መነሻ ገጽዜናወፍ በረር ዜናኢትዮ ቴሌኮም ለአራት ሺሕ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የኪስ ገንዘብ ደጎመ

ኢትዮ ቴሌኮም ለአራት ሺሕ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የኪስ ገንዘብ ደጎመ

ኢትዮ ቴሌኮም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በ13 ዩኒቨርሲቲዎች ለሚገኙ ስምንት መቶ ተማሪዎች በየወሩ ሲያቀርብ የነበረውን የኪስ ገንዘብ ድጎማ በሁሉም የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች በማስፋፋት ለአራት ሺሕ ተማሪዎች ድጋፍ ማድረግ ሊጀምር ነው።

የቴሌኮሙ የማኅበራዊ ግዴታ ክፍል ከሰው ኃይል ጋር በመተባበር ያቀናጀው ይህ ድጋፍ፣ በመጪው ማክሰኞ በሃያት ሬጀንሲ ሆቴል ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና የከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ ፕሬዝዳንቶች በተገኙበት ይፋ ያደርጋል።

ቴሌኮሙ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰፋፊ የማኅበራዊ ኀላፊነት ድጋፎችን ማድረግ ያጠናከረ ሲሆን፣ በ 2011 ለ 70 ሺሕ በገጠር ለሚኖሩ ሴቶች የሞባይል ስልክ በነጻ ለመስጠት ከ 50 ሚሊዮን ብር በላይ ማውጣቱ ይታወሳል። በተመሳሳይም ለ 32 ሺሕ ተማሪዎች ትምህርት ቤት ቁሳቁስ ያቀረበ ሲሆን፣ ይህም ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ 93 ትምህርት ቤቶች የተተገበረ ነው። ለ100 ሴቶችም የፋሽን ዲዛይን ነፃ የትምህርት እድል አመቻችቷል።

በ2011 የበጀት ዓመት መባቻ ላይ እስከ 50 በመቶ ድረስ የታሪፍ ቅናሽ ያካሔደው ቴሌኮሙ፣ በበጀት ዓመቱ 36.3 ቢሊዮን ብር ከአገር ውስጥ ገቢዎች የሰበሰበ ሲሆን፣ 98.3 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ ከዓለም ዐቀፍ አገልግሎት ገቢ ተሰብስቧል። ከዚህ ውስጥም ያልተጣራ ትርፍ 24.5 ቢሊዮን ብር ትርፍ አግኝቷል። ይህም ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃጸር የ5.6 በመቶ ዕድገት አሳይቷል። ለዓመታት ያልተከፈለ 4.7 ቢሊዮን ብር ግብርን ጨምሮ በአጠቃላይ 16.2 ቢሊዮን ብር ግብር መክፈሉንም ከወራት በፊት አስታውቋል።

የኢትዮ ቴሌኮም አጠቃላይ የደንበኞች ቁጥር 43.6 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ የሞባይል ድምፅ ደንበኞች 41.92 ሚሊዮን፣ የዳታና የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች 22.3 ሚሊዮን፣ የመደበኛ ስልክ 1.2 ሚሊዮን እንደሆኑ ታውቋል። በአጠቃላይ የቴሌኮም ተደራሽነት 44.5 ደርሷል።

ቅጽ 2 ቁጥር 60 ታኅሣሥ 18 2012

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች