ከሦስት ዓመት በፊት መቶ ሺሕ ስደተኞችን በግብርና ሥራ ለማሠማራት ቃል ተገብቶ ነበር
በስዊዝርላንድ ዋና ከተማ ጄኔቫ በተካሔደው ዓለማቀፉ የስደተኞች ጉባኤ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ ኢትዮጵያ ለ90 ሺሕ ስደተኞች እና በአካባቢያቸው ለሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የግብርና እና የእንስሳት ልማት ዘርፍ ሥራ ትሰጣለች ሲሉ ቃል ገብተዋል።
ታኅሳስ ሰባት እና ስምንት በተካሔደው ጉባኤ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በተጨማሪም ለ20 ሺሕ ስደተኞች ጥራት ያለው የሙያ ሥልጠና እና ማረጋገጫ ለመስጠት ማሰቧንም ገልጸዋል። ዘላቂነት ባለው መልኩ ለሦስት ሚሊዮን ስደተኞች ታዳሽ ኀይል ለማቅረብም አገሪቱ ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል። በተጨማሪም የኢትዮጵያን የጥገኝነት እና የማኅበራዊ ጥበቃ ዋስትና ለማጠናከርም ቃል ገብተዋል።
እነዚህንም ቃሎች ለመተግበር ከለጋሽ አገራት የሚገኝ ተጨማሪ እና ዳጎስ ያለ እርዳታ እንደሚያስፈልግ ጥያቄ አቅርበዋል። ‹‹ኢትዮጵያ ለስደተኞች እና ለጥገኝነት ጥያቄ አቅራቢዎች ድጋፍ እና ከለላ የመስጠት አኩሪ ታሪክ አላት›› ያሉት ደመቀ፣ ኢትዮጵያ ያሉባት የተለያዩ እንቅፋቶች በሯን በስደተኞች ላይ እንድትዘጋ አላደረጋትም ሲሉ አክለዋል።
ይህን ተከትሎም ኢትዮጵያ የስደተኞችን የመሥራት እና የመንቀሳቅስ መብት የሚያረጋግጥ አዲስ የስደተኞች ጉዳይ አዋጅ ከየካቲት 2011 ጀምሮ በሥራ ላይ ማዋሏ ከተለያዩ ለጋሽ አገራት እና ተቋማት ምስጋናን አስችሯታል። ይህም በአፍሪካ አኅጉር በሥራ ላይ ከዋሉ የስደተኞች ሕጎች ተራማጁ በሚል የተወደሰ ቢሆንም፣ ከአገር ውስጥ ግን ጠንከር ያለ ተቃውሞ አስተናግዶ ነበር። በተለይም በጋምቤላ ክልል ያሉ የተለያዩ ግለሰቦች እና ቡድኖች ድርጊቱ የክልሉን ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ምህዳር የሚቀይር እና ከደቡብ ሱዳን ተሰደው በሚመጡ ስደተኞች ጫና ስር የሚከት ነው ሲሉ ሰላማዊ ሰልፍ ማካሔዳቸውም ይታወሳል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስደተኛ ከሚያስተናግዱ፣ ለስደት መሸጋገሪያነት ከሚመረጡ አገራት ተርታ ስትመደብ፣ የራሷ ከፍተኛ የሆነ የሚሰደድ ዜጋም ያላት አገር ነች። ከዘጠኝ መቶ ሺሕ በላይ ስደተኞችን የምታስተናግድም ሲሆን፣ ከእነዚህ ውሰጥ 46.6 በመቶ የሚሆኑት ከደቡብ ሱዳን የተሰደዱ እንደሆኑ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ መረጃ ያሳያል። ከሶማሊያ የተሰደዱ ሰዎች ቁጥርም 28 በመቶውን ሲይዝ 19 በመቶ ኤርትራ፣ አምስት በመቶ ሱዳን እና ቀሪውን ሌሎች አገራት ይይዛሉ።
