የ‹ዲ ፋክቶ› መንግሥት 30ኛ ዓመት!

0
776

የ›ዲ ፋክቶ›ን ጽንሰ ሐሳብና ምንነት የሚጠቁሙት ግዛቸው አበበ፥ ልብ አልተባለም እንጂ ቀድሞም በኢትዮጵያ ይልቁንም በትግራይ ክልልና በሕወሓት አገዛዝ የ‹ዲ ፋክቶ› መንግሥት ባህርያት ይታዩ ነበር ይላሉ። እንደውም ሠላሳ ዓመት ሞልቶታል ሲሉ ይጠቅሳሉ። አሁን ላይ ስለ መገንጠልና መለየት እንዲሁም ስለ ‹ዲ ፋክቶ መንግሥት› ምሥረታ የሚያስቡትና የሚያወሩት የሕወሓት አባላትና ደጋፊዎች እንጂ ሕዝቡ አለመሆኑንም የተለያዩ ማሳያዎችን በመጥቀስ ያብራራሉ።

ከቻይና ቻንሲ ግዛት የመጡ ቢዝነስ ተኮር ልዑካን ወደ መቀሌ እንዳይሔዱ ቦሌ ላይ ታገዱ የሚለው ዜና በቢቢሲ ተጀምሮ በዶቸቨለና በቪኦኤ በተከታታይ ሰፊ ሽፋን ያገኘ ነበር። በእርግጥ ቻይናዎቹ ወደ መቀሌ ባይዘልቁም ከትግራይ ባለሥልጣናት አንዱ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ከቻይናውያኑ ጋር በቢዝነስ ጉዳዮች መስማማታቸውንና መፈራረማቸውን ከእነዚሁ ሚዲያዎች ሰምተናል።

ይህ ከሆነ በኋላ በዕለተ ሰኞ፣ ታኅሳስ 23/2012 በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተሰጠው መግለጫ አዲስ አበባ ላይም መንግሥት የለም የሚል ዓይነት አንድምታ ያለው ጥበብ የጎደለው ሰበብ ድርደራ ነው። እስከ ዛሬ ከሱዳን ጎንደር፣ ከጅቡቲ አዲስ አበባ፣ ከአማራ ክልል ወደ ትግራይ፣ አንዳንዴም ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ መንገድ ላይ ነበር፣ ሕገ-ወጦች ያሻቸውን እያደረጉ ችግር የሚፈጥሩት። አሁን ደግሞ ቦሌ ላይ ከመንግሥት ዕውቅና ውጭ በጥባጮች መኖራቸው እየተነገረን ነው። ያውም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ነው የተነገረው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቻይናው የልዑክ ቡድን ጉዞ ስለመስተጓጎሉ መረጃው እንዳልነበረው፣ ችግር የፈጠሩት በቦሌ አየር ማረፊያ ያሉ የጥበቃ አባላት ሳይሆኑ እንደማይቀሩና ጉዳዩም እየተጣራ መሆኑን መግለጫ ሰጥቷል። ይህ መግለጫ ስርዓተ አልበኝነትና መንግሥት አልባነትም አንዳንዴ ቦሌ ድርስ ይዘልቃል ብሎ ማረጋገጫ ከመስጠት የሚተናነስ አይደለም። ካልሆነ ግን የራሱን የመንግሥትን አሳፋሪ የጉዳዮች አያያዝ የሚያጋልጥ ነው።

የቻይናዋ የኩንሻን ግዛትና የድሬዳዋ አስተዳደር ተመሳሳዩን ነገር ሲያደርጉ ምንም ችግር ሳይከሰት፣ ወደ ትግራይ ለማቅናት በተዘጋጁት የቻንሲ ልዑካን ላይ ይህ ችግር መከሰቱ ያጠራጥራል። የዐቢይ አሕመድ መንግሥት ብዙም ሳያስብበት ሕወሐትን ለመበቀል ወይም ሕወሐቶችን ለማበሳጨት ወይም በአሳፋሪ መንገድ የበላይነቱን ለማሳየት እርምጃ እንደወሰደና፤ ከዚያም ቆም ብሎ በማሰብ ‹እኔ የለሁበትም!› ብሎ ሥራውን ሽምጥጥ አድርጎ እየካደ መሆኑን ለመጠራጠር በር የሚከፍት ነው።

