በፀጥታ ኃይሎች ሕይወታቸው ስላለፈ ግለሰቦች ማብራሪያ አለማግኘታቸውን ቤተሰቦች ገለፁ

0
689

በሰኔ 17 እና 18/ 2011 በአዲስ አበባ ከተማ በፀጥታ ኃይሎች ሕይወታቸው ያለፈው የጭነት አስተላላፊ የነበሩት የሙሉጌታ ደጀኔ እና የንግድ ባንክ ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ኢሳያስ ታደሰን አሟሟት በተመለከተ ፖሊስ ለወራት ቢያመላልሳቸውም ምንም ዓይነት መረጃም ሆነ ማብራሪያ ማግኘት እንዳልቻሉ የሟች ቤተሰቦች ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ።

የሙሉጌታ ወንድም የሆኑት ዮናስ ደጀኔ እንደሚሉት፣ ለስድስት ወራት የአዲስ አበባ ፖሊስ የአስከሬን እና የመሣሪያ ምርመራ ውጤት እየተጠባበኩ ነው በሚል ሲያጉላላቸው ቆይቷል። ከዚህ በተጨማሪም ሟች ሕይወታቸው እንዳለፈ ፖሊስ ወስዶት የነበረው ኮሮላ መኪና፣ በኪሳቸው የነበረ ኹለት ሺሕ ብር፣ መታወቂያ እና አንድ የእጅ ስልክ እንደተመለሰላቸው ገልፀዋል።

‹‹ሐሰተኛ ሰነድ ይዞ ነበር ያሉት፣ ምንም ነገር መኪናው ወስጥ አላገኘንም፣ አንድ ሳምሰንግ ስልኩንም ጠፍቷል›› ሲሉ ተናግረዋል። ‹‹በዚህ ሳምንት እንኳን አዲስ አበባ ፖሊስ ማክሰኞ ቀጥረውኝ ሄድኩ፤ ከዛ ሐሙስ ና አሉኝ፤ ሐሙስ ስሔድ ደግሞ ለሚቀጥለው ሳምንት ማክሰኞ ቀጠሩኝ፣ እንዲሁ ነው ስድስት ወር የሞላወ›› ብለዋል።
የኢሳያስ እህት የሆኑት ገነት ታደሰ እንደሚሉት ‹‹ከመንግሥት የተሰጠ ትዕዛዝ ነው፤ ምንም ማድረግ አንችልም የሚል መልስ ነው የሰጡን›› ሲሉ ለአዲሰ ማለዳ ተናግረዋል። የወንድማቸውን ገዳይ ባለማወቃቸው ከሞቱ በላይ እንደጎዳቸው ተናግረው፤ ለአሟሟቱ እንድ እንኳ ማብራሪያ ወይም ይቅርታ ያለ አካል የለም። ‹‹ወላጅ አባቴ ይህንን መልስ ለማግኘት ለወራት ቢመላለስም መልስ የሚሰጥ አካል አላገኘም። እንደውም ባለፈው የመኪና አደጋ ደርሶበት እስከ አሁን ያመዋል›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ሰኔ 18/2011 ጠዋት 4 ሰዓት አካበቢ በተለምዶ ሳሪስ አዲስ ሰፈር ድልድይ አካበቢ በሚባለው ልዩ ቦታ ኹለት ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት አድርሰው በመመለስ ላይ ሳሉ ሲቪል የለበሱ የጸጥታ ኃይሎች በመኪና እንደተከተሏቸውና እሳቸውም ለመሸሽ መሞከራቸውን አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል። በዕለቱ ሟች ሙሉጌታ እኚህ ማንነታቸውን ያላወቋቸው ኹለት ሰዎች በመኪና ሲከታተሏቸው፣ መንገዱ በመዘጋቱ በእግራቸው ወርደው ሊሸሹአቸው ሞክረው ነበር፡፡

ኹለት የደንብ ልብስ የለበሱ የፀጥታ ኃይሎች እንደያዟቸው እና ሟች ከሩቅ ሲያዩ የነበሩ የደንብ ልብስ የለበሱ የአዲስ አበባ ፖለሲ አባላትን ‹‹እናንተ ውሰዱኝ እነሱን አላውቃቸውም›› በማለት ደጋግመው ሲጠይቁ እንደነበርም የአካባቢው ነዋሪዎች መግለፃቸውንም አዲስ ማለዳ በዘገባዋ አካትታለች። ከዚህ በኋላም ግለሰቦቹ ሟች ሙሉጌታን ብብቱ ስር እንደመቷቸው እና ምንም እንኳን የአስከሬን ምርመራ ውጤት ባይሰጣቸውም፣ ቤተሰቦቻቸው አስከሬን በተመለከቱ ጊዜ ብብታቸው ስር በጥይት መመታቸውን እና ጭንቅላታቸው ላይም ጉዳት መድረሱን መታዘባቸውን ገልፀው ነበር።

