውጪዎቹ ናቸው የሚመጡት። መንግሥትም ትኩረቱ እነርሱ ላይ ነው፤ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችንም እንዲገቡበት ቢያበረታታ ጥሩ ነው።
በአይኤምኤፍ እና ዓለም ባንክ የተደረጉ የገንዘብ ድጋፎችን በበጎ ጎን ማየት የምችልበት እድል የለም ይሆን፤ ከዚህ በፊት እንደ ምሳሌ ግብጽ የተጠቀሙበት አገራት ስላሉ?
አንዳንዶች ምንዛሬውን ተለዋዋጭ ሲያደርጉ ካፒታል አካውንቱንም ይለቁታል። ኢትዮጵያ ካፒታል አካውንቱ ዝግ ነው። ማንም የውጪ ዜጋ ኢትዮጵያ አካውንት ውስጥ ማስቀመጥ አይችልም፤ ገደብ አለው። ስለዚህ የኢትዮጵያ የወለድ መጠን ከፍተኛ ስለሆነ፣ ብዙ ሰው ነው የሚያስገባው፣ ሰባት በመቶ ለማግኘት። እና ብዙ የውጪ ምንዛሬ ይመጣል።
እና ተለወዋጭነቱ ሲታሰብ እነዚህ ነገሮችም ታስበው መሆን አለበት። ከካፒታል አካውንቱና ከውጪ ንግዱ ጋር አብሮ ተጣምሮ። ምን ምን አብሮ ሔዷል የሚለውንም ማየት ያስፈልጋል። የግብጽ ሌላው እንቅስቃሴ ቱሪዝምን ጨምሮ እንዴት ነበር የሚለውን ማየት ያስፈልጋል። አሁንም የምለው የውጪ ንግዱን ሳያሻሽሉ ወደዛ መሔዱ ጥሩ አይመስለኝም።
ነገር ግን የውጪ ንግድ ገቢ 10 ዓመት ምንም ለውጥ ሊያሳይ አልቻለም ነበር።
አዎን እሱን ነው ማየት ያለብን። ማኑፋክቸሪንግ ተስፋ ተጥሎበት ነበር። በተለይ ኢንደስትሪያል ፓርኩ ለምን ሊሠራ አልቻለም፣ ሠራተኛ ይለቃል፣ ደሞዙ ዝቅተኛ ነው፤ የብቃትና የሙያ ሥነምግባር ጉዳይ ችግር አለ፣ የኤሌክትሪክ ችግር አለ፤ የመንግሥ ቢሮክራሲ ችግር አለ፤ እና ለምንድን ነው ይሄ ችግር የመጣው የሚለውን ማየት ያስፈልጋል።
ታድያ መንግሥት አሁን ምን አማራጭ አለው?
በማሻሻያ ጥቅሉ ያልተካተተ ነገር አለ፤ ቢሮክራሲውን በሚመለከት ምንም ማሻሻያ የለም። መንግሥት እንዴት ነው የራሱን ቢሮክራሲ ሳያሻሻል፣ ኤክስፖርትን የሚሻሻለው? የኃይል አቅርቦትና የሠራተኛ መልቀቅ ችግር እየፈጠረባቸው ነው።
ምንአልባት የኢንዱስትሪ ፖሊሲን መለስ ብሎ ማየት አያስፈልግም?