የድሬዳዋ ባለሥልጣናትም ሆኑ የትግራይ ባለሥልጣናት በተለያዩ ጊዜያት ወደ ቻይና ሄደው የአሁኑን የስምምነት መድረክ ለመፍጠር ሥራ እንደሠሩና ይህን ተከትሎ ቻይናዎች ወደ ክልሎቹ ያመሩ መሆኑ ይታወቃል። ይህ እየታወቀ ቦሌ ላይ ተፈጠረ የተባለው ችግር መከሰቱ አሳፋሪም፣ አስተዛዛቢም ነው። ወደ ትግራይ ለመሔድ የተነሱት ቻይናዎች ጉብኝት ቢስተጓጎልም፣ መንግሥት የትግራይ ክልል ተወካይ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ እንዲፈራረሙ ማድረጉን ነግሮናል።

ጉዞ የሚያስተጓጉል ችግር መፈጠሩ ሲታወቅ ችግሩን ከመቅረፍና ቻይናዎቹ ወደ መቀሌ እንዲያመሩ ከማድረግ ይልቅ፣ የትግራይ ባለሥልጣን ወደ አዲሰ አበባ እንዲመጡ የተደረገው ለምንድን ነው? መንግሥት ጣቱን የቀሰረባቸው የቦሌ ጥበቃዎች ከመንግሥት አቅም በላይ ሆነው ጉዞው ከነ አካቴው እንዲሰረዝ ድርቅ ስላሉ ነውን?
ለማንኛውም የልዑኩ ጉዞ መሰናከሉን ተከትሎ የትግራይ ባለሥልጣናት ተጨማሪ ምሬቶችን እያስተጋቡ ነው። እስከመቼ በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እየተገፋን እንዘልቀዋለን ሲሉም ተሰምተዋል። ይህ ምሬት የሕወሐት ሰሞነኛ ዛቻ ‘ዲ ፋክቶ መንግሥት’ እሆናለሁ የሚል ከመሆኑ ጋር ተደማምሮ ‘ትግራይ ናበይ?!’ (ትግራይ ወዴት?!) እያስባለ ነው።

የሕወሐትና የደጋፊዎቻቸው ጉዳይ
‘ዲፋክቶ’ (de fac-to / dé facto) የሚለውን ቃል ‘…በዕውን ያለ፣ ነገር ግን ሕጋዊ ማንነት ወይም ሕጋዊ ምንነት የሌለው…’ ብሎ መተርጎም ይቻላል። ‘ዲፋክቶ መንግሥት’ በዕውን ያለ፣ የሚገዛው ወይም የሚያስተዳድረው ‘አገርና ሕዝብ’ ያለው አገዛዝ ሆኖ በብሔራዊ ይሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕጋዊ ዕውቅና የሌለው መንግሥት ማለት ነው። እግረ መንገዳችንን ‘ዲ ፋክቶ’ በአገራችን ከሚታዩት ሁኔታዎች አንጻር በሌላ ጉዳይም እየተተገበረ በመሆኑ ስለ ‘ዲ ፋክቶ ኮርፖሬሽን’ እንመልከት።

‘ዲ ፋክቶ ኮርፖሬሽን’ ሕጋዊነት ሳይኖረው ምርት እያመረተ ወይም አገልግሎት እየሰጠ ወይም እየነገደ የሚኖርና ተቋም ይገልጻል። ታዲያ ላለፉት በርካታ ዓመታት ኢትዮጵያችን ውስጥ ‘ዲ ፋክቶ መንግሥት’ እና ‘ዲ ፋክቶ ኮርፖሬሽን’ የሚባል ነገር የለም ሊባል ይችላልን? ለሌሎች የኢትዮጵያ ፖለቲካ ድርጅቶች ሕግ አይፈቅድላችሁም ተብለው የተከለከሉና ለሕወሐትና ፍጥረታቱ ለሆኑት የፖለቲካ ድርጅቶች ብቻ ተፈቅደው በንብረትነት የተያዙ ብሮድካስቲንግ ሚዲያዎች፣ አምራች ድርጅቶች፣ በንግድና አገልግሎት መስጠት የተሰማሩ ኩባንያዎች ‘ዲ ፋክቶ ኮርፖሬሽን’ ሊባሉ አይገባምን?

