እራሳቸውን ያገገሉ እና የታጠቁ ታጋዮች ወደ አገራዊ ምክክሩ እንዲመጡ ኢዜማ ፓርቲ ጥሪ አቀረበ

0
409

ቅዳሜ ግንቦት 25 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ “ራሳችሁን ከምክክሩ ያገለላችሁ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና በትጥቅ ትግል ለውጥ እናመጣለን ብላችሁ በተለያየ የሀገሪቱ ክፍል ጦርነት ላይ ያላችሁ ወገኖቻችን የተሻለው እና አነስተኛ ዋጋ የሚያስከፍለው መፍትሔ ምክክር መሆኑን ተገንዝባችሁ ለሀገራዊ ምክክሩ ዕድል እንድትሰጡ” ሲል ጥሪውን አቅርቧል።

ኢዜማ በዛሬው ዕለት ካወጣው መግለጫ አዲስ ማለዳ እንደተመለከተችው ማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችን ጨምሮ የተለያየ የሚድያ አካላት ትኩረታቸውን በአገራዊ ምክክሩ ላይ እንዲያደርጉና አሉታዊ እና አፍራሽ ከሆኑ ተግባራት በመቆጠብ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን አስተዋፅዖ ማድረግ እንዳለባቸው ፓርቲው ገልጿል።

እንዲሁም “የሀገርና የሕዝብ ደህንነትና ቀጣይነት ከምንም በላይ እንደሚያሳስበው ባለድርሻ ሀገራችን ላይ እየተካሔደ ያለው ሀገራዊ ምክክር የሀገርን እና የሕዝብን ደህንነትና ቀጣይነት በሚያረጋግጥ መልኩ ተጀምሮ በውጤት እንዲጠናቀቅ የተቻለውን እናደርጋለን” ብሏል።

ፓርቲው አክሎም “ይህንን እድል የሚሰጥ ጭላንጭል ተስፋ ስናገኝ ከእኔ መንገድ ውጪ በሚል እና ከግል ጥቅም ባሻገር መመልከት አቅቶን የምናስነሳው ወጀብ በታሪክ አጋጣሚ ካጣናቸው መታጠፊያዎች አንዱ ሆኖ እንዳያልፍ መጠንቀቅ በእጅጉ ያሻል” ሲል አሳስቧል።

ምክክሩን ከጅምሩ በአንክሮ ሲከታተል የቆየ መሆኑን የገለጸው ኢዜማ፤ በሒደቱ መስተካከል አለባቸው ያላቸውን ነቅሶ በማውጣት ጥያቄዎችን እና ምክረ-ሐሣቦችን በማቅረብ ከላይ በተጠቀሰው መልኩ የምክክሩን ስኬት ዓላማ አድርጎ ሲንቀሳቀስ መቆየቱን አመላክቷል።

እስከአሁን በአገሪቷ ውስጥ ያሉትን መሠረታዊ ችግሮች በመፍታት ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እናመጣለን በሚል በላብ አደሩ፣ በአርሶ አደሩ እና በብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ስም የተደረጉ ሙከራዎች ለነበሩት ችግሮች መፍትሔ መስጠት አለመቻል ብቻ ሳይሆን አዳዲስ ችግሮች በመፈልፈል ሁኔታውን ከማባባስ በቀር ምንም ዓይነት ውጤት ሊያስገኙ አለመቻላቸውን አስታውሷል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here