ኢንዱስትሪያል ፓርክ በገጠር ያለውን ወጣት የቀን ሠራተኛ ማድረግ ነው።ብዙ ሰዎችም ሊቀጥር ይችላል። ነገር ግን ግልጽ የሆነ የመደብ ልዩነት ነው የሚያመጣው። በአገሪቱ የኢንዱስትሪ ፓርክ ብታበዛ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የቀን ሠራተኞች ታበዛለህ የተወሰኑ ደግሞ የተሻለ ኑሮ ይኖረዋል። እና ማቀላቀሉ ይሻላል። እኔ በግሌ የምመርጠው ትንንሽ የሆኑ፣ ወጣቱን በየገጠር በትንሽ ከተሞች፣ ለምሳሌ ከቤት ግንባታ ጋር አያይዞ፤ ብዙ ቴክኖሎጂ የማይፈልጉ፤ ትንንሽ ቢዝነሶችን ማስፋት ነው። እና አቀናጅቶ መሔዱ ነው የሚሻለው።
እሱ ግን ተሞክሮ ሳይሠራ ቀርቷል፤
እኔ የምለው ዋናው የፖለቲካ ችግር ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በሥልጣን ለመቆየት ሲባል ባለሙያዎች ሊሠሩት የሚገባውን የፖለቲካ ፍላጎት ይቀላቀልበታል። እውነት ሥራ ፈጣሪ ናቸው ወይስ የፖለቲካ ሰዎችን ለማስገባት ተብሎ የሚደረግ ነው። ብዙ ጊዜ በሩጫ የሚደረግም ነገር አለ፤ ለሚድያ ሽፋን ተብሎ። እንጂ በሚገባ ታስቦበት ባለሙያ መክሮበት፣ ቢዝነሱ ተመዝኖ የሚሰጥ ብድር ነው ወይ፤ ለሚድያ እና ለፖለቲካ ፍጆታ ተብሎ ነው። እና በጥልቀት ማየት ያስፈልጋል። የፖለቲካ ጣልቃ ገብነቱን በጣም መቀነስ ያስፈልጋል። ደጋፊ ናቸው አይደሉም ማለቱን ትቶ በባለሙያ መመልመል ያስፈልጋል።
ከማይክሮ ፋይናንስ ወደ ግል ዘርፉ ማለትም ወደ ባንክ ቢሔዱ ጥሩ ነው ይላሉ?
እኔ ለምሳሌ ባንክ ቢሠራው ይሻላል የመንግሥት ማይክሮ ፋይናንስ ከሚሠራው። ብንክ ትንሽ ኪሳራውን አይቶ ነው። መንግሥት ተጨማሪ ትንሽ ድጋፍ ማድረግ ነው። ብድር ወይም ድጎማ ሊሆን ይችላል። አቅሙም የመገምገሙም በባንኮች ይሻላል፤ የፖለቲካ ፍላጎት የላቸውም፤ የትርፍ ፍላጎት እንጂ። ፖለቲካ በተወሰነ ጉዳይ አቅጣጫ ማሳየቱ ነው የሚሻለው።
በሌላ በኩል አገር በቀል የሪፎርም አጀንዳን እንዴት ያዩታል?
የዋሽንግተን ስምምነት ኮፒ ነው የሚመስለው። የግል ዘርፉን ማልማት፣ የመንግሠት እዳ ቅነሳ፣ የልማት ድርጅቶችን ተጋላጭነት መቀነስ፣ ባንኮች የግል ዘርፉን እንዲደግፉ ነጻነት መስጠት፤ ራሱን የዋሽንግተን ስምምነትን ነው የሚመስለው። በጣም ተመሳሳይ ነው። አሁን ይፋ ወጣ እንጂ መንግሥት ከተቋማቱ ጋር ለረጅም ጊዜ ሲነጋገሩበት የነበረ ነው።
እና ሊበራሊዝምን ወደ መተግበሩ እየሔድን ነው ይላሉ?
