ነፍሰጡር ሚስቱን በጭካኔ የገደለው ግለሰብ በእስራት ተቀጣ

0
725

መስከረም 21/2010 ምሽት 4 ሰዓት በተፈጠረ ጊዜያዊ ጸብ ከሦስት እስከ አራት ወር የሚሆን ጽንስ በሆዷ የነበረውን ሕጋዊ የትዳር አጋሩን በጭካኔ የገደለው ግለሰብ በ16 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጣ።
በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 በተለምዶ ሐያት ኮንዶሚኒየም ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚኖሩት ጥንዶች መካከል በተፈጠረ ጊዜያዊ ጸብ፣ ገዳይ ባለቤቱን እንደገፈተራት ፖሊስ ለአቃቤ ሕግ የላከው የምርመራ መዝገብ ያስረዳል። ሟችም ተመልሳ ስትይዘው የገፈተራት ሲሆን አንድ ሜትር የሚሆን የቱቦ ብረት በማንሳት ጭንቅላቷን እንደመታትም ፖሊስ የሰበሰበው የሰነድ፣ የፎቶ እና የሰው ማስረጃ አመላክቷል።
በዚህ ወቅትም ሟች አልጋ ላይ የወደቀች ሲሆን ግለሰቡ በዚህ ጊዜ በድጋሚ ጆሮ ግንዷን በብረት በመምታት ከፍተኛ ጉዳት አድርሶባታል። በተጨማሪም በሆዷ ላይ መመታቷን የሚገልጸው የአቃቤ ሕግ ክስ፣ በዚህ ምክንያት ሟች ባጋጠማት የደም መፍሰስ ሕይወቷ እንዳለፈ ይገልፃል።
በሟች ሆድ፣ በደረት እና በጭንቅላት ላይ ጉዳት መድረሱን እና በማህጸኗ የነበረ ሦስት/አራት ወር የሆነ ጽንስም ሕይወቱ ማለፉን የሚያሳይ የፎቶ እና የሕክምና ማስረጃ ለፍርድ ቤቱ ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ አቅርቧል፡፡
የቤት ውስጥ ጥቃት በሴቶች ላይ ብቻ የሚደርስ ባይሆንም በዓለም ላይም ሆነ በኢትዮጵያ ያሉ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በወንዶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት በሴቶች ላይ ከሚደርሰው አንጻር እጅግ በጣም ትንሽ የሚባል ነው። ለዚህም በኢትዮጵያ የተሠሩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፣ 40 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ለቤት ውስጥ ጥቃት ሰለባ ሲሆኑ በአንጻሩ ከአንድ በመቶ በታች ወንዶች ናቸው የጥቃት ሰላባ የሆኑት።
የቤት ውስጥ ጥቃት ሰለባዎች ለበርካታ የጤና መቃወሶች መዳረጋቸው እንዳለ ሆኖ፤ ጥቃት ፈጻሚዎች ራሱ ጥቃት ለመፈጸም እንዲነሳሱ ምክንያት የሚሆናቸው ችግሮች እንዳሉ የሥነ ልቦና ሕክምና ባለሞያ የሆኑት ሰናይት ተመስገን ያስረዳሉ። ከእነዚህም መካከል ዝቅተኛ የሆነ ለራስ ያለ ግምት፣ ከፍተኛ የሆነ ቅናት እና ንዴትን መቆጣጠር አለመቻል፣ የዝቅተኛነት ስሜት፣ ያልታከሙ ሥነልቦናዊ ችግሮች፣ ያልተፈቱ የልጅነት አሰቃቂ ክስተቶች/ገጠመኞች፣ ሱሰኝነት ተጠቃሽ ናቸው።
‹‹ነገር ግን እነዚህ የቤት ውስጥ ጥቃት መነሻ ምክንያቶች ለጥቃት ፈጻሚዎችና ለፈጸሙት ተግባር ማስተባበያም ሆነ፣ ለአጥፊዎች ምክንያት መስጫ ሆነው ሊወሰዱ አይችሉም። የቤት ውስጥ ጥቃት የሚፈጥረው ሥነ ልቦናዊ ጫና በራሱ የከፋ ነውና›› ሲሉ አዲስ ማለዳ ስለቤት ውስጥ ጥቃት አነጋግራቸው በነበረ ጊዜ ተናግረዋል፡፡
ምክንያቱን አጥርቶ ማወቁ፤ ጥቃት አድራሾች ድርጊታቸው ምክንያታዊና ትክክል እንደሆነ እንዴት ሊያስቡ እንደቻሉ ለማወቅ ይረዳል ባይ ናቸው። ‹‹ጥቃት ፈጻሚዎች ራሳቸው በልጅነት የኃይል ጥቃት የደረሰባቸው ሊሆኑ ይችላሉ። እናም ኃይልን መጠቀም ግጭትን ለማብረድ ትክክለኛ መንገድ አድርገው ሊያስቡት ይችላሉ። ጥቃት ፈጻሚዎችን መረዳትና መርዳት መቻል፤ አዙሪቱን ለማስቆም ሊረዳ ይችላል። ይህ ማለት ግን ጥቃት አድራሾች ከሕግ ያመልጣሉ ማለት አይደለም።›› ሲሉ ጨምረው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የሴቶችን መብት ከማስከበር አኳያ ሴቶች ከየትኛውም ዓይነት የቤት ውስጥ ጥቃት እንዲጠበቁ ማድረግንም ይጠቅሳል። ይልቁንም አንቀጽ 35 እነዚህን መብቶች ለይቶ ያስቀመጠ ነው። የሕግ ባለሞያዎች እንደሚሉት በጥቅሉ እንጂ በተለይም የቤት ውስጥ ጥቃትን በተመለከተ ይሄ ነው ተብሎ የተቀመጠ አንቀጽም ሆነ ሕግ የለም። ‹‹በተጓዳኝ ለቤት ውስጥ ጥቃት የተሰጠው ትርጓሜ ሁሉን ያማከለ ካለመሆኑ ይዘቱ ጠባብ ነው›› ሲሉ በሕጉ ዙሪያ ሎዛ ጸጋዬ፣ በሴታዊት ለሴቶች ነጻ የትምህርት እድል ድጋፍ ፕሮጀክት አስተባባሪ ገልፀው ነበር።
ክሱን ሲከታተል የቆየው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት፣ ጥቅምት 19/2012 በዋለው ችሎት፣ ግለሰቡ የወንጀል ሕጉን በመተላለፍ በ16 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል።

ቅጽ 2 ቁጥር 59 ታኅሣሥ 11 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here