በድጋሜ ‘ትግራይ ወዴት!’ እንበል። በእርግጥ 2010 ከተጋመሰ በኋላ፣ ሕወሐት ወደ መቀሌ መሸኘቱን ተከትሎ በሕወሐት ሰዎችና በደጋፊዎቻቸው ብቻ ሳይሆን የሕወሐት ተቃዋሚ መስለው በግብራቸው ሕወሐታዊ በሆኑ ግለሰቦችና ቡድኖችም ጭምር ስለ ትግራይ ያልተባለ ነገር የለም።

ባለፉት የሕወሐት/ኢሕአዴግ የአገዛዝ ዓመታት ስለ ዴሞክራሲና ስለ ፌዴራሊዝም ብዙም ተጨንቆ የማያውቀው፣ 2011 ግም ካለበት ጊዜ ጀምሮ ‹ዴሞክራሲን መታደግ› ‹ፌዴራሊዝምን ማስቀጠል› ወዘተ እያለ በሚያካሒዳቸው ስብሰባዎችና ኮንፈረንሶች የተጠመደው መቀሌ ዩንቨርሲቲ፣ ምሁራንና የፖለቲካ ሳይንስ አዋቂዎች እያለ በሚጋብዛቸው ግለሰቦች አማካኝነት የእነዚያ አሳፋሪና አሳዛኝ ወሬዎች ዋና ፋብሪካ ሆኖ ይታያል። ወሬው የሕወሐት ተቃዋሚ ነን በሚሉ የወያኔ ተለጣፊዎች በተለይም ከነሥሙ ‹‹ሣልሳይ ወያኔ›› ተብሎ በሚጠራው ድርጅት አመራሮችም ወሬዎችን ያለማሰለስ ከሚያስፋፉት ተርታ ተሰልፈዋል።

እነዚህ ወገኖች በየሚዲያውና በየተገኙበት ስብሰባ ወዘተ… ‹ትግራይ የኢትዮጵያ አካል መሆኗ እየጎዳት ነው› ከሚል የእንገንጠል ቅስቀሳ ጀምሮ ‹ትግራይ ኢትዮጵያዊት አይደለችም› እስከሚለው የቅኝ ተገዛን፣ ነጻ እንውጣ እሮሮ ድረስ እያስተጋቡ ኹለት ዓመት ሊደፍኑ ነው። ከእነዚህ ምሁራንና ተቃዋሚ ነን ባይ ግለሰቦች አንዳንዶቹ፣ ‹ትግራይ እስከመቼ ነው ኢትዮጵያን የምትሸከማት?› ብለው የሕወሐት አለቆችን የሚቆጡ የሚያስመስል አስቂኝ ድራማ ሲሠሩ ይስተዋላሉ። ይች ድራማ የሕወሐት አለቆች በተደጋጋሚ በተለይም የክልሉ ምክትል ፕሬዘደንት ደብረጽዮን ገብረሚከላኤል (ዶ/ር) ‹…እንገንጠል የሚል ግፊት እየበረታብን ነው፤ ትንሽ ታግሰን ነገሩን እንየው እያልን ሕዝቡን እያረጋጋነው ነው…› እያሉ ከሚናገሯት ጋር የምትሄድና ድራማውን ሙሉ ለማድረግ የምትነገር ነገር ናት።

ኢትዮጵያዊ አይደለንም እና ከኢትዮጵያ እንገንጠል የሚሉት ግለሰቦችና ቡድኖች ከ2010 ጀምሮ ‘ትግራይ ናበይ?’ ለሚለው ጥያቄ የተለያዩ መልሶችን ይዘው ለመቅረብ ሞክረዋል። አንዳንዶቹ በግላጭ ሌሎቹ ደግሞ በተዘዋዋሪ መንገድ የትግራይ ዕጣ ከኤርትራ ጋር መሆኑን ለማስረዳት ሞክረዋል። ሙከራው ዘርዘር ተደርጎ ሲታይ ኹለት ዓይነት ምኞት ይንጸባረቅበታል።

