ኢትዮጵያ ባሕላዊ እንኳን ሊባል የሚችል ፌዴራሊዝም ነበራት?

0
859

በቅርቡ የብሔር፣ ብሔረሰቦች ቀን አከባበርን ተንተርሶ የተለያዩ የፌዴራሊዝም እና የብሔሮች መብት ጉዳዮች እየተነሱ ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል አነጋጋሪና በተለየ መልኩ ጎልቶ የተሰማው ሐሳብ የፌዴራሊዝሙ ጉዳይ ሲሆን ኢሕአዴግ ካመጣው የፌዴራል ስርዓት በፊት ኢትዮጵያ ፌዴራሊዝምን ተግብራለች ወይስ አልነበራትም የሚለውም ጉዳይ የብዙዎችን ቀልብ የሳበ ጉዳይ ሆኖ ነበር።
ከዚህ ጥያቄ ጋር ተያይዞ ሌላኛው ሐሳቦችን የሚከፍለው ጉዳይ ደግሞ የዋለልኝ መኮንን የብሔሮች መብት ጥያቄ ነው። ከእርሱ አምስት ገጽ ጽሁፍ እስከ መጨረሻ አሟሟቱ ድረስ የመገናኛ ብዙኀን ነባርም አዳዲስም መረጃ ሲያስጨብጡን ከርመዋል። ምንም እንኳን እርሱ እንደጀመረው በሰፊው የሚታመነው የብሔሮች ጥያቄ ባልተቀናጀና ያንን ያህል ቀልብ ባልሳበ መንገድ ቀድሞም ብልጭ ድርግም ይል የነበር ቢሆንም ዋለልኝ ግን ጉዳዩን በዘመኑ ልኂቃን ልብ ውስጥ እንዲታተም አድርጎታል። ሐሳቡን በማንገብም እነዚሁ ልሒቃን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ከጎናቸው በማሰለፍ መጀመሪያ ዘውዳዊ ስርዓቱን በመቀጠልም ወታደራዊ አስተዳደሩን ገርስሰው የብሔር ፖለቲካን ከአገሪቱ ዋና ዋና የፖለቲካ ሐሳቦች ተርታ እንዲሰለፍ አስችለውታል።
ፌዴራሊዝም በባሕላዊ መንገድም ቢሆን ነበር የሚለው አስተያየት የሚመነጨው በኢትዮጵያ ዘውዳዊ ስርዓት ውስጥ ያለውን የሥልጣን ክፍፍል በማየት ነው። በዋነኛነት ዘውዳዊ ስርዓቱ አንድ አጼ ወይም ንጉሠ ነገሥት በማዕከላዊ ገዢነት የሚሾሙበትና ሌሎች ንጉሣን እና መሪዎች አካባቢያቸውን የሚያስተዳድሩበት ነበር። ንጉሳኑ እና መሪዎቹ ለአጼው ግብር የሚገብሩና የሚታዘዙ ናቸው። ነገር ግን የሚያስተዳድሩት የራሳቸው ግዛት ያላቸው፣ ግብር የሚሰበስቡ እና የራሳቸው ጦር የሚያደራጁም ናቸው። ለምሳሌ በአጼ ምኒልክ ጊዜ ንጉሥ ተክለሃይማኖት የጎጃም፣ አባ ጅፋር የጅማ፣ ካዎ ጦና የወላይታ አስተዳዳሪዎች ነበሩ። ሦስቱም ግብር የሚያስገብሩ ሲሆኑ የየራሳቸው ጦርም ነበራቸው። ከአባ ጅፋር በስተቀር ኹለቱ ለአጼ ምኒልክ አንገብርም ብለው ጦርነት ገጥመዋቸው የነበረ ሲሆን የኋላ ኋላም በመሸነፋቸው እንዲገብሩ ተገድደዋል። ይሁንና ከሽንፈታቸውም በኋላ ግዛታቸውን ያስተዳድሩ ነበር። አንዳንድ ምሁራን ይህንን ዓይነቱን ስርዓት እንደ ባሕላዊ ፌዴራሊዝም ሲወስዱት ሌሎቹ ደግሞ አይቀበሉትም።