በተመሳሳይ ሰኔ 17/2011 ጠዋት 2 ሰዓት አካባቢ በተለምዶ ብስራተ ገብረኤል ተብሎ ከሚጠራው አካበቢ ወደ ዑራኤል አካባቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የካትሪን ሃምሊን ቅርንጫፍ ከሞተረኛ ጓደኛቸው ጋር በመሔድ የነበሩት ኢሳያስ ከፀጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት ሕይወታቸው አልፏል። የቅርንጫፉ የቢዝነስ ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ግለሰብ፣ ሽንጣቸው አካባቢ በጥይት መመታቻውን ወላጅ አባታቸው አስከሬናቸውን ተመልክተው ማረጋገጣቸውን አዲስ ማለዳ ዘግባ ነበር፡፡ በሞተር ትራንስፖርት ሥራ ይተዳደሩ የነበሩት የኢሳያስ ጓደኛ በተመለከተም፣ በተመሳሳይ ምንም ዓይነት ተጠያቂነት ሳይወስድ መቅረቱን አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች፡፡
የሟች ሙሉጌታ ወንድም የሆኑት ዮናስ እንደሚሉትም፣ ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር እንዳሻው ጣሰው ‹‹ጥቃቱን ያደረሰው የአዲስ አበባ ፖሊስ ሆኖ ራሱን መርምር ማለቱ አግባብ አይደለም›› የሚል ማመልከቻ እንደገበላቸው እና ይህንንም ጠቅሰው ምርመራው በአግባቡ እንዲከናወን ሲሉ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ደብዳቤውን መላካቸውን ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ተባባሪ ፕሮፌሰር ስሜነሀ ኪሮስ እንደሚሉት፣ በኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች የኃይል አጠቃቀም ለመግታት የሚያስችል የሕግ ክፍተት የለም። ነገር ግን መንግሥት ሕዝቡን ለመጨቆኛ ስለሚጠቀምባቸው ሊነካቸው ስለማይፈልግ ሕጉን አይተገብርም፤ ፖሊስም ተጠያቂ ሲሆን የማይታየው ለዚህ ነው ይላሉ።

በተለይም በወንጀል ሕጎች ማስተማር እና ምርምር በማድረግ አንጋፋ የሚባሉት ስሜነህ፣ ጥፋተኛውም ክስ ሰሚውም ፖሊስ ስለሚሆን ለፍትኅ መስተጓጓል ምክንያት ይሆናል፣ የትኛውም ተቋም ራሱን አሳልፎ አይሰጥም ሲሉም ይናገራሉ። ለዚህም የዐቃቤ ሕግ ሚና ቀላል አይደለም፤ እንደ ባለሞያው ገለፃ።

‹‹ዐቃቤ ሕግ ለመጀመሪያ ጊዜ ምርመራ አካሄድኩ ሲል የሰማነው በደኅንነት እና በፖሊሶች ላይ በቅርቡ ባካሔደው ሥራ ነው። ይህ በተለይ የፀጥታ ኃይሎችን ለመመርመር ጥቅም ላይ ሊውል ይገባል። እነዚህ ጥፋተኞችን የሚዳኘው ፍርድ ቤትም ገለልተኛ መሆን ይገባዋል›› ይላሉ።

እንደ ስሜለህ ገለፃ፤ የተጠያቂነት ባህል የሌለው በፖሊስ ላይ ብቻ ሳይሆን ማንኛውም የመንግሥት መዋቅር ያለው ተጠያቂነት ዝቅ ያለ ነው። እንደ አገር ይህንን የተጠያቂነት ባህል መቀየር እና የፖሊስን ሆነ የፀጥታ ኃይሉን ሥነ ምግባር ማሻሻል ለነገ የማይባል ድርጊት ነው።

‹‹በየትኛውም አገር ውስጥ የፀጥታ ኃይሎች ያለአግባብ ኃይለ መጠቀም አለ፣ ነገር ግን እንደዚህ በአደባባይ ሰው ገድሎ ዝም አይባልም። ይህንን ለመቀነስ መሥራት ግዴታ ነው›› ያሉት ስሜነህ ‹‹የሟች ቤተሰቦችም በፍትኀ ብሔር ለደረሰባቸው ጉዳት ማስረጃ ከሰበሰቡ በኋላ ክስ መመሥረት ይችላሉ፡፡ በተጨማሪም ሰብአዊ መብት እና የእንባ ጠባቂም ሐየደው አቤት የሚሉበት የሕግ መዋቅር አለ፡፡ የፖሊስ አዛዦች ምን አልባት የማያውቁ ከሆነ ለእነርሱ ማሳወቅ እንዲሁም ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉም አቤት ማለት አለባቸው።››

አክለውም ተገጂዎች ጋዜጣዊ መግለጫ በማውጣት ‹‹ፍትኅ ይሰጠንኅ› ሲሉ መጠየቅ ይችላሉ። እንደውም ከየትኛውም አማራጭ ይህ ውጤታማ ነውም ይላሉ። አዲስ አበባ የአፍሪካ መቀመጫ በመሆኗ ሚዲያው የተሻለ ፍትኅ እንዲያገኙ እና ይህ ድርጊትም እንዳይደገም በመግለጫ መጠቀሙ የተሻለ መሆኑንም አመላክተዋል።

‹‹መንግሥት የጀመረው የፍትኅ ማሻሻያ ሥራዎች ሲገባደዱ ምን አልባት የተጠያቂነት ጥያቄዎች ይጠቃለላሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። የፀጥታ ኃይሎች በሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጠውን በሕይወት የመኖር መብት ሊጥሱ አይችሉም፣ የፖሊስ ዋናው መቀየር ያለበት አስተሳሰቡ ነው። የፖሊስ ኃይል ከሚለው ቃል ጀምሮ ብዙ ችግር ያለበት ይህ መዋቅር፣ በተለይ በሥልጠና ብዙ ሊሠራበት ይገባል›› ሲሉም አስተያየታቸውን ለአዲስ ማለዳ ሰጥተዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 60 ታኅሣሥ 18 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here