ገጽታውን የቀየረው የባንክ ዘርፍ

0
1165

ከዛሬ 14 ዓመት ጀምሮ ጀምሮ ኑሮውን በታላቋ ብሪታኒያ ያደረገው መክብብ ገብረኪዳን ለዓመታት በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን አፍሰስው ባንክ መመሥረት ፍላጎታቸው ከሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች አንዱ ነው። ይህንን ማድረግ ግን ለመክብብ ቀላል አልነበረም። በተለይም የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፉት ኹለት አስርት ዓመታት በፋይናንስ ዘርፍ ላይ እንዳይሰማሩ በመከልከሉ መክብብን ጨምሮ ብዙዎች በትውልድ አገራቸው ላይ ህልማቸውን ማሳካት አልቻሉም።
ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ነገሮች የተለየ አቅጣጫ ይዘው መምጣት ጀምረዋል። በተለይም በተለያዩ የአውሮፓ አገራት እና በአሜሪካ ጉብኝት እና የተለያዩ ውይይቶች ካደረጉ በኋላ፣ መንግሥት ከዲያስፖራው ማኅበረሰብ ጋር አብሮ ለመሥራት ቃል መግባታቸውን ተከትሎ፣ መንግሥት የተለያዩ ስር ነቀል ለውጦችን እያደረገ ይገኛል።
ከእነዚህም መካከል ዋነኛው የባንክ ኢንዱስትሪ ላይ ዲያስፖራዎች መዋዕለ ነዋይ እንዲያፈሱ እና ከፈለጉም ባንክ እንዲመሰረቱ መፍቀድ ሲሆን፣ ይህ ዓይነቱ ለውጥ እንደ መክብብ ላሉ ሰዎች ጥሩ ዜና ይዞ መጥቷል።
ታዲያ መክብብም ጊዜ አልፈጀበትም። ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ለዓመታት ሲፈልጉና ሲመኙት የነበረውን ባንክ ለማቋቋም እንቅስቃሴ ጀምረዋል። ‹‹የኢትዮጵያ ውስጥ የፋይናንስ ዘርፍ ትልቅ አቅም ያለው እና ያልተነካ ሲሆን፣ በትንሽ ግብይት ብዙ ማትረፍ የሚቻልበት ገበያ አለ›› ሲል መክበብ የባንኩ ዘርፍ ላይ ለምን መግባት እንደፈለገ ያስረዳል። ‹‹እኔም ሆነ ሌሎች መሥራቾች በዘርፉ ላይ ልምድ ስላለን ውጤታማ ለመሆን ጊዜ አይወስድብንም።››
ይህንን አይነት የራስ መተማመን እንዲሁም ውጤታማ እንደሚሆኑ እና በባንክ ዘርፉ ላይ ባለሙሉ ተስፋ የሆኑ ጥቂት አይደሉም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሥልጣን ከያዙ በኋላ ለውጦች መምጣታቸውን ተከትሎ፣ ከአምስት በላይ እስላማዊ፣ ኹለት መደበኛ፣ ኹለት የኮንስትራክሽንና የቤት (ሞርጌጅ) እና ኹለት ዳያስፖራ ባንኮች በምሥረታ ላይ ሲሆኑ፣ አምስት ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ወደ መደበኛ ባንክ ዘርፋቸውን ለመቀየር እንቅስቃሴ ጀምረዋል።
የባንኩ ዘርፍ በኢትዮጵያ – ከየት ወደ የት
የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ግንባር ከዛሬ ሦስት አስርተ ዓመታት በፊት ሥልጣን መያዙን ተከትሎ ድብልቅ የኢኮኖሚ ስርዓት አገሪቷ ተግባራዊ አድርጋለች። ከዚህም ጋር ተያይዞ የባንኩ ዘርፍ ሙሉ ለሙሉ ለኢትዮጵያውያን የግሉ ዘርፍ ተዋንያኖች ክፍት ተደረገ። በዚህም ከ1986 እስከ 1991 ድረስ የተለያዩ ባንኮች የተመሠረቱ ሲሆን፣ አዋሽ ባንክ ከኹሉም ቀዳሚው ነበር።
ዳሽን፣ አቢሲኒያ፣ ሕብረት፣ ወጋገን እና ንብ ባንኮች የአዋሽን ፈለግ በመከተል ተመሥርተው ሥራ ጀምረዋል። እነዚህ ተቋማት የመጀመሪያ ትውልድ ባንኮች የሚባሉ ሲሆን፣ እስከ 1999 ድረስ ለስምንት ዓመታት ምንም ዓይነት ተፎካካሪ ወደ ኢንዱስትሪው አልገባም።
ይሁን እንጂ፤ ከ1999 አስከ 2005 ድረስ ባለው ጊዜ 10 የግል ባንኮች ተመሥርተዋል። እነዚህም ኹለተኛው ትውልድ ባንኮች ተብለው ይጠራሉ። በአሁኑ ሰዓት 16 የግል እና አንድ የመንግሥት ንግድ ባንኮች በሥራ ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ባለፉት ኹለት አስርት ዓመታት ያላቸው የቅርንጫፍ ብዛት በ30 እጥፍ አድርጎ 6 ሺሕ ደርሷል። በተመሳሳይ አንድ የባንክ ቅርንጫፍ በኢትዮጵያ በአማካይ 18 ሺሕ ሦስት መቶ ሰዎች የሚያስተናግድ ሲሆን፣ ከዲጂታል ባንኪንግ ካለመኖሩ ጋር ተዳምሮ የፋይናንስ አገልግሎቶች ተደራሽነትን አነስተኛ እንዲሆን አድርጎታል።
ምንም እንኳን በባንኮች የተለቀቀ አጠቃላይ ብድር በባለፉት አስርት ዓመታት በ12 ዕጥፍ አድጎ በ2011 በጀት ዓመት 740 ቢሊዮን ብር ቢደርስም፣ ኹለት ሦስተኛ የሚሆነው ብድር የተሰጠው ለመንግሥት ተቋማት እና ለመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሲሆን ቀሪው ለግሉ ዘርፍ ተዋንያን ተሰጥቷል። በዚህም የተነሳ ከፍተኛ ቁጥር የሚጠጉ የግል ኩባንያዎች እና ሥራ ፈጣሪዎች ብድር ባለማግኘታቸው ችግር ውስጥ ከመውደቅም በላይ ዕድገት ሊያሳዩ አልቻሉም። ይህም የፋይናንስ ተደራሽነት አነስተኛ እንዲሆን ምክንያት ሆኗል።
በተጨማሪም በአገሪቷ የሚገኙት የንግድ ባንኮች ትኩረታቸውን በከተማ ላይ በማድረጋቸው በገጠር እና አነስተኛ ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የፋይናንስ አገልግሎት እንዳያገኙ እንቅፋት ሆኗል ሲሉ የተለያዩ የፋይናንስ ባለሙያዎች ያነሳሉ። ይሁን እንጂ የቀድሞ የአቢሲኒያ ባንክ ፕሬዝደንት ሙሉጌታ አስማረ፣ ምንም እንኳን ባንኮች ትኩረታቸው በከተማ ላይ ቢሆንም አሁንም በእነዚህ ስፍራዎች አንድ ቅርንጫፍ ከ2300 በላይ ለሆኑ ሰዎች አገልግሎት እንደሚሰጥ በመጥቀስ፣ አዳዲሶቹ ባንኮች ከተማ ላይ ቢያተኩሩም ችግር እንደማይሆን ጠቁመዋል።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ግሩም ካሳ በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ። ‹‹በከተማም ቢሆን በባንኮች የሚሰጡት አገልግሎቶች አነስተኛ እና ተመሳሳይ ሲሆኑ አጠቃላይ የሒሳብ ደብተሮች ቁጥር ለሕዝብ ቁጥር ያላቸው ንፅፅር እንዲሁም አጠቃላይ የተበዳሪዎች ቁጥር፣ ገበያው ገና እንዳልተነካ ያሳያል›› ይላሉ።
ባለፉት ኹለት አስርት ዓመታት በኢትዮጵያ የተከፈቱ የባንክ ሂሳብ ቁጥሮች በ20 እጥፍ አድገው 20 ሚሊዮን የደረሱ ሲሆን፣ ከሌሎች ከሰሃራ በታች ያሉ አገራት ጋር ሲነፃፀር በጣም አነስተኛ ነው። በአሁኑ ሰዓት 20 በመቶ ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ ኢትዮጵያውያን የሂሳብ ደብተር ያላቸው ሲሆን፣ ይህ 82 በመቶ ዜጎቿ የሂሳብ ደብተር ካላቸው ኬንያ እጅጉን ያነሰ ነው።
ታዲያ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የፋይናንስ ተደራሽነት ለማስፋት የተለያዩ እርምጃዎች የተወሰዱ ሲሆን፣ ባንኮች ቅርንጫፎቻቸውን በ25 በመቶ እንዲያሳድጉ መደረጉ እና የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ ተግባራዊ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
አዳዲስ ባንኮች ምን ይዘው ይመጡ ይሆን?
