የባለ አሻራ ትውልዶች ጥያቄ

0
810

‹‹እስከ ምሽት 5፡30 ድረስ ፊልም እያየሁ ነበር። ጠዋት ከእንቅልፌ ስነቃ ግን ዐይኔ ማየት አቁሞ ነበር።›› አለ። በአንዲት ጀንበር ልዩነት የሕይወቱ አቅጣጫ፣ መንገድ እና አካሔዱ የተቀየረበት ጋዜጠኛው ሰለሞን ታምሩ። ገፍቶ ሊያልፍ ያልቻለውን ተራራ ሌላ መንገድ ፈልጎ የማለፍ ጽናትና ጥንካሬ ያለው ወጣት ነው፤ እሱም የሚናገረው ይህንኑ ነው። በብርታቱ ‹አሻራ› የተሰኘ የራድዮን መሰናዶን በኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 በየሳምንቱ ሐሙስ ምሽት ከ3፡00 ሰዓት ጀምሮ ለአንድ ሰዓት ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን ያቀርባል። ከአካል ጉዳት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችንም ያነሳል።
አዲስ ማለዳም ስለ አሻራ የራድዮን ፕሮግራም፣ የፊታችን ሰኞ ታኅሳስ 20/2012 ስለሚካሔደው ኹለተኛው አሻራ ሽልማት አልፎም ስለግል ሕይወቱ አናግራዋለች።

ስለ ሰለሞን
2002 ላይ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ የነበረው ሰለሞን፣ ከእለታት በአንዱ ማለዳ ዐይኑ ማየት ተስኖት ሲነሳ ድንጋጤና ጭንቀት ፋታ አልሰጡትም። ያ ጊዜ ከባድ እንደነበርና የሆነውን ተቀብሎ አዲሱን የሕይወት ምዕራፍ ለመክፈት ሦስት ዓመታት እንደወሰደበት ያስታውሳል። በ2005 ግን አዲስ ሕይወት የዐይነ ስውራን ማዕከል የብሬል ትምህርት ተማረ። የብሬል ትምህርት የጀመረ ቀን ‹‹ምንም ነገር ማድረግ እንደምችል ያኔ ነው የገባኝ›› ያለው ሰለሞን፣ ዐይናማ በነበረ ጊዜ የነበረውን ሕልምና ሐሳብ ሁሉ የዐይኑ ለማየት መጋረድ እንደማይከለክለው ለራሱ እርግጠኛ ሆነ።
‹‹ሥነ ጽሑፍ ስለምወድ ብሬል ስማር መጀመሪያ ሥራዬን ላስነብብ እችላለሁ ብዬ ነው ያሰብኩት።›› ሰለሞን አለ። ባለጸጋ የነበረን ሰው ሐብቱን ቀምቶ ጎዳና እንዲኖር የማድርገ ያህል ስሜት የተሰማው ቢሆንም፣ ‹‹ግን ከዛኛው ሕይወቴ ይህኛው ስኬታማ ነው። እያየሁ ከኖርኩት ሳላይ የኖርኩት ይበልጣል። ሳላይ ዲግሪ ይዣለሁ፣ ሳላይ በምወደው ሙያ ላይ ነኝ፤ ሳላይ ኮምፕዩተር ተምሬያለሁ። ይህን ሁሉ ራሴ ነኝ ያመጣሁት። ተራራውን ገፍቼ ማለፍ አልችልም፤ ግን ማለፊያ መንገድ አግኝቻለሁ።›› ሲል ይገልጸዋል።

በጽናት የታለፈ ተራራ
ከሦስት ዓመት ቆይታ በኋላ 10ኛ ክፍል ገብቶ ተማረ፤ ዩኒቨርሲቲ መግባትም ቻለ። የየሚወደውን የጋዜጠኝነት እና የራድዮን ሥራ ግን ገና 11ኛ ክፍል እያለ ነው የጀመረው። 2011 ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማኅበራዊ ሳይንስ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪውን ተቀበለ። ‹‹ማኅበረሰብ ላይ መሥራት እፈልጋለሁና ገና 11ኛ ክፍል እያለሁ ነው መማር ያለብኝን የመረጥኩት። ገብቼ ሳልንገላታ ጨረስኩ።›› ሲል ያለፈውን ያስታውሳል።

ሰለሞን በልጅነትና ከፍ ሲልም በወጣትነት እድሜ ብርታትን ያወቀበት ወጣት ነው። ይህን ብርታት ከእናቴ ወርሻለሁ ባይ ነው። የእርሱና የሦስት እህቶቹ እናት ገነት፣ አራት ልጆቻቸውን ለብቻቸው ያሳደጉና ለልጆቻቸው አረአያ መሆን የቻሉ ሴት መሆናቸውን ሰለሞን ይመሰክራል። ያደርግላቸው ቢያጣ የከፈተውን ሚድያና ፕሮሞሽን በእናቱ ስም አድርጎታል። ገነት ሚድያ እና ፕሮሞሽን። ‹‹በእኔ ውስጥ የእርሷ ስም እንዲነሳ እፈልግ ነበር። የሚድያ እድል ሳገኝ እርሷ ትጠራበት እርሷ ትመስገንት ብዬ ነው።›› ሰለሞን እንዳለው።

