“ከላሊበላና አክሱም ቅርሶች እኩል ዋጋ ያለው” የጫቡ ቋንቋ የመጥፋት አደጋ ተጋርጦበታል- የቋንቋና ባህል ቅረሳ ረዳት ፕሮፌሰር ክበበ ጸሐይ

0
504

በጫቡ ማህበረሰብ ውስጥ ሴት ልጅ ላይ ጥቃት መፈጸም ሞት የሚያስከትል የተወገዘ ድርጊት ነው

በአዲሱ መዋቅር ደቡብ ምዕራብ ክልል ሸካ ዞን አንዳርቻ ወረዳ እንዲሁም በጋምቤላ ክልል ማጀንገር ዞን መንጊሽ እና ጎደሬ ወረዳ ዉስጥ የሚነገረው የጫቡ ቋንቋ የመጥፋት አደጋ እንደተጋረጠበት ባለሞያዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

ከዓመታት በፊት በኢትዮጲያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል የተካሄደ ጥናት እንደሚያመለክተው በኢትዮጲያ ከሚነገሩ ቋንቋዎች መካከል 21 በመቶ ያህሉ የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸው እንደሆኑ ተመላክቷል። በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ መገኛውን ያደረገው ጫቡ (CHABU/SABO) ቋንቋ ከአፍሪካ የቋንቋ ቤተሰቦች የራሱ የቋንቋ ቅርንጫፍ ያለው አምስተኛ የቋንቋ ቤተሰብ ሊሆን ይችላል ተብሎ የሚታሰበው ቋንቋ አደጋ ውስጥ ካሉት ቋንቋዎች አንዱ ነው።

በጫቡ ቋንቋ ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ የሰሩት እና በደብረብርሀን ዩኒቨርሲቲ የሥነልሳን መምህር እና የቋንቋና ባህል ቅረሳ ረዳት ፕሮፌሰር ክበበ ፀሐይ ታዬ፤ አንዳንድ አጥኚዎች 600፤ ዩኔስኮ ደግሞ ከ400 እስከ 1000 የሚሆኑ ጫቡ ነን የሚሉ ሰዎች እንዳሉ ግምቶች የተቀመጡ መሆኑ ገልጸው እራሳቸው ባካሄዱት የቤት ለቤት ቆጠራ 890 ጫቡ ነን ያሉ ሰዎችን እንዳገኙ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

የዘረመል ጥናት አጥኚዎች ከ4 ሺህ 500 ዓመት በፊት የጫቡ ማህበረሰብ በዚህ ጭካ ዉስጥ ይኖሩ እንደነበረ በማንሳት ይህ ማህበረሰብ የአካባቢው ቀደምት ወይም የመጀመሪያ ነዋሪዎች ናቸው ይላሉ። የቋንቋው ተናጋሪዎች እንደሚገልጹት መነሻቸው የሚኖሩበት ሸካ ጫካ ሲሆን የጫካው መጠሪያ ‘ጫዊ ሻሚ’ የጫቡ ጫካ ተብሎ እንደሚጠራና ቅድመ አያቶቻቸው ይኖሩበት የነበረው ቦታ ላይ ቤተሰብ መስርተው እንደሚኖሩ አንስተዋል።

የጫቡ ቋንቋ ቤተሰብ የትኛው ነው ለሚለው ሁለት ሃሳብ እንዳለ የገለጹት ክበበ ጸሐይ፤ በአፍሪካ ዉስጥ ካሉ አራት የቋንቋ ቤተሰቦች ሁለቱ ማለትም ናይሎ ሳሃራንና አፍሮ ኤዢያቲክ በኢትዮጵያ እንደሚገኙ ጠቁመው የጫቡ ቋንቋን በተመለከተ በቅርብ ጊዜ የተሰበሰቡ ጥናቶች የሚያሳዩት ቋንቋው ከሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጋር የማይዛመድ እና እራሱ ችሎ የቆመ በመሆኑ የራሱ የቋንቋ ቅርንጫፍ ያለው አምስተኛ የቋንቋ ቤተሰብ ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማሉ ብለዋል።