አዎን! ኒዮ ሊበራሊዝም ወደ መከተሉ እየሄድን ነው የሚመስለው። አንዳንድ አገራትኮ እንደውም ይቀላቅላሉ፤ የእኛ ትንሽ የወጣ ነው የሚመስለኝ። የመንግስት የልማት ደርጅቶችን ትሸጣለህ፣ ኢንደስትሪያል ፖሊሲ ይኖረናል ይላል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም የተወሰነ ወደ ኅብረተሰብ እንገባለን ይላል። በአይ ኤም ኤፍ ግን መንግሥት ግብር የሚሰበስበው ለድህነት ቅነሳ እና ዋና ዋና መሠረተ ልማት ነው። ይህ ማለት ኢንደስትሪያል ፖሊሲ ይኖረናል አይኖረንም የሚለውን አጠራጣሪ ነው የሚያደርገው። እንደ አይ ኤም ኤፍ ያሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ‹ኢንዱስትሪል ፖሊሲ› የሚባለውን ቃልም አይወዱትም።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ኒዮ ሊበራሊዝም ላይነሳ ሞቷል፤ ተቀብሯል ብለው ነበርና፤ አሁን መነሳቱ ሲታይ ትክክለኛ አቅጣጫ ላይ ነን ብለው ያስባሉ?
ያንንም ከግምት ውስጥ ማስገባት አለብን፤ ለምን ያኛው ሳይሳካልን ቀረ? ምንስ ጋር ስኬታማ ነበር፣ ምን ጋር አይደለም የሚለውን በደንብ ማየት ያስፈልጋል። ያለፈው 15 ዓመት የተከተልነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ መንግሥት ያኛውንም ልማታዊ መንግሥት ነው ይል ነበር። ግን የተወሰኑት ላይ ነው እንጂ መቶ በመቶ ልማታዊም አይደለም። አንደኛው የልማታዊ መንግሥት መገለጫ ‹ፕሮፌሽናል ቢሮክራሲ› ነው። ጃፓንም ኮርያም በጣም ጥቂት የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነው ያለው፤ በሚኒስትር ሹመት ብቻ ነው። እንጂ እንዳለ ያለው ባለሙያ ነው።
እኛ አገር ይሄ ይጎድለዋል። የመንግሥት ጣልቃ ገብነቱ ይበዛል። ታሪካዊ መሠረቱ የእነርሱም የእኛም ይለያያል። የእነርሱ ታሪካዊ መሠረት የውጪ ወረራ ስጋት መኖር፣ የአገር ውስጥ ሀብት አለመኖር እንዲሁም የአገር ውስጥ ሰፊ ማህበረሰብ መኖር። እኛ ደግሞ ምርጫ ቀውስ ያመጣው ድንጋጤ ነው። እና በታሪኩ መሠረቱ በይዘት ይለያያል።
እነርሱ ደግሞ የመንግሥት ሰፊ ጣልቃ ገብነትም የለውም። የግል ዘርፍን የሚደግፍ መንግሥት ነው።የተወሰነ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት አለ፤ የእኛ ደግሞ በሰፊው ከማይገባው ደረጃ ገብቷል። ምግብ እስከመነገድና ገበያ ማዕከል መክፈት ገብቷል።
እነርሱ የውጪ ንግድ አካሔድም ሆነ ግብም ነበራቸው። የእኛዎቹ ግብም አላስቀመጡም። እና ከስህተት መማርና የበፊቱን ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። በፖሊሲ ደረጃ ግን በጣም በጣም ጥሩ ነጥቦች አሉ፣ በፖሊሲ ደረጃ። በ1994 የወጣው ኢንዱስትሪያል ፖሊሲ፣ በይዘቱ በጣም ጥልቅ ነው በትግበራ ችግር ቢኖርም። ከበፊቱ ዶክመንቶችን ማገላበጥ።
ለምን ይሆን?