አዲስ አበባ ፈረንሳይ ለጋሲዮን የተወለደው ሰለሞን፣ ከአካል ጉዳተኝነት ጋር በተያያዘ ለራሱንም ለብዙዎችንም የተረፈ ነው ሲል ዮሴፍ ኃይለማርያምን (ዮሴፍ ምርኩዝ) ያደንቃል። ታድያ በሰፈሩ ዓለምነህ ዋሴ፣ አየለ ማሞ፣ ድምጻዊ ግርማ ተፈራ፣ ኮለኔል ሳህሌ ደጋጎ፣ ጋዜጠኛ ታደሰ ሙሉነህን እያየ ማደጉ ለሙያውና ለኪነጥበብ እንዲቀርብ አንድ ግብዓት ሳይሆነው አልቀረም።

አሻራ የራድዮን ፕሮግራም
‹‹ስለ ጉዳቴ የሚያወሩልኝ ካሉ ብዬ ፈልጌ ነበር፤ መጀመሪያ ፋና ላይ ነበር፤ አንድ ድምጽ የሚል ፕሮግራም፤ ጥሩ ነገር ያቀርባሉ ግን ከበድ ያሉ ጉዳዮችንም ያነሳሉ። ያንን ስሰማ ቤት ውስት ጓደኞቼ ቀይረው ይሉኛል። ለምን ስላቸው እኛም እንፈራለን፤ በዛ ላይ አንተንም የሚሰማህ ይመስለናል፤ ስለዚህ የሚያዝናናህን ነገር ስማ ይሉኛል።›› ሲል ያስታውሳል። ይህንን ከልቦናው ያላጠፋው ሰለሞን፣ በኢትዮ ኤፍ ኤም ላይ ሥራውን ሲጀምር አዲስ መንገድ ተጠቀመ።

አሻራ የራድዮን ፕሮግራም የተጀመረውና አየር ላይ የዋለው ከኹለት ዓመት በፊት ኅዳር 24/2010 ነው። ይህ ሳምንታዊ መሰናዶ ‹‹እኛ ባለ አሻር ትውልድ ነን፣ እናንተስ?›› ሲል ይጠይቃል። የመሰናዶው ዓላማም ቀድሞ ይሠሩ የነበሩትን ከአካል ጉዳት ጋር የተያያዙ ደረቅ ያለ ይዘት ያላቸውን መሰናዶዎች በአዲስ አቀራረብ በተዝናኖት በኩል መፍጠር ነው።

‹‹አድማጭ እየተዝናና እንዲማር ነው ሐሳባችን። ሰው እንዲሰማልን ነው የፈለግነው።›› ይላል ሰለሞን። ስለዚህም ስኬታማ ሰዎችን በመጋበዝ፣ አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎችን እና ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ፣ መጽሐፍት በመተረክ፣ የአካል ገዳተኞችን ገጠመኝና የፈተኗቸውን ጉዳዮች አዝናኝ ሆኖ እንዲቀርቡ ያደርጋሉ።

በዚህ ታድያ ከአድማጮች የሚያገኙት መልስ መልካም እንደሆነ ሰለሞን ጠቅሷል። ከአካል ጉዳተኞች ይልቅም አካል ጉዳት የሌላቸው አድማጮች በብዛት እንደሚሳተፉ ይጠቅሳል። ‹‹ፕሮግራሙ መዝናኛ ከሆነ ማንም ሰው ይደግፈዋል። ስለ አካል ጉዳተኝነት እንሠራለን አንልም፤ ዝም ብለን ነው የምንሠራው። ርዕስ ሲሰጥ ሰው ይሸሻል። አይቶ ይፍረድ ብለን ነው የምሠራው።›› ሲልም ስለ መሰናዶው ጠቅለል ያለ ሐሳብ አካፍሏል።

ታድያ አሻራ የራድዮን መሰናዶን በየሳምንቱ ሲያቀርቡ ደጋፊ እንደሌላቸው ይጠቅሳል። ‹‹አካል ጉዳተኝነት የሚባለውን ይፈሩታል ይጠሉታል፤ እኛ መዝናኛ ይዘናል ብለን ነው የምናዘጋጀው። ያለ ምንም ስፖንሰር ደጋፊ እየሠራን ነው ያለነው።›› ያለው ሰለሞን፤ እንደውም ጣብያውን በእጅጉ አመስግኗል። ገንዘብ ስላላስገቡ እንዲሁም በይዘት ምክንያት የሚቀነሱ መሰናዶዎች ቢኖሩም፤ ገንዘብ አላስገባችሁም ተብለው እንዳልተቀነሱ በመጥቀስ።