ከማይቀበሉት ውስጥ ታዋቂው የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር እና ፖለቲከኛ መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር) ይገኙበታል። እርሳቸው እንደሚሉት በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን በሚታወቀው መንገድ የፌዴራሊዝም መሰረቱ ዴሞክራሲ መሆን አለበት። ፌዴራሊዝም ማለት ራስን በራስ ማስተዳደር እንደሆነ የሚያስረዱት መረራ የአካባቢ አስተዳደሮቹ በሕዝቦቻቸው ተመርጠው ይሁንታ ያገኙ ያለመሆናቸው እና በጉልበት ሕዝቦቻቸው ላይ ንጉሥ ነኝ ብለው መቀመጣቸው ዴሞክራሲያዊ ያልሆነ በመሆኑ ፌዴራላዊ ሊሆን አይችልም ባይ ናቸው። አጼ ዮሐንስ፣ አጼ ምኒልክ እና አጼ ኃይለሥላሴ እስከ ጣልያን ወረራ ድረስ የራስ አስተዳደርን በተወሰነ መልኩ አቆይተው እንደነበር መረራ አስታውሰዋል።
ነገር ግን ከጣልያን ወረራ በኋላ አጼ ኃይለሥላሴ ይህንን መብታቸውን ወስደውባቸዋል። በመሆኑም ራስን በራስ የማስተዳደሩ አመጣጡም ሆነ አጠፋፉ ተለጥጦ እየተወሰደ ወደ ፌዴራሊዝም እንዲጠጋ ይደረጋል እንጂ የሚያስኬድ አይደለም ይላሉ። ሆኖም ፌዴራሊዝም የሚኖረው የጋራ አገዛዝና የራስ አስተዳደር ሲኖሩ ስለሆነ ኹለቱም በሌሉበት ፌዴራሊዝም ነበር ማለት አይቻልም ያሉት መረራ “የነበረው ነገር እስከ ገበራችሁልኝ ድረስ አልነካችሁም ነው። እንደ እነ አባ ጅፋር እና ወለጋ አካባቢ ያሉት መስፋፋቱን ቶሎ የደገፉት ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ እድል ሲሰጣቸው በአርሲ አካባቢ ያሉት ኦሮሞዎች ግን ተሰብረዋል” ሲሉ ምልከታቸውን በግልጽ አስቀምጠዋል። በማዕከላዊውም ሆነ አካባቢያዊ አስተዳደሩ ሕዝብ ተሳታፊ እስካልሆነ ፌዴራሊዝም ማለቱ የተለጠጠ ነው። እንደ መረራ አረዳድ የፌዴራሊዝም ባሕሪይ የነበረው ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ተመልሳ ስትዋሀድ የነበረው ግንኙነት ነው።
ከዛሬ ኹለት ሳምንት በፊት የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ ዋና ዳይሬክተር እና የፖለቲካ ተንታኙ ጃዋር መሐመድ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ደግሞ ይህ አወቃቀር (ግብር መሰብሰቡና ጦር ማደራጀቱ) የአካባቢ አስተዳደሮቹ በአገር ውስጥ ያሉ ትናንሽ አገሮች ያስመስላቸዋል። ሁኔታው ፌዴራሊዝም የሚመስል ቢሆንም የአካባቢ እና ማዕከላዊ አስተዳደሮቹ ግንኙነት በሕግ ማዕቀፍ የታሰረ ያለመሆኑ ዘመናዊውን ፌዴራሊዝም እንዳይሆን ያግደዋል ብለው ነበር። በባሕላዊ ፌዴራሊዝምነት መወሰድ እንደሚቻል ግን አስቀምጠው ነበር።