አያምኑበትም። የገበያ ውድቀት የመንግሥት ውድቀት የሚሉት ነገር አለ። የልማታዊ መንግሥት ደጋፊዎች የሚሉት፣ የገበያ ውድቀት ስላለ የግድ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ያስፈልጋል ይላሉ። ትክክል፤ አንዳንዴ መንግሥት ደግሞም የግሉ ዘርፍ እንዲገባ ማድረግ አለበት ብለው ያምናሉ። እነዛ ደግሞ መንግሠት መደገፍ ከጀመረ፣ ያ የግሉ ዘርፍ መንግሥት ላይ ተለጣፊ ይሆናል። እና መንግሥት ከሚያመጣው ውድቀት፣ ገበያው የሚያመጣው ውድቀት ትንሽ ነው።
እኛ አገርም ያየነው መንግሥት በመግባቱ ብዙ ነው ያጣነው። የፕሮጀክት መጓተት፣ የእዳ መከመር፣ ለገበያ ቢተው ኖሮ ያን ያህል ላያመጣ ይችላል። ይሄ ክርክር አለ። ግን የመንግሥት ውድቀትም የታረመባቸው አገራት አሉ። ለምሳሌ እነ ታይዋን፣ ጃፓን፣ ኮርያ ተሳክቶላቸዋል። ባህሉ ሳይረዳቸው አልቀረም። ሌላው ምሁሩ የማደግ ግብ ነበረው። ማደግ ምንም ድርድር ውስጥ የማይገባ ነበር። ኅብረሰተብ ውስጥ አገር ወዳድ የሆነ፣ እንደ አገር የሚያስብ ምሁር ስላላች ጠቅሟቸዋል።
እኛ አገር ስትመጣ ክፍፍል አለ፤ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነትም ሰፊ ነው። ይህም ብዙ ኪሳራ ይዞ መጣ። እዛ ተጠያቂነትም አለ። ፖለቲከኞች ለቢሮክራሲው ነጻነት ቢሰጡትም ይቆጣጠሩታል። ሕዝቡም ሚድያውም ይከታተላል። እኛ አገር ግን ሁሉም በአንድ ነገር ተጠፍንጎ ስላለ፤ ሚድያውም አይከታተልም። እና ፖለቲካው ብዙ ነገር አበላሸብን እንጂ ከነርሱ ልምድ መውሰድ እንችል ነበር። ተቋማት ኢንዱስትሪያል ፖሊሲን እንዲደግፉልን የሚከታተለው ነፃ አካል ያስፈልገዋል። የሚድያ፣ የፖለቲካ፣ የሕዝብ ክትትልም ያስፈልገዋል።
ባንኮች የሚሰጡትን ብድር 27በመቶ በቦንድ መልኩ እንዲገዙ የሚያስገድደው ሕግ መነሳቱ የዋጋ ግሽቱን ያባብሰዋል የሚል ፍራቻ አለ። ምን ያስባሉ?
ይሄ ገንዘብ 86 ቢሊዮን ብር ይደርሳል። በአንዴ ሳይሆን በሚቀጥለው አምስትና ስድስት ዓመት ተከፍሎ የሚያልቅ ይመስለኛል። ስለዚህ በዓመት ብሔራዊ ባንክ ለግል ባንክ የሚሰጠውን መገመት ይቻላል። ይህ ማለት ያላቸው ተቀማጭ ሒሳብ በጣም ነው የሚጨምረው። ይህ ማለት በሦስት አራት እጥፍ የማደበር ወይም ከሚለቀቅላቸው ገንዘብ ሦስት አራት እጥፍ የማበደር አቅምን ነው የሚያሳድገው። ባንኮቹ ሰፊ የሆነ የብድር ፍላጎት ስላለ የለቀቁት እንደሆነ ገበያ ላይ ያለው የገንዘብ መጠን ይጨምራል፤ ጥርጥር የለውም። ብሔራዊ ባንክ ይህን ነገር በደንብ ማሰብ አለበት። ብሔራዊ ባንክ የሚጠቀምባቸውን ሌሎች መንገዶች ካሏቸው፣ ግሽበት ሊያመጣ ስለሚችል፣ መሣሪያዎችን በደንብ ማሰብ ያለበት ጊዜ ነው።
ከላይ የተጠቀሱት እንዳሉ ሆነው በባለፈው ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበቱ ደግሞ 20 በመቶ ደርሷል። ይህንንስ እንዴት ያዩታል?
