‹‹ባምር ጠላሁ!››ን ማሸነፍ!

0
506

ዝንጀሮን ‹‹አታምሪም አታምሪም›› ሲሏት፤ ‹‹ባምር ጠላሁ!›› አለች ይላሉ። አንዳንዴ ሳንፈልግ ቀርተን ሳይሆን በተለያዩ በቂ [አሳማኝ ላይሆኑ ይችላሉ] ምክንያቶች መሆን ያለብንን ሳንሆን እንቀራለን። ተመልካችም ‹‹እንዲህ ማድረግ አለባችሁ! እንዲህ መሆን አለባችሁ!›› ሲል፤ ‹ባምር ጠላሁ አለች ዝንጀሮ› እንላለን።
ይህ በዚህ ይቆየንና አንድ ገጠመኜን ልናገር። ባለፈው ሳምንት በአንድ ለቴሌቭዥን ስርጭት በሚውል መሰናዶ ላይ ለመታደም እድል አግኝቼ ነበር። ይህ የሆነው የፕሮግራሙ አዘጋጆች ተሳተፉ ብለው በማኅበራዊ ድረ-ገጽ ባስተላለፉት ጥሪ፤ እኔም ርዕሰ ጉዳዩ የሚስብ ሆኖ ስላገኘሁት ለመሳተፍ በመሻቴ ነው። ታድያ ቀረጻ በሚካሔድበት ስቱድዮ ውስጥ አዘጋጅ፣ ለውይይት ሐሳብ አቅራቢ፣ ታዳሚ፣ የፕሮዳክሽን አባላትና በጠቅላላው መድረኩ ላይ የሚታዩት ወንዶች ብቻ ነበሩ። በአጋጣሚም በስፍራው ካሉት ሰዎች ውስጥ ራሴን ብቸኛዋ ሴት ሆኜ አገኘሁት።
መድረኩ ይህን ያህል የሚያስደንቅ፣ የሴቶችን ጉዳይ የሚመለከት ወይም ታካዊ ክስተት ሆኖ አይደለም። እንደውም በቴሌቭዥን ስርጭት መታየቱም የማይቀር ነው። ግን እንዲህ ባሉ ትንንሽ በሚመስሉ መድረኮች ላይ የሴቶች ተሳትፎ ምን ያህል ነው ብዬ እንድጠይቅ አስገደደኝ። ይህ እንደ ግል እይታዬ ሊቆጠር ይችላል፤ ትልቁ ሹመት ከትንሹ ትጋት ተጀምሮ የሚገኝ ይመስለኛል።
በግሌ አገራዊና ማኅበራዊ እንዲሁም ፖለቲካዊና ጥበባዊ የሆኑ የተለያዩ መድረኮች ላይ እሳተፋለሁ። አንዳንዴም በሥራ አጋጣሚ አንዳንዴ ደግሞ ለራሴ ፍጆታ። የእኛ ሴቶች ተሳትፎ ግን በሁሉም ማለት ይቻላል እጅግ በጣም ጥቂት የሚባል ነው፤ የሌለን በሚመስል ደረጃ።
ሌላው ይቅርና ተከታዩን ለምሳሌ ልጥቀስ፤ ሴታዊት የተሰኘችው የሴቶች መብት ላይ የምትንቀሳቀስ ማኅበር መደበኛ እንዲሁም በተለያዩ አጋጣሚዎች ክዋኔዎችን ታዘጋጃለች። ታድያ ትልልቅ ሐሳብ በሚነሳባቸው፣ ሴቶች ሊመካከሩባቸውና ሊጠቀሙባቸው በሚችሉበት በእነዚህ መድረኮች ላይ የሴት ተሳታፊዎች ብዛት በቂ የሚባል አይደለም፤ በእኔ እይታ።
ግን ለውጥ የሚጀምረው ከዚህም ነው። ለሴቶች እኩልነትና መብት፣ እኩል ሥልጣን ማግኘትና መሰማት እንዲመጣ የሚዳክሩና የሚታገሉ የመብት ተሟጋቾች ውጤት ሊያመጡ የሚችሉት ሴቶች እንዲህ ባሉ መለስተኛ በሆኑ መድረኮች ሳይቀር ተጽእኖ መፍጠር፣ ድምጻቸውን ማሰማት እና ያገባናል ማለት ሲጀምሩ/ ስንጀምር ነው ብዬ አምናለሁ።
ልክ ነው! ‹‹ባምር ጠላሁ!›› የሚሉ ሴቶች አይጠፉም። እንደውም ከኋላ ወንበር ተቀምጬ [በተሳተፍኩበት መድረክ] ከፊት ያሉትን ወንዶች ስመለከት፤ ደኅና ዋል ብላ የሸኘች፣ ቁርስ ያበላች፣ ልብስ ተኩሳ ያዘጋጀች፣ በር ከፍታ እስኪርቅ የተመለከተች፣ እናት፣ ሚስት፣ እህት፣ ሴት ልጅ ታይተውኛል። እነዚህ ሴቶች በህሊናዬ ‹‹ባምር ጠላሁ›› ሲሉኝም ተሰምቶኛል። ግን ደግሞ እየቻሉ ተሳትፎ የማያደርጉም አሉ። ትንሹን ፈተና ማሸነፍ ደግሞ ለትልቁ ትግል ልምድም ጉልበት እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።
እናም ይህንን ለማለት ወደድኩ፤ ተጽእኖ መፍጠርና ለውጥ ማምጣት የምንፈልግ ሴቶች ለቀረቡን መድረኮች መቅረብ ብንችል ጥሩ ነው። በየወሩና በየ15 ቀኑ የሚዘጋጁ የመጽሐፍ ላይ ውይይቶች አሉ፤ ሴቶች በአወያይነትና በሐሳብ አቅራቢነት የተገኙበትን ቀን ብዛት ለመጥቀስም ያሳፍራል። ግን ሴቶች ጠፍተው፤ በፍጹም አይደለም። ‹ባምር ጠላሁ!› ሆኖብን ነው፤ አላውቅም። ጥናት ይፈልጋል መሰለኝ።
እናም ሴቶች! የጥበብ ጉዳይ ከሆነ የሚቀርበን እንቅረበው፣ ማኅበራዊ ጉዳይ የሚመለከተን ከሆነ እንመልከተው፣ ፖለቲካውን ሳንፈራ እንሳተፍ አስተያየት እንስጥበት። ይሄ እንድንታገልለት ጉልበት የሚጠይቀን የእኩልነት ጉዳይ ሳይሆን በእጃችን ያለ የሥልጣን መጀመሪያ ነው። ረጅሙን ጉዞ ያለ አንድ እርምጃና ያለ ዳዴ ልናመጣው ይከብደናል ባይ ነኝ።
ሊድያ ተስፋዬ

ቅጽ 2 ቁጥር 59 ታኅሣሥ 11 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here