የሴቶች ጥቃት በቃል ሳይሆን በተግባር ይቁም !- የትግራይ ሴቶች

0
236

👉🏿 ትኩረት ሰጥቼ እሰራለሁ- የክልሉ ፍትሕ ቢሮ

ማክሰኞ ሰኔ 18 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በትግራይ ክልል እየተበራከተ የመጣውን የሴቶች ጠለፋ እና እገታን በተመለከተ ዛሬ የትግራይ ሴቶች ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄዳቸውን አዲስ ማለዳ ከምንጮቿ ሰምታለች።

ሴቶችን እየታገቱ እና ገንዘብ እየተጠየቁ ከዛም አልፎ እየተገደሉ ባሉበት ጊዜ መንግስት ዝም ሊል አይገባም በማለት ሰላማዊ ሰልፍ ያደረጉ ሲሆን ለሞቱት እና ጥቃት እየደረሰባቸው ላሉ ሴቶች ፍትህ ይስፈን በማለት ድምጻቸውን አሰምተዋል።

በክልሉ ዋና ከተማ መቀሌ እንዲሁም አዲግራት፣ አድዋ እና አክሱም ከተማዎችና ሌሎችም አካባቢዎች የሴቶች መታገት እንዲሁም ግድያ በዝምታ እየታለፈ መሆኑ ለሰልፉ ምክንያት መሆኑን አዲስ ማለዳ ከምንጮቿ ተረድታለች።

የክልሉ የፍትሕ ቢሮ ኃላፊ ሀዲሽ ተስፋ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በማውገዝ ድምፃቸውን ያሰሙ ሴቶች ለመብታቸው መታገላቸውን መቀጠላቸውን ማሳያ ነው በማለት፤ በአሁኑ ወቅት በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት ሕግ እና ፍትሕ ባለበት አገር መከሰት የማይገባው አሳፋሪ ተግባር ነው ብለዋል።

ከወራት በፊት መቀሌ ላይ ዘውዱ የምትባል ወጣት በግድ ወደመኪና ሊያስገቧት በሚታገሉ በማይታወቁ ሰዎች በመኪና ተገጭታ ተገላ መገኘቷን እና ስለጉዳዩ እስካሁን የተባለ ምንም ነገር አለመኖሩን ሰልፈኞቹ አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም በአድዋ አካባቢ የ16 አመቷ ህጻን ማህሌት ተኽላይ “በአሰቃቂ ሁኔታ ለ91 ቀናት ታግታና በግፍ ተገድላ አስከሬኗ ተቀብሮ መገኘቱን አስታውሰው፤ በትግራይ ከጦርነቱ ወዲህ ሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃትና እገታ መባባሱ በተደጋጋሚ የሚገለጽ ድርጊት መሆኑን አመላክተዋል።

የሴቶች ጥቃትና እገታ እንዲቆም በራስ ተነሳሽነት በመሰባሰብ ሰላማዊ ሰልፍ ያደረጉ ሲሆን ወጣት ሴቶች፣ ልጃገረዶች ፣ እናቶች አርቲስቶችና ታዋቂ ሴቶችም መሳተፋቸውን ጠቁመዋል።

ሰልፋቸውንም ወደ ፕሬዝዳንት ቢሮ አካባቢ ሲያደርጉ እንደነበር አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች፡፡ ይህ ዜና ተጠናቅሮ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ከመንግስት አካላት የተሰጠ ምንም አይነት ምላሽ የለም።

በተመሳሳይ በጎንደር ከተማ የሰው እገታ ወንጀል እየተባበሰ በመምጣቱ ምክንያት  ሰኔ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ) ከ12 ሰዓት በኋላ ላልተወሰነ ጊዜ መንቀሳቀስ እንደማይችል የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ አስታውቆ ነበር፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተማዋ በቡድን በሚንቀሳቀሱ ሀይሎች የሰው እገታ ወንጀል እየጨመረ መምጣቱም ተጠቁሟል።

የትግራይ ሴቶች ጥያቄ ወቅታዊና ተቀባይነት ያለው ነው ያለው የፍትሕ ቢሮው መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጿል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here