የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ ማስተካከያ እስከሚደረግ ከዛሬ ጀምሮ በይፋ ከሀገራዊ ምክክር መውጣቱን አስታወቀ 

0
505

ሰኞ ግንቦት 26 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ያስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች እስከሚሟሉ ከዛሬ ከግንቦት 26 ቀን 2016 ጀምሮ ከሀገራዊ ምክክር ሂደት ራሱን እንዳገለለ አስታወቀ።

ኢሕአፓ ዛሬ ለአዲስ ማለዳ በላከው መግለጫ ከሂደቱ እንዲወጣ የተገደደበትን ምክንያቶች ሲያብራራ “የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ከምሥረታው ጀምሮ ችግር የነበረበት በመሆኑ፣ የኮሚሽኑን የሥራ ውጤትም የሚቀርበው ለገለልተኛ አካል ሳይሆን በብልጽግና አባላት ለተሞላው የተወካዮች ምክር ቤት በመሆኑ፣ ምክር ቤቱ ከብልጽግና ፓርቲ ጥቅም አኳያ በመመርመር የኮሚሽኑን የሥራ ውጤት ሊቀበለውም ሆነ ውድቅ ሊያደርገው እንደሚችል በማመን፣ ኮሚሽኑ በተሻለ መልክ ተዋቅሮ ገለልተኛነቱም አስተማማኝ እስካልሆነ ድረስ” ከምክክሩ ራሱን አግልሏል።

ፓርቲው በመግለጫው ገዥው ብልጽግና ለአስቸኳይና ለሁሉን

አቀፍ ድርድር ራሱን አንዲያዘጋጅ፣ “ሀገራችን ከአውዳሚ ጦርነቶች ወጥታ ህዝቡም የሠላም ዐየር የሚተነፍስበት ሁኔታ እንዲፈጠርና እንዲሁም በምንም መልኩ ለሠላማዊ ፖሊቲካዊ መፍትሄዎች ፍለጋ የሚደረጉ ጥረቶችን ብልጽግና እንዳያደናቅፍ” ጥሪ አቀቅርቧል።

የብሄራዊ ምክክር ሂደቱ ሊመረመርና የሚታዩት ህጸጾች ታርመው በአዲስ ሂደት ወደተፈለገው ሀገራዊ መግባባትና የፖለቲካ ሽግግር ሊያስኬድ የሚያችል ሁኔታ መፈጠር አለበት ያለው ኢሕአፓ፤ ግጭቶች እንዲቆሙ እና የፖለቲካ እንዲሁም ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማንሳት የተረጋጋ ኑሮ እንዲኖር በማስቻል ለምክክር ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባ ፓርቲው ማሳሰቡን አዲስ ማለዳ ከመግለጫው ተመልክታለች።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቅዳሜ ግንቦት 24 ቀን 2016 የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት እንዲሁም በርካታ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች በተገኙበት ማካሄዱ አይዘነጋም።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here