በአዲስ አበባ በአምስት ወራት ውስጥ 84 መኪኖች ተሰርቀዋል

0
783

በአዲስ አበባ ከተማ ከሐምሌ 2011 እስከ ኅዳር 2012 ባሉት አምስት ወራት ውስጥ 84 መኪኖች ተሰርቀው መወሰዳቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።
ለኮሚሽኑ በአምስት ወራት ውስጥ የመጡትን አቤቱታዎች መሠረት በማድረግ በተደረገ ክትትል 62 ተሽከርካሪዎች በአሳቻ ቦታዎች ላይ ተጥለው የተገኙ ሲሆን፣ እንደ ጎማ እና የኋላ መመልከቻ መስታወት ያሉ ክፍሎቻቸው ተወስደው መገኘታቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል።
ቀሪ 22 ተሽከርካሪዎች ላይ ከተፈፀመው ዝርፊያ ውስጥ ከ15ቱ ተሽከርካሪዎች ዝርፊያ ጋር ተያይዞ የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ፖሊስ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
አብዛኛዎቹ ሪፖርቶች መኪና የሚያከራዩ ሰዎች የሚያቀርቧቸው ናቸው ያሉት ፋሲካ፣ መኪና የሚያከራዩ ግለሰቦች የሚያከራዩአቸውን ሰዎች ማንነት ሳያረጋግጡ በመስጠት በተሽከርካሪዎቹ ለሚፈፀሙ የንጥቂያ እና ዝርፊያ ወንጀሎች ምክንያት ይሆናሉ ብለዋል። በተጨማሪም መኪኖቹን ለረዥም ጊዜያት ይዘው በመጥፋት የመኪኖቹን አካላት በመነቃቀል ጥፋት የሚያደርሱ እንዳሉ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በመንደር ውስጥ የሚፈፀም የመኪና ሽያጭ ውል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ ነው ያሉት ፋሲካ፣ የመኪና ባለንብረቶች ተሽከርካሪዎቹን በትውውቅ እና በሰፈሮች ውስጥ በሚፈፀም ውል በሕገወጥ መንገድ ይሸጣሉ ሲሉ ገልጸዋል።
የመኪና ስርቆቱ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የሚፈፀም ሲሆን፣ በኪራይ የሚንቀሳቀሱ መኪኖች የወንጀል ድርጊት ከተፈፀመባቸው በኋላ በቀጥታ የሚያዙት የመኪናው ባለቤት ሆነው የተመዘገቡ ግለሰቦች መሆናቸውን እና ፖሊስ በሚያደርገው ምርመራ መኪኖች በሕገ ወጥ መንገድ እንደ ተሸጡ እንደሚደረስበት የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ገልጸዋል።
አክለውም ግለሰቦቹ ተሽከርካሪዎቹን ከሸጡ በኋላ ቀሪ ክፍያ ለማግኘት ችግር ውስጥ በሚገቡበት ጊዜ የመኪና ስርቆት የተፈፀመባቸው በማስመሰል ለፖሊስ እንደሚያመለክቱ ተናግረዋል።
በጦር መሣሪያ የተደገፈ ስርቆት፣ የመኪና እና የመኪና አካላት ስርቆት፣ ተሽከርካሪዎች በመጠቀም የሚፈፀም ዝርፊያ እና የመግደል ሙከራን የመሳሰሉ ዐስር ከባድ ወንጀሎችን በመለየት ኮሚሽኑ ከኅብረተሰቡ ጋር በመተባበር ለመከላከል እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።
የጦር መሣሪያ በመጠቀም በሩብ ዓመቱ የገንዘብ ተቋማት ላይ ያነጣጠሩ ሦስት ዝርፊያዎች መፈፀማቸው እና ሌሎች ኹለት በሙከራ ደረጃ መቆጣጠር መቻሉም ተገልጿል።
እነዚህን ወንጀሎች የሚፈፅሙ ግለሰቦች የከተማዋ ነዋሪ ያለመረጋጋት ስሜት እንዲፈጠርበት ለማድረግ እና ዝርፊያ እና የወንጀል ድርጊቶች የተስፋፉ ለማስመሰል በሚደረግ ጥረት ግነት እንዳስተዋሉ ኮማንደር ፋሲካ ጠቅሰው፣ ወንጀሎቹ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሱ መምጣታቸውን ጠቅሰዋል።
ባለፉት ወራት በአዲስ አበባ ዙሪያ የተፈጠሩ ግጭቶች እና ያለመረጋጋቶች ወደ ከተማዋ ተዛምተው ቢሆን ኖሮ ከፍተኛ ጉዳት ይደርስ ነበር ያሉት ኃላፊው፣ የአዲስ አባባ ፖሊስ ኮሚሽን ከኦሮሚያ ልዩ ዞን ጋር እና የአዲስ አበባ ዙሪያን ከሚያዋስኑ ክፍለ ከተሞች ጋር በመተባበር ግጭቶቹ ወደ ከተማዋ እንዳይዛመቱ ለማድረግ መሠራቱን ተናግረዋል።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንጋፋ የሰላም እና የደኅንነት ጉዳዮች ተንታኝ፣ የወንጀል ድርጊቶቹ በአጠቃላይ በአገሪቱ ያለው አለመረጋጋት ነፀብራቅ ናቸው ያሉ ሲሆን፣ በኅብረተሰቡ ውስጥ የሚገኙ ወንጀል ፈፃሚዎች እንዲሁም ሌሎች ለፖለቲካዊ ትርፍ ወንጀሎችን ሊፈፅሙ እንደሚችሉ ገልፀዋል።
ለውጡን ተከትሎ እንደ ፖሊስ እና ደኅንነት ያሉ ተቋማት ላይ የተደረጉት ለውጦች፣ ተቋማቱን አፈራርሰው እንደ አዲስ ያዋቀሩ በመሆናቸው በተቋማቱ ውስጥ አለመረጋጋት እና ድክመት ይስተዋላል ብለዋል። ተቋማት ላይ ለውጥ ሲደረግ ያላቸውን ጠንካራ ጎን መሰረት አድርጎ ሊሆን ሲገባው፣ ለውጡ የተደረገው ግን ተቋማቱን እንደ አዲስ በማዋቀር ነው ሲሉ ተናግረዋል።
አክለውም በከተማዋ ያለው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ መቀዛቀዝ፣ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰት እና ሥራ አጥነት ወጣቱ ወደ ሱስ እንዲሰማራ አድርጎታል ብለው፣ አስከፊው ነገር ደግሞ ከዚህ ችግር ውስጥ ለመውጣት ብርሃን የሚያሳይ ተስፋ አለመኖሩ ኅብረተሰቡ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል። ይህም ለወንጀል መስፋፋት ከፍተኛ ሚና አለው ሲሉ አብራርተዋል።
እነዚህን ችግሮች እንደ አገር ለመቅረፍ እና አለመረጋጋቶችን ለማስወገድ ሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች እና ምሁራን የተሳተፉበት ፍኖተ ካርታ ሊዘጋጅ ይገባዋል ብለዋል።
ኅብረተሰቡ ከፍጥነት በላይ የሚያሽከረክሩ ተሽከርካሪዎችን፣ ማንኛውንም የወንጀል ድርጊት እና የሚያስጠረጥሩ ሁኔታዎችን ሲመለከት ለኮሚሽኑ በማሳወቅ ከፖሊስ ጋር ሊተባበር እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን አሳስቧል።

ቅጽ 2 ቁጥር 59 ታኅሣሥ 11 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here