አማራ ባንክ በመመሥረት ካሉ አዳዲስ የፋይናንስ ተቋማት አንዱ ነው። በቀድሞ የገቢዎች እና ጉምሩክ ኮሚሽነር መላኩ ፈንታ መሪነት በመመስረት ላይ ያለው ባንኩ፣ እስከ አሁን ወደ ኹለት ቢሊዮን ብር ገደማ የሚጠጋ አክሲዮን ለባለድርሻዎች የሸጠ ሲሆን፣ የመሥራች ኮሚቴዎቹም በአሁኑ ወቅት ያሉ የፋይናንስ ችግሮችን ለመፍታት ቃል ገብተዋል።
‹‹ዓላማችን በአሁኑ ወቅት በባንክ ዘርፍ ያሉ ችግሮችን በመረዳት ይህንን ሊፈቱ የሚችሉ ቀላል እና ዘመናዊ አገልግሎቶችን በማቅረብ ትርፋማ መሆን ነው›› በባንኩ ምሥረታ ወቅት ያሉት መላኩ፣ የፋይናንስ አካታችነት በማሻሻል አኳያ ትልቅ ለውጥ ይዘው እንደሚመጡ ተናግረው ነበር። ይህንን ንግግር ያጠናከሩት የባንኩ ምሥረታ ኮሚቴ አባል መሰንበት ሸንቁጤ በበኩላቸው፣ ‹‹መመሥረት የምንፈልገው ተደራሽ ያልሆነኅ ማኅበረሰብ የሚያገለግል ባንክ መፍጠር ነው›› ያሉ ሲሆን፣ ከታችኛው የአስተዳደር መዋቅር አንስቶ ለዜጎች አክሲዮን የሸጥነው ለዚህ ነው ሲሉ አስረድተዋል።
በእርግጥ አማራ ባንክም ሆነ ሌሎች በምሥረታ ላይ ያሉ የፋይናንስ ተቋማት ቃላቸውን ጠብቀው ይህንን ያደርጋሉ የሚለው በጊዜው የሚታይ ነገር ቢሆንም፣ ባንክን መመሥረትም ሆነ መምራት ቀላል እንዳልሆነ በቅርቡ የታዩ ለውጦች ያሳያሉ። ለምሳሌ፤ በአሁኑ ሰዓት አንድ አነስተኛ የባንክ ቅርንጫፍ ለማስተዳደር ከ150 ሺሕ ብር እስከ ግማሽ ሚሊዮን ብር የሚያስፈልግ ሲሆን፣ መጠናቸው ከፍ ያሉ ቅርንጫፎች ደግሞ ከ100 ሚሊዮን እስከ 300 ሚሊዮን ያስወጣሉ።
ምንም እንኳን በምሥረታ ላይ ያሉት ባንኮች ይህንን ማድረግ እንደማይከብዳቸው የሚመሠረቱበትን የካፒታል መጠን በመግለፅ ቢናገሩም፣ ይህም ቢሆን አዋጭ እንደማይሆን በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ከነዚህም መካከል የሕብረት ባንክ የቦርድ ኃላፊ የሆኑት ዛፉ ኢየሱስወርቅ አንዱ ናቸው።
‹‹በምሥረታ ላይ ያሉ ባንኮች ተፎካካሪ እና ወጤታማ መሆን ከፈለጉ ቅርንጫፍ ማስፋፋት ላይ ሳይሆን ማተኮር ያለባቸው የዲጂታል ፋይናንስ ቴክኖሎጂ አገልግሎቶችን ማቅረብ ላይ መሆን ይኖርበታል።›› ሲሉም አስተያየት ሰጥተዋል።
የኦሮሚያ ባንክ ፕሬዝደንት አቢ ሳኖ ደግሞ፣ በምሥረታ ላይ ያሉት ባንኮች ቅርንጫፍ ማስፋፋት ላይ ማተኮር እንደሌለባቸው ይገልጻሉ። ‹‹ይህንን ካደረጉ ግን ውጤታማ የመሆን ዕድላቸው ጠባብ ከመሆንም በላይ የገበያ ድርሻቸው አነስተኛ ሊሆን ይችላል›› ይላሉ አቢ።