አንዱ ምኞት ከትግርኛ ተናጋሪ የኤርትራ አውራጃወች ጋር በመሆን ‘ትግራይ-ትግርኝ’ የተባለ አገር መመሥረት ነው። ሌላው ምኞት ደግሞ ከየት እንደመጣ የማይታወቅ ‹ምድረ አግአዝያን› የተሰኘ አገር መመሥረት የሚል ነው። ባንዲራ ተሰርቶለት ሲቀነቀን የከረመው ይህ ምኞት፣ ኤርትራን የሚፈልገው በሙሉ ይሁን በከፊል ግልጽ አልሆነም። ኤርትራንና ትግራይን አጣብቆ አገር ለመመሥረት ያለመ ሐሳብ ነው።

ትግራይን ከኢትዮጵያ መገንጠል የሚለው ሐሳብ በተነሳ ቁጥር ብዙው የትግራይ ሕዝብ አምርሮ ስላጣጣለውም ትግራይ አትገነጠልም የሚል የሰላ ትችት ወርዶበታል። እናም አሁን አልፎ አልፎ በአንዳንድ ወገኖች በተለይም በሣልሳይ ወያኔ አመራሮች አንደበት የሚዘወተር ወሬ ብቻ ሆኖ ቀርቷል። ‘ትግራይ-ትግርኝ’ እና ‘ምድረ አጋአዝያን’ ስለሚባል አገር የሚወራው ወሬም በኤርትራውያን ዘንድ ቅስም ሰባሪና አሽመድማጅ ምላሽ ስለጎረፈበት፣ ጉዳዩን መልሶ ማውሳት አሳፋሪና አንገትን አስደፊ ቅሌት ወደ መሆን ወርዷል።

በአገራችን በኢትዮጵያ ውስጥ ላለፉት በርካታ ዓመታት ይህን ‹ዲ ፋክቶ› የሚል መጠሪያ የሚያሟላ መንግሥትና ይህን መጠሪያ የሚያሟሉ ድርጅቶች አሉ። አዎ! በደንብ አሉ። ድምጺ ወያነ፣ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እና ዋልታ በየትኛው ሕግና ደንብ ተቋቁመው ነው በመሥራት ላይ ያሉት? ሕወሐት፣ ብአዴን/ኢሕዴን፣ ኦሕዴድ በትግል ዘመን ባፈሩት ሃብት የተመሰረቱ እየተባሉ በዘርፈ ብዙ እና በከፍተኛ ቢዝነስ ውስጥ የተዘፈቁት እነ ኤፈርት፣ ጥረት፣ ዲንሾ ወዘተስ በየትኛው ደንብና ሕግ ነው ሕልውና አግኝተው በከፍተኛ ደረጃ የአገርን ሃብት የተቆጣጠሩት?
በየጊዜው የሚሰነዘረውን ሐሰተኛ መሸፋፈኛና ማስመሰያ እንተወውና፣ እነዚህ ድርጅቶች ‘ዲ ፋክቶ ኮርፖሬሽን’ የሚለውን መግለጫ በሚገባ የሚያሟሉ ናቸው። እነዚህ ተቋማት በመላ አገሪቱ እንዳሻቸው እየሠሩ ነው ያሉት፣ ነገር ግን ተገቢውን ሕጋዊ መንገድ ተከትለው የተመሠረቱና የሚኖሩ አይደሉም። እነዚህ የሕወሐት/ኢሕአዴግ ተቋማት ግብር ስለሚከፍሉ ሕጋዊ ናቸው ብሎ መከራከር ይቻል ይሆናል፤ ነገር ግን ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች እነዚህን የመሳሰሉ ተቋማት ሊያቋቁሙ ቢሞክሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ስለሆናችሁ አትችሉም እንደሚባሉ ግልጽ ነው።

