ዛሬ የደቡብ ክልል መዲና በመሆኗ የምትታወቀውን የሐዋሳ ከተማን የቆረቆሯት ልዑል ራስ መንገሻ የዐፄ ዮሐንስ አራተኛ የልጅ ልጅ ናቸው። አምና “የትውልድ አደራ” በሚል ርዕስ ግለ ሕይወት ታሪካቸውን ለሕትመት አብቅተዋል። ብርሃኑ ሰሙ መጽሐፋቸውን በማንበብ ለቅምሻ ያህል የሚከተለውን መጣጥፍ አቅርቦናልናል።
በኢትዮጵያ አካዳሚ ፕሬስ ታትመው ለአንባቢያን ከተሰራጩት ሦስተኛው መጽሐፍ ነው። ባለፈው ዓመት በ300 ገጾች ተጠርዞ የቀረበው የልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም የግለ ሕይወት ታሪክ መጽሐፍ በመግቢያው “በአገራችን ታሪክን የመጻፍ አስፈላጊነትና ጠቃሚነት እየጎላ መጥቷል” የሚሉት ባለታሪኩ፣ “እኔንም የሕይወት ታሪኬን እንድጽፍ ያነሣሣኝ ምክንያት ይኸው ነው” ይላሉ። ታሪካቸውን እንዲጽፉ የቅርብና የሩቅ ወዳጆቻቸው ጉትጎታም አስተዋጽኦ አድርጎላቸዋል።
“በአረጋዊነት ዕድሜዬ ማገባደጃ ያዘጋጀሁትን ግለ ሕይወት ታሪክ መጽሐፍ ቀደም ብዬ ያላሰናዳሁበት አንዱ ምክንያት የተሟላ የዕለት ሁኔታ ማስታወሻ መዝገብ ስላልነበረኝ ነው” የሚሉት ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም፥ የ1966 አብዮት ማግስት፣ መኖሪያቸው በነበረው የዐፄ ዮሐንስ 4ኛ ቤተ መንግሥት (መቐለ) የነበራቸው የግልና የቤተሰብ ታሪካዊ ሰነዶች በደርግ መንግሥት መዘረፋቸውንም በምክንያትነት አቅርበው እነዚህን “ችግሮች ተቋቁሞ፣ ግለ ታሪክን ለንባብ ማብቃት፣ በእኔ ዕድሜ ክልል ለደረሰ አረጋዊ የቱን ያህል ፈታኝ እንደ ሆነ አንባቢያን እንደምትረዱት ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።
የሥራና የግል ሕይወት ውሎ፣ የዕለት ማስታወሻ የመያዝ ልምድ አለመኖር፣ አንዱና ዋነኛው ምክንያት ሆኖ፣ ኢትዮጵያን በመሳሰሉ በማደግ ላይ ባለ አገራት አንድ የዕድሜ ባለፀጋ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ፣ ሕልፈቱን በእሳት አደጋ ከወደመ ቤተ መጻሕፍት ጋር አነፃፅረው የሚገልጹት ምሁራን አሉ።
የወዳጅ ዘመዶቻቸውን ጉትጎታ አክብረው፣ ግለ ሕይወት ታሪካቸውን “የትውልድ አደራ” በሚል ርዕስ፣ ለአንባቢያን ባቀረቡት በልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም መጽሐፍ፣ የባለታሪኩን ሥራና ገድል ከማመልከቱም ባሻገር፣ አገርና ሕዝብን የሚጠቅሙ በርካታ አዝናኝና አስተማሪ ታሪኮች ቀርቦበታል። በመጽሐፉ ካስደመሙኝ ታሪኮች ጥቂቱን በወፍ በረር ለማስቃኘት እሞክራለሁ።
ከልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም የልጅነት ትዝታዎች መሐል፣ ለማወቅ ፍላጎቱ በፈፀመው ድርጊት “ተንኮለኛ” ስለተባለው ልጅ የቀረበው ታሪክ አንዱ ነው። ልዑሉና ጓደኞቻቸው በባላባት ትምህርት ቤት ሲማሩ የተፈፀመ ድርጊት ነው። የባላባት ትምህርት ቤት በወቅቱ የሚገኘው በአሁን የፖሊስ ሠራዊት መኮንኖች ክበብ ግቢ ውስጥ ነበር። ልጆቹ ከቤት ወደ ትምህርት የሚመላለሱት በሁለት ፈረስ የሚጎተት ባለ አራት እግር ትልቅ ሠረገላ ነበር።
“ከእኛ ውስጥ አንድ ተንኮለኛ ልጅ ነበር። የእኛ ጋሪ ነጂ ደግሞ አንድ ዓይና ነበረና ከዕለታት አንድ ቀን ያ ተንኮለኛ ልጅ እንደቀልድ አድርጎ፣ ‹አባባ አለባቸው፣ ይቺን ዓይንህን እንደዚህ ቢይዙብህ ምን ታደርጋለህ?› ይልና ዓይኑን ሲይዘው፥ አለባቸው የፈረሶቹን ልጓም ለቀቀላቸው። ይኼኔ፣ ፈረሶቹ ፈረንሳይ ኤምባሲ ፊት ለፊት ባለው ቁልቁለት ያለ ቁጥጥር ጋልበው፣ በመጨረሻ ተገለበጥን። ነገር ግን እኛም ሆንን ፈረስ ነጂያችን አባባ አለባቸው ምንም አደጋ አልደረሰብንም።”
የሜካናይዝድ እርሻ ብዙም በማይታወቅበት ዘመን ባሕላዊ እርሻቸውን የማሳደግና የማዘመን ጥረት ማድረግ ጀምረው ስለነረ የአርሲ ገበሬ የተተረከው ታሪክ ሌላው አስደማሚ ታሪክ ብቻ ሳይሆን፥ ‹እንደዚያ ዓይነት መነሳሳትና ጅማሬዎች መሠረታቸው ሰፍቶ ማደግ ያልቻሉበት ምክንያት ምንድነው?› የሚል ጥያቄ የመጽሐፉ አንባቢያን እንዲያነሱ የሚጋብዝ ነው።
አቶ ብሩ የሚባሉት አርሶ አደር ሠላሳ ያህል ገበሬዎችን ቀጥረው ያሠሩ ነበር። ለቅጥር ሠራተኞቻቸው ቤት ሠርተው፣ የሚያስፈልጋቸውን ነገር የሚገበያዩበት ገበያ በዚያው መንደር ውስጥ አቋቁመውላቸው ነበር። በእርሻ ለሚረዷቸው ገበሬዎች በካኪ ጨርቅ መለዮ (‹ዩኒፎርም›) ልብስ አሰፍተውላቸዋል። በዚህ ተግባሮቻቸው ዝነኛ ሆነው ስለነበር ዐፄ ኃይለሥላሴ ወደ አርሲ በሔዱበት አጋጣሚ የአቶ ብሩ እርሻና ሥራን ጎብኝተዋል።
“አቶ ብሩ የሚኖሩት በትንሽ ቦታ ላይ፣ አንድ ትንሽ ቆርቆሮ ቤት አሠርተው ነው። ምርታቸው ግን ከፍተኛ ስለ ነበረ፣ አንድ ትልቅ አዳራሽ (መጋዘን) ነበራቸው። ትራክተር አልነበራቸውም፤ ስድሣ ጥንድ በሬዎች ነበሯቸው። እነዚህን በሬዎች ለብቻቸው እየቀለቡ፣ በሚገባ ይዘዋቸዋል። የነበራቸው አስተሳሰብና አሠራር ልዩና ፍሬውም ከፍተኛ በመሆኑ ውጭ አገር እንዲጎበኙ ከተደረጉ የኢትዮጵያ ምርጥ ገበሬዎች መካከል አንዱ ሆነው፣ አሜሪካ ድረስ ተጋብዘው ሔደው ያዩ ሰው ነበሩ።”
