የአምቦ ጎጆዎች

0
862

አለፍ አለፍ ብሎ የልዩ ኃይል መለዩ የለበሱና መሣሪያ የታጠቁ ፖሊሶች ይታያሉ። ጠበብ ያለ መንገዷ በርከት ያሉ ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች ውር ውር ይላሉ፤ የተወሰኑ የጭነት መኪናዎችም ዳር ዳር መንገድ ይዘው ያታያሉ። ጭር አላለችም፤ ነዋሪዎቿ ማልደው እንቅስቃሴ ጀምረዋል። ብዙ ጊዜ ስሟ በሰላም የማይነሳው አምቦ እንቅስቃሴዋ ላይ የተለየ ነገር አይታይም፤ ሕይወት፣ ኑሮ ቀጥሏል።

ለከተማዋ ያልተሠራ እጅግ ብዙ ቀሪ ሥራ እንዳለ መታዘብ ይቻላል። መልኳን በሥሟ ልክ አልኳሉላትም ወይም ቀና እንዳትል አንዳች የጨከነባት እንዳለ፣ እድገቷ ወደፊት ከሚስበው ወደኋላ የሚጎትተው ይበረታል። አዲስ ማለዳም ከተወሰነ ትዝብቷ በቀር ከተማዋን ዞር ዞር ብሎ ለማየት ጊዜ ማግኘት አልሆነላትም። የአማቦ ጎጆዎችን የመቃኘት እድል ግን ገጥሟታል።

የአምቦ ጎጆዎች የነዋሪዎቿ ሕይወት የሚገኝባቸው ናቸው። በፈገግታና በመረዳዳት የተሞሉና የሚሞቁ ናቸው። በሮቻቸውን ከፍተው ‹‹ኑ ግቡ›› የሚሉ እንግዳ ተቀባዮች ተቆጥረው አያልቁም። ከዚህም ባለፈ የጉዞው ግብ በጭቃ ብቻ ያለእንጨት ማገር የተሠሩና ለአካባቢ ጥበቃ ትልቅ ጥቅም አላቸው የተባሉ ቤቶችን መጎብኘት ነበር።
ሰይፉ ታደሰ መምህር ናቸው። መብራትም ሆነ ንጹህ ውሃ ከሌለበት ከከተማዋ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ራቅ ብሎ በሚገኘው ዳሌ ዳዌ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የሚያስተምሩት። ከአምቦ ወደዚህ ትምህርት ቤት የሚያደርሰው መንገድ ብዙ መኪና የተመላለሰበት አይደለም። ይልቁንም ሞተሮች በብዛት ይታያሉ። አምስት ሰዎችን በአንዴ ይዘው የሚሔዱ ሞተሮችንም በፍጥነት መንገዱን ይመላለሱበታል። በተረፈ በፀሐይ ኃይል የሚሠራው በትምህርት ቤቱ የሚገኘው የመብራት አገልግሎት ፀሐይ ስትዳምን ብርሃኑን በጊዜ የሚያደበዝዝ፣ በክረምቱ ጭራሽ ብርሃን ከመስጠት የሚታቀብ ነው። በዚህ መካከል ግን የመምህርነት ሥራን የሙጥኝ ብለው የያዙ እንደ ሰይፉ ታደሰ ያሉ መምህራን ይገኛሉ።

ሰይፉ ትዳር መሥርተው የአንድ ልጅ አባት ሆነዋል። ቤታቸው ከትምህርት ቤቱ ቅጥር ጊቢ ውስጥ ነው። በቅድሚያ ትምህርት ቤቱን ጎብኝተን ስናበቃ ያቀናነውም ወደ እርሳቸው ጎጆ ነው።