ለእነዚህ ተቋማት መኖር ዋስትና የሆናቸው የሕወሐት አጼ በጉልበቱነትና የፈለገውን ለማድረግ ራሱን ከሕጎች በላይ ያስቀመጠ ቡድን መሆኑ ነው። ኢሕአዴግ የሚለውን መሸፋፈኛ ስንገላልጠው ደግሞ የ‹ዲ ፋክቶ›ነት መመዘኛዎችን በሚገባ የሚያሟላውን ሕወሐትን እናገኘዋለን። ሕወሐት ሲያሻው በመንግሥት ውስጥ ሌላ መንግሥት ይሆናል፣ ትግራይን በአገር ውስጥ ሌላ አገር ያደርጋታል።

ሕወሐት ከፌዴራላዊው ሥልጣን በተጨማሪ በየትኛውም ክልል እጁን ማስገባት፣ ያሻውን መሾምና መሻር፣ በክልሎች የፖለቲካ የበላይነቱንና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ ወዘተ ሙሉ መብቱ ሆኖ ኖሯል።
ሕወሐት ይህን ሁሉ በጠራራ ፀሐይ እንዲያደርግ የሚፈቅድለት ሕግም ሆነ የሕገ-መንግሥት አንቀጽ ኖሮ አይደለም። የፌዴራሊዝምን የጨዋታ ሕግ ሽሮ፣ በትዕቢት ‹መሣሪያው ካለኝ ምን ታመጣለህ?› ብሎ፣ በየክልሉ የመለመላቸውንና ለግል ጥቅማቸው ሲሉ በወዶ ገብነት የተንበረከኩለትን ግለሰቦች ተጠቅሞ፣ ሕገ-ምድርንና ሕገ-ሰማይን ሁሉ ችላ ብሎ፣ ተቃውሞዎች ሲነሱም ግፍና ሰቆቃን በመጠቀም ጭጭ እያሰኘ ጭምር ነው።

ከመጋቢት 1980 ጀምሮ ከፊል ትግራይ፣ ከሚያዝያ/ግንቦት 1981 ጀምሮ ደግሞ ሙሉ ትግራይ በሕወሐት እጅ ውስጥ የገባች ክፍለ አገር/ክልል ናት። ከመጋቢት 1980 ጀምሮ የደርግ/ኢሰፓ መንግሥት ብዙውን የትግራይ ክፍል ትቶ በመቀሌ፣ ሽረ-እንዳሥላሴ፣ ማይጨው እና በዙሪያቸው ብቻ መጠነኛ ሥልጣን የነበረው ሲሆን፣ የሽረ-እንዳሥላሴውን አውዳሚ ጦርነት ተከትሎ፣ ከሚያዝያና ግንቦት 1981 ጀምሮ ደግሞ የደርግ መንግሥት ሙሉ በሙሉ ትግራይን ጥሎ ወጥቶ ነበር። ስለዚህ ቢያንስ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ትግራይ ከሕወሐት ሌላ ገዥ ኖሯት አያውቅም።

ግንቦት 1983 ሕወሐት ደርግን ጠቅልሎ ማሸነፉንና የአራት ኪሎውን ቤተ-መንግሥት መረከቡን ተከትሎ፣ ሕወሐት የመላ ኢትዮጵያ ገዥ መሆኑ ተረጋግጧል። ሰኔ 1983 ላይ ኮንፈረንስ ተካሂዶ በተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች አማካኝነት የሽግግር መንግሥት ተቋቋመ ቢባልም፣ የሽግግሩ ቻርተር በወረቀት ላይ ሰፍሮ፣ በተግባር የታየው ግን ሕወሐት ራሱ በጠፈጠፋቸውና አታሎ ወይም አግባብቶ ሎሌዎቹ ባደረጋቸው ቡድኖች ሽፋን የሁሉም ክልሎችና የኢትዮጵያም ገዥ እሱና እሱ ብቻ መሆኑ ነው።