በ1953 ሐዋሳ ከተማን በመመሥረት የሚታወቁት ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም፣ በሲዳማ ጠቅላይ ግዛት ካሳለፉት የሥራ ዘመን ጋር በተያያዘ፣ በርካታ መረጃ አስፍረዋል። የሲዳማ ጠቅላይ ግዛት ዋና ከተማ የነበረችው ይርጋለም፤ በአዲስ ዋና ከተማ እንድትተካ የተደረገበት ምክንያት ምን እንደነበር፤ በዚህ ዙሪያ የተደረጉ ውይይቶችና ሥምምነቶች ምን እንደሚመስሉ፤ ሐዋሳ በ1949 መቆርቆሯን፣ የከተማ ፕላን ጥናት ከተደረገላት በኋላ የሲዳማ ጠቅላይ ግዛት ርዕሰ ከተማ እንድትሆን የተወሰነው በ1953 መሆኑን፤ ለራስ ተፈሪያን የሻሸመኔ መሬት በምን ምክንያት እንደተበረከተ፤ ራስ ተፈሪያን ብቻ ሳይሆኑ ለ“ሥመ ጥር ሐማሴኖች” በሻሸመኔ መሬት እንደተሰጠ… ያኖሩት መረጃም አለ።
በዘመኑ ሻሸመኔ በአርሲ አስተዳደር ሥር ነበረች። በሻሸመኔ ከተማ ዳርቻ ላይ “ሥመ ጥር” ለተባሉ የሐማሴኖች ተወላጅ ኤርትራዊያን እንዲኖሩበት መሬት የተሰጣቸው “ኢትዮጵያ አገራቸውን ከጠላት የተከላከሉና የተዋጉ” በመሆናቸው ምክንያት እንደ ምስጋናና ሽልማት ነበር። “እነዚህ ሠፋሪዎች ‹ሥመ ጥር ሐማሴን› በሚል መሬት እንዲሰጣቸው ከመደረጉም በላይ፥ ቶሎ ብለው ወደ ልማት ተግባር እንዲገቡ፣ ሻሸመኔ ላይ ለእርሻ የሚያገለግሉ በሬዎችና (ለሥራ) የሚያስፈልገው ገንዘብ ለእያንዳንዱ አርበኛና ታጋይ ተሰጥቶታል።”
ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም ከልጅነታቸው አንስቶ በበርካታ ሥራና ኃላፊነቶች ውስጥ ሲያልፉ የተተቹበትና የተመሰገኑበት አጋጣሚ ብዙ ነው። በሐሰት የተወነጀሉባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት አልነበሩም። አንዱ የሐሰት ውንጀላ አቅራቢ ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩምን መነሻ አድርጎ ትግራይና የትግራይ ሕዝብን በሙሉ በዚህ መልኩ ሊከስ የሞክሮ ነበር፤ “ትግራይ ዘላለም እንዳወከ፣ በመንግሥት ላይ እንዳመፀ የሚኖር ሕዝብ ነው። በጠላት ጊዜ እንዲህ አድርጎ፤ አምባራዶም ላይ ራስ ሙሉጌታን ወግቶ፤ ራያ እንዲህ አድርጎ…” ሆኖም ክስና ውንጀላው ሲመረመር ሐሰት ሆኖ ተገኘ። ይህ ገጠመኝና ታሪክ ዛሬም ‹በሐሰት የመወነጃጀል ባሕላችን ያልተቋረጠበት ምክንያት ምን እንደሆነ፣ ግለሰብን ማዕከል አድርገን ጎሳን፣ ብሔርና ሕዝብን በአንድ የመፈረጅ ልማዳችን ዘመን ተሻግሮ ዛሬም መታየቱ ለምን ይሆን?› የሚል ጥያቄ እንዲነሳና ለውይይትም የሚጋብዝ ነው።
ከቦሌ እሰከ መስቀል አደባባይ ያለውን 4 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመሥራት ከገጠማቸው ችግር አንዱ፣ ዛሬም ከሚታየው ልግምተኝነት ጋር ተመሳሳይ ነበር። መንገዱን ለማስጠረግ በማዘጋጃ ቤት ሥር የነበሩት የውኃና የኤሌክትሪክ መሥመሮችን ለማንሳት የሥራ ክፍል ባለሙያዎቹ ትብብር ያስፈልግ ነበር። “በአንድ ወር አጠናቁልን” ተብለው ከተጠየቁት መሐል ሥራውን በ15 ቀን ጨርሶ ያስረከበ ነበር። ከተሰጠው ጊዜ አንድ ወር ጨምሮ፣ በሁለት ወርም መጨረስ ተቸግሮ፣ ጉዳዩ ወደ ክስ ከሔደ በኋላ፣ በንጉሠ ነገሥቱ ውሳኔ ተገድዶ ወደ ሥራው የገባው “የውኃ ልማት ክፍል” በሁለት ወር ማጠናቀቅ ያቃተውን ሥራ፣ በ8 ሰዓታት ጊዜ ውስጥ ሠርቶ አስረክቧል።