የጭቃ ቤቶቹ
ዳሌ ዳዌ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ12 ዓመታት በፊት የተገነባ ሲሆን፣ ክፍሎቹ ከጭቃ የተሠሩ ናቸው። ከጭቃ ሲባል ሙሉ ለሙሉ ከጭቃ እንደማለት ነው እንጂ እንደሚታወቀው ዓይነት በእንጨት ማገር የሚሠራው አይደለም። መሠረቱ ከተገነባ በኋላ በጭቃ የተሠሩ ጡቦች ወይም ብሎኬቶች ተደርድረው ነው የትምህርት ክፍሎቹን የሠሩት። ይህም ትልቁ ግቡና ዓላማው እንጨትን አለመጠቀምና የደን ሐብትን መጠበቅ ነው።
‹‹በእንጨት የተሠራውን ምስጥ ይበላዋል፤ ትንሽ ዓመት ቆይቶ ወዳቂ ነው።›› ይላሉ አስተማሪው ሰይፉ። መኖሪያ ቤታቸውም በተመሳሳይ ከጭቃ የተሠራ ነው። ሆኖም ያ መሆኑ የፈጠረባቸው ስጋት አለመኖሩንና እንደውም ምሽት ላይ ቤቱ ሙቀት እንዳለው ጭምር ወደ ጎጇቸው ስንዘልቅ ነግረውናል።

በእርግጥ ቀደም ብለው መምህር ሆነው ባገለገሉባቸው አካባቢዎች በእንጨት ማገር የተሠሩ ቤቶች ውስጥ ኖረዋል። እሱን ብቻ ሳይሆን በትምህርት ቤቱ ጊቢ ውስጥ ሳይቀር ከጭቃ ቤቱ በኋላ የተሠራ የእንጨት ቤት ይታያል። በእንጨት ማገር የተሠራው ቤት ታድያ አጋድሎ በሚያሰጋ ደረጃ ላይ መድረሱን አዲስ ማለዳ መታዘብ ችላለች። እንግዲህ ‹በጭቃ ብቻ›› የተሠራ ቤትን ማን ያምናል? ግን በትክክል እነዚህ ቤቶች በእንጨት ከተሠሩት ልቀውና ተሽለው ተገኝተዋል፤ እድሜያቸውና አሁን ያሉበት ሁኔታም ይህን ይመሰክራል።

ሰይፉ በበኩላቸው አቅም ኖሮኝ የራሴን ቤት ከሠራሁ በጭቃ የመሥራት ሐሳብ አለኝ ብለዋል። ከጥራትም ከጥንካሬም አንጻር እመርጠዋለሁ ሲሉ ነው።

ቤቱ እንዴት ነው የሚሠራው ስትል አዲስ ማለዳ ጠይቃለች። በአምቦ ጭቃ ቴክኖሎጂ የሥራ አስተባባሪ ዘሪሁን ቱፋ ስለ እነዚህ ቤቶች መለስ ብለው ሲገልጹ፤ በአምቦ የጭቃ ቤቶችን የመገንባቱ ባህል የተዋወቀው በጀርመን የልማት አገልግሎት በተባለ ተቋም ድጋፍ የተጀመረ ነው ይላሉ። ያንን ተከትሎ ከ14 ዓመት በፊት የመጀመሪያው ቤት በአምቦ ተሠራ። ይህም እስከ አሁን ንቅንቅ ሳይል የሚገኝ ነው።

ለዚሁ ሲባል የምርምር ማዕከል መሠራቱን ዘሪሁን ጠቅሰዋል። ይህም የተለየ ምርምር የሚከናወንበት ሳይሆን ያለውን አፈር በተወሰኑና ጥቂት ምርመራዎች ለግንባት የሚሆኑ ስለመሆናቸው የሚለዩበት ነው። ግንባታውም ሲጀመር ማንኛውም በእንጨት ማገርና በጭቃ ለሚሠራ ቤት እንደሚዘጋጅ ሁሉ፤ ጭቃው በሚገባ ከጭድ ጋር ተደርጎ ይታሻል፤ ይቦካል። ቤቱን ለመሥራት የሚወስደው ጊዜ በወቅት ሊለያይ እንደሚችል ዘሪሁን ያስረዳሉ። በፀሐያማው ወቅት በቶሎ ማለቅ ሲችል በክረምት ግን ጭቃው በቶሎ ስለማይደርቅ ተጨማሪ ጊዜ ይጠይቃል።
ጭቃው ተቦክቶና ቀላል በሆኑ መሣሪያዎች በጡብ መልክ ተዘጋጅቶ በተዘጋጀለት ጥላ ስር ይቀመጣል። ፀሐይ ኃል በርትቶ ካገኘው ሊሰነጠቅ ይችላልና እንዲደርቅ ለማድረግም ጥላ ስር ማስቀመጥ ብልሃቱ ነው። በዚህ መሠረት ቢያንስ 3 ሳምንት ይወስድበታል። መገጣጠምና ጡቦቹን በጭቃ እያገናኙ መሥራቱ ሲቀጥል፤ ከወር በላ ጊዜ የሚፈጅ አይደለም።