በመጋቢት 1980 ከተወሰኑ የትግራይ አካባቢዎች፣ ከ1981 መገባደጃ ጀምሮ ደግሞ ከመላው ትግራይ የኢትዮጵያ አረንጓዴ-ቢጫ-ቀይ ባንዲራ ወርዶ የሕወሐት ባንዲራ የትግራይ ባንዲራ ተብሎ ብቻውን መውለብለቡ ሊረሳ የማይገባው ትውስታ ነው። በ1984 በትግራይ ተቋርጦ የነበረው መደበኛ የመንግሥት ሥራ እንደ አዲስ ሲጀምሩ፣ በትምህርት ቤቶችና በየመሥሪያ ቤቱ ሲውለበለብ ይታይ የነበረው የሕወሐት/ትግራይ ባንዲራ ብቻ ነበር።

በትምህርት ቤቶች የማለዳ የንባዲራ ሰልፍ ላይ የሚዘመረው የሕወሐት የበረሀ መዝሙር እንደ ትግራይ ብሔራዊ መዝሙር ተደርጎ ሲሆን እየተዘመረለት ወደ ዓላማው የሚወጣው ባንዲራም ያው የሕወሐት/ትግራይ ባንዲራ ነበር።
በብዙ ቦታዎች የትግራይ ሰዎች ‘እኛም እንደ ኤርትራ ተገንጥለናል እንዴ!’ እያሉ በመገረም ይጠይቁ ነበረ። በዚያን ጊዜ ኤርትራ ገና ሪፈረንደም አላካሔደችም። በስምምነቱ መሰረት የኤርትራ ሕዝብ በድምጹ እስኪወስን በኤርትራ የኢትዮጵያ ባንዲራ እንደሚውለበለብ፣ ኢትዮጵያውያን እስከ ሪፈረንደሙ ኢትዮጵያዊነትን አንዲሰብኩና መገንጠልን እየተቃወሙም ቢሆን ቅስቀሳ እንዲያካሂዱ የተፈቀደ ቢሆንም፣ በተግባር ይህን ነገር መሞከር ግን እያረፈና ‘ሥራ እየፈታ’ ለነበረው የሻእቢያ ጠመንጃ ሲሳይ ሊያደርግ የሚችል ነገር ሆኖ ይታይ ነበር። ለዚህ ነው የትግራይ ሰዎች ‹እኛም እንደ ኤርትራ ተገነጠል እንዴ› ሲሉ የተሰሙት።

አዎ! ትግራይ ውስጥ በጣም ብዙ ሰዎች የኢትዮጵያ ባንዲራ በመሥሪያ ቤታቸው ለምን እንደማይውለበለብም ይጠይቁ ነበር። በጎላ ድምጽ ይህን መሰል ጥያቄ ሲጠየቅባቸው ከነበሩ ቦታዎች አክሱም 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አንዱ ነው። በዚህ ትምህርት ቤት በጣም ብዙ መምህራን የኢትዮጵያ ባንዲራ እንዲውለበለብ ከመጠየቅ አልፈው የኢትዮጵያ ባንዲራ የማይውለበለብ ከሆነ በሰልፍ ቦታ አንገኝም እስከ ማለት የደረሰ ተቃውሞ አሰምተው ነበር።
የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተሮች፣ ‹‹ከፈለጋችሁ እንጨት ተክላችሁ የራሳችሁን ባንዲራ ማውለብለብ ትችላላችሁ፣ እኛ ግን የተዋደቅንለትን ይህን (የሕወሐት) ባንዲራ ነው የምናውለበልበው›› ሲሉ መልስ የሰጡበት ጊዜ ነበር።

የኢትዮጵያ ባንዲራ በትግራይ ትምህርት ቤቶች፣ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና በበአላት ወቅትም በጎዳናዎችና በአደባባዮች በክልሉ መንግሥት ትዕዛዝ መውለብለብ የጀመረችው የባድሜው ጦርነት ግም ሲል ነው። ይህን ሃቅ ማንም በዚያን ዘመን ነገሮችን ልብ በሚልበት ዕድሜ ላይ የነበረ የትግራይ ተወላጅና በሥራ ጉዳይ በትግራይ ይኖር የነበረ ሰው የሚያስታውሰው ነው። ከ1990 በፊት የኢትዮጵያ ባንዲራ ቀለማት የሚታዩት በእናቶችና በወጣት ሴቶች የሐበሻ ቀሚስ ጥለት ላይ፣ በአንዳንድ ቤቶች የውስጥ ግድግዳ ተለጥፎ ወዘተ… ብቻ ነበር።