የፖለቲካ አለመረጋጋት ላይ የሆነች አገር ላይ ስር ነቀል የኢኮኖሚ ለውጥ ማድረግ ችግር ሊፈጥር ስለሚችል አይመከርም። በጣም መሠረታዊ የሆነ ለውጥ ነው የሚያስፈልገው። አገር በተረጋጋችበት ሁኔታ ቢሆን የተሻለ ነበር። ለምን እንዳቻኮሉት አልገባኝም። ተጽእኖው ቀላል ላይሆን ስለሚችል ጥንቃቄ ያስፈልጋል። አሁን ያለው የዋጋ ግሽበት የብዙ ሰዎችን ሕይወት አናግቷል፣ የበለጠ እንዳያናጋው ጊዜ መውሰድ ያስፈልጋል። ከዛም በፊት የብሔራዊ ባንክ አቅምን ማሳደግ ያስፈልጋል።
ዓለም አቀፍ የፋይናንስ አዘጋገብ (አይ ኤፍ አር ኤስ) ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ግዢ ያላቸው ድርጅቶች በግዴታ መተግበር አለባቸው ተብሏል። በዚህ ደረጃ ሊተገበር የሚችል ነው?
መጀመሪያም ሳይታሰብ የተጀመረ ጉዳይ ነው። የዓለም አቀፍ ፋይናንስ ዘገባ በምዕራቡ ዓለም ብዙ ተጠቃሚ አለው። በፍላጎቱ ነው የተፈጠረው። እኛ አገር በተወሰነ ጫና አመጣነው። ወደ ትግበራ ሲገባ በአገሪቷ ውስጥ ስንት የሂሳብ ሠራተኛ አለ የሚለውን ከግምት ውስጥ መንግስት አላስገባም። ይህን አዘጋገብ የሚረዳ የሂሳብ ባለሙያ በመቶ ነው ያለው። ዘገባው ቀድሞ ከነበረበት ደረጃም ሰፈቷል፣ ሌላው ቀርቶ ዘገባውን አይቶ መረዳት እንኳ የሚችል ተጠቃሚ የለም። ይሄ ሁሉ በሆነበት ሁኔታ የአንድ ሚሊዮን ግዢ ያላቸውን እንዲተገብሩ ማስገደድ ተገቢ አይደለም።
ወጪውም ቀላል አይደለም። አንድ ሚሊዮን ግዢ ላለው ኩባንያ፣ ለባለሙያ ብዙ ብር የሚከፍልበት ምክንያት አይገባኝም። ባንኮች በዚህ ላይ ሲታገሉ በርካታ የሒሳብ ሠራተኞች አይገቡበትም። እና እነዚህን ማካተቱ ጥቅሙ አይታየኝም፣ ተጠቃሚም የለውም። ዝም ብሎ ወጪ ማብዛት ነው።
ስለዚህ አዋጁን ማረም ያስፈልጋል?
የግድ ማረም ያስፈልጋል። በዋናነት የሰው ፍላጎት ያለባቸውና ትልልቅ ቢዝነሶች እንጂ ትንንሽ ቢዝነሶች ምንም አይሠራላቸውም። ትንንሾቹን እንደውም ከዚህ ማውጣት ነው። በፈቃደኝነት ካደረጉ ጥሩ ነው፤ ያንን ማበረታታት ነው። አንድ ሚሊዮን ገቢ ያለው ሠላሳ እና አርባ ሺሕ ለባለሙያ መክፈል የለበትም። ተጠቃሚ ለሌለው ነገር ለምን ተብሎ ነው ወጪ የሚወጣው። የሚጠቀመው ሰው ቢኖር ጥሩ ነበር። ከምሳሌ የባንክን ሪፖርትን በተወሰነ ደረጃ የሚጠቀም አለ። የአንድ ትንሽ ቢዝነስ ማንም አይጠቀምበትም።
ባለፉት ዓመታት የአካውንቲንግ ልምዱን እድገት እንዴት ያዩታል?