የኢትዮ-ጅቡቲ የምድር ባቡር ምሥረታ 75 ዓመት በሚያከብርበት ወቅት፥ በየ25 ዓመቱ ይታደስ የነበረውን ውል እንዲፈርሙ የተጠየቁት ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም “ኢትዮጵያ ከምድር ባቡር ምንድነው ያገኘችው? ፈረንሳይ በባቡር ትራንስፖርት ቴክኖሎጂ ዛሬ የት ደርሳለች? የሐዲዱን ስፋት ብንመለከት 75 ሳንቲ ሜትር ነው፤ የዓለም አቀፍ ደረጃው 1.5 ሜትር ነው… ፈረንሳይ የኤሌክትሪክ ባቡር ሠርታ በሰዓት 300 ኪሎ ሜትር የሚጓዝ ባቡር አላት…” የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት፣ ውሉ አዳዲስ ሕጎች እንዲካተቱበት፣ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን በተሻለ ተጠቃሚ የሚያደርግ ሕግ እንዲወጣ በመጠየቃቸው፥ ኢትዮጵያዊያን “ለዚህ የበቁ ከሆኑ መሸለም ይገባቸዋል…” ተብሎ ፈረንሳይ ኤምባሲ ተጠርተው ‹ሌጆን-ድ-ኦኔር› ኒሻን› መሸለማቸውን ያስነብቡናል። በዚያ ዘመን የባቡር ትራንስፖርት ቀርቶ የመኪና መንገድም መሠራት የለበትም የሚሉ ባለሥልጣናት በመኖራቸው ነበር የፈረንሳይ መንግሥት “ኢትዮጵያዊያን ለዚህ ደረሱ ወይ?” ብሎ ሊጠይቅ የቻለው።
የልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም “የትውልድ አደራ” የግለ ሕይወት ታሪክ መጽሐፍ በ1950ዎች ስለተካሔደው የአባይ ሸለቆ ጥናት፣ መልካም አስተዳዳሪ ባለበት ነብርና ፍየል አስማምቶ ማኖር እንደሚቻል ማሳያ የሆነ ታሪክ፣ በአክሱም ከተማ መስጊድ፣ በመካ መዲና ቤተክርስቲያን የማይሠራበት “ምክንያት” ምን እንደሆነ፣ “ምግብ ለሥራ” በአገራችን ከመቼ ጀምሮ ተግባራዊ መሆን እንደጀመረ… በርካታ መረጃና ታሪኮችን ይዟል። ታሪክን የመጻፍ አስፈላጊነትና ጠቃሚነት እየጎላ የመጣው በዚህ ምክንያት ስለሆነ፥ የሚጠበቅባቸውን ግዴታ ለተወጡት ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም በአንባቢያን ሥም ምስጋና ይድረሳቸው።
ብርሃኑ ሰሙ በተለያዩ የሕትመት ብዙኃን መገናኛዎች ለሁለት ዐሥርት ዓመታት የሠሩ ሲሆን፣ የመጽሐፍት ደራሲም ናቸው፡፡ በኢሜይል አድራሻቸው ethmolla2013@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ፡፡
ቅጽ 1 ቁጥር 3 ኅዳር 22 ቀን 2011