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት ሲሳይ መንግሥቴ (ዶ/ር) የሰጡት ሙያዊ አስተያየት የዘውዳዊ ስርዓቱን ለኹለት ከፍሎ የሚያይ ነው። ጉዳዩን ከሥሩ ሲያስረዱም በዓለም መንግሥታት ላይ የሚታየው የአስተዳደር ስርዓት ሲዳሰስ ባህላዊ መልክ ያለው የፌዴራል ሥርዓት የሚባል አለ ይላሉ። ለምሳሌ በታሪክ የእስራኤል 12ቱ ነገዶች አንድ ማዕከላዊ አስተዳደርና ነገዶቹ ደግሞ ራሳቸውን ያስተዳድሩ ስለነበር የፌዴራል ስርዓት በእነሱ እንደተጀመረ ይነገራል። ከዚያ ሌላም በስዊዘርላንድ ካንቶኖች የሚባሉ የአስተዳደር አካባቢዎች ነበሩ ያሉት ሲሳይ የጋራ አስተዳደርም ኖሯቸው ለረጅም ጊዜ በኮንፌዴሬሽን መልክ አብረው የቆዩበት እና በቅርብ ጊዜ የተሟላ የፌዴራል ስርዓት የመሰረቱበት ሁኔታ እንደ አንድ ባህላዊ የፌዴራሊዝም ስርዓት ይቆጠራል ብለዋል። ሌላ ያነሱት ምሳሌ ዘመናዊ አስተዳደር በአሜሪካ በ1781 (እ.ኤ.አ.) ከመመስረቱ በፊት በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር የነበሩ ዐሥራ ሦስት ግዛቶች የጋራ አመራር እንዲኖራቸው አድርገው ኮንፌዴሬሽን መመስረታቸው ነበር። ዐሥር ዓመት አካባቢ ከተጠቀሙበት በኋላ እየተዳከመ ሲሔድ ወደ ተሟላ ፌዴሬሽን የሔዱበት ሁኔታ አለ። ስለዚህ እንደዚህ ዓይነቶቹን ባህላዊ ፌዴራሊዝም በሚል ልንወስዳቸው እንችላለን ብለዋል።
የኢትዮጵያን ያገረ መንግሥት ታሪክ ዋቢ ያደረጉት ሲሳይ ብዙዎቹ ንጉሠ ነገሥታት ወይም አጼዎቹ በሥራቸው ንጉሦች፣ ራሶች፣ ደጃዝማቾች ተብለው አካባቢያቸውን የሚያስተዳድሩበት ሁኔታ ነበረ። ያንን ስናይ ባህላዊ የፌዴራል ስርዓት በአንድ ወይም በሌላው መልኩ ተግባራዊ ይደረግ እንደነበር ልናነሳ እንችላለን። ነገር ግን በዘመናዊ አስተሳሰብ የፌዴራላዊ ስርዓት ከሚጠይቀው መስፈርት አንጻር በእርግጠኝነት የፌዴራል ስርዓት ባህሪይ ነበረው ለማለት ያስቸግራል ሲሉ ያስረዳሉ። ትክክለኛው ሊሆን የሚችለው ያልተማከለ አስተዳደር ለዘመናት በእዚች አገር ላይ ነበር የሚለው ነው ብለዋል።
ዘመናዊ የፌዴራል ስርዓት ለመሆን የሚቀሩትን ነገሮች ሲተነትኑ ዘመናዊ ፌዴራሊዝም የሚመሰረተው በተጻፈ ሕገ መንግሥት መሆኑ እና የእኛ አገሩ አስተዳደር ደግሞ ይኼ እንደሚጎለው ይጠቅሳሉ። ይህ ሕገ መንግሥት ፖለቲከኞችም ሆኑ የተቀሩት ልኂቃን ተነጋግረው የማዕከላዊ እና የአካባቢ መንግሥታት የሚኖራቸው የሥልጣን ክፍፍል በግልጽ የሚያስቀምጥ መሆኑን ያስረዳሉ። በኹለተኛነት አሉ ሲሳይ ፌዴራል ስርዓት የሚያስፈልገው የምርጫ ስርዓት ነው። መረራ ቀደም ብለው ገልፀውት እንደነበረው ስርዓቱ የሚቋቋመው በጋራ አመራርና በአካባቢ አስተዳደር (ራስ ገዝ የሆነ) እንደሆነ ሲሳይም ያስረዳሉ። የጋራ አመራሩም ይሁን የአካባቢ አስተዳደሩ የሚመራው በምርጫ በሚወከሉ ፖለቲከኞች ነው። መሰረታዊ መርሆዎቹ እነዚህ ናቸው በማለት ሲሳይ ያስረዳሉ።
