በፍትሕ ስርዓቱ ላይ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ሁኔታ የለም በማለት የትግራይ ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ኃላፊዎች ስራ መልቀቂያ አስገቡ 

0
424

ማክሰኞ ሰኔ 18 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የትግራይ ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንት የጀመሯቸውን ስራዎች በአግባቡ ለመቀጠል የሚያስችል ሁኔታ በማጣታቸው ኃላፊነታቸውን በፈቃዳቸው መልቀቃቸውን ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ አስታውቋል።

የክልሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በፕሬዝዳንቱ ዶ/ር ጸጋይ ብርሃነ እና ምክትል ፕሬዝዳንቱ ገብረአምላክ የዕብዮ ተፈርሞ ትላንት ሰኔ 17 ቀን ለትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት በተላከው ደብዳቤ ለዘጠኝ ወራት ለቆዩበት ኃላፊነት ምስጋና አቅርበው በፈቃዳቸው ስራ ለመልቀቅ ጠይቀዋል።

ይኹን እንጂ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ የጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንቱ በጉዳዩ ላይ በይፋ ምላሽ አልሰጠም።

የከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ኃላፊዎች በመልቀቂያ ደብዳቤያቸው እንደገለጹት በፍትህና የዳኝነት ስርዓቱ ለውጥ ለማምጣት ያሰቧቸውን፣ በእቅድ የያዟቸውን እና የጀመሯቸውን የለውጥ ስራዎች ለማሳካት የሚያስችል ሁኔታ ማግኘት አልቻሉም።

በዚህም የተነሳ በክልሉ የፍትሕ እና የዳኝነት ስራ ውስጥ እያጋጠሙ የሚገኙ እና “አሁንም ያልተሻገርናቸው” ሲሉ የገልጿቸው ተግዳሮቶችን ለመፍታት በሌላ መንገድ የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ በመግለጽ “በፍላጎታችን ስራችንን ለመልቀቅ መወሰናችንን በትህትና ለማሳወቅ እንወዳለን” ማለታቸውን አዲስ ማለዳ ከደብዳቤው ተመልክታለች።

የትግራይ ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና ምክትላቸው ያቀረቡትን ጥያቄ የጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንቱ አገናዝቦ እንዲቀበለው ጠይቀው ምላሽ እስከሚያገኙ በኃላፊነታቸው ላይ ላልተጠቀሰ ጊዜ እንደሚቆዩ ተገልጿል።

ሁለቱ ኃላፊዎች በትግራይ ክልል ተቀስቅሶ ለሁለት ዓመታት ከቆየው የእርስ በእርስ ጦርነት በኋላ የፕሪቶሪያ ስምምነትን ተከትሎ የተሾሙ ሲሆን ያለፉትን ዘጠኝ ወራት በኃላፊነት ቆይተዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here