ሕወሐት ሞሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካን መክፈቱን ተከትሎ ሲሚንቶ ወደ ሱዳን እንደሚልክ ይወራል። ሕወሐት ለዚህ ፋብሪካው ከሱዳን የደንጋይ ከሰል ሲመጣና የፋብሪካው ምርት የሆነውን ሲሚንቶ ወደ ሱዳን ሲልክ በራሱ ፍላጎትና ፈቃድ እንጅ እሱ ራሱ አዛዥና ናዛዥ የሆነበት ማዕከላዊው መንግሥት ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር እያደረገበት አልነበረም። ሕወሐት ገቢው ሲዳብር የኢትዮጵያው መንግሥት ሕወሐት/ኢሕአዴግ የገቢ ድርሻ አልጠየቀበትም።
ሕወሐት ትግራይ ውስጥ በከፈተው የሥጋ ፋብሪካም የሕወሐትን ‹ዲ ፋክቶ› መንግሥትነት የሚረጋግጥ ሥራ ሠርቷል። የመቀሌው አሉላ አባነጋ አውሮፕላን ማረፊያ የዓለም ዓቀፍ ደረጃ ያለው አውሮፕላን ማረፊያ እንዲሆን መደረጉን ተከትሎ፣ ሕወሐት የሥጋ ፋብሪካ ምርት ወደ አረብ አገራት የመላክ ተደጋጋሚ ሙከራ አድርጋለች። ይህ የሕወሐት ራሱን የቻለ የሥጋ ኤክስፖርት ሥራ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የማእከላዊ መንግሥት አካላት ችላ ያለና በሕወሐት ‘ዲ ፋክቶነት’ ብቻ ሊካሄድ የተሞከረ ንግድ ነው።

በእርግጥ አጀማመሩ ላይ ሥጋው ወደ አረብ አገራት ከደረሰ በኋላ የሚደረግበትን ምርመራ ማለፍ ስላልቻለ ኤክስፖርቱ ለሕወሐት ገቢ ከማስገኘት ይልቅ አሳፋሪ ሸቀጥ ሆኖ በእሳት ተቃጥሎ ይወገድ ነበር። ኢትዮጵያም ትከስር ነበረ። ይህ የሕወሐት ንግድ አሁን በምን ደረጃ ላይ አለ ቢባል፣ የሚሰማ ነገር የለም።

ወርቅ፣ ብር፣ ዶላር ወዘተ… ማከማቸት በጭምጭታ እየተሰሙ ብዙ ዓመታትን ያስቆጠሩ ሕወሐት ብቻ የሚያደርጋቸው (ሌሎች ክልሎች የማይሞክሯቸው) ተግባራት ናቸው። በየዓመቱ ከትግራይ ወደ ማዕከላዊ መንግሥት የሚላካው ወርቅ ከ800 እና ከ900 ኪሎግራም ወደ 95 እና 100 ኪሎ ግራም መውረዱ ተሰምቷል። የት ሄደ? ሕወሐት ሌሎች በይፋ ያልተነገሩ ወይም በምስጢር የተያዙ ሥራዎችንም እንደሠራና እንደሚሠራ በጭምጭምታ ይነገራል። ታዲያ ምን ጎደለውና ምንስ ሊያሞላ ይሆን መንግሥት መሆን አለብኝ የሚለው?
ለማንኛውም ከ1982 ጀምሮ ትግራይ በዲ ፋክቶ አገዛዛ ስር ናት፤ ትግራይ በዚህ መንገድ እየተጓዘች እነሆ 2012 ላይ ደርሳለች። ሕወሐቶች እንደ አዲሰ ‘ዲ ፋክቶ መንግሥት’ እንመሰርታለን ቢሉም፣ እኛ ግን እንኳን ለ30ኛው ዘመነ ዲፋክቶአችሁ አበቃችሁ እንላቸዋለን።

ግዛቸው አበበ መምህር ናቸው።
በኢሜይል አድራሻቸው gizachewabe@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 60 ታኅሣሥ 18 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here