እነዚህ ቤቶች በአምቦ ከተማ በትንሹ 14 ዓመት መቆየት ችለዋል፤ ያለ አንዳች መሰንጠቅ። እንደውም አስቀድሞ በጥናትና በሥራው ላይ የተሳተፉ አውሮፓውያኑ አንድ ሺሕ ዓመት ድረስ ይቆያል ሲሉ መግለጻቸውን ዘሪሁን ያስታውሳሉ። ‹‹እሱ ይቆየን›› ያሉት ዘሪሁን፤ ‹‹እኛ ቢያንስ መቶ ዓመት ይቆያል ብለን ይዘናል›› ሲሉ ገልጸዋል።
እነዚህ ቤቶች የደን መጨፍጨፍን ለመቀነስ ሁነኛ መሣሪያ ናቸው። በየቀኑ ለሚገነቡ ጥቂት ለማይባሉ ቤቶች ሁሉ የሚጨፈጨፈው ዛፍ እንዲተርፍም አማራጭ መንገድ ነው። ታድያ የአምቦ ነዋሪዎች ይህን የቤት አሠራ አውቀውበት እንዲሠሩ ለማስቻል ለም ኢትዮጵያ በተባለ ድርጅት በኩል ሥልጠናዎች ይሰጡ ነበር፤ ተሰጥተዋልም። ሥልጠናውን ወስደው ቤታውን ራሳቸው ከሠሩ ቤተሰቦች መካከል ወደ አንዱ አቀናን።

ኤርምያስ ነብይ ሞቅ ደመቅ ባለ፣ የንግድ እንቅስቃሴ ደምቆ በሚታይበት የአምቦ ከተማ አካባቢ ከባለቤታቸው ጋር መኖር ከጀመሩ ኻያ ዓመታትን ቆጥረዋል። በአምቦ ኪዳነምህረት ቤተክርስትያን በክህነት ያገለግላሉ። ልጆቻቸውን አምቦ ከተማ ላይ ወልደው፣ መርቀውና አስመርቀው ኩለው ድረዋል፤ የልጅ ልጅ ለማየትም በቅተዋል። ዛሬም በአምቦ ጎጇቸው ውስጥ ደስተኛ ሆነው እየኖሩ ይገኛሉ።

መጠጊያ ያልነበራቸውና ቤት ሳይኖራቸው የቆዩት ቀሲስ ኤርምያስ፣ ባለቤታቸው ሥልጠናውን ማግኘት ችለው ነበር። አምስት ወራትን ከወሰደው ሥልጠና በኋላ፣ ባሳዩት ጥሩ እንቅስቃሴና ብርቱ ተሳትፎ ምስጋና ከተቸራቸውና ቤት እንዲሠሩ ቦታ ከተሰጣቸው ኹለት እናቶች መካከል አንደኛዋ ለመሆን ችለዋል። እናም ቤቱን ሠርተው ጨርሰው ከ1997 ጀምሮ በዚህ ቤት ኑሮ ጀመሩ።

‹‹ጭቃ ቤት ውስጥ መኖር ይናድብን ይሆናል ስጋት ፈጥሮባችሁ አያውቅም›› ከጋዜጠኞች የቀረበላቸው ጥያቄ ነበር። ‹‹እስከሚናድ ክርስቶስ ወደ አንዲያው ቤት ሊወስደን ይችላል›› አሉ ባለቤታቸው። ቤቱ ስጋት ፈጥሮባቸው እንደማያውቅ አጥብቀው ሲገልጹ። ኤርምያስም ቀበል አድርገው፣ ‹‹እንደውም አስፋፍተን መብራት ገባልን፣ ውሃም እንደዛው።›› ሲሉ የቤቱን ሁኔታ ለምንታዘብ ሰዎች አስረዱን።

