በ6 ወር ወስጥ 38 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የኤሌክትሪክ መስመሮች ተዘረፉ

0
652

ባለፉት ስድስት ወራት በመላው ኢትዮጵያ 38 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች እና ትራንስፎርመሮች ተዘረፉ። በአማራ፣ በደቡብ፣ ትግራይ እና ቤኒሻንጉል ክልሎችም ድርጊቶቹ መስፋፋት መጀመራቸው ታውቋል።
በአዲስ አባባ እና በዙሪያዋ ባለፉት ስድስት ወራት በ38 ትራንስፎርመሮች ላይ እና በተለያዩ አካባቢዎች ላይ በሚገኙ የማስተላለፊያ መስመሮች ደግሞ ከ 74 ጊዜ በላይ ስርቆቶች ተፈፅመዋል። ስርቆቱን ተከትሎ በሚፈጠረው የኃይል መቋረጥ በርካታ ኢንዱስትሪዎች ከሥራቸው ተስተጓጉለዋል ሲል የገለጸው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ በተጨማሪም በንጹሕ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እና መሰል ማኅበራዊ አገልግሎቶች ላይ እንቅፋት መፍጠሩንም ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።
ይህ ጥቃት እና ስርቆት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ መምጣቱን እና ይህ ዝርፊያ በዜጎች የእለት ተእለት ኑሮ ላይ እየፈጠረ ካለው ችግር ባሻገር፤ ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ተቋማት እና በአነስተኛ የንግድ ሥራዎች ላይ ቀላል የማይባል ጫና እየፈጠረ መሆኑን የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ መላኩ ታዬ ገልፀዋል።
አገልግሎቱ አንድ ትራንስፎርመር ለመግዛት እስከ 500 ሺሕ ብር ወጪ ያደርጋል። አንድ ትራንስፎርመርም ከ 300 እስከ 400 ለሚሆኑ ቤቶች የኤሌክትሪክ ኃይል ያደርሳል፤ በአማካይም እስከ 25 ዓመታት አገልግሎት ይሰጣሉ ተብሎ ይገመታል። 10 ሺሕ ብር የሚያወጣ ሽቦ ለመዝረፍ ሲባል ከፍተኛ ገንዘብ የፈሰሰባቸውን መሠረተ ልማቶች እያወደሙ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ከዝርፊያዎቹ ባሻገርም በአንዳንድ አካባቢዎች ስርቆት ሳይፈጸም መሰረተ ልማቶቹን ብቻ በማውደም በኅብረተሰቡ ላይ ጉዳት ማድረስን ዓላማ ያደረጉ እና ግጭቶችን መሰረት ያደረጉ ውድመቶች ይከሰታሉ የተባለ ሲሆን፣ አሁን በተደረሰበት ቴክኖሎጂ በየትኛው አካባቢ ብልሽት እንደተከሰተ ለማወቅ አለመቻሉን ተከትሎ ለበርካታ ቀናት ኃይል ተቋርጦ እንዲቆይ ያደርጋል ብለዋል።
በአንዳንድ አካባቢዎች በመንገድ መብራቶች ላይ የደረሱ ጉዳቶች ጨለማን ተገን አድርገው ለሚፈፀሙ ወንጀሎች ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ላይ ይገኛሉ ተብሏል። ድርጊቱን የሚፈፅሙ እና የተሰረቁትን ንብረቶች የሚገዙ ግለሰቦችን ለሕግ ለማቅረብ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እየተሠራ መሆኑም ተገልጿል።
የስርቆት ወንጀሉ በጠራራ ፀሐይ ትልልቅ ዕቃ ማጓጓዣ ተሽከርካሪዎችን ሳይቀር በመጠቀም እንደሚፈፀም የሚገልጹት መላኩ፣ ድርጊቱን የሚፈፅሙት ግለሰቦች የአገልግሎቱን ሠራተኞች ልብስ በመልበስ እና በመመሳሰል መሆኑን ይገልጻሉ። ‹‹ኅብረተሰቡም አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ሲመለከት የመጠየቅ መብት አለው። የአገልገሎቱ ሠራተኞች ለጥገና ሥራ ሲወጡ ማንነታቸውን የሚገልጽ መታወቂያ እና የተመደቡበትን ሥራ የሚያመላክት ደብዳቤ ስለሚይዙ እርሱን በማየት ሊያረጋገጥ ይገባል›› ብለዋል።
ለእያንዳንዱ መሰረተ ልማት አገልግሎቱ ጥበቃ ማቆም አይችልም ያሉት መላኩ፣ ኅብረተሰቡ እነዚህን መሰረተ ልማቶች የመጠበቅ እና የመንከባከብ ኀላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በሳለፍነው ሳምንት ከቆቃ ኃይል ማመንጫ ለሞጆ ማሰራጫ ጣቢያ ኃይል በሚያስተላልፍ መስመር ላይ በደረሰ ስርቆት፣ በሞጆ እና አካባቢው የኃይል እና የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ተቋርጦ መቆየቱ ይታወሳል።

ቅጽ 2 ቁጥር 59 ታኅሣሥ 11 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here