አኔ ኦዲት ላይ ነበርኩ። ረጅም ዘመን የነበረ ሙያ ነው። ከተለያየ ዓለም የተወሳሰደ ነው። ከትምህርት የሚወሰድ አለ። በተግባር መጀመሪያ የጀመሩ ሰዎች ያላቸው አሻራም አለ። ኢትዮጵያ ትጠቀም የነበረው፤ ወጥ ስታንዳርድ አልነበረም። ትምህርት ቤት የሆነ ነገር ትማራለን፣ ኩባንያዎች ከአገራቸው ይዘውት የመጡት ልምድ አለ፣ የራሳቸው ሪፖርት የሚያወጡም አሉ። መንግሥት ደግሞ 1979 ያወጣው የኢንዱስትሪ መመሪያ አለ። የዚህ ሁሉ የተቀላቀለ ነው፤ የግልም የለም። ወጥ አይደለም፤ ለንጽጽር የሚመችም አይደለም። ይሄ አዘጋገብ ወጥ የሆነ አሠራር እንዲኖር አድርጓል። ያ ጥሩ ጎኑ ነው። ዝም ብሎ ከመውሰድ ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ይሆናል አይሆንም የሚለውን መመርመር ያስፈልጋል። በጥሩ ጎን ዓለም አቀፍ ተቋማት ለንጽጽር ይረዳቸዋል። ኦዲቱም በራሱ መንገድ ነው ያደገው። የባለሙያ አለመኖር፤ የሥነ ምግባር ችግር፣ የደሞዝ መውረድ ተጠያቂነት አለመኖሩ የራሱን ችግሮች ፈጥሯል።
የባንኩ ዘርፍ ላይ ለውጥ እንደሚመጣ ይታሳባል፤ በቀጣይ አምስት ዓመት ምን ይጠብቃሉ?
እንደውም አሁን ነው ያሳሰበኝ፤ 16 የግል ባንክ አለ። አገሪቱን በሙሉ በቅርንጫፍ ሞልተውታል። ውድድር ያለበት ዘርፍ ነው። ባለፉት ስምንት ዓመታት የገቡ ትንንሽ ባንኮች እንደ ትልልቆቹ ትርፋቸው አልጨመረም፤ እዛው ላይ ናቸው። ይሄ ባለበት፣ በዛ ላይ የብሔራዊ ባንክ ቢል ተነስቷል፤ የማበደር አቅማቸውን የሚያሳድጉበት እድል የለም፤ 11 ባንክ ገበያው ላይ መምጣት ማለት ዘርፉ ምን ሊሆን፣ የትስ ቅርንጫፍ እንደሚከፈት አላውቅም። አዲስ አበባ እንደሆነ በየሰፈሩ የባንክ ቅርንጫፍ አለ። 11 ባንኮች ቢጨመሩበት፤ አሁን ካለው ላይ በምን ያህል ሊጨምር እንደሚችል ማሰብ ነው።
የዛሬ አራት ዓመት ብሔራዊ ባንክ ብዙ ባንኮች ተሰልፈውበት ነበር። ያኔ ካፒታሉን ወዲያው ነው ወደ አምስቶ መቶ ሚሊዮን ብር ያሳደገው፣ እናም በምሥረታ ላይ የነበሩ ብዙ ባንኮች ፈርሰዋል። ምክንያቱም በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ባንክ ወድድር ይፈልጋል፤ አዲስ ምርት እንዲመጣ፣ ደንበኞች የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ ያግዛል። የመኪና እና የቤት ብድር ይመጣል። ግን ከዛ በላይ ፋይናንስ ዘርፉ የተረጋጋ መሆን አለበት። ውድድሩ ችግር ውስጥ ይዟቸው የሚገባ መሆን የለበትም። ብሔራዊ ባንክ እንዳለፈው ካፒታል ይጨምራል ብዬ ነበር የጠበኩት፣ ግን 11 ባንክ ተጨምሮበት፤ አሁን ያለው የዘርፉ ሁኔታ ትንሽ ያሳስበኛል።
የትርፍ መጠናቸው ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል ከሚል ስጋት ነው ይህን ያሉት?