የቋንቋው ተናጋሪዎች ቁጥራቸው መቀነስ የጀመረው ከ1 ሺህ 400 ዓመታት በፊት መሆኑን በመግለጽ እርሻ የሚያርሱና ከብት የሚያረቡ ማህበረሰቦች ወደእነሱ አካባቢዎች በመምጣታቸው ጫቡዎች ለአደን ይጠቀሙት የነበረው ጫካ በሌሎች መያዙ ዋነኛው ምክንያት መሆኑን ተመራማሪው ያነሳሉ። ከሌሎች ማህበረሰቦች ጋር በመጋባት እና በመዋለድ መቀላቀላቸውም ለጫቡ ቋንቋ ተናጋሪዎች ቁጥር መቀነስ አንድ ምክንያት መሆኑን ዶክተር ክበበ ጸሀይ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

“እንዲሁም ጫቡዎች የሚገኙበት አካባቢ ላይ ሆነ ተብሎ ሌሎች እንዲሰፍሩበት ይደረጋል” የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ክበበ ጸሀይ “ጫቡዎች ከታወቁ ጫካውን ይዘው የራሳቸው የሆነ አስተዳደር ሊኖራቸው ይችላል የሚል ስጋት በመኖሩ ስለዚህ ከመታወቃቸው በፊት ቢዋጡ የሚል ሃሳብ ያለ ይመስላል” ይላሉ።

ለምሳሌ 890 ከሚሆኑት ዉስጥ በቋንቋው አፋቸውን የፈቱት 643 ብቻ ሲሆኑ፤ 73ቱ በሁለተኛ ቋንቋነት የሚናገሩ ናቸው። 18 የሚሆኑት ደግሞ አፋቸውን ያልፈቱ ህጻናት እንዲሁም 156 ያህሉ ቋንቋውን መናገር ባይችሉም በዘር ጫቡ እንደሆኑ ገልጸዋል።

የቋንቋ መጥፋት ወይም መዳከም በአንድ ማህበረሰቡ ውስጥ የሚገኙ ታሪኮች፣ ልዩ ልዩ የዓለም እይታዎችን፣ ስርዓቶችን፣ ባህሎችን ከማጥፋቱ ባሻገር ብዝሃነትን የሚሸረሽር መሆኑንም ይነሳል።

የጫቡ ማህበረሰብ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አዳኞች እና በጫካ ዉስጥ የሚገኙ ስራ ስር በመልቀም ይኖሩ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፤ በአሁኑ ሰዓት ሌላውን ማህበረሰብ በማየት በመንደር እየተደራጁ በመኖር የእርሻ ስራ በመጀመር የጓሮ አትክልት እንደ ጉደሬ፣ ቡና፣ በቆሎ፣ ሙዝ እና ሸንኮራ የመሳሰሉትን እያለሙ ይገኛሉ። ጫቡዎች ከዚህ ቀደም ‘ፈንጂ’ ከሚባል ዛፍ የሚዘጋጅ የቅጠል ሽርጥ እንዲሁም የፍየል ቆዳ ሳይቀደድ እንደብርድ ልብስ፣ ምንጣፍ እና ኮፍያ ይጠቀሙት የነበረ ሲሆን ከቅርብ አመታት ወዲህ ወደ ገበያ ሲወጡ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመቀላቀላቸው ልብስ መልበስ መጀመራቸውን ባለሞያው ገልጸውልናል። የሚገርመው “ባህላዊ ልብሳቸው ሲነግሩን እና ሲያሳዩን የቅርብ ጊዜ ትዝታቸው ነው የሚመስለው” ይላሉ።

ቋንቋ መግባቢያ ብቻ ሳይሆን የባህል፣ የማንነት እና የቅርስ ክምችት ቢሆንም አሁን ላይ በዓለም ፈጣን የሆነ ለውጥ ሳቢያ በርካታ ቋንቋዎች የመጥፋት አደጋ እንደተጋረጠባቸው የስነ ቋንቋ ዘርፍ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ጫቡ ቋንቋ፤ አንድ ቋንቋ የመጥፋት አደጋ ተጋርጦበታል የሚያስብሉ ወሳኝ ወሳኝ የሆኑ ምልክቶችን ማሳየቱን የሚገልጹት ረዳት ፕሮፌሰር ክበበ ጸሀይ ጫቡ ቋንቋ የሞት አፋፍ (critical endangered) የሚባለው ደረጃ ዉስጥ የሚካተት እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል። በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) መመዘኛ መስፈርቶች መሰረትም በሁሉም በኩል አደጋ ላይ ያለ ቋንቋ ነው።