አዲስ የፀደቀው አዋጅም እነዚህ ስደተኞች የመኖሪያ እና የሥራ ፈቃድ እንዲያገኙ የሚፈቅድ ሲሆን፣ ከሦስት ዓመታት በፊት በአሜሪካ ኒው ዮርክ ከተማ በተደረገው ጉባኤ ኢትዮጵያ የገባቻቸውን ዘጠኝ ቃሎች ለመፈፀም አንዱ እርምጃ ተደርጎ ይወሰዳል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩም በኒውዮርኩ ጉባኤ ኢትዮጵያ የገባቻቸውን ዘጠኙን ቃሎች አስታውሰው፣ ከተለያዩ አጋሮች ጋር በጋራ በመሆን ለመፈፀም ያደረገችው ጥረት የተሳካ ነበር ብለዋል።
ይህም ከካምፕ ውጪ የሚኖሩ ስደተኞችን እንዲሁም እስከ ከፍተኛ ትምህርት ድረስ ያሉ ስደተኞችን ቁጥር መጨመር እና አዲስ የፀደቀው የስደተኞች ሕግ እና በተለይም የስደተኞችን የመዘዋር መብት ማሻሻሉ ኢትዮጵያ ያሳካችው ቃል እንደነበርም አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት አራት አዲስ ቃሎችን የገባው ከሦስት ዓመታት በፊት በአሜሪካ ኒው ዮርክ ከተማ በተደረገው ጉባኤ ላይ፣ ኢትዮጵያ ከስደተኞች ጋር በተያያዘ የገባቻቸውን ዘጠኝ ቃል ኪዳኖች ለመፈፀም ዘግይታለች የሚል ግፊት እየተሰማ ባለበት ወቅት ነው።
ኢትዮጵያ ይህንን ቃል ተግባራዊ ለማድረግ እንዲያስችላት ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት 202 ሚሊዮን ዶላር በላይ የገንዘብ ድጋፍ ማግኘቷን ከዓለም ባንክ የተገኙ ሰነዶች ይጠቁማሉ። ይህ ገንዘብ በስደተኞች ጉዳይ ላይ የሚያስፈልጉ የሕግ እና የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ከመደገፍ ጀምሮ ስደተኞች እና በአካባቢያቸው የሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለመገንባት የታሰበ ነው።
ኢትዮጵያ በኒው ዮርኩ ጉባኤ 75 ሺሕ ስደተኞችን ከስደተኛ ካምፖች በማስወጣት እና ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው እንዲኖሩ ለማድረግ ቃል ገብታ ነበር፤ መታወቂያ እና የመኖሪያ ፈቃድ እንዲያገኙም እንዲሁ። በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙ ስደተኛ ሕጻናትን ቁጥር ለመጨመር እና ስደተኞች ሊያለሙት የሚችሉትን 10 ሺሕ ሄክታር በመስኖ የሚለማ መሬትን ለማቅረብም እንዲሁ ቃል ገብታ ነበር።
ሆኖም ሕጉ ተግባራዊ መሆን ባለመቻሉ ምክንያት እስከ አሁን ድረስ በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞች ከመጠለያ ጣብያ ውጪ መኖር እና በሕጋዊ ሥራ ላይ መሠማራት እንዳልቻሉ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ባለሞያዎች ተናግረዋል። ለመቶ ሺሕ ስደተኞች የግብርና ሥራ ለሠላሳ ሺሕ ስደተኞች ደግሞ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሥራ እድል ለመፍጠር የተገባው ቃልም፣ እስከ አሁን ተፈፃሚ ባልሆነበት ሁኔታ፣ ተጨማሪ 90 ሺሕ ስተደተኞች በግብርና ሥራ ላይ እንዲሰማሩ የተገባውን ቃል መፈፀም ባይቻል አገሪቱ በለጋሾቿ ዐይን እምነት ሊያሳጣ ይችላልም ይላሉ።
ይህንን ቃል ኢትዮጵያ ፈፅማዋለች ብለው እንደማያምኑ እንዲሁም ለመፈፀምም ከባድ እንደሆነ የሚገልጹት፣ የፌዴራሊዝም መምህር አሁን ባለው የፖለቲካ ውጥረት ውስጥ ስደተኞችን በመስኖ የሚለማ መሬት በክልሎች እንዲያለሙ ማድረግ አዳጋች ነው ይላሉ። ይህም በተለይ በጋምቤላ እና በሶማሌ ክልል ጫናው እንደሚበረታ እና ከመሬት ባለፈ የውሃ እና ሌሎች የተፈጥሮ ሃብቶች አጠቃቀም ላይም እንቅፋት መፍጠሩ አይቀርም ብለዋል። ከዚህ ይልቅ እንብዛም የፖለቲካ መካረር በሌለባቸው የኢንቬስተመንት ዘርፎች ላይ እንዲሰማሩ ማድረጉ የተሻለ ነበር ሲሉ ሐሳባቸውን አጋርተዋል።
ይህ ቃል ከመገባቱ በፊትም ከክልሎች ጋር ግልፅ የሆነ መግባባት እና ፍትኀዊ የሆነ የስደተኛ መስተንግዶ ክፍፍል ከሌለ፣ በካምፕ ውስጥ ያሉ ስደተኞች በነበሩ ጊዜ እንደነበረው ዓይነት መረጋጋት ላይኖር ይችላል ይላሉ።
አገሪቱም አንድ መቶ ሺሕ ሠራተኛ ይቀጥራሉ ተበለው በሚገመቱ የኢንዱስትሪ ፓርኮቿ ውስጥ 30 በመቶውን ለስደተኞች ለመስጠት በኒው ዮርኩ ጉባኤ ቃል ገብታ የነበረ ሲሆን፣ በጄኔቫው ጉባኤ ላይም ይህ ስለመሳካቱ የተጠቀሰ ነገር የለም።
በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የተፈጠረው ሰላም ተከትሎም የስደተኞች ቁጥር አሻቅቧል የሚሉት መምህሩ አያይዘው፣ ይህ በተለይ በከተሞች እየፈጠረ ያለው ጫና ቀላል የማይባል መሆኑን ይገልፃሉ። በተለይም ኹለቱ ሕዝቦች መካከል ያለው የባህል፣ የመልክ እና የቋንቋ አንድነት ስደተኞች ከካምፕ ውጪ በተለይም በከተሞች መገኘታቸውን እንዲያሻቅብ አድርጓል።
‹‹ስደተኞችን ተቀብሎ ማስተናገድ በዓለም አቀፍ ሕጎች የየአገራት ግዴታ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ግን በተጠና አኳኋን የስደተኞችን ምዝገባ እና የሥራ እድል ፈጠራ መምራት ካልቻለ በሌሎች የአፍሪካ አገራት የምናየው አይነት የሕዝብ ቁጣ ሊቀሰቅስ ይችላል›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ‹‹አገሪቱ የገባችበት የውጪ ምንዛሬ እጥረት የለጋሽ አገራትን ድጋፍ ከመቼውም ጊዜ በላይ አንገብጋቢ ቢያደርገውም፣ ለዓመታት የቤት ሥራ የሚሆኑ ቃሎችን በመግባት ለማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ መዳረግ የለባትም›› ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይገኙበታል ተብሎ በተጠበቀው በዚህ ጉበኤ፣ የኢትዮጵያን ልዑክ የመሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዚህ ጉባኤ ላይ ለመገኘት ቢፈልጉም፣ የእርሳቸውን የግል ትኩረት የሚጠይቅ አስቸኳይ ሥራ ስለገጠማቸው መገኘት አልቻሉም›› ብለዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 59 ታኅሣሥ 11 2012



