በዩኒቨርሲቲዎች የሰዓት እላፊ ተጣለ

0
570

የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስቴር በ45 የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች ከንጋት 12 ሰዓት በፊት እና ከምሽት አንድ ሰዓት በኋላ ከግቢ ውጪ አንዳይንቀሳቀሱ መመሪያ አስተላለፈ። በዩኒቨርሲቲዎች ዉስጥ በተፈጠሩ ክስተቶች ተማሪዎች እየተጎዱ በመሆናቸው ለተወሰነ ጊዜ የሰዓት እላፊ እገዳ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ መመሪያው መተላለፉን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ ባስተላላፈው መመሪያ መሰረት ተማሪዎች ከሰዓት እላፊ በኋላ ከግቢ ዉጭ እንዳይገኙ በተጨማሪም የግቢ ጥበቃ ኀላፊዎች፣ ፌዴራልና የክልል ፀጥታ አካላት ከሰዓት እላፊዉ ዉጭ የተገኘ ተማሪ ደኅንነት በተመለከተ ኃላፊነት አይወስዱም። የተማሪዎች መኝታ ቤት ፕሮክተሮች ተማሪዎች ከዶርም ዉጭ ከአራት ሰዓት በኋላ እንዳይገኙ ክትትል እንዲያደርጉም ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል።

የሚኒስቴሩ የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ደቻሳ ጉርሙ እንዳሉት፣ ‹‹ይህ ውሳኔ ወለጋ ዩኒቨርስቲ ሞቶ የተገኘው ተማሪ የተገደለው አሳቻ ሰዓት መሆኑን እና ጥፋተኛ ተብለው ከዩኒቨርሲቲው የሚታገዱ ወይም የሚባረሩ ተማሪዎች ሌሎች አማራጮችን እንዳይጠቀሙ በሚቻለው አቅም ሁሉ ለተማሪዎቹ ሕይወት ሙሉ ጥንቃቄ ለማድረግ በሚል የተወሰነ ነው›› ሲሉ ገልጸዋል።

በተመሳሳይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በፌዴራል ፖሊስ እንዲጠበቁ ተወስኖ የነበር ሲሆን፣ ይህንንም ተቋማቱ አስፈላጊ አይደለም በሚል መቃወማቸው ይታወሳል። ነገር ግን የፌዴራል የትምህርት ተቋማት ቢጠበቁም አሁንም ግጭቶች እንደቀጠሉ ነው።

በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሂደቱ በድጋሚ የተቋረጠ ሲሆን፣ በዩኒቨርሲቲው ብሔርን መሰረት ያደረገ አለመግባባት በተፈጠረ ብጥብጥ የታሰሩ ተማሪዎች እንዲፈቱ በሚል ምክንያት የተደረገ የትምህርት ማቆም አድማ መሰረት፣ ተማሪዎች ትምህርት ማቆማቸዉ እና ወደ ቤታቸዉ መመለሳቸውን የድሬዳዋ ተማሪዎች ተናግረዋል። በተጨማሪም በዩኒቨርሲቲዉ ያሉ ተማሪዎች በፀጥታ አስከባሪዎች ላይ ድንጋይ እየወረወሩ እንደነበር እና በዩኒቨርሲቲዎች ያሉ ተማሪዎች ላይ ፌዴራል ፖሊስ ጉዳት እንዳደረሰ የዐይን እማኝ ተማሪዎች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በዮኒቨርሲቲዎች ዉስጥ የሚፈጠሩ የሰላም መደፍረስ ለማረጋጋት እና በመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውስጥ መማር ማስተማር ሂደት እንዲቀጥል ይረዳል በማለት የሳይንስ እና ከፍተኛ ሚኒስቴር አማካኝነት፣ ከ25 ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን ጨምሮ የተለያየ አካላትን ያሳተፈ ዉይይት ተደርጓል። በዚህ መሠረት ከተለያዩ ከፌዴራል የመንግሥት መሥሪያ ቤት የተወጣጡ ኃላፊዎችን በማካተት ቡድን ወደ ዩኒቨርሲቲዎች ተሰማርተዉ ዉይይት ከተጀመረ ቀናት ተቆጥረዋል።

በወሎ ዩኒቨርሲቲም በተያዘው ሳምንት ግጭቶች ተነስተው የነበር ሲሆን፣ የመማር ማስተማር ሂደቱም መስተጓጎሉን አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ተወካዮች ተናግረዋል።

በመሆኑም በዩኒቨርሲቲዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን ትምህርት በሁሉም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ከሚቀጥለዉ ሳምንት በኋላ ይጀምራል ተብሏል።

ቅጽ 2 ቁጥር 60 ታኅሣሥ 18 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here