የተናጋሪዎቹ ቁጥር አነስተኛ መሆን፣ በቋንቋው ምንም የተጻፉ ነገሮች አለመኖራቸው፣ በሚኖሩበት አካባቢ እነሱ የሌሎችን ቋንቋ መናገር መቻላቸው እና ሌላው ማህበረሰብ የእነሱን መናገር አለመቻሉ እንዲሁም በአካባቢው ያሉ ትምህርት ቤቶች ትምህርት የሚሰጡት በሌላ የአካባቢው ቋንቋ መሆኑ ቋንቋው የመጥፋት አደጋ እንደተጋረጠበት ማሳያ እንደሆኑ ባለሞያው ይናገራሉ።

ጫቡ ከሌሎች በኢትዮጵያ ከሚነገሩ ቋንቋዎች የተለየ መሆኑና ምናልባትም አምስተኛው የቋንቋ ቤተሰብ መሆኑ የሚታመን በመሆኑ፤ ቢጠፋ በዉስጡ የሚኖሩትን ሌሎች ቅርንጫፎችን ሁሉ ነው ይዞ የሚጠፋው በማለት “ሌሎቹ ዘሮቹ አልቀው ብቻውን የቀረ ስለሆነ የእርሱን ዘር ቋንቋ ወክሎ መረጃ የሚሰጥ ስሌለ ዋጋው ያን ያህል ከፍ ያለ ነው” ሲሉም አሳስበዋል።

የጫቡ ቋንቋ የአምስተኛ የቋንቋ ቤተሰብ ነው እንዲባል ካደረጉ ጉዳዮች መካከል በአማርኛ ቋንቋ ‘እኔ’ የሚለው ቃል ለሁለቱም ጾታዎች ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን፤ ነገር ግን በጫቡ ቋንቋ፤ ለሴት እና ለወንድ ‘እኔ’ የሚለው ቃል የተለያየ መሆኑን የጥናት ባለሞያው ገልጸዋል። እንዲሁም በአማርኛ ቋንቋ ‘እኛ’ የሚለውን ቃል ለብዛት ሲጠቀም ጫቡ ግን ለሁለት እና ከሁለት በላይ ሰዎች የተለያዩ ቃላትን የሚጠቀሙ ሲሆን ለወንዶች እንዲሁም ለሴቶች የተለያዩ ቃላትን ይጠቀማሉ ይላሉ።

በተመሳሳይም ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ቋንቋዎች አንደኛ መደብ ጾታ ሳይለዩ ወንዱም ሴቱም በአንድ አይነት ተውላጠ ስም ሲጠሩ በጫቡ የተለየ መሆኑ እና በአንደኛ፣ ሁለተኛና ሶስተኛ መደብ ጾታ፣ ነጠላ ቁጥር እና ብዙ ቁጥር የሚለይ መደብ ያለው ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ቋንቋ መሆኑን አመላክተዋል።

የጫቡ ቋንቋ ለጽሁፍ የሚጠቀመው የትኛውን ፊደል ነው? በሚል አዲስ ማለዳ ለጥናት ባለሞያዉ ያቀረበችው ጥያቄ “ቋንቋው ጽህፈት ላይ ዉሏል ለማለት አያስደፍርም። ቋንቋውን በጽሁፍ ለማስቀመጥ የተሰራ ምንም አይነት ስራ የለም። ምንም በጫቡ ቋንቋ የተጻፈ ነገርም የለም” ብለዋል።

ነገር ግን በጥናታቸው ወቅት በየትኛው የአጻጻፍ ዘዴ ቢጻፍ ትመርጣላቹ ተብሎ ሲጠየቁ 95 በመቶ የሚሆኑት ሰዎች አማርኛ በሚጻፍበት አጻጻፍ ቢጻፍ እንመርጣለን የሚል ምላሽ እንደሰጡ ገልጸዋል። እንዲሁም መጽሃፍ ቅዱስ ቢተረጎም ደስ እንደሚላቸው እና ትምህርት በራሳቸው ቋንቋ መማር እንደሚፈልጉ የገለጹ መኖራቸውንም ተመራማሪው ነግረውናል።

የጫቡ ማህበረሰብ የተለየ የሚያደርጋቸው የተወሰኑ ባህሎች እንዳሉት ረዳት ፕሮፌሰር ክበበ ጸሐይ ገልጸው፤ ለአብነትም በጫቡ ማህበረሰብ ውስጥ ሴት ልጅ ላይ ጥቃት መፈጸም ሞት የሚያስከትል የተወገዘ ድርጊት በመሆኑ አንዲት ሴት ወደ ጫካ ለብቻዋ ስትሄድ ጥቃት ይደርስብኛል ብላ በጭራሽ አትሰጋም።

