በሁሉም ክልሎች ለማለት በሚያስችል ሁኔታ የዘፈቀደ እስር፣ የጅምላ እስር ወይም የፍርድ ቤት ውሳኔ አለማክበር ተፈጽሟል- የኢሰመኮ ዓመታዊ ሪፖርት 

0
299

ዓርብ ሰኔ 28 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሰኔ 2015 እስከ ሰኔ 2016 ድረስ ያለውን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ዓመታዊ ሪፖርት ይፋ አድርጓል።

132 ገጾችን የያዘው ዓመታዊ ሪፖርት በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክልሎች የትጥቅ ግጭቶች፣ ጥቃቶች ወይም የጸጥታ መደፍረሶች ከሐምሌ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. እስከ ግንቦት ወር 2016 ዓ.ም. የተመዘገቡ ሲሆን፣ በዚህ ሳቢያ በታጣቂ ኃይሎች እና በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በተወሰዱ እርምጃዎች በሲቪል ሰዎች ላይ የሚደርስ የሞት እና የአካል ጉዳት አሳሳቢነት እንደቀጠለ ተመላክቷል።

በተለይም በትጥቅ ግጭት ዐውድ ውስጥ በሲቪል ሰዎች ላይ የሚደርሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንደቀጠሉ እና እንደተስፋፉም በሪፖርቱ ተመላክቷል።

አዲስ ማለዳ ከኮሚሽኑ ባገኘችው የሪፖርት ማጠቃለያ በትጥቅ ግጭት፣ በግጭት ውስጥ በቆዩ አካባቢዎች እንዲሁም ግጭት በሌለበት ሁኔታም ጭምር የሚፈጸም ከሕግ ውጪ የሆኑ የሲቪል ሰዎች ግድያ አሳሳቢ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል በሲቪል ሰዎች ላይ በትጥቅ ግጭቱ እንዲሁም በግጭቱ ዐውድ ውስጥ ከሚደርሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች በተጨማሪ ሲቪል ሰዎችን ዒላማ ያደረገ እገታ አሳሳቢነት ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን ሪፖርቱ አሳስቧል።

ለ10 ወራት በጸናው የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጅ ወቅት ከኮማንድ ፖስቱ ትዕዛዝ ውጪ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በሲዳማ፣ በማእከላዊ ኢትዮጵያ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች የሚዲያ እና የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸው ተጠቁሟል።

የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ መጽደቅ በዚህ ዓመት ከተከናወኑ የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ማሻሻያ ስራዎች መካከል ዋነኛ እንደሆነም በሪፖርቱ ተገልጿል።

የመንቀሳቀስ መብትን በተመለከተ በሪፖርቱ እንደተመላከተው በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ባለው የጸጥታ ሁኔታ ወይም በሚጣሉ ገደቦች ምክንያት በየብስ የሚደረግ እንቅስቃሴን አዳጋች አድርጓል።

በተጨማሪም የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ወይም በታጣቂ ቡድኖች ለተከታታይ ቀናት የሚዘጉ መንገዶች ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ችግር እየፈጠሩ፣ በሸቀጦች ዋጋ እና በገቢ እንዲሁም በጤና እና ትምህርት አገልግሎቶች ተደራሽነት ላይ ጫና እያደረሱ ሲሆን በዘንድሮ በጀት ዓመትም በተለይ በአማራ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ እና በኦሮሚያ ክልሎችም መቀጠላቸውን ሪፖርቱ ጠቁሟል።

በመጪው ዓመት ትኩረት እንዲሰጣቸው ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ማሳሳቢያ ከሰጠባቸው ጉዳዮች መካከል የትጥቅ ግጭቶች በሰላማዊ ውይይት መፍታት፣ የሀገራዊ ምክክር እና የሽግግር ፍትሕ ሂደት ተዓማኒ አተገባበር ማረጋገጥ፣ ከፍርድ ቤት ትእዛዝ ውጪ በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎች ሁሉ በአፋጣኝ መልቀቅ አልያም የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ማድረግ፤ በሰብዓዊ መብቶች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ በሚያሳድሩ ሕግ እና ፖሊሲዎች ላይ ማሻሻያ ማድረግ፤ በጥበቃ ሥር ያሉ ሰዎች እና የታራሚዎች የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ማሻሻልና ማረጋገጥ ዋነኞቹ ናቸው።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here