ለአካል ጉዳተኝነት ማን ትኩረት ሰጠ?
አካል ጉዳተኝነት ላይ ያተኮሩና መረጃዎችን የሚያቀብሉ መሰናዶዎች ጥቂት ናቸው። ሆኖም የተሻለ ነው። ይሁንና የሕትመት ሥራዎች ግን የሉም ማለት ይቻላል። ሰለሞን ነገሩ ከባድ እንደሆነ ሳይጠቅስ አልቀረም። እንኳንና ለብሬል እንዲሁም የወረቀት ዋጋ መጨመሩ አስቸጋሪ መሆኑንም አንስቷል። ሆኖም የቴክኖሎጂ መኖር ለአካል ጉዳተኞች ችግሩን እንዳቀለለ ይጠቅሳል። በዚህና በሌሎች ምክንያቶችም በአካል ጉዳተኝነት ላይ መሥራት ከባድ ስለመሆኑ ግን አጥብቆ ይገልጻል።

ማኅበራትም በዚህ ላይ ተጽእኖ ማሳደር እንዳልቻሉና ይህን ያህል ለውጥ ማምጣት እንዳልሆነላቸው ሲያነሳ፤ ‹‹ማኅበራት ተጽእኖ ሊፈጥሩ አይደለም፤ ተገቢውን መረጃ አይሰጡም።›› የሚለው ሰለሞን፤ ከጥቂቶቹ በቀር አብዛኞቹ ለራሳቸው ጉዳይ ፈልገው ካልሆነ በቀር ጆሮአቸውን ክፍት አድርገው የሚያዳምጡ እንዳልሆኑ ይጠቅሳል።

አሻራ ሽልማት
‹‹አገራችን ላይ እንዳሉ ሌሎች ሽልማቶች ሁሉም የሚያየው እንዲሆን እፈልጋለሁ።›› ይላል ሰለሞን፣ ስለ አሻራ ሽልማት ወደፊት ርዕይ አዲስ ማለዳ ስትጠይቀው። ባለፈው ዓመት ኅዳር 24 ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሔደው ይህ የሽልማት መሰናዶ ዘሚ የኑስ፣ አማረ አስፋው፣ ጋዜጠኛ ደረሰ ታደሰ እና ሌሎች ብዙም ስማቸው ያልተነሳ ነገር ግን በአካል ጉዳት ላይ ትልልቅ ሥራ የሠሩ ሰዎች ተሸላሚ ሆነዋል። ሽልማቱም እንዲህ ያሉ ብዙ ዓመታት ስለ አካል ጉዳተኝነት የሠሩ ሰዎች፣ ማኅበራት፣ ተቋማት፣ ድርጅቶኅ የመሸለም፣ እውቅና የመስጠት፣ ተሰሚ እንዲሆኑ ማጉላትና ድጋ እንዲያገኙ የማሳወቅ ዓላማ አለው።

ይህ ሽልማት ቀጣይነት እንዲኖረው ደጋፊ ማስፈለጉ አያጠራጥርም የሚለው ሰለሞን፣ ሽልማቱ ለጊዜው ደጋፊ የሌለው መሆኑን ጠቅሷል። የአምናው የአሻራ ሽልማት መሰናዶ በብዙዎች ድጋፍ የተከናወነ መሆኑን ያወሳው ሰለሞን፣ ዘንድሮ በኹለተኛው የአሻራ ሽልማት ተመሳሳይ ድጋፍ ባይገኝም መጋቢ ሐዲስ እሸቱ ዓለማየሁን ጨምሮ፣ ተዋናይ ፍቃዱ ከበደ፣ ኮሜድያን ተፈሪ ብርቄ እና ሌሎችም በነጻ ለማገልገል የፈቀዱ መሆናቸውን ጠቅሷል። ሸገር የብዙኀን ትራንስፖርት ድርጅትም ሦስት ባሶችን በእለቱ እንግዶችን በየአቅጣጫው ለማድረስ እንደመደበላቸው ጠቅሷል።

ሰለሞን አሁንም ከሚያስብበት ትልቅነት ለመድረስ ሲል አላረፈም። አሻራ ሽልማት በጎ አድራት ማኅበር ተብሎ እንዲያድግና ተጽእኖ መፍጠር የሚችል እንዲሆን ይመኛል። አሁን ላይ በሙሉ የጋዜጠኝነት ሥራ ላይ የሚገኘው፣ አሻራ የራድዮ ፕሮግራምን በዋና አዘጋጅነት የሚመራውና በኤዲቲንግም ኃላፊነቱን ተቀብሎ የሚያቀናጀው ሰለሞን፣ ህልሙን ለማሳካት ጉዞውን እንደሚቀጥል ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል። ተራራውን ከፍቶ ማፍ ቢከብድ እንኳ አዲስ መንገድ መፈለጉን እንደማይተውም ጭምር።

ኹለተኛው አሻራ ሽልማት ታኅሳስ 20/2012 ብሔራዊ ቴአትር ይከናወናል። ሰለሞን ይህን ጥያቄ በሽልማቱ መርሃ ግብር ላይ እፎም በየሳምንቱ ባለው የራድዮን መሰናዶ ላይ ያነሳል። ‹‹እኛ ባለ አሻራ ትውልድ ነን፤ እናንተስ?››

ቅጽ 2 ቁጥር 60 ታኅሣሥ 18 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here