የአየር መንገድ ግሩፕ መሰረታዊ የሠራተኛ ማኅበር የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበላይ አመራሮች በሠራተኛ ማኅበሩ የመደራጀት መብት ላይ ጣልቃ እየገቡ እንደሆነ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የኤርፖርቶች ድርጅት መዋሃድን ተከትሎ በኹለቱ ተቋማት የነበሩ የሠራተኛ ማኅበራትን ወደ አንድ ለማምጣት ከ ሐምሌ 2009 ጀምሮ የኹለቱ ማኅበራት ተወካዮች መካከል ድርድር መደረጉን ተከትሎ፣ ኹለቱ ማኅበራት ወደ አንድ እንዲሆኑ በማድረግ ግንቦት 2011 መወሰኑን ገልጿል።
አዲሱ ማኅበርም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነባሩ ማኅበር እና የድርጅቱ አመራሮች በጋራ እና በተናጠል በመሆን በወቅቱ የተደረገው ምርጫ ትክክል አልነበረም በማለት ለሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ማመልከታቸውን አስታውቋል።
ከዚህ በተጨማሪም አየር መንገዱ ዋና አብራሪዎች በማኅበሩ አባልነት እንዳይመዘገቡ ለማድረግ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ነው ያለ ሲሆን፣ ማኅበሩን ለመመሥረት በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ለማኅበሩ አመራሮች እንዲሁም ለሠራተኞች በስብሰባዎች ላይ እንዳይገኙ፤ ከተገኙም ከሥራ እንደሚባረሩ በተለያዩ መንገዶች ማስፈራሪያዎችን ሲልክ እንደነበር አስታውሰዋል።
የመደራጀት ጥያቄውንም በተመለከተ ለአየር መንገዱ በተደጋጋሚ ለመነጋጋር ሞክረናል ያለው ማኅበሩ፣ የምንጽፋቸውን ደብዳቤዎች ለመቀበል እንኳን ዝግጁ አይደለም ብለዋል። እንዲሁም አሠሪው ከሠራተኞች ደሞዝ ላይ በመቁረጥ ገቢ እንዲያደርግ ብንጠይቅም ምላሽ አልሰጠንም ሲሉ ጠቅሰዋል።
በሠራተኞች ላይ የሚደርስ አስተዳደራዊ ጫና ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን ያስታወቀው ማኅበሩ፣ ሠራተኞች በቀላል ምክንያቶች ከሥራ በመሰናበት ላይ መሆናቸውን እንዲሁም በአዲሱ ማኅበር እንዳይመዘገቡ ከፍተኛ ማስፈራሪያ እየተደረገ መሆኑን በተጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አስታውቋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 60 ታኅሣሥ 18 2012



