ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ማስረጃዎችን መስጠት ጀመረ

0
789

ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለዐስር ዓመታት አቋርጦት የነበረውን ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ለተማሩ እና ዩኒቨርሲቲው የሚጠይቀውን መስፈርት ላሟሉ ተመራቂዎች ዋናውን የትምህርት ማስረጃ ሰርተፍኬት መስጠት መጀመሩን አስታወቀ።

ከ 2002 ጀምሮ በዩኒቨርሲቲው ትምህርታቸውን ላጠናቀቁ ተማሪዎች ዋና የትምህርት ማስረጃ መስጠት ማቆሙን ተከትሎ፣ በርካታ ጥያቄዎች ሲነሱበት ቆይቷል። በያዝነው ዓመት ግን በመጀመሪያ ዙር ለ150 ጥያቄ አቅራቢዎች የትምህርት ማስረጃዎችን መስጠቱ ተገልጿል።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሬጅስትራር ዋና ኀላፊ ዘውዴ ፀጋዬ ከ2002 ጀምሮ በተተገበረው የአስተዳደር ለወጥ ምክንያት የትምህርት ማስረጃዎችን ማተም አልተቻለም ነበር። በመሃልም ሥራውን ለማከናወን የበጀት እጥረት በማጋጠሙ ሥራው ተቋርጦ ቆይቶ ነበር ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አክለውም፣ ችግሩ በማታ እና በቀን እንዲሁም በርቀት ከመጀመሪያ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በዩኒቨርሲቲው በተከታተሉ ተማሪዎች ላይ መፈጠሩ የገለፁ ሲሆን፣ ከዐስር ዓመታት በላይ ሥራው ተቋርጦ በቆየቱ ከፍተኛ የማስረጃ ፍላጎት እንዲኖር አድርጓል ብለዋል።

ከእነዚህ በተጨማሪ በኹለተኛ ዙር ከ110 ጥያቄ አቅራቢዎች የትምህርት ማስረጃዎችን ለማቅረብ ዝግጅት ላይ ነን ያሉት ኀላፊው፣ የትምህርት ማስረጃዎቹ መሰጠት መጀመሩ እምብዛም አልተሰማም፣ ሲሰማ የጥያቄው ቁጥር ከፍ ይላል ብለዋል።

አባይ ማተሚያ ድርጅት የህትመት ሥራውን በማከናወን ላይ ሲሆን፣ ህትመቱ ምስጢራዊ መሆኑን የገለፁት ዘውዴ፣ አሁን ሥራው እየተጀመረ በመሆኑ ከአንድ ወር እስከ ሦስት ሳምንት ባለው ጊዜ ውስጥ የትምህርት ማስረጃ ለጠየቀ ተማሪ ለማድረስ በመሠራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

ከ1993 ጀምሮ ታትመው የተቀመጡ እስከ አሁን ያልተወሰዱ የትምህርት ማስረጃዎች አሉ። ባለቤቶቻቸው የወጪ መጋራት እና መሰል ግዴታዎች ባይኖሩባቸው እንኳን እስከ አሁን አልወሰዱም። ይህ ደግሞ ለማስቀመጥ እና ጥበቃ ለማድረግ ከፍተኛ ችግር እንደፈጠረባቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

‹‹አትሞ ለማስቀመጥ በቂ የገንዘብ እና የቦታ አቅርቦት ስለሌለን ያለፈው ስህተት እንዳይደገም ጥያቄውን በሚያቀርቡት ሰዎች ልክ እያዘጋጅን በመስጠት ላይ ነን። በየጊዜው በርካታ ጥያቄዎች ይነሳሉ። እኛም በጊዜያዊነት ችግሩን ለመቅረፍ ለተቋማት ደብዳቤዎችን በየቀኑ እንፅፋለን›› ያሉ ሲሆን፣ አሁን የህትመት ሥራው መጀመሩ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ይረዳናል ብለዋል።

አንድ የትምህርት መረጃን ለማግኘት ከሦስት ሳምንታት እስከ አንድ ወር ጊዜ የሚወስድ ሲሆን፣ ይህም የፎርጅድ መረጃዎችን ለመከላከል በሚሠሩ ሥራዎች እና በምስጢራዊ ህትመት ምክንያት የመጣ መሆኑን ዩኒቨርሲቲው ገልጿል።

የህትመት ሥራው በቅርብ የተጀመረ በመሆኑ የሚወስደው ጊዜ እንደሚረዝም እና ወደፊት ጠያቂዎች እስከ አንድ ሳምንት ባለ ጊዜ ውስጥ የትምህርት ማስረጃዎቻቸውን እንዲያገኙ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑ ተጠቅሷል።

ቅጽ 2 ቁጥር 60 ታኅሣሥ 18 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here