የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሕንጻ ለንግድ ቤቶች ኪራይ ክፍት ተደረገ 

0
238

ማክሰኞ ሐምሌ 02 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና መስሪያ ቤት ይገኝበት የነበረው ሕንጻ ከዚህ ቀደም በፒያሳ ዙሪያ ሲሰሩ ለነበሩ ነጋዴዎች ለኪራይ ክፍት መደረጉ ተገለጸ።

አዲስ ማለዳ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ባገኘችው መረጃ ከዚህ በፊት ፒያሳ አካባቢ የተለያዩ የንግድ አገልግሎት ሲሰጡ ለነበሩ የወርቅ መሸጫ ሱቆች፣ ባቅላባ ቤት፣ የመዋቢያ እቃ መሸጫ ሱቆች፣ የእጅ ሰዓት መሸጫ፣ አልባሳት መሸጫ ቤቶች፣ ኬክ ቤቶች፣ የቡና ቤቶች እና ሌሎች በአካባቢው የንግድ አገልግሎት ሲሰጡ ለነበሩ ድርጅቶች ቅድሚያ በመስጠት ሕንጻውን ማከራየት ይፈልጋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና መስሪያ ቤት ሜክሲኮ አካባቢ ወደሚገኘው የንብ ባንክ ሕንጻ እንደተዘዋወረም ታውቋል።

በፒያሳ አካባቢ ከላይ በተገለጹት የንግድ ዘርፍ አገልግሎት ሲሰጡ እንደነበር ከሚመለከተው አካል የተረጋገጠ ማስረጃ በማቅረብ ከሐምሌ 8 እስከ 12 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ፒያሳ በሚገኘው ኤሌክትሪክ ህንጻ ምድር ወለል ቢሮ ቁጥር 001 መከራየት የምትፈልጉትን የቦታ ስፋትና ወለል በመጥቀስ በንግድ ቤቱ ባለቤት/ህጋዊ ወኪል የተፈረመ የኪራይ ፍላጎት ማሳወቂያ ደብዳቤ እንዲያስገቡ ተጠይቋል።

ከዚህ ቀደም በአካባቢው የንግድ አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ ስለመሆኑ ማስረጃ ማቅረብ፣ የታደሰ ንግድ ፍቃድና የዘመኑ ግብር መክፈላቸው ማረጋገጫ ማቅረብ፣ በተቋሙ የህንጻ አስተዳደር ህግና አሰራር ለመተዳደር ዝግጁ መሆን፣ ምሽትን ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ በሚያስቀምጠው የጊዜ ገደብ አገልግሎት መስጠት፣ ተቋሙ በሚያወጣው የገበያ ኪራይ ዋጋ ተመን ኪራይ መክፈል ዋና መስፈርቶች ናቸው ተብሏል።

ተቋሙ የሚቀርበውን የተከራዮች ብዛትና የቦታ ኪራይ ፍላጎት መሰረት በማድረግ ከሐምሌ 12 ቀን በኋላ ቀጣይ ሂደቱን እንደሚያሳውቅ አስታውቋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here