ከዚያ ባሻገር ምርጫ ለማድረግና ሕገ መንግሥትን በጋራ ለማጽደቅ እና የሥልጣን ክፍፍል ለማድረግ ዴሞክራሲያዊ የሆነ ውይይት በፌዴራላዊ ስርዓት ምስረታ ላይ እንደሚያስፈልግ ሲሳይ ያብራራሉ። “በንጉሠ ነገስታቱ ጊዜ እንዲህ ዓይነት ነገር የለም። ጉልበት ያለው ንጉሠ ነገሥት ወደ ሥልጣን ሲመጣ ሌሎቹን ይጨፈልቃቸዋል። ለምሳሌ ንጉሠ ነገሥ ኃይለሥላሴ በየአካባቢው የነበሩትን ንጉሶች፣ ራሶችና ሌሎችም አስተዳዳሪዎችን አስቀርቶ የራሱን ታማኞች ከማዕከል እየላከ ነበር የሚሾመው። የጅማው አባጅፋርን፣ የጎጃሙ ንጉስ ተክለሃይማኖትን እና የራስ ኃይሉን የዘር ሐረግ አስተዳደር ያስቀረው ልጆቹንና ሌሎች ታማኝ ሰዎችን በመላክ ነው። የወሎን የራስ አስተዳደር ያስቆመው ልጁን አስፋወሰንን በመላክ ነበር። ስለዚህ ጠንካራ ንጉሠ ነገሥት ወደ ሥልጣን ሲመጣ የአካባቢ አስተዳዳሪዎች ይዳከማሉ። ማዕከላዊ መንግሥትን የሚመራው ንጉሠ ነገሥት ደካማ ሲሆን ደግሞ የአካባቢ ንጉሦችና ራሶች ይጠናከሩና የማዕከላዊ መንግሥቱ ይዳከማል” ሲሉ ሁኔታውን ከታሪክ ጋር አጣቅሰው የተነትናሉ።
ስለዚህ ያልተማከለው አስተዳደር በአጼ ዮሐንስ፣ በአጼ ምኒልክ እና ከዚያም በፊት በነበሩት ነገሥታት ነበር ማለት ይቻላል የሚሉት ሲሳይ አጼ ኃይለሥላሴ ግን ይህንን የአስተዳደር ዘይቤ ሙሉ በሙሉ አስወግደውታል፤ ከዚያም በኋላ ደርግም ያልተማከለውን አስተዳደር በግልጽ ያስቀረበት ሁኔታ እንዳለ አብራርተዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ዋለልኝ መኮንን የብሔሮችን መብት አስመልክቶ ያነሳውን ጥያቄ የፌደራሊዝሙ ምሁር ሲሳይ ሲገመግሙ ይህንን ሐሳብ ባመጣበት በአጼ ኃይለሥላሴ ጊዜ ብሔሮች ራሳቸውን የማስተዳደር ሥልጣናቸው ተቀምቶ በዘር ሐረግ እንኳን ሲመሩ የነበሩት የወሎ፣ የጎጃም፣ የጅማ እና ሌሎችም የአካባቢ አስተዳደሮች በማዕከላዊ ሹመኞች መቀየራቸውን ያስታውሳሉ። ከዚያ በፊትም በምኒልክ የተዳከሙ የአካባቢ አስተዳደሮች አሉም ሲሉ ሁኔታው ምን ያህል እየተቀየረ እንደመጣ አጽንኦት ይሰጣሉ። ስለዚህ ዋለልኝ በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ ይህን ሐሳብ ሲያቀርብ ፍጹም የሆነ የተማከለ አስተዳደር እንደነበር በመጥቀስ የአካባቢ አስተዳደር ብሎ ነገር እንዳልነበር ይደመድማሉ። ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበት ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ ካለመኖሩም በተጨማሪ የመልማት እድላቸው በጣም ዝቅተኛ እንደነበር ያስረዳሉ። ከዚያም አልፎ የአንዳንዶቹ ብሔር ብሔረሰቦች ቋንቋ ተንቆ ሥማቸውን መቀየር የደረሱበት ወይም በባሕላቸውና በቋንቋቸው እንዳይኮሩ እኩል እውቅና እንዳያገኙ የተደረጉበት ወቅት ነበር ብለዋል።