በተጨማሪም “በማህበርሰቡ ሴት ልጅ ክቡር ናት ያለፍላጎቷ አትዳርም። ከትዳር በኋላም ያለ ሴቷ ፍላጎት ምንም አይነት ግንኙነት አይደረግም”። እንዲሁም በተለምዶ ወንዶችና ሴቶች አንድ ላይ ተሰባስበው በሚገኙበት ሰዓት ሁሉንም በወንድ መጥራት የተለመደ ሲሆን በጫቡ ማህበረሰብ ግን ከወንዶች መሃል ሴት ካለች ሁሉንም በሴቶች የመጥራት ልማድ መኖሩን ጠቁመዋል።

የጫቡ ቋንቋን ለመታደግ “ኃላፊነቱ የሁሉም ነው። ባለሙያዎች፣ ፖለቲከኞች፣ የሚዲያ አካላት እንዲሁም ምሁራን የራሳቸው ድርሻ ሊወጡ ይገባል። እንዲሁም የቋንቋዎች አካዳሚ በመባል የሚጠራው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚገኘው ማዕከል ስራው እንደ ጫቡ ያሉ ቋንቋዎችን ማጥናትና እንዲዳብሩ ማድረግ ነው” ሲሉ ረዳት ፕሮፌሰር ክበበ ጸሀይ ተናግረዋል።

እንዲሁም እንደ አንድ ማህበረሰብ ብሄር እውቅና ሊሰጣቸው ይገባል የሚሉት ባለሞያው ማህበረሰቡ ቋንቋው ቅርስ መሆኑ አውቀው ሊጠብቁት እንደሚገባ በሚረዳበትና እንዲያሳድገው ግንዛቤና ማበረታቻ መስጠት አስፈኣጊ መሆኑን አንስተዋል።

“ጥናቱ ካጠናቀቅኩ በኋላ ለብሔረሰቦች ምክር ቤት፣ መጀንገር ዞን፣ ሸካ ዞን፣ የጫቡ ቋንቋ ማህበርሰቦች እውቅና ማግኘት የሚችሉበት መንገድ እንዲመቻች ስራዎችን ለመስራት ሞክሬያለው። በወቅቱም ይኼን መሰል ጥያቄ በርካታ ስለሆነ በአንድ ላይ ምላሽ ይሰጣል የሚል መልስ ነበር ያገኘሁት፤ ቋንቋው የመጥፋት አደጋ የተጋረጠበት በመሆኑ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ነበር አሁን ላይ ተስፋ ቆርጬ ትቼዋለው” ብለዋል የቋንቋና ባህል ቅረሳ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ክበበ ጸሐይ።

“ትንሽ ተናጋሪ ያለው ቋንቋ ሁሌም የመጥፋት አደጋ ዉስጥ ነው” ያሉ ሲሆን “ቋንቋ የማይጨበጥ ሃብት ነው። በአንድ ቋንቋ ዉስጥ ባህል፣ ፍልስፍና፣ አስተሳሰብ፣ እውቀት፣ ስርዓት፣ ልማድ እና ወግ አለ ይሄ ሁሉ ነው አብሮ የሚጠፋው። ቋንቋው ከአክሱምና ላሊበላ የማይተናነስ ዋጋ ነው ያለው አንድ ቋንቋ ጠፋ ማለት አንድ ትልቅ ቤተ መዛግብት እንደወደመ ነው የሚቆጠረው” ይላሉ።

ኢትዮጵያ ካሏት ከ80 በላይ ቋንቋዎች መከከል 52ቱ የራሳቸውን ፊደል ቢቀርጹም ከዚህ ውስጥ 40ዎቹ ፊደላቸውን በላቲን ፊደላት ሲቀርጹ 12ቱ ብቻ የኢትዮጵያን ፊደል ተጠቅመው የራሳቸውን ፊደል መቅረጽ ችለዋል። ኦንጎታ፣ አንፊሎ፣ ናርቦሬ፣ አርጎባ፣ አንጌ፣ ባሌ፣ ባስኬቶ፣ ባኢሶ፣ ቡዲ፣ ቡርጂ፣ ጉጂ፣ ዳሰነች፣ ጋንዛ፣ ቅማንት፣ ዲሜ፣ ሀዞ ፣ሀሮ እና ሌሎችም የመጥፋት አደጋ ከተደቀነባቸው ቋንቋዎች መካከል የሚጠቀሱት ናቸው።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here