የብድር ጥራትስ? ለምሳሌ ቁጠባ መሰብሰብ ያስፈልጋል። ይህን ለማድረግ ወይ ካሉት ላይ መውሰድ ነው ወይም ከሚፈጠረው ላይ ነው። ይህን ለማድረግ ብዙ ወጪ ይፈልጋል፤ እንደበፊት ላይሆን ይችላል። ከፍተኛ ትርፍ ማግኘቱ ይቀንሳል። በርግጥ የባለአክሲዮኖች ትርፍ ክፍፍልም እየቀነሰ ነበር። በቅርቡ ለኹለት ዓመት ብቻ ነው የተረጋጋው፣ 31 በመቶ አማካይ ሆኗል። እሱ ብቻ ሳይሆን የብድር ጥራት ያሳስባል፤ የማይመለሱ ብድሮች መብዛታቸው አይቀሬ ነው። ጥራታቸው/አቅማቸው ዝቅተኛ ለሆኑ ተበዳሪዎች ብድር ሊያቀርቡ ይችላሉ።
መቆጣጠሩ ግን ላይከብድ ይችላል። ብሔራዊ ባንክ ለተለመደው አሠራር አቅም አላቸው፤ እነዚህ ባንኮች አዲስ ቴክኖሎጂ ይዘው የሚመጡ አይደሉም፤ የተለመደ ነገር ነው። ኢስላሚክ ባንክም ቢሆን ልምድ አለን። ንግድ ባንክ ለዚህ የሚሆን መስኮት አዘጋጅቶ አገልግሎት ይሰጡ ነበር። ስምንት ዓመት ቀላል አይደለም፤ አሁን ሙሉ ለሙሉ ያንን አገልግሎት የሚሰጥ መምጣቱ ከዛ የተለየ ነገር አያመጣም። ምንአልባት የሚሰጡት ብድር መጠን ይጨምራል። ከዛ ውጪ ውድድራቸው ነው የሚያሳስበኝ።
ባንኮቹ መዋሐድ አለባቸው ብለው ያስባሉ። ከትንሽ ትልልቅ ባንኮች እና ብዙ ትንንሽ ባንኮችስ የትኛው ይሻላል ይላሉ?
ሁኔታው ነው የሚፈጥረው። ለምሳሌ በእንግሊዝ አሁን ያሉት ትልልቅ ባንኮች አምስት ናቸው። ትንንሾቹ በጣም ብዙ ናቸው። በተለያየ መልክ፤ አንዳንዶቹ ክልላዊ አንዳንዶቹ ሰፈራዊ፣ አንዳንዱ የተወሰነ ኅብረተሰብ ክፍል ላይ ሲያተኩሩ ሌሎች የተወሰኑ ምርቶች ላይ ነው ትኩረታቸው። ያ የአንድ አገር ታሪካዊ አጋጣሚ የሚፈጥረው ነው። ስላስገደድካቸው አይሆንም፤ እንዋሐድ ቢሉም አሁን ባለው ሁኔታ ፈቃደኛ ላይሆኑ ይችላሉ። የማስገደዱ ነገርም አይታየኝም። ውድድሩ በጣም አሳሳቢ ከሆነ ካፒታል መጨመሩ ላይ ነው መታየት አለበት።
ማይክሮፋይናንስ ተቋማት ወደ ባንክነት ሲቀየሩ ፤ የመጀመሪያ ግባቸው ድህነት ቅነሳ በመሆኑ፣ በድህነት ውስጥ ያለውን ሕዝብ ላያገለግሉ ይችላሉ የሚል ስጋት አለ። ይህ ክፍተት አይፈጥርም?
