ኹለተኛ ዙር የኤሌክትሪክ ታሪፍ ማሻሻያ በያዝነው ወር መጨረሻ ይተገበራል

0
1074

ከ2011 ጀምሮ በአራት ዓመታት ተከፋፍሎ በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ላይ የሚደረገው የታሪፍ ማሻሻያ ኹለተኛ ዙር ከታኅሳስ ወር መጨረሻ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።
አገልግሎቱ በኢትዮጵያ የነበረው የአገልግሎት ታሪፍ ከ12 ዓመታት በላይ ማሻሻያ ሳይደረግበት የቆየ መሆኑን በማንሳት፣ እንዲሁም እየጨመረ ከመጣው የኤሌክትሪክ ፍላጎት እና ደንበኛ ብዛት ጋር የሚመጣጠን አገልግሎት ለመስጠት በሚያስችል ሁኔታ የገቢ አቅሙን ለማሳደግ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ለአራት ተከታታይ ዓመታት ተግባራዊ የሚደረግ ታሪፍ ማሻሻያ በመቅረፅ ወደ ተግባር መግባቱ ይታወቃል።

የመኖሪያ ቤት የታሪፍ ማስተካከያው ሰባት እርከን ያለው ሲሆን፣ በዚህ እርከን ውስጥ የሚገኙ የመጀመሪያዎቹ ሦስት እርከኖች ላይ ድጎማ እንደተደረገ ተገልጿል። አዲሱ የክፍያ ስርአትም ተጠቃሚዎች እንደቀድሞ በእየ እርከኑ ያለውን ታሪፍ በመደመር የሚከፍሉበት ሳይሆን የፍጀታ መጠናቸው በሚያመላክተው እርከን ውስጥ ብቻ ያለውን እንዲከፍሉ የሚያደርግ እንደሆነ የድርጅቱ መረጃ ያመላክታል።

ተግባራዊ በሚደረገው የኹለተኛው ዙር የታሪፍ ማሻሻ፣ያ በወር እስከ 50 ኪሎ ዋት የሚጠቀሙ ደንበኞች የታሪፍ ጭማሪው የማይመለከታቸው ሲሆን እስከ 200 ኪሎ ዋት ለሚጠቀሙ ደንበኞች እንደየ ደረጃቸው ድጎማ እንደሚደረግላቸው ታውቋል።

ከ200 ኪሎ ዋት እስከ 500 እና ከዚያ በላይ ኃይል በሚጠቀሙ የመኖሪያ ቤት ደንበኞች ላይ በእያንዳንዱ ኪሎ ዋት ሰዓት ከ70 ሳንቲም ጀምሮ እስከ አንድ ብር የሚደርስ ጭማሪ እንደሚኖርም ተገልጿል።

አገልግሎቱ በእየዓመቱ እየጨመረ የሚመጣውን የኤሌክትሪክ ፍላጎት ለማሟላት ከፍተኛ የገንዘብ አቅም ውስንነት እንዳለበት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ መላኩ ታዬ ጠቅሰዋል። ከኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚገኘውን ትርፍ ድርጅቱ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር እንደሚካፈል የገለፁት መላኩ፣ የአገልግሎት ድርጅቱ ድርሻ 40 በመቶ መሆኑን አንስተዋል።

የታሪፍ ማሻሻያው አገልግሎቱ የሚያከናወናቸውን የጥገና እና ኃይልን የማዳረስ ሥራዎችን ለማጠናከር እንደሚረዳ የገለፁት መላኩ፣ አሁንም ከሌሎች የዓለም አገራት ጋር ሲነጻጸር ርካሽ የኃይል አቅርቦት በኢትዮጵያ ይገኛል ብለዋል። አክለውም የኃይል ፍላጎቱ በእየዓመቱ 13 በመቶ እንደሚያድግ ገልጸው፣ እስከ አሁን ከአጠቃላይ የአገሪቷ ሕዝብ 44 በመቶ የሚሆነው ብቻ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እያገኘ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ማሰራጫ መስመሮች በርካታ ዓመታትን ያስቆጠሩ መሆናቸው ኃይልን በሚፈለገው ደረጃ እና ጥራት ማቅረብ እንዳይቻል ማድረጉንም አክለዋል።

በእየዓመቱ እስከ 2014 የሚደረገው የታሪፍ ማሻሻያ ኅብረተሰቡ ኃይልን በቁጠባ እንዲጠቀም ለማድረግ እንደሚረዳ የተገለፀ ሲሆን፣ የአገልግሎት ድርጅቱ ያለበትን የገንዘብ እና የግብዓት እጥረት ችግሮች ለማቃለል እና ኃይል ባልደረሰባቸው አካባቢዎች ኃይልን ለማዳረስ አቅም እንደሚፈጥር ተገልጿል።

አገልግሎቱ እስከ 2017/18 የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ለጠቅላላው ማኅበረሰብ ማዳረስ የሚል ግብን አስቀምጦ እየሠራ ይገኛል።

ቅጽ 2 ቁጥር 60 ታኅሣሥ 18 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here