ኔክሰስ ሆቴል ከስዊዘርላንዱ ስዊስ ኢን ሆቴል ጋር የብራንድ ስምምነት አደረገ

0
1093

ሆቴሉ ውሉ ለአስር አመታት እንደሚቆይ ገልጿል

በአዲስ አበባ ከሚገኙ ባለኮኮብ ሆቴሎች መካከል ሆኖ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው ኔክሰስ ሆቴል መሠረቱን በአውሮፓ ካደረገው ከስዊዝ ኢን ሆተል ጋር በገባው የፍራንቻይዝ ውል፣ ሥሙን ወደ ‹ስዊስ ኢን› በመቀየር እና የስዊዝ ኢን ሆቴሎች ሰንሰለትን ደረጃ በመጠበቅ በመጪው አንድ ወር ወደ ሥራ ሊገባ እንደሆነ አስታወቀ።

በቦሌ ክፍለ ከተማ በተለምዶ አንበሳ ጋራጅ አካባቢ የሚገኘው ሆቴሉ፣ ሙሉ ለሙሉ ሥሙን የማይተው ሲሆን ‹‹ስዊስ ኢን ኔክሰስ›› በሚል ሥያሜ ወደ ሥራ ይገባል። ለወራት በዘለቀው የሆቴሉን ደረጃ ከፍ የማድረግ ሥራም የተለያዩ አነስተኛ የማሻሻያ ሥራዎች እያከነወነ ሲሆን፣ ወደ ሥራ ለመግባትም በስዊዘርላንድ ከሚገኘው የስዊስ ኢን ሆቴሎች ዋና መሥሪያ ቤት የሽያጭ ፍቃድ ማግኘቱንም አክሎ ገልጿል። ሆቴሉ ከሥያሜ በሻገር የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ለውጥ ማድረጉን የገለጸ ሲሆን፣ ይህ ውልም ለአስር ዓመታት እንደሚቆይ አስታውቋል።

በተጨማሪም 15 ሚሊዮን ብር ባወጣው እድሳት የሆቴሉን ደረጃ ከፍ ለማድረግ አንዳንድ የሆቴሉን መሰረተ ልማቶች መቀየሩንም የሆቴሉ ባለድርሻ እና ምክትል ሥራ አስኪያጅ ዜና ዳዊት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። አክለውም ከመሠረታዊ የአገልግሎት መሠረተ ልማቶች ለውጥ ባሻገርም የሆቴሉ ዋና መግቢያ ላይ የኹለቱን ሆቴሎች ብራንድ በሚያሳይ መልኩ ለውጥ በመደረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል። ‹‹ቴራሳችን ደረጃውን የጠበቀ ዝግጅቶችን ለማዘጋጀት የሚረዳ መንገድ እየገነባን ነው›› ያሉት ዜና ‹‹ከአንድ ወር በኋላ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለተጠቃሚዎች በአዲሱ መዋቅር እና ጥራት አገልግሎት ይሰጣል›› ብለዋል።

ሆቴሉ ካሉት 151 ክፍሎች ሙሉ በሙሉ የስዊስ ኢንን የጥራት ደረጃ ማሟላታቸው የተገለፀ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ የምግብና የመድኀኒት የጤና ክብካቤ አስተዳደር እና ቁጥጥር ባለሥልጣን አዲስ በደነገገው ትንባሆ ሕግ መሰረት ለዉጦች መደረጋቸውንም ተናግረዋል።

ሰዊስ ኢን ሆቴል እና ሪዞርቶች መቀመጫው በስዊዘርላንድ ላንቺስተር ሲሆን፣ በግብፅ በተለይም በካይሮ፣ ሳዉዲ አረቢያ እንዲሁም በተለያዩ አዉሮፓ አገራት የየራሳቸዉ አገር ጥራት መሰረት ከሦስት እስከ አምስት ኮከብ ያላቸዉ ቅርንጫፎች አሉት።

በኢትዮጵያ ከኔክሰስ ሆቴል ጋር የሚሰጠው የአራት ኮከብ ደረጃ ሲኖረው፣ አሁን ከሚደረጉ ማሻሻያዎች በኋላ ወደ አምስት ኮከብ ሊያድግ ይችላል የሚል ግምት እንዳላቸዉ ምክትል ሥራ አስኪያጁ አስታዉቀዋል። ከስዊስ ሆቴል ጥራት ጋር ተወዳዳሪ ለመሆን በሚደረገዉ እድሳት ላይ በቂ እና ምቹ የመኪና ማቆሚያ ማግኘት እንደከበዳቸዉ እና የማስፋፋት እንዲሁም ምቹ የሚሆንበትን መሰናዶ እንደሚሠራበት ዜና ተናግረዋል።

የሆቴሉ ማኔጅመንት ላይ ለዉጥ እንደሚደረግ እና አዲሱ ማናጀር ከስዊዘርላንድ አገር የሚመጣ ሲሆን፣ የዓለም ዐቀፍ ጥራት ደረጃን ለመጠበቅ የሆቴሉን ሠራተኞች በጠቅላላ የቋንቋ እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጥ ሥልጠና እንደሚሰጥ አስታዉቀዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 60 ታኅሣሥ 18 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here