ትልቁ አገሪቱ ውስጥ ያለው አነስተኛ የብድር አገልግሎት ሰጪ አማራ ብድር ተቋም ነው። ስለዚህ አማራ ክልል ላይ የሚፈጥረው ክፍተት አለ። አሁን ተቋሙ ታች ድረስ ወርዶ ቀበሌና ወረዳ ደረጃ ብድር ይሰጣል። ያንን ጥሎ የሚመጣ ከሆነ ክፍተት ይፈጠራል። እዛው እየሠራ ለምን ሌላ አጋዥ ባንክ አይፈጥርም። ያለውን ወደ ባንክ የሚቀይር ከሆነ፣ ምንም ጥርጥር የለውም፤ አገልግሎት የሚሰጠው የኅብረተሰብ ክፍል በፍጹም የተለየ ነው የሚሆነው፣ እናም ሰፊ ክፍተት ይፈጥራል። እና ይህን ማሰብ ያስፈልጋል።
ኢስላሚክ ባንክን ከሐይማኖት ጋር የማገናኘት ነገር በስፋት ይስተዋላል። እዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?
እንደ እኛ ባለ ኅብረተሰብ ውስጥ ሰው ሃይማኖታዊ እይታ ሲኖረው ለእኛ አዲስ ነው። ሐይማኖታዊ ስያሜ ይዞ ሲመጣ ብዙ ሰው ሐሳብ ላይ ይወድቃል። ግን መታወቅ ያለበት የተለመደውን የባንክ አገልግሎት የማይጠቀም የኅብረተሰብ ክፍል አለ። ምሥራቁ የኢትዮጵያ ክፍል ስንሔድ ሙስሊሙ ኅብረተሰብ፣ አዲስ አበባም ብዙ ነጋዴ፣ ብድርም ተቀማጭ የማይጠቀም ብዙ የኅብረተሰብ ክፍል አለ። ይህ ኅብረተሰበ ክፍል በሐይማኖት ምክንያት ከፋይናንስ አገልግሎት ርቋል።
ይህን ኅብረተሰብ ከሐይማኖት ተጣጥሞ የሚሔድ የፋይናንስ ምርት ይፈልጋል፤ ሰፊ ክፍተት አለ። እንደ ንግድም ሲታሰብ ተደራሽ ያልሆነ ገበያም አለ። እነዚህ ሰዎች ሐይማኖታዊ ፍላጎት ብቻ ኖሯቸው አይደለም ባንክ ለመክፈት ያሰቡት። ገበያም ስላለ ነው። እነዚህ ሰዎች ሰፊ ክፍተት እንዳለ አውቀዋል፤ መደበኛውንም ሆነ ሌላውን የባንክ አገልግሎት የማይጠቀም ሰው አለ። ስለዚህ ባንኮቹን የመሠረቱ ሰዎች ለዛ ኅብረተሰብ ክፍልም አገልግሎት ለመስጠት ከሐይማኖቱ የተጣጣመ የፋይናንስ አገልግሎት አቅርበውለታል። ከሐይማኖት ጋር ተጣጥሞ የሚቀርብ ሌላ ብዙ አገልግሎት አለ፤ ምግብን ጨምሮ። እኛ አገር ምግብ የሚቀርበው ከሐይማኖት ጋር ተጣጥሞ አይደለም እንዴ? በውጪም እንደዛው ነው።
እንደውም ወደፊት ኢንሹራንሱንና ማይክሮ ፋይናንሱን መጨመር አለበት። ሰፊ የሆነ የኅብረተሰብ ክፍል በሐይማኖታዊ ምክንያት አገልግሎቱን እየተጠቀመ አይደለም። በፋይናንሱ ስርዓት አልተካተተም። ስለዚህ ይህን ኅብረተሰብ ክፍል ለማካተት ምስረታው አስፈላጊም ተገቢም ነው። ከአገሪቱ ሕግ ጋር የተጣጣመ ነው። ሊያሳስበን የሚገባው የአገሪቱ ሕግ ተከብሯል ወይ፣ የመከታተል አቅም አለ ወይ፣ እንደ ብሔራዊ ባንክ ደግሞ ይህን አገልግሎት ያውቀዋል ወይ፣ መቆጣጠር እንችላለን ወይ? የሚሉት ናቸው።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here