ለም ኢትዮጵያ በ1992 ሥራውን በይፋ የጀመረ የአካባቢ ጥበቃ እንቅስቃሴ ነው። ይህን እንቅስቃሴ በማስጀመር በኩል የኢፌዴሪ ፕሬዘዳንት ሆነው ያገለገሉት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ቀዳሚና የመጀመሪያ ተጠቃሽ ናቸው። ከእርሳቸው ቀጥሎ ቆስጠንጢኖስ በርሔ (ፒኤችዲ) በእንቅስቃሴው ዋና መሪ በመሆን አገልግለዋል።

በለም ኢትዮጵያ የፕሮጀክቱ አባል የሆኑት ዘሪሁን ኢሮ፤ ሥራው እንዲቀጥል ሥልጠና በመስጠትና ግንዛቤም በማጨበጥ ለም ኢትዮጵያ እንቅስቃሴ ያደርግ እንደነበር አስታውሰዋል። መነሻው የተፈጥሮ ጥበቃ ቢሆንም በታሰብ ልክ ብዙዎችን የእንቅስቃሴው አካል ማድረግ ግን እንዳልተሳካ ጠቅሰዋል። በትምህርት ቤቱ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎችም በጭቃ የተሠሩተን ቤቶች አይተው ይሠራሉ፣ ሥልጠና ያገኙትም ይተገብራሉ ተብሎ ቢጠበቅም ያ ሳይሆን ቀርቷል።

‹‹እንደ ማንኛውም በእንጨትም እንደሚሠራ ቤት ወጪው ሲቦካ ነው። እንጂ ማንም ሰው በቀላሉ መሥራት ይችላል›› ያሉት ዘሪሁን ኢሮ፣ ሆኖም ብዙዎች እንዳልተጠቀሙበት አውስተዋል። ‹‹የግንዛቤ እጥረት አለ፤ አሁንም በእንጨት ነው የሚሠራው። ገበሬው ጋር ቀርቦ ማስተማር ያስፈልጋል። እኛም ማስተማር አለብን፤ መቀስቀስ አለበት።›› ሲሉ አክለዋል። ለዚህም አስቀድሞ የጭቃ ቤት ሥራው በትምህርት ቤት እንዲጀመር የሆነው የወደፊት አገር ተረካቢዎች የሚወጡበት ቦታ በመሆኑ የተሻለ ግንዛቤ ሊኖራቸው ያስችላል በሚል እሳቤ ስለመሆኑም አክለው አስታውሰዋል።

ሆኖም የደን ሐብት እየቀነሰና ዛፎች እያለቁ እየሔዱ በመሆኑ፣ ወደዚህ የጭቃ ቤት ሰዎች ሊመጡ ይችላሉ ሲሉ እምነታቸውን ገልጸዋል። ከቀደመው እንቅስቃሴው በእጅጉ የቀነሰው ‹ለም ኢትዮጵያ›ም ከዚህ በኋላ በአዲስ መልክ ሥራውን ለመሥራት መንቃቱን ጠቁመዋል። የተዳከመውን የገንዘብ ምንጭ በማነቃቃት እንዲሁም በመንግሥት ተቋማት በኩልም መዘናጋቱን እንዲወገድ ጫና በመፍጠር ሥራው ይቀጥላል ብለዋል።

በእርግጥም አካሔዱ ወደዛ እንደሆነ የመጀመሪያው ምልክት ታይቷል ማለት ይቻላል። ከ‹ሶሊድ ኧርዝ አፍሪካ› የተሰኘ የአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚሠራና መቀመጫውን ኖርዌይ ያደረገ ድርጅት ከለም ኢትዮጵያ ጋር በጋራ ለመሥራት ዋዜማ ላይ ናቸው። በሶሊድ ኧርዝ አፍሪካ› የአካባቢ ተወካይ ዮሐንስ ታፈሰ በበኩላቸው፤ 2013 ጀምሮ አካባቢ ጥበቃ ላይ ለመሠማራትና እንጨት ቤቶችን በጭቃ ቤቶች ተክቶ ተፈጥሮን ለመጠበቅ እንጨት እንዳይባክን ለማድረግ ድርጅቱ እየሠራ ነው ብለዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 60 ታኅሣሥ 18 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here