በምሥረታ ላይ ያሉ ብዙዎቹ ባንኮች የፋይናንስ ዘርፉን ለመቀላቀል ከገፋፋቸው ምክንያቶች አንዱ በሥራ ላይ ባሉ ተቋማት እየተመዘገበ ያለው ትርፍ ሲሆን፣ ይህም ለብዙ አክሲዮን ገዢዎች ዘርፉን ተመራጭ አድርጎታል። ይሁን እንጂ፤ በባለፉት አስር ዓመታት የግል ባንኮች አጠቃላይ ትርፍ ያለማቋረጥ እድገት አሳይቷል። ይህም ባለፈው በጀት ዓመት መጨረሻ ወደ 21 ቢሊዮን ብር ደርሷል።
ይሁን አንጂ፤ የኢንዱስትሪው አማካይ የባለ አክሲዮኖች ትርፍ/ድርሻ ከዛሬ አስር ዓመት በፊት በመቶ ብር 39 ብር የነበረው ወደ 31 ብር ደርሷል። በኢንዱስትሪው የተመዘገበው ትልቁ የባለ አክሲዮኖች ድርሻም በተመሳሳይ ወቅት ከ100 ብር ወደ 63 ነጥብ 2 ብር ወርዷል።
የወደፊት እርምጃዎች
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም ባለፉት 12 ወራት የተለያዩ አዋጆችን፣ መመሪያና ደንቦችን አውጥቷል። የውጪ ምንዛሬ ገቢን ለመጨመር ከተደረጉ ማሻሻያዎች ጀምሮ፣ የኢስላሚክ ባንኮች መቋቋም እና የምንዛሬ ተለዋዋጭ እንዲሆን መፈቀድ ተጠቃሽ ናቸው።
ሌላው ትልቁ ለውጥ የፋይናንስ ዘርፉ ለዳያስፖራው ክፍት መሆኑ ነው። ይህንን የሚመለከተው አዋጅም፣ የባንክ ድርሻ እንዲኖራቸውና በዛ ላይ መዋዕለ ንዋይ እንዲያፈሱ ፈቃድ አግኝተዋል። ይሁንና ድርሻቸውን የሚወስዱት በአገር ውስጥ ገንዘብ እንጂ በውጪ ምንዛሬ አይደለም። ‹‹ይሄ ተስፋ አስቆራጭ ነው፤ በብዙ ድካም ያገኙትን የውጪ ምንዛሬ ይዘው እንዲሸሹ ነው የሚያደርገው›› ይላሉ፤ አዲስ በሚመሠረት የዳያስፖራ ባንክ የመሥራች ኮሚቴ አባል የሆኑ ግለሰብ።
በብሔራዊ ባንክ የተደረገው ሌላው ማሻሻያ ጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማ ትልልቅ ብድሮችን እንዲሰጡ መደረጉ ነው። ይህንን ታድያ በበጎ ጎኑ የሚያዩት አልጠፉም፤ በዚህም ነባሮቹ ትልልቅ አገልገሎት ወደ መስጠት ሲሻገሩ አዳዲስ ተቋማት ከስር ይወጣሉ ተብሎ ይታሰባል።
ከአዲስ ማለዳ እህት ኅትመት ኢትዮጵያን ቢኅነስ ሪቪው መጽሔት የተወሰደ

ቅጽ 2 ቁጥር 59 ታኅሣሥ 11 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here