ዋለልኝም ታስሮ በነበረበት ጊዜ የታዘበው ነገር ይህንን ስሜት እንዲያመጣ አድርጎታል ብለው ሲሳይ ያምናሉ። “በዚያን ጊዜ በብዛት ታስረው የነበሩት ኦሮሞዎችና ኤርትራዊያን ሲሆኑ ከዚያ ቀጥሎ ትግሬዎችም ሌሎቹም ብሔር ብሔረሰቦች ነበሩበት። አብረውት የታሰሩትን ሰዎች እያናገረ የታሰሩበትን ሁኔታ ሲረዳ እና በትምህርትም ይሁን በአጠቃላይ ሕይወቱ የታዘበውን ሲያጤን ይኼ ስርዓት ለሕዝቦች የሚጠቅም አይደለም እና ብሔር ብሔረሰቦች ተገቢውን እውቅና አላገኙም የሚል አስተሳሰብ አዳበረ። በተለይም የአማራ እና ትግሬ ባሕልና ሃይማኖት የበላይነት ያለበት አገር ነው የሚል መደምደሚያ ነው የነበረው። የአማራ እና ትግሬን ሸማ እና የክርስትና ሃይማኖት እንዲቀበሉ ጫና ይደረግባቸዋል ብሎ ያምን ነበር። ነገር ግን በኋላ ላይ ትግሬ የምትለዋ እየቀረች አማራ የምትለዋ እየጎላች መጣች። የትግራይና የኦሮሞ የብሔር ፖለቲከኞች አማራን በጠላትነት ፈርጀው ስለተነሱ ትግሬ የምትለዋን እየተዉ አማራ የምትለዋን እያጎሉ መጡና አማራ ላይ የተሳሳተ ግንዛቤ ለማስያዝ ተሞከረ” በማለት ያብራራሉ። ለብሔርተኞች እንደ ጀግና ለአንድነት አቀንቃኞች ደግሞ “የውሾን ነገር ያነሳ…” በሚል መንገድ በአብዛኛው የሚወሰደው ዋለልኝ መኮንን ያነሳው የብሔሮች መብት አሁንም መቋጫው የራቀ ጥያቄ ይመስላል።
እንደመደምደሚያ
በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ዘውዳዊ አገዛዝ የዘመናዊ ፌዴራሊዝምን ባህሪያት እንደማያሟላ መረራ ጉዲናም፣ ጃዋር መሐመድም ሆኑ ሲሳይ መንግሥቴ ይስማማሉ፤ ነገር ግን ቀደምት የመንግሥት አስተዳደሮች ፌዴራሊዝም የሚመስል ነገር እንደነበራቸው ደግሞ ሦስቱም አይክዱም። በሌላ በኩል መረራ ጉዲና ከኹለቱ ራቅ ባለ ሁኔታ ፌዴራል ነበር ማለት ጉዳዩን መለጠጥ ነው ብለው ቢያምኑም የሥልጣን ያልተማከለ መሆን ሳይሆን በዘመናዊ ፌዴራሊዝም ውስጥ ዴሞክራሲ ያለው ቁልፍ ቦታ ያለመኖሩን ነው እንደ ማሳያ የወሰዱት። ጃዋር እና ሲሳይ ባሕላዊ ፌዴራሊዝም ተብሎ ሊወሰድ እንደሚችል ያምናሉ። ነገር ግን ሲሳይ በዋነኛነት በኃይለሥላሴ እና በትንሹም ቢሆን በምኒልክ ጊዜ የነበረው የራስን በራስ ማስተዳደርን የመጣስ እንቅስቃሴ ከዚያ በፊት የነበረው ስርዓት ላይ ስለሚያጠላ ያልተማከለ አስተዳደር ተብሎ ቢጠቃለል ይሻላል ብለው ያምናሉ። በመሆኑም የዘውድ አገዛዙ መጨረሻ አካባቢ ከታየው ጥሰት በፊት ባህላዊ ፌዴራሊዝም ኢትዮጵያው ውስጥ ነበር፤ ነገር ግን በኃይለሥላሴ ጊዜ ሒደቱ ተቀልብሶ ሥልጣን ተማክሏል።

ቅጽ 2 ቁጥር 59 ታኅሣሥ 11 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here